ታኅሣሥ ፪፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ከደጋጎቹ ቅዱሳን አባቷና እናቷ ኢያቄምና ሐና የተወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ቀን የከበረ ነው፡፡ በበጎ ምክር በእግዚአብሐርም ፈቃድ ይህ ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ኢያቄምና ሐና “….ሆዷ ዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን እንስጥ” ብለው በመማከር መባዕም ጨምረው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡

ከዚያም እንደደረሱ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስን አግኝተው ስለ ሥዕለታቸው በነገሩት ጊዜ መጥቅዕ ደውሎ ሕዝቡን በመሰብሰብ “የምግቧ ነገር ይያዝልኝ” አለ፤ ቀጥሎም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስተ ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፤ ካህኑ ዘካርያስም ለእርሱ የመጣ ስለመሰለው “ዛሬስ ክብሬን በሰው ፊት ሊገልጽልኝ ነው” በማለት ሊቀበል ሲነሣ መልአኩ ግን ወደ ላይ ራቀበት፤ የእርሱ ተከታይ ስምዖንም በተመሳሳይ መልኩ “እንኪያስ ለእኔ የመጣ ይሆናል” በማለት ሊቀበል ሲቀርብ ለእርሱም ራቀበት፤ ቀጥሎም የቀሩት ካህናቱ፣ አባትና እናቷ እንዲሁም ሕዝቡ በሙሉ በተራ ቢቀርቡም መልአኩ ራቀባቸው፤ ይህን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ እንዲህ አለ፤ “ጥበበ እግዚአብሔር አይመረምርምና ምናልአባት ለዚህች ብላቴና የመጣ እንደሆነ እንይ፤ ሐና ትተሻት እልፍ በይ” አላት፤ እርሷም እንደተባለችው ትታት እልፍ አለች፤ እመቤታችንም ድክ ድክ እያለች እናቷን መከተል ስትጀምር መልአኩ ፈጥኖ ወርዶ፣ አንድ ክንፉን አንጽፎ፣ አንድ ክንፉን ጋርዶ በሰው ቁመት ልክ ከመሬት ከፍ አድርጎ መግቧት ዐረገ፡፡

ካህናቱም ይህን በተመለከቱ ጊዜ “የምግቧ ነገር ከተያዘለንማ ትግባ እንጂ” ብለው ደናግል ከሚኖሩበት ቦታ/መካነ ደናግል/ አስገቧት፡፡ ቅድስት እናታችን ድንግል ማርያም ታኅሣሥ ሦስት ቀን በሦስት ዓመቷ ብፅዓት ተደርጋ የእግዚአብሔር አገልጋይ ትሆን ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥታለች፡፡ ገና በሕፃንነቷ በተቀደሰችው የአምላክ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንድትኖርም ተደረገ፡፡ ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ እየተመገበች መላእክት እየጎበኟት ፲፪ (ዐሥራ ሁለት ዓመታት) በቤተ መቅደስ ኖራለች፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ /ክፍል አንድ/፣ ገጽ ፹፭-፹፮