«ለራሱ ገንዘብ የሚያመቻች በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ባለጠጋ ያልሆነ ሰው እንዲህ ነው»

ሦስተኛ እሑድ

 

 /ሉቃ. 12.21/

ጌታችን በይሁዳ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ከህዝቡ አንድ ሰው ቀርቦ፡- «መምህር ሆይ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው» አለው፡፡ ጌታችን ግን ወደዚህ ምድር የመጣው፣ ለመለኮታዊ /ሰማያዊ/ ዓላማና የሰውን ልጆች ለማዳን እንጂ በሰዎች ምድራዊ ኑሮ ገብቶ ሃብትን ለማከፋፈል ባለመሆኑ፣ ዳግመኛም እርሱ የመጣው ራስን ለሰው መስጠትን፣ ፍቅርንና አንድ መሆንን የምትሰብከውን ወንጌልን ለመስራት በመሆኑ «አንተ ሰው ፈራጅና አካፋይ እንዲሆን በላያችሁ ማን ሾመኝ?» በማለት ይህንን ሊያደርግ እንደማይወድ ከተናገረ በኋላ አጋጣሚውን በመጠቀም አብረውት ለነበሩት እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፤ «የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፤ ከመጎመጀትም ሁሉ ተጠበቁ»፡፡
ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፡- «አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት፡፡ እርሱም፡- ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ እንዲህ አደርጋሁ ጎተራዬን አፍርሼ ሌላ እሰራለሁ በዚያም ፍሬዬንም በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፡፡ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ ዕረፊ፤ ብዩ፤ ጠጪ፤ ደስ ይበልሽ፤ እላታለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔር ግን አንተ ሰነፍ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፡፡ ይህስ የሰበሰብከው ለማን ይሆናል? አለው፡፡ ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው፡፡»

ጌታችን በምሳሌ ካስተማረ ከዚህ ትምህርት ሁለት ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡

1. ስለ ሀብት ያለን አመለካከትና የሃብት አጠቃቀማችን ምን ሊሆን እንደሚገባ፤- ይህ የጌታችን ትምህርት ለሐብት ያለን አመለካከትና የሐብት አጠቃቀማችን ክርስቲያናዊ መሆን  እንዳለበት የሚያስተምር እንጂ ሐብትን እና ባለሐብትነትን ወይም ባሐብቶችን የሚነቅፍ አስፈላጊ አይደሉም የሚል አይደለም፡፡

ሐብት /ገንዘብ/ መሰብሰብ፣ መማርና ማወቅና በተለያየ ደረጃ መመረቅ፣ ወይም እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ለአንድ ሰው የሕይወቱ ግብ ሊሆኑ አይገባቸውም፤ አይችሉም፡፡ ቁሳዊና አእምሮአዊ ሐብቶች ሲገኙ ጠቃሚ የሚሆኑትና ትርጉም የሚኖራቸው እንደ የአንድ ዓላማ /ግብ/ ማስፈፀሚያ መንገዶች /ስልቶች/ ሲታሰቡ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነና፣ ለምን እንደምንፈልጋቸው፣ ሲገኙም ለምን እንደምናውላቸው በትክክል ሳናውቅ /ሳናስብ/ ብንሰበስባቸው ሲገኙ ትርፋቸው «ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ» ብሎ መጨነቅና ከዚያም ያለ ዓላማ የተሰበሰቡ ስለሆኑ በእነርሱው መገኘት ብቻ መደሰት መጀመር «አንቺ ነፍስ ለብዙ ዘመን የሚቀር በርከት አለሽ… ደስ ይበልሽ» ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ስንኖር ዓላማችን ድኅነት /መዳን/ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ሐብት /ቁሳዊ፣ አእምሮአዊ…/ ለማግኘት ማሰብና ለዚህም መውጣት፣ መውረድ፣ መድከም የሚገባን፤ ካገኘነውም በኋላ ልንጠቀምበ የሚገባን፤ ከዚሁ አለማችን ከድኅነት አንጻር /ወደዚያ እንደሚያደርስ መንገድ/ ብቻ ነው፡፡ ባዕለ ጠግነታችን እንዲህ ያለ ካልሆነ «አንተ ሰነፍ»፣ «በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልሆንክ» አስብሎ ያስወቅሳል፡፡

ትክክለኛው የሀብት አጠቃቀምና «በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ የሚያደርግ» አካሄድስ እንዴት ያለ እንደሆነ?

ቅዱስ አውግስጢኖስ /Augstine/ እና ቅዱስ አምብሮስ /Ambrose/ የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜዎቻቸው ላይ የሚከተለውን አስተምረዋል፤

ቅዱስ አውግስጢኖስ

ጠቢቡ ሰሎሞን  በመጽሐፈ ምሳሌ «ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብት ነው» ይላል /ምሳ-13-8/ ይህ ቂል ሰው ግን እንዲህ ያለ /ለነፍሱ ቤዛ የሚሆን/ ሃብት አልነበረውም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው ለድሆች እርዳታ በመስጠት /እፎይታ በመሆን/ ነፍሱን እያዳናት አልነበረም፡፡ የሚጠፉ ሰብሎችን /ፍሬዎችን/ እያሰባሰበ ነበር፤ እደግመዋለሁ፤ በፊቱ ሊቆም ግድ ለሆነው ለጌታ ምንም ነገር ባለመስጠቱ ምክንያት ለመጥፋት ተቃርቦ ሳለ እርሱ ግን የሚጠፉ ሰብሎችን ይሰበስብ ነበር፡፡ ለፍርድ ሲቀርብና «ተርቤ አላበላኝም» የሚለውን ቃል ሲሰማ የት ይገባ ይሆን? ነፍሱን በተትረፈረፈና አላስፈላጊ በሆነ ምግብና ድግስ ለመሙላት እያቀደና እነዚያን ሁሉ የተራቡ የድሆች ሆዶች በልበ ሙሉነት ችላ እያለ ነበር፡፡ የድሆች ሆዶች ከእርሱ ጎተራ በተሻለ ሀብቱን በደኅንነት ሊጠብቁለት የሚችሉ ቦታዎች መሆናቸውን ግን አልተረዳም ነበር፡፡ …ሃብቱን በድሆች ሆድ ውስጥ ቢያስቀምጠው ኑሮ በምድር ላይ በእርግጥም ወደ አፈርነት ይለወጥ ነበር፤ በሰማያት ግን ከምንም በላይ በደኅንነት ይቀመጥለት ነበር፡፡ ለሰው ነፍስ ቤዙው ሀብቱ ነው፡፡

ቅዱስ አምብሮስ

ይህ ሰው እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ሳይረዳ ለእርሱ ጥቅም በሌለው መልኩ ሀብትን እያከማቸ ነው… የዚህ ዓለም ነገሮች ሁሉ የሚቀሩት በዚህ ዓለም ነው፤ ምንም ያህል ሃብት ብንሰበስብም ለወራሾቻችን ትተነው እንሄዳለን፡፡ ከእኛ ጋር ልንወስዳቸው የማንችላቸው ነገሮች ደግሞ የእኛ አይደሉም፡፡ የሞቱ ሰዎችን የሚከተላቸው መልካም ምግባር ብቻ ነው፡፡ ርኅራሄና በጎነት ብቻ ነው፡፡ ወደ መንግስተ ሰማያት መርቶ የሚወስደን ይህ ነው፡፡

በማይረባው ገንዘብ በመንግስተ ሰማያት ያማሩ መኖሪያዎችን እንግዛ ነው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ አስተምሮናል «የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ለራሳችሁ ወዳጆችን አድርጉ፡፡» /ሉቃ. 16-9/
/Ancient Christian Commentary on Scripture/ volume3 /Luke/ page 208/

2/ ሁለተኛው ከዚህ ጌታችን በምሳሌ ካስተማረው ትምህርት የምንማረው ያለነውና የምንኖረው እያንዳንዷን ቀን የምናሳልፈው በእርሱ ቸርነት መሆኑን መዘንጋት እንደሌለብን ነው፡፡

ይህ ሰው ልክ ዕድሜውን ሰፍሮ በእጁ የያዙ ይመስል፣ ወይም ዕድሜ እንደ ሰብል ተዘርቶ ከመሬት ይገኝ ይመስል እንዲህ ሲል እናገኘዋለን፡፡ «አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለው፣ ዕረፉ ብዬ ጠጪ ደስ ይበልሽ….»

ነገር ግን እንኳን ለብዙ ዘመናት ሊኖር ቀርቶ ያቺን ሌሊት አልፎ የሚቀጥለውን ቀን ፀሐይ እንኳን እንደማያይ ተነገረው፡፡ «አንተ ሰነፍ፤ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፡፡» ተባለ፡፡

ይህ የሁላችንም ችግር ነው ስለ ኑሯችን፣ አገልግሎታችን እና ህይወታችን ስናቅድ የእግዚአብሔርን ቸርነት ረስተን ሁሉ ነገር በእጃችን ያለ እናስመስለዋለን፡፡ ይህ ግን አለማስተዋልና «አንተ ሰነፍ» አስብሎ የሚያስወቅስ ነው፡፡

ማድረግ የሚገባንን ግን ከቅዱስ ዳዊት እንማራለን፤ ቅዱስ ዳዊት ደካማነቱን በመታመን እንዲህ እያለ በትሁት ልብ ይዘምራል፤

«ሰው በዘመኑ እንደ ሳር ነው
እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል
ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና
ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና»
የእግዚአብሔር ምህረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፡፡» /መዝ.102-11/

እኛም እንደርሱ ህይወታችን አንድ ጊዜ ወጥቶ ወዲያው ፀሐይ እንደሚያጠወልገው ሳር፣ ከበቀለ በኋላ ለዓመት እንኳን መቆየት እንደማይችል የዱር አበባ ቆይታው አጭርና በእኛ እጅ ያልተወሰነ መሆኑንና ደካማነታችንን ማሰብ ይገባናል፡፡ ይህንን አስበንም እንደ ቅዱስ ዳዊት፤

አባት ልጆቹ እንደሚራራ እግዚአብሔር እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤
ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና…አቤቱ አፈር እንደሆንን አስብ፤
ሰው ዘመኑ እንደ ስር ነው፡፡»

እያልን ደካማነታችንን በማመን ፈቃዱን፣ ቸርነቱን ልንጠይቅ፤ ይገባናል፡፡ ዕቅዳችንም፤ ቅዱስ ያዕቆብ እንዳስተማረን ከአፍ ሳይሆን ከልብ «እግዚአብሔር ቢፈቅድ… ይህንንና ያንን እናደርጋን /ያዕ.4-15 / የሚል መሆን አለበት፡፡

 
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር