ስብከት
ቅድስት ቤተክርስቲያን አምልኮቷን የምትፈጽምበት እጅግ የተደራጀ ሥርዐተ አምልኮ አላት፡፡ ከዚህ ሥርዓተ አምልኮ አንዱ ክፍል ዓመታዊ የምስጋና መርሐ ግብር እና የሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ የተደራጀ ነው፡፡
ሀ. ቀናትን መሠረት በማድረግ
በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ጥልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጊቶች እና ክንውኖች በዓመቱ ውስጥ ቀናት ተመድበውላቸው በበዓላትና በአጽዋማት መልክ ይታሰባሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እነዚህን በዓላትና አጽዋማት የምታከብርበት ዓመታዊ መርሐ ግብር እና በበዓላቱና በአጽዋማቱ የሚታሰበውን ነገር አስመልክቶ አባላቶችን የምታስተምርበት ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡
እንደዚህ ባለ መርሐ ግብር ከሚታሰቡት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮችና ያስተማራቸው ትምህርቶች /ፅንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሳኤ፣ ዕርገት፣ ደብረ ታቦር፣ምጽአት/፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት /ልደቷ፣ ዕረፍቷ፣ ቤተመቅደስ መግባቷ፣ ድንቅ ተአምራት ያደረገችባቸው ዕለታት/፤፣ የቅዱሳን በዓላት /ልደታቸው፣ ዕረፍታቸው፣ ተአምራት ያደረጉባቸው. . / ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለ. እሁዶችን /ሳምንታትን/ መሠረት በማድረግ
መስከረም 8 ቀን እሁድ ቀን ቢውል ያ እሁድ «ዘካርያስ» ተብሎ ይጠራና የመጥመቁ ዮሐንስ አባት የካህኑ የዘካርያስ ነገር ይታሰብበታል፡፡
ከመስከረም 9 እስከ 17 ያለው እሁድ /እና በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ፍሬ» ይባላል፡፡ በዚህ እሁድ እግዚአብሔር ለምድር ፍሬን እንደሚሰጥ ይታሰባል፡፡
በዚህ መልኩ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሑዶች በሙሉ ምን እንደሚታሰብ የሚገልጽ መርሐ ግብርና ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ ይህም በተለያዩ ወቅቶች ያለውን የአየር ጠባይ እና የግብርና እንቅስቃሴ ያገናዘበ ነው፡፡
«ስንክሳር» የሚባለው መጽሐፍ ከመስከረም አንድ እስከ ጳጉሜን 5/6 ድረስ የሚታሰቡ ቅዱሳንን እና ክንውኖችን ዝርዝር ታሪክ ይዟል፡፡
«ግጻዌ» የሚባለው መጽሐፍ በየዕለቱ /በየእሁዱ/ ከሚታሰበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት /ከመልእከታተ ጳዉሎስ፣ ከሰባቱ መልእክታተ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከወንጌል/ መርጦ ያቀርባል፡፡
የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትም /ድጓ፣ ዝማሬ፣ምዕሪፍ፣ ዝማሬ መዋስዕት/ በዚህ መርሐ ግብር መሠረት የተዘጋጁ ሲሆኑ በየዕለቱ ስለሚታሰቡት ነገር ዝርዝር እና ጥልቅ የሆኑ ትምህርቶችን እና ምስጋናዎችን የያዙ ናቸው፡፡
በዚህ «ስብከት» በሚለው ዓምድ ሥር ይህንን መርሐ ግብር፣ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት አድርገን ትምህርቶችን እናቀርባለን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓምድ ስር የሚቀርቡት ትምህርቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
1. ሳምንታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር በእያንዳንዱ እሁድ/ሳምንት/ የሚታሰቡትን ጉዳዮች አስመልክቶ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
2. ወቅታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር ቀናትን መሠረት አድርገው ከሚከበሩት በዓላት መካከል ዋና ዋናዎቹን በተመለከተ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
3. ሌሎች– ይህ ንዑስ ዓምድ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ስብከቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡
አዘጋጆቹን በጸሎት በማሰብ፣ በሚቀርቡ ስብከቶች ላይ አስተያየት በመስጠትና ስብከቶችን በመላክ ለዚህ ዓምድ መጠናከር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡ እግዚአብሔር ሐሳባችንን እንድንፈጽም ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡