የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና÷ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ። ማቴ. 2÷20

ኅዳር ፮ በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ያረፉበት ነው። ይህ የቍስቋም ተራራ በግብጽ ከሚገኙ ተራራዎች አንዱ ሆኖ እመቤታችን በሚጠቷ (ከስደት በምትመለስ ጊዜ) ከተወደደ ልጇና ከቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ጋር ያረፈችበት ቦታ ነው።

መዘምር ወመተርጕም ቅዱስ ያሬድ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእናቱ ከእግዝእትነ ማርያም ጋር በዚህ ቦታ ላይ ማረፉንና የቦታውን ታላቅነት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይናገራል። ቅዱስ ያሬድ ስለቦታው ታላቅነት ሲናገር <<ይቤ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳሳት ሶበ ቦዕኩ ውስተ ዝንቱ ቤት አዕረፈት ነፍስየ እምጻማ ዘረከበኒ በፍኖት ኀበ ኃደረት ቅድስት ድንግል ምስለ ፍቁር ወልዳ ኢየሱስ ክርስቶስ : የጳጳሳት አለቃ ቴዎፍሎስ ቅድስት ድንግል ከተወደደ ልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳረፈችበት ወደዚህ ቦታ በገባሁ ጊዜ በመንገድ ካገኘኝ ድካም ሰውነቴ አረፈች አለ>> ይልና <<መንግሥቱ ሰፋኒት ዘእምቅድመ ዓለም ወልደ ቅድስት ማርያም ኃሠሠ ምዕራፈ ከመ ድኩም ንጉሥ ዘለዓለም ግሩም እምግሩማን ብርሃነ ሕይወት ዘኢይጸልም ኃደረ ደብረ ቍስቋም ኃይል ወጽንዕ ዘእምአርያም : ዓለም ሳይፈጠር በመንግሥቱ ያለ በንግሥናው የነበረ (መዝ.፸፫÷፲፫) ቅድስት የምትሆን የማርያም ልጅ እንደ ደካማ ማረፊያን ፈለገ (ማረፍን የሚሻ ሥጋን ለብሷልና) ፍጥረታቸው ግሩም ከሆነ ከቅዱሳን መላእክት እጅግ የረቀቀ ግሩም : የማይጨልም ብርሃኑ ዘለዓለማዊ የሆነ የሕይወት ብርሃን(ዮሐ. ፩÷፱) በአርያም ላሉ ለሰማያውያን መላእክት ሁሉ ኃይላቸው ብርታታቸው የሆነ እርሱ በቍስቋም ተራራ ላይ አደረ>> በማለት እርሱ የመላእክት ንጉሣቸው (ሃይ. አበ ዘሄሬኔዎስ ምዕ. ፯÷፯) የሆነ በዚህ ተራራ ላይ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትሕትና መገለጡን ይመሰክራል።

ይህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት በቍስቋም ተራራ ላይ ክንፋቸውን በእመቤታችንና በተወደደ ልጇ ላይ የዘረጉበትና በሰማይ ምስጋና በምድርም ሰላም ይሁን እያሉ የዘመሩባት ናት።

ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን። በረከቷም ከሁላችን ጋር ይኑር። ለዘለዓለሙ አሜን።

ምንጭ፦ ስንክሳር ዘኅዳር ፮፣ ዝክረ ቃል ዘቅዱስ ያሬድ (ዘቍስቋም)