“ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ” (ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም)

በእንዳለ ደምስስ

አስተርእዮ ቃሉ አስተርአየ፤ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕፀኗ አድሮ የተወለደበት (በሥጋ የተገለጠበት)፣ አንድነት፣ ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍትም በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚውልና ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞት እጅግ ተደንቆ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል።(ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም)፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ እንዴት ነው ቢሉ፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ነገረ ማርያም በተሰኘው የምስጋና መጽሐፍ በስፋት ይተርኩታል፡-

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስልሣ አራት ዓመቷ ከዚህ ዓለም ዐርፋለች፡፡ እንደምን ነው ቢሉ ሦስት ዓመት ከወላጆቿ ከሐና እና ከኢያቄም፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ ስትፈትል ኑራለች፡፡ በዐሥራ አምስት ዓመቷ ከቤተ መቅደስ ወጥታም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ አድሮ ተወልዷል፡፡ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሀገር ሀገር፣ ረሃቡንና ጥሙን ታግሳ እስከ ዕለተ ስቅለቱ አብራው ኑራለች፡፡ በስቅለቱ ጊዜም እጅግ ይወደው ከነበረው ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በመስቀሉ ሥር ተገኝታለችና እናቱን ለቅዱስ ዮሐንስ አደራ ሰጥቷታል፡፡ ለቅዱስ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን በእርሱ በኩል ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥታናለች፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ቤትም ዐሥራ አምስት ዓመታትን ኖራለች፡፡ እነዚህን ስንደምር ለስልሣ አራት ዓመታት በዚህ ምድር ላይ እንደኖረች እንረዳለን፡፡

ስልሣ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራም ጥር ፳፩ ቀን በዕለተ እሑድ ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት።  እርሷም “ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?” አለችው። ወደ ሲኦል ወስዶም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ሁሉ ነፍሳት ቤዛ ይሆንላቸዋል” አላት። እርሷም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት ሥቃይ ከተመለከተች በኋላ አዝና “ይሁን” አለችው። ቅዱስ ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ ነፍሷን በመላእክት ዝማሬ በይባቤ ወደ ሰማይ አሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ “የእመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ” አላቸው። (ተአምረ ማርያም)፡፡

ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ቀድሞ ልጇ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ በትዕቢት ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። ጌታችንም መልአኩን ልኮ በሰይፍ እጁን ቆረጠው፣ ከአጎበሩም ተንጠልጥሎ ቀረ። ታውፋንያ የደረሰበትን ተመልከቶ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ በደመና ነጥቆ፣ ከገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስ ሲመለስም ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት ሆነው “እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ቅዱስ ዮሐንስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፣ እንደ ልጇ ተነሥታለች።

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፣ ዛሬ ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ከሐዘኑ የተነሣ ከደመናው ላይ ወደ መሬት ሊወድቅ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን እነርሱ ትንሣኤዬንና ዕርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃልና ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሄዶ ሐዋርያት በተሰበሰቡበት “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው፡፡ “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር? ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ሁል ጊዜ ልማድህ ነው፣ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ” ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሯ ሄደው ቢከፍቱት የእመቤታችንን ሥጋ አጡት፡፡ ሁሉም ደንግጠው በቆሙበት ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ “እመቤታችንስ ተነሣች፣ ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን ሰጥቷቸው ለበረከት ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት “ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን፣ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች። ቅዱስ ያሬድ በዚህ ተደንቆም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ተናገረ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ እንደማትቀር፣ እንደምትነሣና እንደምታርግ ጠቢቡ ሰሎሞንም ምሥጢር ተገልጦለት ሲናገር “ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ መልካምዋ ርግቤ ሆይ ነዪ” በማለት ተናግሯል፡፡(መኃ.፪. ፲)፡፡ ምንም እንኳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች ብትሆንም የሥጋ ሞት ለማንም እንደማይቀር ሲያስረዳም “ርግብየ ተንሥኢ ወንዒ፣ ርግቤ ሆይ ተነሺ፣ ነዪ” አለ፡፡

በተአምረ ማርያም መግቢያ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርና ቅድስና የተጠቀሰውን በማስከተል ጽሑፋችንን እናጠቃልል፡- “እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የወልድስ ማደሪያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን ማርያም የመንፈስ ቅዱስ ቤት የሆነ ማነው? ለሰው ኃጢአት ሳይሠራ መኖር ይቻለዋልን? ከአራቱ ባሕሪያት ከተፈጠረ ሰው ከእመቤታችን በቀር እሳትን የተሸከመ፣ ኃጢአትንም ያልሠራ የለም፤ እመቤታችን ማርያም ከመላእክት ይልቅ ንጽሕት ናት፣ እመቤታችን ማርያም ከሴቶች ሁሉ ትበልጣለች፡፡ የእመቤታችን ማርያም ሐሳብ እንደ አምላክ ሐሳብ ነው፡፡ የእመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፣ የአምላክን መልክ ይመስላል፡፡ እመቤታችን ማርያም ንጽሕት በመሆንዋ አምላክን እንዲያድርባት አደረገችው፡፡ እመቤታችን ማርያም ለአምላክ የደስታ ማደሪያ ሆነችው፡፡ እመቤታችን ማርያም አምላክን በድንግልና ወለደችው፡፡ እመቤታችን ማርያም በነቢያት ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በሐዋርያትም ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፍጥረት አንደበት ትመሰገናለች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አክብሯት ለእኛ ለኃጥኣን መድኃኒታችን ስለሆነች፡፡ በጎ አገልግሎትም ለሚያገለግሉት ዋጋውን ትሰጠዋለች፣ ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ እመኑባት እሷ መድኃኒታችን ናትና፡፡ በሥዕሏ ፊት ስገዱ ለሥዕሏም ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ፣ ስም አጠራሩም አይታወቅ፡፡ (ተአምረ ማርያም መግቢያ)፡፡

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *