“ከፊት ይልቅ ትጉ”(፪ኛ ጴጥ.፩፥፲)
በቀሲስ ኃለ ሚካኤ ብርሃኑ
ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ጽሑፋችን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ከፊት ይልቅ ትጉ” በማለት ያስተማረውን መነሻ አድርገን እንዴት መትጋት እንዳለብን እና በምን መትጋት እንደሚገባን የተወሰኑትን ተመልክተን ነበር፡፡ አሁንም ከዚያው ቀጥለን ልንተጋባቸው የሚገቡንን ሐዋርያው ዘርዝሮ ያስተማረንን እንመለከታለን፡፡
“በበጎነትም ዕውቀትን ጨምሩ”
ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክቱን ሲጽፍ ራሱን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ እና ሐዋርያ በማለት ከገለጸ በኋላ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስላገኘነው ጽድቅና ድኅነት በማብራራት ከዚህ ዓለም የጥፋት ምኞት በመሸሽ የክብሩ ወራሾች እንሆን ዘንድ ስለ ተሰጠን ተስፋ ዕለት ዕለት መትጋት እንደሚያስፈልገን በሰፊው ገልጾታል፡፡ ለዚህም ነው “እናንተ ግን በሥራው ሁሉ እየተጋችሁ በእምነት በጎነትን በበጎነትም ዕውቀትን ጨምሩ” በማለት ልንተጋባቸው የሚገባንን ሁሉ ዘርዝሮ የሚነግረን::
ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው በጎነት ዕውቀት ሊጨመርበት ያስፈልጋል፡፡ ዕውቀትም እውነቱን ከሐሰት፣ ብርሃንን ከጨለማ፣ ሕይወትን ከሞት ጣፋጩን ከመራራ የመለየት አቅም እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ እንግዲህ እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ”(ማቴ.፲፥፲፮)በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማራቸው፡፡ ብልህነትን ከእባብ የዋህነትን ከርግብ መማር እንደሚገባን በቅዱሳን ሐዋርያት አንጻር ተሰበከልን፡፡ ምክንያቱም በጎነታችን ለሞኝነትና ለመታለል እንዳይዳርገን ሁሉን በመመርመር መፈተን እንድንችል እንጂ በጎነትን ያለ ጥበብና ዕውቀት እናድርግ ብንል ተላላዎች ሊያደርገን ስለሚችል በበጎነት ላይ ዕውቀት ሊጨመርበት ያስፈልጋል፡፡
ሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስም የሚሰበክልንን ትምህርት መለየት እና ስለ ማንነታችን በሃይማኖታዊ ዕውቀት መመዘን እንደሚያሻን አስተምሮናል፡፡ “በሃይማኖት ጸንታችሁ እንደሆነ ራሳችሁን መርምሩ፤እናንተ ራሳችሁን ፈትኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር እንዳለ አታውቁምን? እንዲህ ካልሆነ ግን እናንተ የተናቃችሁ ናችሁ” (፪ኛቆሮ.፲፫፥፭) በማለት ራሳችንን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለን በእግዚአብሔር ቃል ሚዛን መፈተሽ የሚያስችል ዕውቀት ሊኖረን እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
“በዕውቀት ንጽሕናን ጨምሩ”
ዕውቀት ብቻ በራሱ አያጸድቅም፡፡ ወደ ጽድቅ ለመምራት ግን በመሳሪያነት ያገለግላል፡፡ ብዙዎች ዐዋቂዎች ነን ባዮች እግዚአብሔርን ማየት አልቻሉም፡፡ በዕውቀታቸው ሳይታበዩ ንጽሕናን ገንዘብ ያደረጉ ቅዱሳን አበው ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ከብረው ይኖራሉ፤ ስለዚህ ዕውቀት ንጽሕና ቅድስና ሊጨመርበት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው እነርሱ እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ.፭፥፰) በማለት የልብ ንጽሕና እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚያስችልና ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት እንደሚውል ያስተማረው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ ሳይሆን ልባችንን መርምሮ ለእርሱ የሚመች ማንነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ ይህንን እውነታ በሃይማኖታዊ ዕውቀት መርምሮ የተረዳ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት አስተማረን(መዝ.፶፥፲)፡፡ ስለዚህ ባወቅን ልክ ወደ ንጽሕና ለመድረስ ማቅናት ይኖርብናል፡፡
“በንጽሕና ትዕግሥትን ጨምሩ”
ከላይ እንዳየነው ንጽሕና ያለ ድካም የሚገኝ አይደለም፡፡ በብዙ ድካምና በብዙ ውጣ ውረድ ፈተናን ሁሉ ተቋቁሞ የዐይን አምሮትን እና የልብ ክፉ መሻትን ተቆጣጥሮ ራስን ከኃጢአት በመለየት የሚገኝ ክብር ነው፡፡ ንጽሕና ስንል የልብ ነው፡፡ እሱም በትዕግሥት ጸንተን የምንቆምበት እንጂ ትናንትን ሆነን ዛሬ የማንገኝበት ወይም ዛሬን ሆነን ነገ ላይ የማንውልበት መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም በነበር የምንተርከው ሳይሆን ሆነን የምንገኝበት ነውና ትዕግሥትን መላበስ ይኖርብናል፡፡
ትዕግሥት ፈተናን በጽናት ለማለፍና በትጋት ለመሻገር ያስችላል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ”(፩ኛቆሮ.፲፥፲፪) በማለት እንዳስተማረን ንጽሕናን በንስሓ ይዘን በትዕግሥት ፈተናዎችን ሁሉ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ፈተና ጠንካራውን ደካማ፣ አማኙን ተጠራጣሪ፣ አሸናፊውን ተሸናፊ ለማድረግ በሰይጣን ታስቦ የሚመጣ ቢሆንም ከፈተና በኋላ የሚገኝ የድል አክሊል እንዳለ በማሰብ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ የሠይጣንን አሳብ መቃወም ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ መጨረሻ እንደደረሰ የሚያሳዩ የመከራ ምልክቶችን ከዘረዘረ በኋላ “እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል” (ማቴ.፳፬፥፲፫) በማለት ትዕግሥትን እስከ መጨረሻው አጽንቶ መያዝ እንደሚገባ አስተምሮናል፡፡
“በትዕግሥት እግዚአብሔርን ማምለክ ጨምሩ”
በወንጌል ትዕግሥትን ያዘወተረ እርሱ ይድናል እንደተባለ ሁሉ እግዚአብሔርን በትዕግሥት ሆነን ስለ ሁሉ ነገር ማመስገን አለብን፡፡ ፈተናዎች ቢበዙብንም እንኳ መታገሥና ለበጎ እንደሚሆን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል “በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ ነገር ግን ጽኑ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና”(ዮሐ.፲፮፥፴፫) ብሎ እንዳስተማረን በትዕግሥት ሆነን እግዚአብሔርን ማምለክ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል ሰውና መላእክት ለምስጋና እንደተፈጠሩ ሁልጊዜ ማሰብ ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ስሙን ቀድሶ መንግሥቱን ይወርስ ዘንድ ነው እንጂ እንዲሁ እንደ እንስሳ አየበላና እየጠጣ በዘፈቀደ እንዲኖር አይደልም ስለዚህ የሰው ተቀዳሚ ሥራው ሊሆን የሚገባ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን በማምለኩ የእግዚአብሔር ስጦታ ይበዛለታል፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያአጋጃትን የማታልፈውን መንግሥቱን የሚያወርሰው ስሙን ቀድሶ ሕጉን ጠብቆ ለኖረ ሁሉ እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
“እግዚአብሔርንም በማምለክ ወንድማማችነትን ጨምሩ”
ማንም ሰው እግዚአብሔርን አመልካለሁ ቢል የወንድማማችነት ፍቅር ሊኖረው ይገባል፡፡ አንተ ትብስ እኔ ተባብለው መረዳዳትና መተሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ወንድምን መርገም አይገባም፡፡ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩላቸው… የተባለውን የወንጌሉን ቃል መፈጸም ያሻል፡፡
የእግዚአብሐየር ልጆች የሚታወቁበት እውነተኛ ፍቅር ምን መምሰል እንዳለበት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደልም” (፩ኛዮሐ.፫፥፲) በማለት ጽድቅን ማድረግ ወንድምን መውደድ እንደሆነ አስረድቶናል፡፡
ሃይማኖታችንን ጠብቀን ምግባራችን አቅንተን ለመኖር የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡
ይቆየን…
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!