“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል ሦስት                                           

በእንዳለ ደምስስ

ጉባኤ ቃና፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቆይታዎ ግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፍዎ አጋጠሞኛል የሚሉት ችግር ከነበረ ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔ በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፌ ገጠመኝ የምለው ችግር የለም፡፡ እንዲያውም ራሴን እንደ ዕድለኛ ነበር የምቆጥረው፡፡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፌ በርካታ ጥቅሞችን ነው ያገኘሁት፡፡ ከመምህራኖቼ፣ ከጓደኞቼ፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረኝ ግንኙነት በጣም ጠንካራና ጤናማ ነበር፡፡ በጣም የሚገርምህ ኅብረተሰቡ ራሱ ተማሪውን ይንከባከባል፣ ያቀርብሃል፤ ስለዚህ እንደ ችግር የማነሳው ገጠመኝ የለኝም ማለት እችላለሁ፡፡ ለዚህም በቅርበት ራስን መግለጥና በቅንነት መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ስለሌሎች ሕይወት እንጨነቅ ነበርና ያለንን ለመስጠት ወደ ኋላ አለማለት ያስፈልጋል፡፡

መንፈሳዊ ሕይወታችን መደበኛ ትምህርታችንን በአግባቡ እንድንከታተል፣ ዓላማ እንዲኖረን፣ ጠንቃቃ እንድንሆን ስለሚያደርገን ተጠቃሚዎች ነን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ሌሎች ውጫዊ ነገሮች እንዳይረብሹንና መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊያጨናግፉ ከሚችሉ ነገሮች እንድንርቅ አድርጎናል፡፡

በአገልግሎት ላይ ግን አንዳንድ ይገጥሙን የነበሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደ ምሳሌ ባነሳ፡- አንዳንድ ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ ባለመቻላቸው እኛም አጥብቀን ባለመከታተላችን ሃይማኖታቸውን የቀየሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ያሳዝኑኛል፡፡ ከዚህ ውጪ አብረውን ይማሩ የነበሩ ወንድሞቻችን በተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት ያረፉ ልጆች ነበሩ፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ነገር እንጂ እንደ ችግር የሚነሣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላው አንድ ወቅት ሕመም ገጥሞኝ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠንክሬ እማር ስለነበር ከትምህርት ክፍሉ ከሁሉም ተማሪ የእኔ ውጤት ነበር ከፍተኛው፡፡ ስለዚህ እንደ ችግር ከምቆጥራቸው ይልቅ እንደ መልካም ነገር የምቆጥራቸው ነገሮች ይበዙብኛል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተመራቂዎች ሲመረቁ የሰጡትን ሜዳልያ ምክንያት አድርገው እርስዎን እንደ አርአያ ይቆጥራሉ፡፡ እነርሱም ከፍተኛ ውጤት አመጣለሁ፣ ሜዳልያዬንም እንደ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ ለማኅበረ ቅዱሳን እሰጣለሁ ብለው ይጀምራሉ፣ ሲፈጽሙም ቃላቸውን ጠብቀው ሲሰጡ እንመለከታለን፡፡ ለመሆኑ ያኔ እንዴት ሊያስቡትና ሜዳልያዎን ሊሰጡ ቻሉ? ምክንያትዎ ምን ነበር?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡-  ገና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስንገባ ከአቀባበል ጀምሮ የተደረገልን እንክብካቤ፣ ምክራቸው፣ በተለይም ጠንካራ ተማሪዎች እንድንሆን፣ ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም፣ ጎበዝ ተማሪ እንድንሆን፣ ይህንን ማድረጋችን ለራሳችንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚጠቅም፣ በአገልግሎትም እንድንሳተፍ ይመክሩን ነበር፡፡ እኛም ይህንን እንደ መመሪያ ወስደን የምናወጣውን የጊዜ አጠቃቀም ተግባራዊ እያደረግን ውጤታማ ሆነን ለመውጣት ረድቶናል፡፡

የመጀመሪያ ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ላይ ፈተና እንደጨረስን በዕለቱ ነበር ከጓደኞቼ ጋር አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ ስለ ውጤት የምጨነቅበት ጊዜ አልነበረም ቤተሰብ ይናፍቅሃል፣ ዕረፍት ትፈልጋለህ፡፡ የዕረፍት ጊዜያችንን ጨርሰን ስንመለስ ቀጥታ ያመራነው ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ አንድ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ያገለግል የነበረ ወንድማችን የእኔን ውጤት ቀደም ብሎ ሰምቶ ስለነበር በደስታ ነው የተቀበለኝ፡፡ “እንኳን ደስ ያለህ! ከሁሉም ተማሪ የአንተ ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡ ጎበዝ! በርታ! እንዲህ ዓይነት ተማሪ ነው የምንፈልገው” ብሎ አበረታታኝ፡፡

ከእኔ ይልቅ እርሱ የነበረው የደስታ ስሜት እስከ ዛሬ አይረሳኝም፡፡ ወዲያውኑ ነው “እኔ ለወንድሞቼ ብዬ የተለየ የሠራሁት ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ጠንክሬ ተምሬያለሁ፡፡ የእኔ ውጤት ወንድሞቼን እንዲህ የሚያስደስታቸው ከሆነ በዚሁ ጥረቴ እቀጥላለሁ፤ ስጨርስም ሜዳልያዬን ለእነርሱ ነው የምሰጠው” ብዬ ቃል ገባሁ፡፡ እግዚአብሔርም ረድቶኝ የትምህርት ክፍሌንና የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ አሸናፊ ሆኜ ጨረስኩ፡፡ በገባሁት ቃል መሠረትም በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም ማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በጉባኤው ላይ ተገኝቼ ሜዳልያዬን ሰጠሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  እርስዎ የሰጡት ሜዳልያ ለበርካታ ተማሪዎች ውጤታማነት መነሳሳትን ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡ ሜዳልያቸውንም እያመጡ ለማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ ያበረክታሉና ይህንን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔ ለማኅበረ ቅዱሳን ሜዳልያውን የሰጠሁት ሌሎችን ለማነሳሳት ብዬ አልነበረም፡፡ ለወንድሞቼ ደስታ ስል ነበር ይህንን ያደረግሁት፡፡ ነገር ግን በሂደት ለሌሎች መነሳሳትና ውጤታማነት አስተዋጽኦ አድርጎ ከሆነ መልካም ነው፡፡ እኔም በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት ተምረው የዲቁና ማዕረግን ተቀብለው ይወጣሉ፡፡ እርስዎ ይህ ዕድል ገጥሞዎት ነበር? 

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡-  አዎ፡፡ ግቢ ጉባኤ ከገባሁ በኋላ ነው የአብነት ትምህርት የተማርኩትና ዲቁና እስከመቀበል የደረስኩት፡፡ በጣም ጠንካራ ጉባኤ ቤት ነበር፡፡ መምህራችንም በጣም ትጉህ ነበሩ፡፡ ወንበር ዘርግተው ከማስተማር በተጨማሪ ተማሪዎቻቸውን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ይዘው ገብተው ማኅሌት ያስቆሙናል፣ ከአገልግሎት ጋር እንድንተዋወቅ፣ በሄድንበት ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ከማገልገል ወደ ኋላ እንዳንል ይመክሩናል፡፡ ወርኀዊ በዓላት ይሁን ዓመታዊ በዓላት ከኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አልፈን አጎራባች አጥቢያዎች ድረስ ይዘውን እየሄዱ ማኅሌት እንድንቆም ያደርጉናል፣ በብዛት መኅሌት ላይ የምገኘው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች   ነበርን፡፡ በተለይም የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ማኅሌት ከተማው ውስጥ ካሉት ሁሉ ደማቁ ነበር፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲልኩ ግቢ ጉባኤ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያበረታቱ እንዳሉ ሁሉ ጊዜያችሁን ይሻማባችኋል፤ ወደ ግቢ ጉባኤ እንዳትገቡ እያሉም የሚያስጠነቅቁ ወላጆች አሉና ከተሞክሮዎ ተነስተው ለወላጆች ምን ይመክራሉ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡– ግቢ ጉባኤ እንዳይገቡ የሚያደርጉ ወላጆች ግቢ ጉባኤን ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ከቤተሰቦቻቸውም ጋር አብረው እየኖሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አትሂድ የሚል ወላጅም ያጋጥምሃል፡፡ ግንዛቤ ከማጣት ነው ያልተገባ ፍርድ የሚሰጡት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ ልጆቹን ቤተ ክርስቲያን አትሂድ የሚል ወላጅ ስለ እምነቱ ያለውን ግንዛቤ በትክክል ተረድቷል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ነገር ግን ወላጆች አንዳንድ ከሚያይዋቸውና ከሚሰሟቸው አሉታዊ መረጃዎች የተነሳ ሰንበት ትምህርት ቤትን ወይም ግቢ ጉባኤያትን የሚስሉበት መንገድ ትክክል ካለመሆን የመነጨ ነው፡፡

በትክክል ግቢ ጉባኤን ወይም ሰንበት ትምህርት ቤትን የሚያውቅ ወላጅ ግን እንዲህ አይልም፡፡ እንዲያውም ዘመኑ ከሚያመጣቸው አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶችና መረጃዎች የተነሳ ልጆቻቸው እንዳይበላሹባቸው ስለሚሰጉ ወደ ግቢ ጉባኤና ሰንበት ትምህርት ቤት የሚልኩ በርካታ ናቸው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ማድመጥ፣ መንገድ መምራት፣ ትክክለኛውን መስመር ይዘው እንዲያድጉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለልጆቻቸው የሚበጃቸውን የማሳየት፣ ከልጆች በተሻለ ስለ ጉዳዩ ከፍ ያለ ግንዛቤው ያላቸው እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች በአብዛኞቹ በተመሳሳይ የዕድሜ ክልልና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አካባቢያቸውም ሆነ ወላጆቻቸው በተበታተነ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ እኩል ግንዛቤ መፍጠር አይቻልም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ግን ወላጆችን አሰባስቦ ማስተማር የሚቻልበት ጉባኤ ሊፈጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ቢኖራት ኖሮ አሁን የምናያቸው ችግሮች አይፈጠሩም ነበር፡፡ የሀገር መሠረቱ ወላጆቻችን ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእኔ እናት ዘመናዊ ትምህርት የተማረች አይደለችም፣ ነገር ግን ሀገሯን የምትወድ፣ ዘወትር ቤተ ክርስቲያን የምትሳለም፣ እኛንም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ ግፊት የምታደርግ እናት ናት፡፡ በእርሷ አቅም ልትነግረን፣ ልታሳየን የፈለገችውን ነገር ነፍጋ አላሳደገችንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ፣ ጥሩ ዜጎች እንድንሆን የከፈለችው ዋጋ አለና በእኛ እርሷም ደስተኛ ናት፡፡

ትምህርት ቤት ገብቶ የወጣውና ፊደል የቆጠረው፣ ዲግሪ፣ ዶክትሬት አለኝ የሚለው ወላጅ ግን ለልጁ ምንድነው የሚመኝለት? ምን እንዲሆንልት ነው የሚፈልገው? ለዚያ የሚመጥን ሥራ ከወላጆች ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ግቢ ጉባኤ አትሂዱ ሳይሆን ሂዱ ግን ስትሄዱ ይህንን አድርጉ፣ ይህንን ደግሞ አታድርጉ ብሎ ለይቶ ሊመክር፣ ሊከታተል ይገባዋል ወላጅ፡፡ ግቢ ጉባኤ እንዳይሄዱ ቢፈልጉ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ሂዱ ብለው ልጆቻቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ መርዳት አለባቸው፡፡ ወላጆች በማያውቁት ነገር ላይ የማይገባ ሐሳብ ባይሰጡም መልካም ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጊዜው እየከፋ ነው የመጣው፡፡ ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሆኗል፣ ሁሉም አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ያላለፉበትን መንገድ ልምድ ካላቸው ሰዎች ቢጠይቁ፣ ከልጆቻቸው ጋር ቢመካከሩ መልካም ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ የአገልግሎት መስኮች ላይ ስለተሰማራ እዚህ ላይ እንደሚቸገር ይገባኛል፡፡ እኔም የአገልግሎቱ አካል ስለሆንኩ በቅርብ የምረዳው ነው፡፡ ወላጆች ላይ መሥራት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ላይ መሥራት ማለት ነው፡፡ በተለይ አሁን በእኛ ዕድሜ ላይ ያሉ ወላጆች ላይ ቢሠራ ልጆቻቸውን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ማስተማር ልጆቻችን ኮሌጅ ሲገቡ አይቸገሩም፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኮትኩተው የማደግ ዕድሉን ስለሚያገኙ ኮሌጅ ሲገቡ ሁሉንም ዐውቀውና ተረድተው ይገባሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከሄድን ለውጥ ሊመጣ ችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ ብዙዎቹ ከአገልግሎት ይርቃሉ፡፡ ሕይወት ከምረቃ በኋላ እንዴት መሆን አለበት ይላሉ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ይህንን በሁለት መንገድ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ያስተማርናቸው ሁሉ አገልጋይ እንዲሆኑ መመኘት መልካም ቢሆንም በቅድሚያ ጥሩ ምእመን ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ጥሩ ምእመን መሆን ከቻለ ልጆቹን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያድጉ የሚያደርግ ከሆነ አላገለገለም ልንለው አንችልም፡፡ ጥሩ ምእመን ጥሩ አገልጋይ ነው፡፡ የሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እኛም ባሉበት አጥቢያ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው የምንመክራቸው፡፡ ስለዚህ አስተምሯልና ግዴታ ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ መግባት አለባቸው ልንል አንችልም፡፡ ካገኘነው የጣነውን መቁጠር ልማድ ስለሆነብን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤ ውስጥ ያስተማራቸው ሁሉ ጠፍተዋል ማለት አይደለም፡፡ ጥሩ ጥሩ ምእመናንን ማፍራታችንም ማሰብ አለብን፡፡ ሌላው ከምረቃ በኋላ የቤተሰብ ኃላፊ መሆን፣ ቤተሰብ የማስተዳደርና የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት፣ ልጆችን መንከባከብ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሁሉ ስለሚሻሙት ሁሉም በአባልነት ያገልግል ማለት አይቻልም፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማጠናከር አንጻር ሊያከናውናቸው ወይም ሊያሻሽላቸው ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮችን ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ውጤታማ አገልግሎት እያከናወነ እንዳለ ሁላችንም የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የነገዋን ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅምና የሚታደግ ትውልድ ለመፍጠር ወላጆች ላይ መሥራት አለበት እላለሁ፡፡ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎቻችን በዕረፍት ጊዜያቸው ከመላው ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲመካከሩ ማድረግ ያለውን ክፍተት እንዲሞላ ያደርገዋል፡፡

አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ማስተባበሪያ ውስጥ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ስለሆነ አጠናክሮ መቀጠል፣ መጻሕፍትን በአግባቡ ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅመን የገጽ ለገጽ ትምህርቶችን ማሠራጨት፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን   ማበልጸግ፣ በሞባይል ስልኮቻቸው ተከታታይ ትምህርቶችን በድምጽ ወይም በጽሑፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠር፣ የግቢ ጉባኤያት ኅብረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ከግቢ ጉባኤ ከወጡ በኋላ በሥነ ምግባር የታነጹና በተመረቁበት ሙያ በብቃት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ሁል ጊዜ ራሳቸውን ለማሻሻል የሚተጉ እንዲሆኑ መንገዱን ማመላከት ያስፈልጋል፡፡ ለደረስንበት ደረጃ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ላልደረስንበት ደግሞ በሥራ ላይ የታገዘ ትጋት ሊኖር ይገባል፡፡

አሁን ተመርቀው የሚወጡ ልጆች የሚቀጥለውን የሕይወት ምዕራፍ አንድ ብለው የሚጀምሩበት ነው፡፡ በተሠማሩበት የሥራ መስክ ጠንካራና የሚመሰገኑ ባለሙያዎች እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡   እንደ እከሌ ተብለው እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በምንም ነገር ውስጥ ጠንክረው ሳይሠሩ በአቋራጭ የሚገኝ ነገር የለምና እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *