ሆሳዕና በአርያም
ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ወይም አቤቱ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ በዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት የሚከበር በዓል ሲሆን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው። ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
“አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡” (ዘካ. ፱÷፱) በማለት በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
በወንጌሉም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ “በፊታችሁ ወደአለችው መንደር ሂዱ ያን ጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛለችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የሰው ንብረት ዘርፈን እንዴት እናመጣለን? ብለው መፍራታቸውን የተረዳው ጌታችንም “ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፡፡
ልብሳቸውንም በአህያውና በውርንጫይቱ ላይ አድርገው ጌታችንም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉለት፤ ዘንባባ እና የዛፎችንም ጫፍ ጫፍ እየቆረጡ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ (ማቴ. ፳፩÷፩-፲፩) ልብሳቸውን ማንጠፋቸውም ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ክብርና ምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋ በዝማሬና በአመስጋኞች ጩኸት ተናወጠች፡፡
የሕዝቡ ጩኸትና ደስታ ያበሳጫቸው ፈሪሳዊያንና አይሁድ የሚያመሰግኑትን ዝም እንዲያሰኝ ጌታችንን ቢጠይቁትም “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል” ብሎ መልሶላቸዋል፡፡ በነቢዩ ዳዊት “ከሚጠቡ ሕፃናትና ከልጆች ምሥጋናን አዘጋጀህ” (መዝ. ፰÷፪) ተብሎ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም የአርባ የሰማንያ ቀን የዓመት የሁለት ዓመት ሕፃናትም አመስግነውታል፡፡ አዋቂዎችም ሕፃናትም “ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ማመስገናቸው “መድኃኒት መባል ለአንተ ነነይገባሃል” ማለታቸው ነው።
በበዓለ ሆሣዕና ከሚነሳው ታሪክ ውስጥ የአህያዋና የውርንጫዋ ጉዳይ ነው፡፡ ጌታችን ኪሩቤል በሚሸከሙት ዙፋን የሚቀመጥ አምላክ ሲሆን ትሁት ሆኖ በአህያ ላይ ተቀመጠ፡፡ አህያዋን ከነውርንጫዋ “ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ የሰውን ልጅ ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት የመጣ አምላክ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አህዮቹን ፈተው ማምጣታቸው ሥልጣነ ክህነታቸውን ያመለክታል፡፡ “በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” እንዲል፡፡
በአህያ ላይ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው የምትመች የማትቆረቁር የወንጌልን ሕግ ሰጠኸን ሲሉ ነው፡፡ በአህያ የተቀመጠ ሰው በፈረስ እንደተቀመጠ ሰው ፈጥኖ አያመልጥም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከፈለጉኝ አያጡኝም ሲል በአህያ ተቀምጧል፡፡
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ፲፮ ምዕራፍ ነው፡፡ ፲፬ቱን በእግሩ ሄዶ ሁለቱን በአህያዋ፣ በውርንጫይቱ ደግሞ ሦስት ጊዜ ቤተ መቅደሱን ዞሯል፡፡ ይህም የሦስትነቱ ምሳሌ፣ አሥራ አራቱን በእግሩ መሄዱ አሥርቱ ትእዛዛትን፣ አራቱ ደግሞ የአራቱ ኪዳናት ማለትም ኪዳነ ኖኅ፣ ክህነተ መልከ ጼዴቅ፣ ግዝረተ አብርሐም እና ጥምቀተ ዮሐንስን ያመለክተናል፡፡
ከግለሰብ ደጅ የተፈታችን አህያ “ጌታዋ ይፈልጋታል” ብሎ ያስፈታት በፈጣሪነቱ ወይም ስለፈጠራት ገንዘቡ ስለሆነች ነው፡፡ አህያን ያልናቀ አምላክ እኛም ከኃጢአት ርቀን ብንፈልገው ማደሪያዎቹ ሊያደርገን ፈቃዱ ነው፡፡ የአህያዋን መፈታት የፈለገ ጌታ እኛም ወደ ካህናት ቀርበን ኃጢአታችንን ተናዘን ከበደል እሥራት እንድንፈታ ይፈልጋልና፡፡
ሆሣዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። በዋዜማዎቹ ዕለታት ከቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከሆነው ከጾመ ድጓ “ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት …’’ በማለት ይዘመራል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው “ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ (መዝ. ፻፲፯፥፣፳፮) በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች፤ በቤተ ክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ከአራቱም ወንጌል ዕለቱን የሚመለከቱ ምንባባት ይነበባሉ፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፳፩፥፩-፲፯)፤ ከቅዱስ ማርቆስ (ማር. ፲፩፥፩-፲)፤ ከቅዱስ ሉቃስ (ሉቃ.፲፱፥፳፱-፴፰)፤ ከቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ. ፲፪፥፲፪-፳)።
በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!