ስደትና ምሥጢሩ

በመ/ር ተመስገን ዘገየ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ያለውን ወቅት ዘመነ ጸጌ በማለት ሰይማ ወቅቱ ላይ ያተኮረ አገልግሎት ትፈጽማለች፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “እስመ ናሁ ክረምት ኀለፈ ወዝናም ገብአ ድኀሬሁ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ፤ እነሆ ክረምት አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦችም በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬም ቃል በምድራችን ተሰማ” እንዲል (መኃ. ፪÷፲፩-፲፪)

“እነሆ ክረምት አለፈ” በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን የተናገረው የእስራኤል የመከራ ዘመን ማለፉን ለማመልክት ሲሆን መከራን በክረምት መስሎ ተናግሮታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በምሥጢር ሲተረጉሙት የአዳም የመከራ ዘመን አለፈ ማለት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ይህንን ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ የተሰደደችበትን ጊዜ ታስባለች፡፡ በጌታችን ልደት ሰብአ ሰገል የሕፃኑን መወለድ ተረድተው ሊሰግዱለትና ግብር ሊያገቡለት በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተ ልሔም ለመድረስ ፍለጋቸውን ባጠናከሩበት ወቅት “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ ሄሮድስም በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ በየት እንደሚወለድ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በይሁዳ ክፍል በቤተ ልሔም እንደሆነ ነገሩት፡፡ ሰብአ ሰገልን በምሥጢር አስጠርቶም በቤተ ልሔም መሆኑን ነግሮ ሲመለሱ በእርሱ በኩል እንዲመጡ ዜናውንም እንዲያበስሩት አሰናበታቸው፡፡ (ማቴ. ፪፥፩-፰)

ሰብአ ሰገል በኮከቡ ተመርተው ቤተ ልሔም ደርሰው ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰግደው የሚገባውን ወርቅ፣ ከርቤ እና ዕጣን አቅርበው፣ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ በተነሡ ጊዜም የጌታ መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይገቡ ስለ ነገራቸው በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሄዱ፡፡ ይህን የተረዳው ሄሮድስ በሰብአ ሰገል ማታለል ተበሳጨ “…ወአዘዘ ሐራሁ ወፈነወ ይቅትሎ ኩሉ ሕጻናተ ዘቤተ ልሔም ወዘኩሉ አድያሚሃ፤ ወታደሮቹን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ ያሉ ሕፃናትን ሁሉ ግደሉ ብሎ አዝዞ ሰደደ፡፡” (ማቴ.፪÷፲፮)

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን የቤተ ልሔም ሕፃናትን እልቂት በተመለከተ “… አየሁም እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፡፡ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ” በማለት ገልጾታል፡፡ (ራዕ. ፲፬÷፩-፫) በዚህም ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ተሰደደች፤ ዲያብሎም አሳደዳት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የእመቤታችን ስደት በተመለከተ ሲገልጽ “…ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የ፲፪ ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርሰዋም ጸንሳ ነበር፤ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች። ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩት …” (ራዕ. ፩፥፩-፬)

ሴት የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ናት፣ የክርስቶስም አካል ናት፡፡ የምትታየው ቤተ ክርስቲያን በተጋድሎ ላይ ያለች ስትሆን የማትታየው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድል ያደረገችው ናት፡፡ ፀሐይ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በቀንም በሌሊትም የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ነው፡፡ ጨረቃ የተባሉ ቅዱሳን፣ ፲፪ ከዋክብት የተባሉት ፲፪ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ “ምጥ” ስንል በተለያየ ዘይቤ እንደ አገባቡ ይተረጎማል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ “ምጥ” ያለው የድንግል ማርያምን መንገላታት፣ የግብፅ በረሃ ስደትና ጭንቀትን ለማመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ኢሳይያስ እና ሙሴ ምጥን እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ልጆች ሆይ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል” ይላል (ገላ. ፬፥÷፲፱) ሙሴ “አሕዛብ ሰሙ፣ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው” ይላል፡፡ (ዘጸ. ፲፭፥÷፲፬) እንዲሁም ነቢዩ ኢሳይያስ “ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፣ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፣ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም ከድንጋጤም የተነሣ አላይም” ብሏል፡፡ በተጨማሪም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ በጢሮስ ወሬ ምጥ ይይዛቸዋል” እንዲል፡፡ (ኢሳ. ፳፫፥÷፭)

የስደት ምክንያቶች  

ስደት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጦርነት፣ በወረርሽኝ፣ እና በሌሎችም ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች መነሻነት ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ አድካሚ ጉዞ፣ መራብ፣ መጠማት እና ሌሎች ችግሮችም ያጋጥማሉ፡፡

በሕግ የተከለከሉ ሥራዎችን በመሥራት ለስደት የሚዳረጉም ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ አዳም   “…እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር አምላክን ድምጽ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ አዳምና ሚስቱ ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ” በማለት እንደተገለጸው፡፡ (ዘፍ.፫÷፰) እንደ እስራኤል ሀገራቸው በጠላት በተወረረ ጊዜ ተማርከው ለስደት የሚዳረጉ “… በውኑ ይህ  ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ  ነውና?  እርሱና ዘሩስ   በማያውቁት ምድር ስለምን ተጥለው ወደቁ?” እንደተባለ (ኤር. ፳፪÷፳፰) የሰው ሕይወት ጠፍቶባቸው የሚሰደዱም አሉ፡፡ “… ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፡፡ ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፤ በምድያም ምድርም ተቀመጠ፡፡ (ዘፍ. ፪÷፲፩-፲፮) እንደ ሄሮድስ በሥጋዊ ቅንዓት ተነሳሥቶም አንዱ መንግሥት ሌላውን መንግሥት ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝብ ለስደት ይዳረጋል፡፡

እግዚአብሔር ለምን ወደ ግብፅ መሰደድን መረጠ?

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድ ምክንያት አንዱ ቀደምት አበው ወደ ግብፅ ተሰደው ስለነበር ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

፩. አብርሃም ከሚስቱ ከሣራ ጋር በምድር ሁሉ ላይ ረሃብ በሆነ ጊዜ ወደ ግብፅ ተሰዶ ነበር፡፡ ግብፅም በደረሱ ጊዜ አብርሃም እንዳይገድሉት ስለፈራ ሣራን ስለ አንቺ ነፍሴ ትድን ዘንድ ወንድሜ ነው በዪ ብሏት ነበር፡፡ (ዘፍ. ፲፪÷፲-፳)

፪. ዮሴፍ በወንድሞቹ ተሽጦ ወደ ግብፅ ተሰዷል፡፡ ፲፯ ዓመት በሆነው ጊዜ ከአባቱ ልጆች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር በግ ይጠብቅ ነበር፡፡ ያየውንም ሕልም ለወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ እነርሱም በቅንዓት ተነሣስተው ወንድማቸውን ከሚገድሉት ለእስማኤላውያን ሊሸጡት ተስማሙ፡፡ “እነዚያ እስማኤላውያን ነጋዴዎችም ሲያልፉ ወንድሞቹ የሴፍን ጎትተው አወጡት፤ ለእስማኤላውያንም በሃያ ብር ሸጡት፡፡ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት” እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፴፯፥፳፰)

ጌታችን ለምን ተሰደደ?

፩. ስደትን ለቅዱሳን ባርኮ ለመስጠት፣

፪. ትንቢተ ነቢያትን ለመፈጸም፣ (ኢሳ.19÷1፤ (ሆሴ. ፲፩÷፩))

፫. ገዳማተ ግብጽን እና ገዳማተ ኢትዮጵያን ለመባረክ፣

፬. ሰይጣንን ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ፡፡

የስደት ቆይታቸውን በተመለከተ

ቅዱስ ዮሐንስ የስደት ቆይታ ጊዜያቸውን በዕለት በወርና በዓመት ገልጾታል፡፡ “ከመ ትትዐቀብ   በህየ በኩሉ መዋዕል ዐሠርተ ወክልዔተ ምዕተ ወተሰዓ ዕለተ፤ ሴቲቱም በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች (ራዕ. ፲፪÷፮)፤ አርባዓ ወክልዔተ አውራኀ፤ ለአርባ ሁለት ወር ሥልጣን ተሰጠው (ራዕ.፲፫÷፭)፤ ዘመን፣ ወአዝማን፣ ወመንፈቀ ዘመን፤ ዘመን ያለው ፩ ዓመት፣ ወአዝማን ሲል ፪ ዓመት፣ ወመንፈቅ ሲል ስድስት ወርን ለማመልከት ነው፡፡ ስንደምረው ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ይሆናል፡፡(ራዕ.፲፪÷፲፬)

ልዩ ልዩ መከራን በመቀበል ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብፅ ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ መሞቱን የእግዚአብሔር መልአክ ለአረጋዊው ዮሴፍ ተገልጦ “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሞተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ” በማለት ተናገረው፡፡ አረጋዊው የሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ፡፡ (ማቴ. ፪፥፳፩) ይህም የሚያመለክተን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስደትን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጆች መስጠቱንና ስለ ስሙ የሚሰደዱ ብፁዓን እንደሚሰኙ ሲያስተምረን ነው፡፡ “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው” በማለት እንደገለጸው፡፡ (ማቴ. ፭፥፲)

ስደትን ከላይ እንደተመለከትነው እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰደደ ሁሉ በየዘመናቱ በተለያዩ ምክንያቶች ልንሰደድ እንችላለን፤ በርካታ ጸዋትወ መከራንም ልንቀበል እንችላለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ በጽናት መከራውን ተቋቁሞ ማለፍ ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡

አበ ብዙኀን አብርሃም ከዘመዶቹ ተለይቶ ወደማያውቀው ምድር ሲሰደድ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፤ ከሀገርህ፣ ከዘመዶችህም፣ ከአባትህም ቤት ተለይተህ ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ” በመባሉ በእምነት፣ በተስፋ ወጥቷልና ዘሩን እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደ ምድር አሸዋ እንዳበዛለት ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ (ዘፍ. ፲፪፥፩) እኛም በተለያዩ ምክንያቶች ስደት በገጠመን ጊዜ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገን ከመከራው ሁሉ ሸሽጎ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንዲያደረገን አምላከችን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *