ባልንጀራ

በእንዳለ ደምስስ

ክፍል ሁለት

መልካም ባልንጀርነት

ሰዎች በሚኖራቸው የእርስ በእርስ መስተጋብር መልካም ባልንጀርነትን ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት እና የነቢዩ ናታን ግንኙነትን ማንሣት እንችላለን፡፡

ነቢዩ ዳዊት የወዳጁንና የጦር አበጋዙ ኦርዮን ሚስት “የባልንጀራህን ሚስት፣ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ” (ዘጸ.፳፥፲፯) የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ ቤርሳቤህን በማስነወሩና እርሷም በማርገዟ ኦርዮንን ማስገደል አማራጭ አድርጎ ወሰደው፡፡ ጦር ሜዳ ሳለም አስገደለው፡፡ እግዚአብሔርም በዝምታ አላለፈውም፡፡ ይገስጸው ዘንድ ባልንጀራውን ነቢዩ ናታንን ላከበት።

ነቢዩ ናታንም እኔ ስለ ባልንጀራዬ ምን አገባኝ ሳይል ብልሃት በተሞላበት መንገድ በምሳሌ አስረድቶ ስለ ጥፋቱ ነግሮ በንስሓ እንዲመለስ የድርሻውን ተወጣ፡፡ ይህ የመልካም ባልንጀርነት ውጤት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፡፡ “ልቡ ንጸህ የሆነ፣ እጆቹም የነጹ፣ በነፍሱ ላይ ከንቱ ያልወሰደ፤ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ፣ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ይቀበላል” ይላል፡፡ (መዝ.፳፫፥፬)

መልካም ባልንጀርነትን ሊያጠነክሩ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን እንመለከት፡

ሀ.  ማመንና መታመን፡- በቅርባችን ያሉትን እናትና አባታችን፣ ቤተሰቦቻንን፣ ጓደኞቻችንን፣ ወይም በጎ ነገር ያደረጉልንን ልናምን እንችላለን፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በፊት እግዚአብሔርን ማመን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ   ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በእርሱም እጸና ዘንድ ዛሬ የኦሪት ጽድቅ ሳይኖረኝ ክርስቶስን በማመን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጽድቅ አለኝ እንጂ፡፡” (ፊልጵ. ፫፥፱) በማለት እግዚአብሔርን ማመን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ማመን ብቻ ሳይሆን መታመንም እንደሚያስፈልግ ሲያመለክት ደግሞ “የተጠራህለትንና በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ለመቀበል መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል” (ጢሞ. ፮፥፲፪) ሲል ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስን እንዳሳሰበው ላመኑት ነገር ታምኖ መገኘትን አስፈላጊነት ያሳየናል፡፡ በዚህም መሠረት መልካም ባልንጀርነትን ለመመሥረት ጓደኛን ማመን፣ እንዲሁም ራስም ታምኖ መገኘት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ችግር ማንሣት ያስፈልጋል፡፡

 የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከቤተሰብ መራቃቸው፣ ራሳቸውን እንዲመሩ ነጻነትም ስለሚሰማቸው ጓደኛ ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ከመንፈሳዊነት ይልቅ ሥጋዊውን በማሰብና በማድረግ ለተጠሩለት ዓላማ ታምነው መገኘት ይሳናቸዋል፡፡ ስለዚህ ጓደኛዬ ማነው? ሊሉ ይገባል፡፡ በሃይማኖት የሚመስላቸውን፣ ለአገልግሎት የሚያበረታቸው፣ ምሳሌም የሚሆናቸው፣ በትምህርታቸውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሊደጋገፉ የሚችሉ መሳዮቻቸውን መምረጥ ይገባቸዋል፡፡ ብዙዎች ውጤት አልባ ሆነው የሚቀሩት ለሥጋዊ ፍላጎታቸው በማድላት በሚፈጽሙት ያልተጋባ ድርጊት ከዓላማቸው ሲሰናከሉ እንመለከታለንና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚያምኑትና እነርሱም ሊታመኑለት የሚችሉትን ባልንጀራ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

ለ. ራስን አሳልፎ መስጠት፡- መልካም ባልንጀርነት ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ነው፡፡ ባልንጀራህ በሚደርስበት ችግር ተካፋይ በመሆን ቢወድቅ ማንሣትን፣ ቢቸገር የችግሩ ተካፋይ መሆንን፣ ሁል ጊዜም መልካምን መመኘት ይጠይቃል፡፡

ባልንጀርነትን ለማጽናት ማመንና መታመን እንደሚገባ ሁሉ ባልንጀራ በተቸገረ ጊዜ ከጎኑ በመሆን ደስታውንም ሆነ   ችግሩን መካፈል ይገባል፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ስለ ባልንጀራ/ጓደኛ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ እንኳ ቢሆን መከፈል ያለበትን መሥዋዕትነት መክፈል የመልካም ባልንጀርነት መገለጫ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ላይ አድሮ “ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱ አሳልፎ ይሰጣል” በማለት እንደተናገረው ጌታችን የአዳምና የልጆቹን በደል ተሸክሞ በመስቀል ላይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት በመስቀል ላይ ውሏል፡፡ (ዮሐ.፲፥፲፩) የሰውን ልጆች ነጻ ያወጣ ዘንድ ነፍሱን እስከመስጠት ታማነ፤ ቤዛም ሆነ፡፡ ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠትን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንማራለን፡፡ “እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ጽፏል፡፡ (ፊልጵ.፪፥፰)፡፡ መልካም ባልንጀራም ስለ ወዳጁ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ቢሆን የታመነ ሊሆን  ይገባዋል፡፡ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ.፲፭፥፲፫) እንዲል፡፡

መልካምን ማድረግ፡- የባልንጀርነት መገለጫ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ለባልንጀራ መልካምን ማድረግ ነው፡፡ “መልካም ሰው ከልቡ መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል”ና (ማቴ.፲፪፥፴፭) በማለት እንደገለጸው ሁል ጊዜ ስለ ባልንጀራ መጸለይ፣ በችግሩም ጊዜ አብሮ መቆምን፣ በሰላሙም ጊዜ አለመለየት፣ ከባልንጀራም ጋር መሆን ይገባል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን በረከት ይገኛል፡፡ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሙንም እሰጣችኋላሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፣ አትፍሩም” ይለናል፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)

ትእዛዛትን መጠበቅ፡- ከስድስቱ ትእዛዛተ ወንጌል አንዱ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው፡፡ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ስንል ከልብ በመነጨ ፍቅር ተመሥርተን ውጣ ውረዱን፣ ደሰታም ሆነ ሐዘኑን መጋራትን ያመለክታል፡፡ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ ትኩረት ያደረጋል ባልንጀርነት፡፡

ትእዛዛትን መጠበቅ ከቻልን ከእግዚአብሔርም ከሰውም ጋር ያለን ግንኙነት የጠበቀ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከክፉ እንርቃለን፡፡ “ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካም ነገርን ያወጣል” እንዲል፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፫) ባልንጀራን ወደ ትክክለኛው መንገድ መምራት የመልካም ባልንጀርነት መገለጫ ነው፡፡ ትእዛዛትን የሚጠብቅ ሰው በባልንጀራው ላይ ክፉ ነገርም አያደርግም፡፡

በአጠቃላይ በሃይማኖት፣ በምግባር ታንጾ የሚኖር ሰው ለባልንጀራው ፍቅር ይኖረዋል፡፡ በባልንጀራው ላይ ክፉም አያደርግም፤ ሁል ጊዜ በባልንጀራው ደስታ እርሱም ይደሰታል እንጂ፡፡ ሌላውን መውደድ ስንችል እንግዚአብሔርን እንወዳለን፤ እርሱም ይወደናል፡፡ “… ባልንጀራህንም እንደ ራስህ መውደድ ከመባና ከመሥዋዕት ሁሉ ይበልጣል” ነው የተባልነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው መልእከቱ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” (፩ቆሮ. ፲፭፥፴፫) ብሎ እንደተናገረው ከክፉ ባልንጀራ ርቀን፣ ክፉ የሆነውንና ከባልንጀራችን የወረስነው ክፉ ዐመል አስወግደን መልካምን እያደረገን እንኖር ዘንድ ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *