ቅዱስ መስቀል

በዲ/ን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረው መስቀል ያደርግ የነበረው ተአምራት በመቃወም አይሁድ እንደቀበሩት በአብዛኛዎቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ይተረካል፡፡ አይሁድ በሮማውያን ላይ እስከአመጹበት፣ ኢየሩሳሌም ከክርስትና በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከጠፋችበት እስከ ፸ ዓ.ም ድረስ መስቀሉ በክርስቲያኖች እጅ ነበር፡፡ ይህም ቆስጠንጢኖስ ለኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ ለአቡነ መቃርዮስ በጻፈው እና እነ አውሳብዮስ መዝግበው ባቆዩት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተገልጧል፡፡ ቀጣዮቹ ፫፻ ዓመታት ለክርስቲያኖች የመከራ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የሮም ቄሣሮች ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱባቸው ዓመታት ስለነበሩ መስቀሉን የመፈለግ ጉዳይ በልብ ይታሰብ እንጂ በተግባር ሊሞከር አልተቻለም፡፡

መስቀሉና ንግሥት ዕሌኒ

ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች መስቀሉን ከጠፋበት (ከተሰወረበት) ያገኘቸው ንግሥት ዕሌኒ መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ ድርሳነ መስቀል ዘየካቲት እና ዘመጋቢት እንደተገለጸው እስከ ፫፻፲፰ ዓ.ም ተሰውሮ የነበረው መስቀል ያለበትን ይገልጽላት ዘንድ አስቀድማ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠየቀች፡፡ ከዚያም በሮሜ ሀገር የሚኖሩ ሊቃውንትንና ጥበበኞችን ሰብስባ የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መሰቀል ዜና ንገሩኝ አለቻቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ቀራንዮ በሚባል ቦታ አዳምና ልጆቹን ለማዳን የክብር ባለቤት ጌታችን እንደ ተሰቀለ፣ በጎልጎታም እንደተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሳ፣ በዐርባ ቀንም በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ ተረከላት፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ፈጽሞ ደስ አላት፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየጠየቀች ሰባት ዓመት ያህል ቆየች፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላም ልጅዋ ቆስጠንጢኖስን በመንግሥቷ ዙፋን አስቀምጣ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ትፍልግ ዘንድ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ በ፫፻፳፭ ዓ.ም አየሩሳሌም ደርሳ አይሁድንም ሰብስባ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ያለበትን ንገሩኝ፣ አባቶቻችሁ ወዴት እንደቀበሩት አሳዩኝ አለቻቸው፡፡ እነርሱ ግን እኛ የሆነውን አናውቅም፣ አባቶቻችንም መስቀሉን በምድር ውስጥ አልቀበሩም፣ ነገር ግን ስማቸው ኪራኮስ እና አሚኖስ የሚባሉ ሁለት አረጋውያን በእኛ ዘንድ አሉ፡፡ እነርሱም ስለዚህ ጉዳይ ይነግሩሽ ዘንድ ጠይቂያቸው አሏት፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ወደ ቤተልሔም ገብታ “የታላቁ ንጉሥ ሀገሩ ቤተልሔም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል” እያለች የመስቀሉን ነገር ይገልጽላት ዘንድ ለሰባት ቀናት እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር በመስገድ ማለደች፤ ጸለየች፡፡  ከዚያም ወደ ዮርዳኖስ፣ ቆሮንቶስ፣ ደብረ ታቦር፣ ቀራንዮ፣ ጌቴ ሴማኒ ሔዳ ሰባት ቀን ጾመች፣ ጸለየች፣ በጎልጎታ ድንኳኖቿን ተክላ ከተመች፡፡ በጾምና በጸሎት ብዙ ዕንባ በማፍሰስ እስከ ዐርባ ቀን ቆየች፡፡

በመጨረሻም በአረጋዊው ኪራኮስ አመላካችነት፣ በዕጣን ጢስ ጠቋሚነት ክቡር መስቀሉን ፈልጎ ለማግኘት ቁፋሮው ከመስከረም ፲፯ እስከ መጋቢት ፲ ቀን ወደ ስድስት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ፈጀ፡፡ በመጨረሻም መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉ ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ዕለቱን ታከብረዋለች፡፡

ቅዱስ መስቀሉና ኢትዮጵያ

ግማደ መስቀሉን ካገኙትና ከጠበቁት ሀገሮች ኢትየጵያ ሀገራችን አንዷ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዛግብት እንደሚገልጹት ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ የጀመረው በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ሲሆን፣ በግሸን አምባ የተቀመጠው ደግሞ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን መንግሥት ነው፡፡

በዐፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግሥት በግብፅ ሡልጣን እና በኢትዮጵያ ንጉሥ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት አንድ የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡ የልኡካን ቡድኑ መሪ የኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ አባ ዮሐንስ ነበሩ፡፡ ልኡካኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲደርሱ የዐፄ ሰይፈ አርእድ ልጅ ዐፄ ዳዊት የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆነው ነበር፡፡ ፓትርያርኩ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን ችግር በውይይትና በስምምነት ፈትተው አስማሟቸው፡፡ ዐፄ ዳዊት በነበራቸው ቀና መንፈስ አቡነ ዮሐንስ የኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ ዕሌኒ ንግሥት አስቆፍራ ካስወጣቸው ከጌታ መስቀል ክፋይ ለበረከት እንዲልኩላቸው ወርቅ፣ አልማዝ ሌላም የከበረ ማዕድን ገጸ በረከት አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌም መልእክተኞችን ላኩ፡፡ መልእክተኞቹ ኢየሩሳሌም ደርሰው ገጸ በረከቱን ለፓትርያርኩ ከሰጡ በኋላ ፓትርያርኩ የጌታችንን ግማደ መስቀል የቀኙ ክፋይ ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ላኩላቸው፡፡

ግማደ መስቀሉ በግብፅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት በግብፅ ሡልጣን እና በንጉሥ ዳዊት መካከል ለኢትዮጰያውያን ተሳላሚዎችና ለነጋዴዎች ጥበቃ ማድረግን ጭምር የሚያካትት ስምምነት አካሔዱ፡፡ ግማደ መስቀሉን የያዙት የዐፄ ዳዊት መልእክተኛችም ያለ ችግር ወደ ኢትዮጵያ ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ዐፄ ዳዊት መልእክተኞቹን ለመቀበል ሲሔዱ መንገድ ላይ መሞታቸውን የጥቅምት ፱ ቀን ፲፬፻፬ ዓ.ም ታሪካቸው ይናገራል፡፡ ያን ጊዜ ግማደ መስቀሉ በሱዳን ስናር በሚባል ቦታ ነበር፡፡

ግማደ መስቀሉ ኢትዮጵያ የገባው መስከረም ፲ ቀን ሲሆን ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግሸን አምባ ላይ ያስቀመጡት መስከረም ፳፩ ቀን በወሎ ክፍለ ሀገር ግሸን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ ነው፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የካቲት ፳፻፭ ዓ.ም

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *