በዓለ መስቀል

በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ
        ክፍል -፩
ሀ. ትርጒም
ከዚህ በታች የሁለቱን ቃላት መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በማሳየት ወደ ዋናው ትንታኔ ለመግባት እንሞክራለን። በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት አተረጓጎም መሠረት “በዓል” የሚለው ቃል ለዕለት (ለቀን) ሲነገር የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፣ በዓመት፥ በወር፥ በሳምንት የሚከበር፣ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፣ . . . ወዘተ በማለት ተተርጒሟል። (ኪ.ወ.ክ ፪፻፸፱።) “መስቀል” የሚለውን ደግሞ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ፣ . . .ወዘተ ብለው በማለት ተርጉመውታል (ኪ.ወ.ክ ፰፻፹፫።)እነዚህ ቃላት ዘርዘር ተደርገው በምሥጢር ሲብራሩም እንደሚከተለው ሊገለጹ ይችላሉ።
             ፩. በዓል፦ ዕለታት ለእግዚአብሔር ክብር ገላጭና መታሰቢያ ሆነው ከሌሎቹ ዕለታት ሲለዩ የበዓል ቀናት ተብለው ይጠራሉ። በባሕርዩ ቅዱስ የሆነው አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የጸጋ ቅድስና ከሰጣቸው ፍጥረታት መካከል አንደኞቹ ዕለታት ናቸው። እነዚህም ቅዱሳት ዕለታት ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ።
               ፪. መስቀል
ሀ. የጌታችንን መከራ በመሳተፍ እርሱን በትንሣኤ (በክብር) የምንመስልበት አንዱ የመንግሥተ ሰማያት በር ነው። ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ገልጾልናል። መስቀሉን አስመልክቶ ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶችም መካከል ለማሳያ ያህል ብናነሣ፦
 “መስቀሉን የማይዝ፥ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” (ማቴ. ፲፥፴፯)
 “እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝም” (ማቴ. ፲፮፥፳፬)
ለ. ሞትና ዲያብሎስ ድል የተደረጉበት መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ ነው።
ሐ. ዓለም ከዘለዓለም ሞት የዳነበት፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት፣ ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣበት፣ የተዘጋው የገነት ደጅ የተከፈተበትና አባታችን አዳም ከልጆቹ ጋር ወደ ቀደመ ርስቱ ተመልሶ የገባበት የምሥጢር ቁልፍ ነው።
መ. በዳግም ምጽአት ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ለሁሉ የሚታይ የሰው ልጅ ምልክት ነው። (ማቴ. ፳፬፥፴።)
ሠ. የክርስቲያኖች ትምክሕታቸው (መመኪያቸው) ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ. ፮፥፲፬።) በማለት እንደገለጸው።
ረ. የሚማፀኑበትና የሚተማመኑበት ክርስቲያኖች ከጠላት ፍላፃ የሚያመልጡበት ትእምርት (ምልክት) ነው። (መዝ. ፶፱፥፬።)
ሰ. ክርስቲያኖችን አሸናፊ የሚያደርግ ኀይለ እግዚአብሔር ነው። “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።” (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰።) እንዲል።
ሸ. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ዙፋን፥ የአዲስ ኪዳንም መሠዊያ ነው።
ቀ. ቅዱሳን መላእክት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር በተዋጉ ጊዜ ኃይል ይሆናቸው ዘንድ እግዚአብሔር በክንፋቸው ላይ የቀረፀላቸው የማሸነፋቸው ምሥጢር ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ)
በዓለ መስቀል ክርስቲያኖች በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስንና ቅዱስ የኾነ መስቀሉን የሚያከብሩበትና አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚገልጡበት የከበረ ዕለት ነው። ምእመናንና ምእምናት ጸንተው ምድራዊ የተጋድሎ ሕይወታቸውን በድል አድራጊነት የሚፈጽሙበት መኾኑን የሚመሰክሩበት እና በማያምኑበት ዘንድም እንኳን በናፍቆት የሚጠበቅ በዓል ነው። በዓለ መስቀልን በማክበር ክርስቲያኖች የክርስቶስን መከራ የሚሳተፉበትና በትንሣኤው የተገኘውን ሕይወትና ክብር የሚካፈሉበት ማለትም ክርስቶስን የሚመስሉበት፥ ለትውልድ ቀረፃም አዎንታዊ ሚና ያለው ተግባራዊ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው። ከዘጠኙ ንዑሳት የጌታ በዓላት መካከል አንደኛው በዓለ መስቀል መኾኑ ይታወቃል። ይኸውም መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ቀናት በአንድነት እንደ አንድ ቀን (በዓል) ተቆጥረው ነው።

                                                                       ለ. ክብረ መስቀል
መስቀሉ እንደሚታወቀው ሁሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ይገልጽ ዘንድ፣ሞትን በሞቱ ይገድለው ዘንድ፣ ትንቢቱንና ምሳሌውን ይፈጽም ዘንድ፣ መስተፃርራንን (ጠላቶች የነበሩትን) ያስታርቅ ዘንድ፣ የዲያብሎስን ጥበብ ያፈርስና ወጥመዱን ይሰብር ዘንድ፣ ጥበበኛ ነን ብለው የሚመኩ የክፉዎችን ጥበብና ምክር ከንቱ ያደርግ ዘንድ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ዐደባባይ የተሰቀለበት የክብር ዙፋኑ ነው።
በዓለ መስቀሉን በምናከብርበት ወቅት ሁሉ እነዚህን ምሥጢራት ማሰብ ይኖርብናል። ከበዓላተ መስቀልም በልዩ ሁኔታ ወርኃ መስከረም ከደመራው በዓልና ከመስቀሉ ጋር በተያያዘ ለማስታወስ እንገደዳለን። ይህ ወር ምድር በሥነ ጽጌያት፥ ሰማይም በሥነ ከዋክብት የሚያጌጡበት ከመሆኑም በላይ ምድሩ፣ ሰማዩና ዘመኑ በመስቀሉ በረከት መሞላቱና ፍጥረታት ሁሉ በመስቀሉ እንደሚባረኩ በልዩ ድምቀት የሚታሰብበት ልዩ ወር ነው።
በብሔራዊ ደረጃ (በዐዋጅ) የምናከብርበትም ምክንያት የነገረ ድኅነት ትምህርታችን አካል በመሆኑና በክርስቲያኖች ልቡና ታትሞ ያለ የሕይወታችን ዓርማ ስለሆነ ነው። በመላው ዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅና ዛሬም ተፈልጎ ሊገኝ በማይችል ልዩ፣ ድምቀትና ውበት የምናከብረው በመኾናችንም በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎን ቀልብ (ስሜት) ከመላው የዓለም መዓዝናት ለመሳብ በቅተናል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ሊመዘገብም መቻሉ የክብረ መስቀሉ መዓዛ ዓለሙን ምን ያህል እያወደና እየማረከው መሆኑን ያመለክታል።
                                       ሐ. መስቀሉን የምናከብረው እንዴት ነው?
መስቀሉን በላዩ ላይ ተሰቅሎ ያከበረውና የቀደሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል። እኛ መስቀሉን እናከብራለን ስንል ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ባደረገው ቤዛነት የፈጸመልንን የማዳን ሥራ እንመሰክራለን ማለታችን ነው። በዓል የምንለውም ይህንኑ ምስክርነት በልዩ ልዩ መንገድ የምንገልጽበትን ዕለት ማለታችን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህንን ምስክርነት ለመስቀሉ እንዴት እንደሚሰጡ እንደሚከተለው እናያለን።

  ይቀጥላል……………………………..

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *