መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::




የጌታችን ልደት እና የመላእክት አገልግሎት
ሊቃውንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እና ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ከምሥጢራት ዅሉ በላይ ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ከማድነቅ ሌላ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በመገረም ይህን ጥበብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ኾኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚኾን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፡፡ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው የእግዚአብሔርን ሰው የመኾን ምሥጢር እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹በጐለ እንስሳ ተወድየ አሞኀ ንግሡ ተወፈየ ወከመ ሕፃናት በከየ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ፤ በእንስሳት በረት ተጨመረ፡፡ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፡፡ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ቍ. ፲፯)፡፡
ለብርሃነ ልደቱ መዘጋጀት
ዛሬም እኛ በኀጢአት ስንዋከብ ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ኾነናል፡፡ አንዳንዶቻችን በምናስበው ዐሳብ፣ በምንሠራው ሥራ ውስጥም የአምላክን ሰው የመኾን ምሥጢር ረስተነዋል፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ ነው፡፡ ስለዚህ ያጣነውን ይህን ጸጋ ለማግኘትና ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡ ስለዚህ እስኪ እኛም በእነዚህ ሳምንታት የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ኹኔታ እየዘከርን፣ ያለንበትን አኗኗር እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ለማየትና ለማግኘት እንትጋ፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንስጥ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃንም ‹‹አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፥ ተቅበዝብዘናልና እባክህ ሰብስበን›› እያልን እግዚአብሔርንእንማጸነው፡፡
ኖላዊ ኄር
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል፡፡ ምንደኛ (ቅጥረኛ) እረኛ ግን ለበጎቹ አይጨነቅም፤ በጎቹም አያውቁትም (ዘካ. ፲፩፥፬-፭፤ ዮሐ. ፲፥፩-፲፪)፡፡ ዛሬም በእናት ቤተ ክርስቲያናችን የተሾሙ አባቶች እንደነሙሴ፣ እንደነዳዊት፣ እንደነብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚጨነቁ ሊኾኑ ይገባል፡፡ እኛ ምእመናንም እግዚአብሔር አምላካችን መልካም እረኞችን እንዳያሳጣን መለመን ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ራሳችንን ለሃይማኖታችን ማስገዛት፣ መልካም እረኞችንም አብነት ማድረግና መከተል ይጠበቅብናል፡፡
ክርስቲያናዊ ኑሮ በዘመነ አስተምሕሮ
በባሕሩ ዓለም ውስጥ የምትገኘው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰዎች በፈቃደ ሥጋቸው ተሸንፈው ባመጡት ጥላቻ፣ ኑፋቄ፣ ክህደት፣ ፍቅረ ንዋይ፣ በአጠቃላይ በልዩ ልዩ የኀጢአት ማዕበልና ሞገድ እየተናወጠች ናት፡፡ ይህን ማዕበልና ሞገድ ጸጥ በማድረግ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ሰላምንና ጽድቅን ማስፈን የሚቻለውን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ኾነን ‹‹ጌታ ሆይ እንዳንጠፋ አድነን?›› እያልን እንማጸነው፡፡ የሰላሙ ዳኛ፣ የሰላሙ መሪ፣ የሰላሙ ጌታ፣ የሰላሙ ንጉሥ፣ የሰላሙ ባለቤት እርሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን፣ መረጋጋትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ካወጀ በቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር፣ አንድነት ሰላም ይሰፍናልና፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላዎች መጠበቅ እንደሚገባ አሳሰቡ
ብፁዕነታቸው ይህን መልእክት ያስተላለፉት በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዐርባ ምንጭ ከተማ በደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተካሔደው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ‹‹እናንተ ግን ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ፡፡ በውጭ ባሉት ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል›› (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፲፫) በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ መናፍቃንን አወገዙ
ተወግዘው የተለዩት ግለሰቦች ‹ምስሉ ፈረደ›፣ ‹ፍጥረቱ አሸናፊ›፣ ‹ያሬድ ተፈራ›፣ ‹በኃይሉ ሰፊው› እና ‹እኩለ ሌሊት አሸብር› እንደሚባሉ፤ ከእነርሱ መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ መዓርገ ቅስና፤ ያሬድ ተፈራ እና እና በኃይሉ ሰፊው መዓርገ ዲቁና እንደ ነበራቸውና ሥልጣነ ክህነታቸው እንደ ተያዘ፤ የሰንበት ት/ቤት አገልጋይ የነበረውን እኩለ ሌሊት አሸብርን ጨምሮ ከዚህ በኋላ ዅሉም ግለሰቦች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት እንደ ተለዩና ‹አቶ› ተብለው እንደሚጠሩ ብፁዕነታቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቍጥር 148/11/2010፣ በቀን 01/03/2010 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ በተሐድሶ ኑፋቄ ውስጥ ኾነው ሕዝበ ክርስቲያኑን እያደናገሩ የሚገኙ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትንና ምእመናንን በአጠቃላይ የዐሥራ ሦስት ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ከክህነት አገልግሎት፤ ምእመናኑ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አባልነት መታገዳቸውን ያሳወቀ ሲኾን፣ በደብዳቤው ከተጠቀሱ ግለሰቦች መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ ይገኙበታል፡፡
ጾመ ነቢያት
ይህን ምሥጢር በማሰብ በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋይዜማ ድረስ እንድንጾም አባቶቻችን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይህ ጾም፣ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲኾን፣ በስያሜም ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወቅቱ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ የተፈጸመበት ስለ ኾነም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት በጾሙበት ማለት ከልደተ ክርስቶስ በፊት ባለው ወቅት ጾመዋልና፡፡
በአውሮፓ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ሥርዓተ ትምህርት ተመረቀ
እንደ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ገለጻ ወጥ የኾነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር በአውሮፓ የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናትን ለማስተማር ከባድ ከሚያደርጉት ኹኔታዎች ተቀዳሚው ምክንያት ሲኾን፣ ይህን በመገንዘብ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ባወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል ባለሙያዎችን በመመደብ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል፡፡
ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ታስቦ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማርኛ ቋንቋ እና የመዝሙር ጥናት የተሰኙ አምስት የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ሲኾን፣ የትምህርቶቹ አርእስትና ይዘቶችም በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላትንና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
‹‹በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤›› (ዘፀ. ፴፫፥፫)፡፡
ቅዱሳኑን መመልከት እግዚአብሔርን መመልከት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የከበረ ዕለት፣ እስራኤል በመንገድ ላይ እንዳይጠፉ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት፣ ጥበቃና መሪነት ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ መግባታቸውን የምናስብበት በዓል ነው፡፡ ቤቱ የእርሱ ቢኾንም መታሰቢያነቱን ለወዳጆቹ፣ ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ እግዚአብሔር ይሰጣል (ኢሳ. ፶፮፥፬)፡፡ ልዩ ከኾነው ስሙ ጋር ስማቸው አብሮ እንዲነሣ ያደርጋል፡፡ አድሮባቸው ሥራ ሠርቷልና እንዲሁ አይተዋቸውም፤ እንዲታሰቡለት ያደርጋል እንጂ፡፡ በቤቱም በፊቱም እነርሱ ሲታሰቡና ሲከብሩ ደስ ይሰኛል፡፡ ምንጩም ፈቃጁም እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚፈሩ፣ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ፤›› እንዳለ ነቢዩ (ሚል. ፫፥፲፮)፡፡ ቅዱሳኑ ስሙን በፍጹም አስበዋልና እግዚአብሔር ደግሞ ስማቸው በሌሎች (በእኛ) እንዲታሰብ ፈቅዷል፡፡ ከዚህ አኳያ ከእስራኤል ዘሥጋ ነጻ መውጣት ጋር ‹‹ስሜ በእርሱ ስለ ኾነ›› (ዘፀ. ፳፫፥፳) የተባለለት ቅዱስ ሚካኤል፣ በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን መታሰቢያው ይከበራል፡፡
አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – የመጨረሻ ክፍል
ፓትርያርክ አትናቴዎስን በግፍ ወደ ግዞት ቦታ እንዲሔዱ የፈረደባቸው የቂሣርያው ጉባኤ፣ ‹‹አርዮስ ተጸጽቶ ከክሕደቱ መመለሱን የሚያመለክት መጣጥፍ አቅርቧል›› በሚል ሰበብ አርዮስን ከግዝቱ ፈቶ ነጻ አወጣው፡፡ አትናቴዎስ ወደ ግዞት በመላካቸው አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን ምቹ ጊዜ አግኝተው ስለ ነበር አርዮስን ወደ ሀገሩ ወደ እስክንድርያ ለመመለስ ይሯሯጡ ጀመር፡፡ የአርዮስ ነጻ መውጣትም ንጉሡ በሚኖርበት በቊስጥንጥንያ በይፋ እንዲከበር በማሰብ አርዮስ በወዳጆቹና በደጋፊዎቹ ታጅቦ ወደ ቊስጥንጥንያ እንዲሔድ አደረጉ፡፡ በዚያም በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ከቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጋር እንዲቀድስና ወደ ክርስቲያን አንድነት መግባቱ በይፋ እንዲታወጅ ዝግጅት ተደርጎ ሳለ ሆዱን ሕመም ተሰምቶት ወደ መጸዳጃ ቤት ሔዶ በዚያው ቀረ፡፡ አርዮስ ስለ ዘገየባቸው ደጋፊዎቹ ሔደው ቢያዩት ሆድ ዕቃው ተዘርግፎ ሞቶ አገኙት፡፡ በዚህም ‹‹የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት በአርዮስ ላይ ተገለጠ›› ተብሎ በብዙ ሰዎች ዘንድ ታመነ፡፡ ሆኖም በአርዮስ ሞት የተበሳጩ አንዳንድ የአርዮስ ደጋፊዎች የእግዚአብሔርን ፍርድ አይተው ከክሕደታቸው በመመለስ ፈንታ ‹‹አርዮስ የሞተው በመድኃኒት ተመርዞ ነው›› ብለው ማውራትና ማስወራት ጀመሩ፡፡