«የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ህዝብ ትሰጣለች»

አራተኛ እሑድ

 /ማቴ.21-46/

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ የተወለደው፣ ያዳገው፣ እየተመላለሰም የመንግስተ ሰማያትን መቅረብ ወንጌል /የምስራች/ ያስተማረው ለዚህ ዓላማ አስቀድሞ ባዘጋጀው ሕዝብ /በአይሁድ/ መካከል ነው፡፡
አምላክ ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በእውነት እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ /አምላክ/ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ይህ ነገር እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯቸው በተስፋ የሚጠብቁ ህዝቦች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ከአብርሃም፣ ከይስሃቅና ከያዕቆብ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ይህንን ህዝብ የማዘጋጀቱን ሥራ ጀመረ፡፡

በኋላም ይህንን ህዝብ አምላክነቱን በግልጽ በሚያስረዳ መልኩ በብዙ ተአምራት ከግብጽ በማውጣት፣ ህግ እና የአምልኮ ሥርዓት በመስጠት፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር በማስገባት ነገሩን አጠናከረ፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ነቢያትን በመላክ፣ በማስተማርና ትንቢት በማናገር ቀስ በቀስ ይህ ህዝብ ዓለምን የሚያድነውን የመሲህን መምጣት ተስፋ እንዲያደርግ አደረገ፡፡ እንግዲህ አምላክ ሰው ሆኖ የተወለደው ይህ ሁሉ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ አይሁድ መሲሁ የሚወለድበት ቦታ ቤቴልሔም እንደሆነ ሳይቀር ከተናገሩት ትንቢቶች የተነሳ ያውቁ ነበር፡፡ (ማቴ. 2-5)

ነገር ግን ጌታችን ሰው ሆኖ በተናገረው ትንቢት መሠረት በተወለደ ጊዜ አይሁድ ፣ በተለይም ካህናቱና ጸሐፍቱ /የመጻሕፍት መተርጉማኑ/ ሊቀበሉት አልወደዱም፡፡ «ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል» በማለትም ይከሱት ሊያጠፉትም ይሞክሩ ነበር፡፡

ጌታችን ግን የሰውን ድካም የሚያውቅና የሚሸከም አምላክ በመሆኑ በአንድ በኩል ይህን ችግራቸውን ለመቅረፍ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ አለመሆኑን የሚያስረዱ ነገሮችን /ራሱን ዝቅ በማድረግ ሳይቀር/ እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ማንነቱን ተረድተው ይቀበሉትና ይድኑ ዘንድ አምላክነቱን የሚገልጡ ተአምራትን በማድረግ ከ 3 ዓመታት በላይ አስተማራቸው፡፡ እነርሱ ግን ልባቸውን አደነደኑ፡፡

ጌታችንም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ካደረገ በኋላ  ይህንን ዓለም ሞቶ የሚያድንበት ወቅት በደረሰ ጊዜ አምላክነቱንና የመጣበትን ዓላማ በግልጽ ማሳየትና መናገር ጀመረ፡፡ በአህያ እና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ንጉስነቱን፤ መሲህነቱን በሚገልጥ አኳሃን «በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው» እየተባለለት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፣ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ «ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት» እያለ በቤተመቅደሱ ንግድ የሚነግዱትን በታላቅ ስልጣን አስወጣቸው፡፡(ማቴ 21)

እነዚህንና ሌሎች አምላክነቱን በግልጽ የሚመሰክሩ ነገሮች ማድረጉን ሲመለከቱ ወደ እርሱ እየቀረቡ «እስኪ ንገረን ይህንን በማን ስልጣን ታደርጋለህ፤ ወይስ ይህን ስልጣን የሰጠህ ማን ነው ብለው ጠየቁት» /ማቴ. 21-23/

ጌታችንም ጊዜው ደርሷልና ማንነቱን፣ የመጣበትን ዓላማ እና ወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን በምሳሌ እያደረገ በግልጽ ነገራቸው፡፡ ከእነዚህ ምሳሌዎች አንዱ በእግዚአብሔር እና በሕዝበ እስራኤል /በአይሁድ/ መካከል ያለውን ግንኙነት፣ የእርሱንም ማንነት ያስተማረበት በወይኑ ቦታ ያሉ ገበሬዎች /ጢሰኞች/ ምሳሌ ነው፤ ጌታችን እንዲህ አላቸው፡፡ /ማቴ. 21-35-96/

«ሌላ ምሳሌ ስሙ የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፣ መጥመቂያም ማሰለት ግንብም ሰራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ ሀገር ሄደ፡፡ የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፣ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ፡፡ ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤  ሌላውንም ወገሩት፡፡ ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ እንዲሁም አደረጉባቸው፡፡ በኋላ ግን ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው፡፡ ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ፡፡ ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት፡፡ እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚወጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋ » እርሱም « ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል » አሉት፡፡

ጌታም እንዲህ አላቸው…… « የእግዚአብሔር መንግስት በእናንተ ትወስዳለች፡- ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች »…. የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉ ሣለ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለዩት ፈሩአቸው፡፡

በዚህ ምሳሌ ወይን ተብለው የተጋለጡት አይሁድ ናቸው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 34-5-1 ላይ

 
«ከግብጽ የወይን ግንድ አወጣህ፣
እህዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ፣
በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፣
ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች
……..
ቅርንጫፎችዋም እስከ ባህር፣ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች» /መዝ. 79-8-11/

ያለውን ቅዱስ አውግስጢኖስ ሲተረጉም የሚከተሉትን ነጥቦች ያስቀምጣል፡
– ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ የተባለው እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ስላወጣቸው ነው፡፡
– አህዛብን አባረርህ ፤ እርስዋንም ተከልህ የተባለው እግዚአብሔር የተስፋይቱን ምድር ለእስራኤል የሰጠው አሞራውያንን፣ ኬጤያውያንን፣ ኢያቡሳውያንን፣….. ሌሎቹንም በዚያ የነበሩትን ህዝቦች አባሮ በመሆኑ ነው፡፡
– በፊትዋም ስፍራ አዘጋጀህ፣ ሥሮችዋንም ተከልህ የተባለው እስራኤል ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር ርስት ሁና ስለተሰጠቻቸው /ስለተተከሉባት/ ነው፡፡
– ቅርንጫፎችዋ እስከ ባህር፣ ቡቃያዋም እስከ ወንዙ ዘረጋች የተባለው ለእስራኤል የተሰጣቸው የተስፋይቱ ምድር የተዘረጋቸው ከሜዲትራንያን /ታላቁ/ ባህር እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ በመሆኑ ነው/ ዘፍ-34-5፣ መዝ-72-8/ /st.Augstine, Exposition on the Psalms, /
ቅዱስ ዳዊት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነቢያትም ህዝበ እስራኤልን በወይን መስለው አስተምረዋል፡፡

ጌታችንም በወይን ቦታ፣ በወይን ቦታ ገበሬዎች እና በወይን ቦታ ባለቤት መስሎ የተናገረው በዘመናት የነበረውን በመግቢያችን ያየነውን የአይሁድን እና የእግዚአብሔርን ግንኙነት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ምሳሌ አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርት /ስብከት/ ላይ «ጌታችን በዚህ ምሳሌ በርካታ ነገሮችን አመልክቷል» ካለ በኋላ የሚከተሉትን ይዘረዝራል፤ /Homily 68

– ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔር ለህዝቡ የነበረው ቸርነት ጠብቆት መግቦትና ቸርነት
– እነርሱ /አይሁድ/ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ገዳዬች እንደነበሩ /ሰራተኞች ነቢያትን መግደላቸው/
– እነርሱ በዘመናት ሁሉ ክፉ ቢሆኑም እግዚአብሔር ግን ልጁን ከመላክ ወደ ኋላ እንዳላለ
– የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አምላክ አንድ እንደሆነ
– ጌታ አይሁድ እንደሚገድሉት አስቀድሞ እንደሚያውቅና እነርሱም ይህ ምን አይነት ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው
– የአይሁድን ከተስፋው መውጣትና የአህዛብን የእግዚአብሔር ሕዝብ መባል፡፡

በመጀመሪያ ከዚህ ምሳሌ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር እናያለን፡፡ ወይኑን የተከለው፣ ቅጥር የቀጠረለት፣ መጥመቂያ የማሰላት ፣ የወይኑ ባለቤት ነው፡፡ ይህ ግን የገበሬዎቿ ሥራ ነበር፡፡ እርሱ ግን ሌላውን ሁሉ ሰርቶ ለእነርሱ መጠበቅን ብቻ ተወላቸው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከግብጽ አውጥቶ ህዝቡ ባደረጋቸው ጊዜ ለእነርሱ ባለው ፍቅር ምክንያት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን መግባተን፣ ህግ ፣ ከተማ፣ መቅደስ፣ መሠዊያ፣ የአምልኮ ሥርዓት በመስጠቱ የሚያመለክት ነው፡፡

ይህንንም ሰጥቶ ባለቤቱ ርቆ ሄዷል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ህግጋቱን አለመፈፀማቸውን፣ ቃል ኪዳናቸውን አለመጠበቃቸውን በየቀኑ አለመቆጣጠሩን ትዕግስቱ መብዛቱን የሚያመለክት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ የወይኑን ፍሬ ማለትም መታዘዛቸውን፣ መገዛታቸውን አምልኮታቸውን ለመቀበል አገልጋዩቹን ነቢያትን ላከ፡፡ እነርሱ ግን ይህንን ፍሬ  አልሰጡም፡፡ ነቢያቱን ገደሉ፣ አቃለሉ እንጂ ፤ መልሶም በዚህኛው ስራቸው ተጸጽተው ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ ሌሎች አገልጋዬችን ላከ፡፡ እነዚህንም ግን እንደ ቀደሙት አደረጓቸው፡፡ ከክፉ ነገራቸው ፈቀቅ አላሉም፡፡

በኋላ «ልጄንስ ያፍሩት ይሆናል» ብሎ ልጁን ላከው፡፡ ነበያቱን ሁሉ ባልተቀበሉ ጊዜ ነቢያት ከሠሩት የበለጠ የሚሰራው የነቢያት አምላክ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሁኖ መሲህ ተብሎ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ «…ልጄንስ ያፍሩት ይሆናል» ማለቱ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በኋላ እነርሱ የሚያደርጉትን (እንዳይቀበሉት) አለማወቁን አይደለም፡፡ እርሱስ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ ጌታ በምሳሌው እንዲህ ያለው እነርሱ ሊያደርጉ ይገባቸው የነበረውን ለማመልከት ነው፡፡ አዎ፤ ወደ እርሱ ሮጠው መሄድና ይቅርታ ወጠየቅ ነበረባቸው፡፡

እነርሱ ግን ምን አደረጉ፤ «እንግደለው» ተባባሉ፡፡ ጌታችን እንደሚገድሉት ማወቅን ብቻ ሳይሆን የት እንደሚገድሉት /ከከተማ ውጪ/  ማወቁንም «ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት» በማለት አመልክቷል፡፡

ጌታችን ይህንን ካደረገ በኋላ በራሳቸው ላይ እንዲፈርዱ አደረጋቸው፡፡ ይህም ነቢዩ ናታን ንጉስ ዳዊት በኦርዮ ላይ በደል ከፈፀመ በኋላ በራሱ ላይ እንዲፈርድ እንዳደረገው ነው፡፡

እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው «የወይኑ አትክልት ጌታ በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል»፤ እነርሱም እንዲህ ብለው በራሳቸው ላይ ፈረዱ፤

«ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል፡፡»

ጌታም  የፈረዱት በራሳቸው ላይ መሆኑን በማመልከት «የእግዚአብሔር መንግስት ከእናንት ትወሰዳለች፣ ፍሬዋንም ለሚያደርግ ህዝብ ትሰጣለች» በማለት እነርሱ አስቀድመው ለእግዚአብሔር ህዝብ ለመሆን የተመረጡ ቢሆንም በእምቢተኝነታቸውና መድኃኒታቸውን ባለመቀበላቸው ምክንያት እንደማይድኑ፤ ከእነርሱ ይልቅ ድኅነት ተስፋውንም ሆነ ትንቢቱን ለማያውቁ አሕዛብ እንደምትሆን ነገራቸው፡፡
 
በዚህ ጊዜ አይሁድ ምሳሌዎቹን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን፤ የፈረዱትም በራሳቸው ላይ መሆኑን ተረዱ፡፡ ይህንን ተረድተውም ግን ከክፋታቸው ለመለሱ አልወደዱም ቅዱስ ማቴዎስ እንደሚነግረን ህዝቡን እንደ ነቢይ ስላዩት ህዝቡን ፈርተው ተውት እንጂ ሊገድሉት ፈልገው ነበር፡፡ በስልጣን ፍቅር እና በከንቱ ውዳሴ ፍትወት ዓይናቸው ታውሮ ነበርና ምሳሌው፣ ትንቢቱም ሆነ የህዝቡ ጌታን መቀበል ሊመልሳቸው አልቻለም፡፡

ስለዚህ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጌታን ለመግደል ምክራቸውን /ውሳኔያቸውን/ ፈፀሙ፤ በምክራቸው መሠረትም ይዘው ሰቀሉት፡፡ ከተስፋው፣ ከድኅነቱ ወጥተው ቀሩ፡፡

«የእግዚአብሔር  መንግስት ከእርሱ ተወሰደች፡፡» ተስፋውን ትንቢቱን የማያውቁ አሕዛብ ግን የክርስቶስን  ወልደ እግዚአብሔርነትና መድኃኒትነት ተቀብለው የእግዚአብሔር ሕዝቦች ክርስቲያኖች ተባሉ ፤ «የእግዚአብሔር መንገስት ፍሬዋን ለሚያደርግ ሕዝብ ተሰጠች»   

ወስብሐት ለእግዚአብሔር