መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ጾመ ፍልሰታ
በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ዅላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡
ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ካለፈው የቀጠለ
‹‹ምእመናን ጾም (ሱባዔ) ከመጀመራቸው በፊት የሥጋን ኮተት ዅሉ ማስወገድ አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ዅሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባዔ የሚያቋርጣቸውን ጉዳይም አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡ በኋላም ሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ተሰጣቸው ጸጋ መጠን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመን መርዳት የማይችል ደግሞ ምክርና ሐሳብ በመስጠት ክርስቲያናዊ ድርሻውን ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂት በመመገብ፣ ብዙ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን ያህል እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተም ሥርዓት ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ ልብስ መኾን የለበትም፡፡››
ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ
‹‹‹ፍልሰታ ለማርያም› የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾን ‹ፍልሰታ› ማለት ደግሞ ‹ፈለሰ› ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ፍልሰት› ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን (መፍለስን) ያመለክታል፡፡ እመቤታችን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደ ተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር የእመቤታችንን ሥጋ እንዲገልጥላቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን በማየት በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለኾነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቍረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡››
የ፳፻፱ ዓ.ም ጾመ ፍልሰታን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ በረከት
በዘመነ ብሉይም ኾነ በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር ሞገስና ጸጋ አግኝተው ለቅድስና ደረጃ የበቁ ቅዱሳን ዅሉ ጸሎታቸውና ተማኅጽኖአቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይኾን ለዓለሙ ዅሉ እንደሚተርፍ ቅዱስ መጽሐፍ በትምህርትም ኾነ በተግባር ያረጋገጠውና የመዘገበው ነው፡፡ ይልቁንም ‹‹እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ‹ምልእተ ጸጋ ነሽ፤ ደስ ይበልሽ››› ብሎ እግዚአብሔር በመልእክተኛው ያረጋገጠላት ቅድስት ድንግል ማርያም ባላት ከፍተኛ የእግዚአብሔር ባለሟልነት በጸሎቷ፣ በአማላጅነቷና ወደ እግዚአብሔር በምታቀርበው ተማኅጽኖ ግዳጃችንን እንደምትፈጽም የቃና ዘገሊላው ምልጃዋና የተገኘው በረከት በቂ ማስረጃችን ነው፡፡
ዘመነ ክረምት – ክፍል ሦስት
የባሕር እና የወንዞች ሙላትም የምድራዊ ሕይወት መከራን፣ ሥቃይን፣ ፈቃደ ሥጋን (ኀጢአትን) እና ፈተናን፤ ዳግመኛም በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት የሚመጣ ሰማያዊም ኾነ ምድራዊ ቅጣትን ያመለክታል፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የተአምራቱን ብዛት ይገልጻል፡፡ ‹‹ወዓሠርከኒ ውስተ ማይ ብዙኅ ወኢይትዐወቅ ዓሠርከ፤ መንገድህ በባሕር ውስጥ፤ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤›› እንዳለ መዝሙረኛው (መዝ. ፸፮፥፲፱)፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር መንፈስ በመላው ዓለም ሰፍኖ እንደሚኖርና በሃይማኖት በምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው እርሱን የሚሹ ዅሉ ይቅርታውን እንደ ውኃ በቀላሉ እንደሚያገኙት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ‹‹እስመ ማይ ለኵሉ ርኩብ›› እንዲሉ ሊቃውንት፡፡ እኛም የኀጢአት ባሕር እንዳያሰጥመን፤ የኀጢአት ወንዝም እንዳይወስደን ተግተን ነቅን ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ እንደ ውኃ ለዅሉም የሚፈሰው የእግዚአብሔር ይቅርታው ደርሶን የመንግሥቱ ወራሾች እንኾን ዘንድም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን እናስገዛ፡፡
ማኅበረ መነኮሳቱ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ
ምንኵስናን ከሊቅነት፣ አባትነትን ከሥራ ጋር አስተባብረው የያዙት የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የቅኔ መምህሩ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ እንደ ገለጹልን በገዳሙ አካባቢ የሚገኘውን በጎርፍ የተሸረሸረ ሸለቆ በመከባከብ በ፲፱፻፹ ዓ.ም የተጀመረው የልማት ሥራ ገዳሙን በፌዴራል ሁለተኛ፤ በክልል ደግሞ አንደኛ ደረጃ እንዲያገኝና የክብር ሜዳልያ እንዲሸለም አድርጎታል፡፡ ዳሩ ግን ይህ የልማት ውጤት በበረዶው ምክንያት ከጥቅም ውጪ ኾኗል፡፡ ፍራፍሬውና ደኑም ተጨፍጭፏል፡፡ የጠበል መጠመቂያ ቦታዎች ተናውጠዋል፡፡ ንቦችም ከቀፎዎቻቸው ወጥተው ተሰደዋል፡፡ የመነኮሳቱና አብነት ተማሪዎች መኖርያ ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሰባ ሄክታር በላይ የሚገመት ሰብል በበረዶው ናዳ መውደሙን ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ተጋድሎ
በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡
ዘመነ ክረምት – ክፍል ሁለት
ዝናም ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበል ቤት እንዲያፈርስ፤ ንብረት እንዲያወድም በክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያጋጥም ፈተናም በእምነት መዛል፣ በመከራ መያዝ፣ መቸገር፣ መውጣትና መውረድ ያጋጥማል፡፡ ዝናም ለጊዜው እንዲያስበርድና ልብስን እንዲያበሰብስ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ ያዝላል፡፡ ነገር ግን ዝናም፣ ጐርፍና ማዕበል ጊዜያቸው ሲደርስ ጸጥ እንደሚሉ ዅሉ፣ ምድራዊ ፈተናም ከታገሡት የሚያልፍ የሕይወት ክሥተት ነው፡፡ ስለዚህ ዅላችንም እምነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት በውኃ ሙላትና በማዕበል ከሚመሰል ውድቀት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ዝናም ሲመጣ የውኆችን ሙላትና ጐርፉን ሳንፈራ ወደ ፊት የምናገኘውን ምርት ተስፋ እንደምናደርግ፣ በሃይማኖታችን ልዩ ልዩ ፈተና ሲያጋጥመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ዅሉንም በትዕግሥት እናሳልፍ፡፡
ኤጲስ ቆጶሳቱ ሳይለግሙ ምእመናንን እንዲያገለግሉ ፓትርያርኩ አሳሰቡ
‹‹እግዚአብሔር የሰጣችሁን ሕዝብ በቀንም በሌሊትም ከእርሱ ሳትለዩ፣ በዅለንተናዊ ሕይወታችሁ ባለ አቅማችሁ ዅሉ ሳትለግሙ አገልግሉት፡፡ ከስደት፣ ከእንግልት ተገላግሎ የልማት ኃይል በመኾን አገሩን እንዲገነባ፤ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዲጠብቅ ያለመታከት አስተምሩት፡፡ ከመንፈሳዊ መሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ኤጲስቆጶስነት ድረስ እየመገበና እየተንከባከበ ለታላቅ ክብር ያበቃችሁን ሕዝብ የልቡን ሃይማኖታዊ ትርታ እያዳመጣችሁ በወቅቱ እየደረሳችሁ አስተምሩት፤ አጽናኑት፡፡ ልጆቹን በተኩላዎች ከመነጠቅ አድኑለት፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከሐሺሽ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከሱሰኝነት፣ ከሥራ ፈትነትና ከመጤ ጎጂ ባህል እንዲላቀቅ አድርጉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ከሃይማኖት አባቶች የሚፈልገው ይህንኑ ነው፡፡››
ማኅበረ ቅዱሳን በአፋን ኦሮሞ ያሳተማቸው መጻሕፍት በከፊል
ማኅበረ ቅዱሳን በአፋን ኦሮሞ ካሳተማቸው መጻሕፍት መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤