የዘይቱ ነገር

አንድ ሰው በጣም የሚወደው ልጅ ነበረው፡፡ ለዚህ ልጁ ሕይወትን ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ እንዴት መኖር እንደሚችል ሊያስተምረው ይጥር ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም የተሳካለት አልመሰለውም፡፡ ልጁ በፊቱ የመጣለትን ነገር በማድረግ የሚነዳና ምንም አይነት መንፈሳዊነትና ጥበብ የሞላው ሕይወት እንዳላዳበረ ገባው፡ በአካባቢው በጥበቡ የታወቀ አንድ አባት ነበረና የሕይወት ጥበብ እንዲማር ወደዚያ ጠቢብ አባት ላከው፡፡

ልጁ ወደጠቢቡ አባት በመሄድ እንዲህ አለው፣ “ሕይወቴን መንፈሳዊነትና ጥበብ በተሞላው ሁኔታ እንዴት መምራት እንዳለብኝ ለመማር ነው የመጣሁት”፡፡ ጠቢቡ “አሁን ትንሽ ስራ አለብኝ ፣ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ቆይተህ ተመለስ፡፡ እስከዚያው ግን አንድን ነገር እንድታደርግ ስራ ልስጥህ” በማለት፣ በእጁ አንድን የሻይ ማንኪያ ሰጠውና በማንኪያው ላይ ዘይትን ሞላበት፡፡ ከዚያም እንዲህ አለው ፣ “በቤተክርስቲያን ውስጥ እየተዘዋወርክ ያሉትን ድንቅ ቅርሶች በመመልከት ሁለት መጠበቅ ያለብህን ሰዓታት አሳልፍ፡፡ አንድ ነገር ግን ተጠንቀቅ፣ በፍጹም ይህ በማንኪያው ላይ ያለው ዘይት መፍሰስ የለበትም”፡፡ ልጁ አደራውን ተቀብሎ፣ ስንት ሰዓት እንደሆነ ከቃኘ በኋላ ቤተክርስቲያኑን ለመጎብኘት በእጁ ዘይት የሞላበትን ማንኪያ ይዞ በቀስታ በመራመድ ወጣ፡፡

ልጁ ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ጠቢቡ አባት ተመለሰ፡፡ ጠቢቡ ካስገባው በኋላ ፣ “በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በግድግዳው ላይ የተሰቀለውን የጥንት ስእል አየኸው? የታወቁ የገዳሙ አባቶች አስር ዓመት የፈጀባቸውን የአትክልት ስፍራ አየኸው? የዓለምን እውቀት በሙሉ የያዘውንስ የመጽሐፍት ቤት አየኸው?” ልጁ አፍሮ አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ለካ ለሁለት ሰዓታት ሲዘዋወር ትኩረቱ ሁሉ በእጁ የያዘው ማንኪያ ላይ የተቀመጠው ዘይት እንዳይፈስ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሊያስተምረው የፈለገው ነገር እንደተሳካለት ገባውና፣ “እንደገና በማንኪያ ያለውን ዘይት ይዘህ ሂድና እነዚህ የነገርኩህንና ሌሎችም አስገራሚ ቅርሶች እንደገና ተመልክተህ ተመለስ” አለው፡፡

ሁለተኛ እድል ስላገኘ ትንሽ ተንፈስ ያለው ወጣት ተመልሶ ወጣ፡፡ ለሁለት ሰዓታት ጉብኙቱን ካጧጧፈ በኋላ በፈገግታ ተመለሰና ያየውን ሁሉ ለጠቢቡ ነገረው፡፡ እስኪጨርስ ጠብቆ ጠቢቡ፣ “እንዳይፈስስ ያልኩህ ዘይት የት አለ?” አለው፡፡ ልጁ፣ ጎንበስ ብሎ በእጁ የያዘውን ማንኪያ ሲያየው ለካ ዙሪያውን በመመልከት ሲደነቅ ዘይቱን ችላ ስላለው ዘይቱ ሙልጭ ብሎ ፈስሷል፡፡ ጠቢቡ አባትም እንዲህ አለው፣ “ስኬታማ ሕይወት ማለት እምነትና ምግባር የተሞላውን ሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡

እምነትና ጥበብ የተሞላበት ሕይወት ማለት ዙሪያህን እያየህ በማድነቅ ስትኖር በእጅህ ላይ ያለውን አደራ አለመዘንጋት ነው”፡፡ በሕይወታችን ልክ እንደ ዘይቱ በጥንቃቄ መያዝ ያለብን አደራዎች አሉን፡፡ ከዚያው ጋር ደግሞ ልክ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንዳሉት አስደሳች ጥንታዊ ቦታዎች የመደሰትን እድል የሚሰጡን ሁኔታዎች አሉ፡፡ እውነተኛ ሰው እነዚህን ሁለቱን በሚዛናዊነት የያዘ ሰው ነው፡፡

ስንጫወት ፣ ስንዝናና ፣ ስንደሰትና በማሕበራዊው ግንኙነታችን ውስጥ ያለውን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ ስንፈነድቅበት ፣ ከዚያ የተነሳ በእጃችን ላይ ያለው አደራ ችላ እንዳይባልና ዘይቱ እንዳይፈስ መጠንቀቅ የጥበብ ሁሉ ጥበብ ነው፡፡ ልክ ይህ ወጣት በእጁ ያለውን ዘይት በዙሪያው ካለው ታላላቅ ነገርን የማየት እድል ጋር አስታርቆና ሚዛናዊ አድርጎ መውጣትና መግባት እንደነበረበት እኛም እንዲሁ! በዙሪያችን ካለው ጨዋታና መዝናናት ብዛት የተነሳ የተለመዱ ችላ በማለት ማፍሰስ የማይገቡን የአደራ “ዘይቶች” . . .

” ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።”

†የማቴዎስ ወንጌል 25:4†

ምንጭ-ቬነሲያ ገጽ