ኒቆዲሞስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ
እንኳን ለዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት (ኒቆዲሞስ) አደረሳችሁ/አደረሰን።
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመዋዕለ ሥጋዌው በኪደተ እግር ከቦታ ቦታ እየተመላለሰ የምስራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር። በአንድ በኩል ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዛ ስለነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲህ ይፈልጋሉ እና ነጻ አውጭ የሚፈልጉበት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለደከመ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክሞ ነበር። መሲህ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ ሰራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህም ነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መሲህ ነኝ ብሎ ሲመጣ ለመቀበል ፈቃደኞች ያልነበሩት። ለዚህም ማሳያ ይሆነን ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዐቢይ ጾም አንዱን ሳምንት አድርጋ በሰባተኛው ሳምንት እንደምታከብረው በዕለቱ በሚነበበው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ፫÷፩-፲፪ እንደተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ ጥያቄና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ይገልጽልናል።
ኒቆዲሞስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲኾን ኒኮስ ድል፣ ደሞስ ሕዝብ ነው። ትርጓሜውም ድል ማድረግ ወይም አሸናፊነት(victory of the people or conqueror of the people) ማለት ነው። ከእስራኤላዊ ወገን የሆነ እስከ መጨረሻው ከተከተሉት አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ እና ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ነው። በዚያን ጊዜ የአይሁድ አለቆች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ምልክት አሳየን” እያሉ ይፈታተኑት በነበረበት ወቅት ጌታችን ስለ ሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢያስተምራቸውም እነርሱ ባልገባቸው ጊዜ የእጆቹን ተአምራት የታመሙትን ሲፈውስ እየተመለከቱ ልባቸውን ከማቅናት አምላክነቱን ከማመን ይልቅ የኦሪት ሕጋችንን ሻረ በማለት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ጊዜ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነው (ዮሐ. ፫÷፩)፣ ፈሪሳዊው (ዮሐ. ፫÷፩)፣ መምህረ እስራኤል የሆነው(ዮሐ. ፫÷፲)፣ ምሁረ ኦሪት (ዮሐ. ፯÷፶፩) የሆነው ኒቆዲሞስ ግን እንደ ባልንጀሮቹ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይቃወም በሌሊት ወደ እርሱ ዘንድ እየሔደ ወንጌልን ይማር ነበር። ጌታችን ኢየሱስም በነፍስ የታመሙትን በቃሉ፣ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ በመምህርነቱ ሳይታበይ፤ አለቅነቱን፣ ባለጸጋነቱን፣ እና ሥልጣኑን መመኪያ ሳያደርግ፤ በልቡናው የተሣለውን እውነትን ማግኘት ፈለገ፤ ከጌታውና ከመምህሩ ከክርስቶስ ዘንድ በሌሊት ይገሰግስም ነበር። (ዮሐ. ፫፥፩) ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠትም ጀመረ፦ “መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና።” (ዮሐ.፱፥፳፬፤ ሐዋ.፲፥፴፰)።
፩. ለእምነት ከመምጣቱ አስቀድሞ በሌሊት መጣ የሚለውን ለማጠየቅ
፪. በኋላ ጌታውን ለመገነዝ የሚመጣ ነውና ለግንዘት ከመምጣቱ አስቀድሞ ወደ ጌታ መጣ ሲል ነው (ዮሐ. ፲፱፥፴፱-፵)።
፫. በመዓልት ከሚመጡ ሰዎች አስቀድሞ በሌሊት መምጣቱን ለማጠየቅ ነው።
፬. የቀን ልቡና የማይሰበሰብ ባካና ነው ኅሊና ይሰረቃል፤ የሌሊት ልቡና ደግሞ የተሰበሰበ እና ክት ነው፤ ትምህርቱን ለመረዳት በቀን ሳይሆን በሌሊት መምጣቱን ልቡናውን ለጌታ መስጠቱን ለማጠየቅ ነው።
፭. ከንቱ ውዳሴን ሽቶ ማለትም አንተ የአይሁድ አለቃ ስትሆን እንዴት ትማራለህ እንዳይባል ሰው በማይመጣበት ከሰው ተለይቶ ሊማር ሽቶ በሌሊት መጣ።
፮. ምሁረ ኦሪት ነውና ምሥጢር ሊያደላድል ነው። በቀን ጌታን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው ስለነበር ለመጠየቅ አልተመቸውም ነበር። ጌታም በአእምሮ ያልጎለመሱ ሰዎችን ያስተምር ነበርና በምሳሌ እየመሰለ ያስተምራቸው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ “እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” እንዲል አጥንት ለመቆርጠም አልደረሱም ነበር (፩ኛቆሮ. ፫፥፩-፫)።
ኢትዮጵያዊው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው እንደገለጸው “ኒቆዲሞስ ስሙ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ ወይቤሎ በጽሚት ረቢ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ ወበምጽአትከ አብራህከ ለነ ወሰላመ ጸጎከነ አንሥእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ፤ አስቀድሞ በሌሊት ወደርሱ ይሔድ የነበረ ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው በቀስታ “ሊቅ ሆይ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው። ኒቆዲሞስም ወደ እርሱ ሔደ፤ ረቢ ኢየሱስንም ሊቅ (አዋቂ) እንደሆንክ ለማስተማር ከአብ ዘንድም እንደመጣህ እኛ እናውቃለን፤ በምጽአትህም አበራህልን፤ ሰላምንም ሰጠኸን፤ ኃይልህን አንሳ፤ መጥተህም አድነን አለው።” ብሎ እንደገለጸልን ይህ ኒቆዲሞስ በትጋት ከመምህሩ ከአምላኩ እንዴት እንደተማረ እና የተማረውንም እንዴት በተግባር እንደገለጽ ያስረዳናል። ይሄንንም በማድረጉ በመትጋቱ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታው በመገስገሱ ከእግሩ ስር ቁጭ ብሎ በመማሩ “ለምሥጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት ሆነ (ዮሐ ፫÷፩-፳፩) ኒቆዲሞስ ገና ምሥጢሩ ስላልገባው “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኀፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” በማለት ለጌታ ጥያቄ አቅርቧል (ዮሐ. ፫፥፮፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፳፫) “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና” (ኤፌ. ፭፥፳፮) ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ያኔ ገና ምሥጢሩ ሊገለጥለት ግን አልቻለም ነበር። “ይህ እንደምን ይቻላል?” በማለትም ጌታን ጠይቋል በኋላ ግን በመጠኑ ሲገባው “አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው” (ዮሐ ፯÷፶፩) “ፈሪሳዊያንን ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን” ብሎ አይሁድን ተከራክሮ አሳፍሯቸዋል ወደ ፍጹምነት ደረጃ ሲደርስ ደግሞ “በሌሊት ይማር የነበረ በግልጽ ጌታን ለመገነዝ በቃ” (ዮሐ ፲፱÷፴፰) “ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ በዋለበት እየዋሉ በአደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሲማሩ የነበሩ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በስተቀር ሁሉም ሲበታተኑ በዘጠኝ ሰዓት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር። ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ሥጋ ከጲላጦስ ለምኖ የገነዘ፣ የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር”። ይህም “ወአልቦ ፍርኃት ውስተ ተፋቅሮትነ ፍጹም [ፍቅር ፍርኃትን አውጥቶ ይጥላል]” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፯፥፶፰፤ ፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፰) የኒቆዲሞስን ፍጹም ለጌታችን ያለውን ፍቅር ያሳየናል።
ኒቆዲሞስ ለብዙ ነገሮች አርአያ የምናደረገው ሲሆን ለአብነትም ያክል የሚከተለውን እናስታውስ፦
፩. ትግሃ ሌሊት (በሌሊት መትጋት) – ኒቆዲሞስ ቀን እየሠራ በሌሊት ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት ሁኖናል። ኒቆዲሞስ ወደ ጌታው ለመማር የሄደው በእኩለ ሌሊት ነበር። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰኝህ ዘንድ እነሣለሁ ይላል። (መዝ. ፻፲፰፥፷፪) ኒቆዲሞስ በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም ሰንበት በጸሎተ ቅዳሴ የሚዜመው የክቡር ዳዊት መዝሙር ፦ “ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፤ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው [በሌሊት ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ፈተንኸኝ፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፣ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር]” (መዝ.፲፮ ÷ ፫—፬) ይህን የሚያስረዳ ነው። ሊቁ ማር ይስሐቅ “ሌሊት ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው” እንዳለ ራስን በቀንም በሌሊት ከሚመጣ ፈተና መጠበቅ ይገባል። ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ “ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ጸሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው። እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ እደር” ይላል። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም “በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ እንዳለ”( መዝ ፻፴፬÷፩)። ሌሊት በባሕርይው ኅሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው። ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው። ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ ለኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን መምጣት ልጅነትን ለምናገኝበት የምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት እንደተገለጠለት እኛም በሌሊት በነግህ ጸሎት በመትጋት ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ ዕውቀት ሰማያዊ ምሥጢር ይገለጥልናል። እኛም ኒቆዲሞስን አብነት አድርገን ከዚህ የፈተና ዓለም ለማምለጥ በኦርቶዶክሳዊ ሰውነት እንድንጸና በትጋት ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀንና በሌሊት ልንገሰግስ በኪዳኑ በማኅሌቱ በቅዳሴው ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል።
፪. ጽንዐ ሃይማኖት (በሃይማኖት መጽናት) – ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ (ዮሐ ፲፱፥ ፴፰) ለታላቅ ክብር በመብቃት እስከመጨረሻው በመታመን አርአያችን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ በላከው በ፪ኛይቱ መልእክቱ እንደገለጸው ክርስትና በጅምር የሚቀር ሳይሆን እውነትን ሳንፈራ በመመስከር በተጋድሎ የምናሳልፍበት ለፈጸሙትም የድል አክሊል የሚያገኙበት ሕይወት ነው (፪ጢሞ ፬፥፰)። መከተል ብቻ ሳይሆን መታመንም እንደሚገባ ካሳዩን አንዱ ኒቆዲሞስ ነው። በዚህም በጌታችን ትምህርት ተስበው ተአምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ የተገኙት ጥቂቶቹ ውስጥ የሆነው ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ በመኖር በሃይማኖት መጽናትን ያሳየን። ቀራንዮ የምግበ ነፍስ ቦታ ናትና ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ጻድቅ ነው። የክርስትና አገልግሎት ሲመቸን የምንሳተፍበት ፈተና ሲበዛ የምንሸሽበት አይደለም። የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው። ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው። የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋሕዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር። በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምሥጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምሥጢራት አክሊል ምሥጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ። ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምሥጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር ፻፲ወ፭) ብሏል።
፫. አትሕቶ ርዕስ (ራስን ዝቅ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ (፫÷፩)፣ መምህረ እስራኤል (፫÷፲)፣ ምሁረ ኦሪት (፯÷፶፩) ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትሕትና አርአያነትን እንማራለን። በዚያን ዘመን በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ሥልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በሕዝቡ ላይ የሚመጻደቁ በጌታችንም ላይ የሚዶልቱበት የሚሳለቁበት ሕጋችን ተሻረ በማለት እውነተኛዋን ትምህርት ለመቀበል ያልወደዱበት እንዴውም ወደ ጌታ ትምህርት የሚሄዱትን የሚነቅፉበት እነርሱም የሚያምጹበት ሰዓት ነበር። ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል። ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ እያለ አስጠንቅቋቸዋል። መልካም ሥራም ማድረግ እንዳለባቸው ስለ ህጉም አስተምሯቸዋል (ማቴ ፭ ፥፳፣ ማቴ ፲፮፦ ፮)። ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው። ሹመት እያለው (የአይሁድ የምክር ቤት አባል ሆኖ) ሁሉ ሳይጎድልበት እውነትን ለማወቅ ሊቅነቱ ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ። መምህረ ትሕትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትሕትናውን ተቀብሎ “ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምሥጢረ ጥምቀትን አስተማረው።
፬. አልዕሎ ልቡና (ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ የምሥጢረ ጥምቀት ( ዳግመኛ የመወለድን ምሥጢርን) ለማወቅ ልቡናውን ከፍ ከፍ አደረገ (ዮሐ ፫÷፩-፳፩)። መጽሐፍ እንደሚነግረን ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር። ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ኅብረት ወጥቶ በትሕትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ። ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትሕትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡ ነገር ግን ጌታችን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምሥጢረ ጥምቀትን ገለጸለት። ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ ምእመናንን በማነቃቃት ልቡናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ “አልዕሉ አልባቢክሙ [ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ]” ብሎ የሚያዘው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሥጢር እንዲገለጽልን፣ ከሥጋዊው መብል ሃሳብ ወደ ሰማያዊው መብል ልቡናችንን እንድናነሣ ሲያሳስብ ነው። ምእመናንም በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ የቅዱስ ኤጲፋንዮስን ትእዛዝ ሲያሰማ “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” በማለት እንመልሳለን። ይሄም የኒቆዲሞስ ትጋት አርአያነት እኛም ክርስቲያኖች በጸጋ የተሰጡንን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ልቡናችንን ከፍ ከፍ አድርገን በመንፈሳዊ እውቀትና ልዕልና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት፣ እንዴት በጽድቅ መመላለስ እንዲገባንና ስለምንወርሳት መንግሥተ ሰማይ መማር ማወቅ እንዳለብን ያስረዳናል፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ምሳ ፱፥፲፩)
፭. ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክርነት) – ኒቆዲሞስ ማንንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ጌታችንን የሚከሱትን በእውነት መንገድ የሚሄዱትን አይሁድን አሳፈራቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ” በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል (ዮሐ.፲፰፥፴፯)። በተጨማሪም “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል (ማቴ.፲፥፴፪-፴፫)፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን” በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል (ዮሐ ፫÷፲፩)። በዚህም ኒቆዲሞስ ከጌታው የተማረውን በአይሁድ ፊት ሳይፈራ እና ሳያፍር ሥለ እውነት ሲመሰክር “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል (ዮሐ ፯፥፶-፶፪)። ምሁረ ኦሪት ነውና ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል። በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው (ሉቃ ፲፪፥ ፰)። ቤተክርስቲያን “ሰማዕታት” እያለች የምትዘክራቸው ቅዱሳን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ናቸው። በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጂ አያስመሰግንም (ማቴ ፲፥፴፪)። ሐዋርያው “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም” እንዳለ እኛም እንደ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክሮች እንሁን (፪ቆሮ ፲፫፥፰)። ስለዚህም ነው ይሄንን ሳምንት ኒቆዲሞስ ብለን ናከብር አርአያችን አድርገን የተደረገለትንም ያደረገለትንም በማሰብ ስለ እውነት መመስከር የሚገባን፡፡
አምላከ ኒቆዲሞስ ልዑል እግዚአብሔር ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን ገልጾ እንዳዳነው እና እንዳከበረው ለእኛም ምሥጢሩን ይግለጽልን፤ ማስተዋሉን አድሎ የተማርነውን አጽንተን እስከ መጨረሻው ድረስ ታምነን በጥበብ በሞገስ በምግባር በሃይማኖት ጸንተን ስሙን ለመቀድስ ክብሩን መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን ጥበቡን ያድለን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦
፩. ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ
፪. ጾመ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ
፫. መዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ
፬. https://eotcmk.org
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/በሰ/ት/ቤቶች/ ማ/መ/ማ/ቅ ሩቅ ምሥራቅ ማእከል ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል
መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
ቻይና