ቤተ ክርስቲያን

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

ቤተ ክርስቲያን ሦስት ትርጉም ያለው በዘርፍና በባለቤትነት የተቀመጠ ስም ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቲያኖች መገናኛ መሰብሰቢያ በዓት ማለት ነው፡፡ይህም ክርስቲያኖች በአንድነት የሚጸልዩበት፣ የሚሰግዱበት፣ ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታና የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡(ኢሳ. 56፥7 ፣ ኤር. 7፥10-11 ማር. 11፥17 ሉቃ.19፥46 ) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የራሳቸው የጸሎት ቤት በተወሰነ ቦታ አላደረጉም፣ የተለየ ሕንጻ አላሰሩም ነበር፤ ነገር ግን ወደ አይሁድ ቤተ መቅደስ በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡እንዲሁም በግል የክርስቲያን ቤቶች በተለያዩ ክፍሎች እየተገናኙ ይጸልዩ ቅዱስ ቁርባንን ያዘጋጁ ነበር፡፡ክርስትና እየተስፋፋና እየታወቀ ከሄደ በኋላ ቤተ ክርስቲያንም በፊልጵስዩስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጌታችን ፈቃድ ከተሰራ በኋላ ክርስቲያኖች ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉት በቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆን ጀመረ፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩ ምኩራብና መቅደስም አገልግሎታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አስረከቡ፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ስንል ሁለተኛው ትርጉም የክርስቲያኖች አንድነት «ማኅበረ ምዕመናን» ማለት ነው፡፡ ይህም በአንድ ጌታ  በአንድ እምነት እና በአንድ ጥምቀት አምነው የተጠመቁ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኙ፣  በዚህ ምድር በአንድ አሳብ እና ተስፋ የሚኖሩ፣ በመጪው ዓለምም በእግዚአብሔር መንግስት በዘለዓለማዊ አንድነት የሚኖሩ ክርስቲያኖችን የሚያመለክት ነው፡፡
በሦስተኛውና የመጨረሻው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ስንል እያንዳንዱን ምዕመን ማለታችን ነው፡፡ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ አታውቁምን ? ›› በማለት የገለጸው ነው፡፡ (1ቆሮ.6፣19) ክርስቶስ ለሰው ልጆች የፈጸመውን የማዳን ሥራ አምኖ  በስመ ሥላሴ የተጠመቀ እያንዳንዱ ምዕመን ማኅደረ ክርስቶስ «ቤተ ክርስቲያን» ይባላል፡፡
አሁን አሁን በሚታየው የክርስቲያኖች አስተሳሰብ ከመጀመሪያው ትርጉም ውጪ ለተቀሩት ሁለት ትርጉሞች ትኩረት ሲነፈጋቸው ይስተዋላል፡፡ ለሕንፃ  ቤተ ክርስቲያን  ከምንሰጠው አክብሮት ጋር ሲነጻጸር ለግል ክርስቲያዊ ሕይወታችን እና ለአንድነታችን የምንሰጠው ትኩረት አናሳ ሆኗል፡፡ክርስቲያናዊ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነና ይህን አንድነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግና የሚያስገኘውን ዋጋ እንዲሁም ይህን አንድነት የማይጠብቁ የሚያገኛቸውን ቅጣት አስመልክቶ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ የሰጠውን ትምህርት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ስለ ቤተ ክርስቲያን (ምዕመናን) አንድነት
ስለዚህ ሁሉንም እኔ አንድ ሰው ፈጽሞ በትጋት ስለ አንድነት እንደሚሠራ ሠርቻለሁ፡፡ መከፋፈልና መጥፎ አመለካከት ባለበት እግዚአብሔር አያድርም፡፡ ነገር ግን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንጂ ምንም ዓይነት ሁከት እና ጥል እንዳታደርጉ እመክራችኋለሁ፡፡ እንድነትና ስምምንት በመካከላችሁ ይኑር፡፡ በአንድነት ጽኑ፡፡ አንዱ ለሌላው ይጸልይ፤ ይህም ለሁላችሁ ይገባልና በተለይ ካህናት ጳጳሱን ማበረታታት አለባቸው፡፡
ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ሞትን በማሸነፉና ሰይጣንን ድል በመንሳቱ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው አንድነት ተመልሶለታል፡፡ ይህን ሊያደርግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ስለነበረ የእግዚአብሔር ሰው መሆን የግድ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ነገር ክርስቶስን ማክበር ይገባናል፡፡ እርሱም እኛን ያከበረን ነው፡፡በአንድ ላይ በአንድነት በመታዘዝ ፍጹም አንድ ወደ ሆነ አስተሳሰብና አመለካካት ትመጣላችሁ፡፡በዚህም ስለ አንድ ነገር ሁላችሁም አንድ አይነት የሆነ ንግግር ትናገራላችሁ፡፡የክርስቲያን የመጀመሪያ ጠባይ መሆን ያለበት አንዲት በሆነች እምነት ፍጹም አንድ የሆነና ራስ ወዳድ ባልሆነ መንፈስ መዋደድ ነው፡፡
ለቅዱስ ፖሊካርፐስ በላከው መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡- ለአንድነት ትኩረት ስጥ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና፤ እግዚአብሔር አንተን እንደ ያዘህ ሁሉንም በደንብ ያዛቸው፤ በሕይወትህ እንደ ፍጹም ሯጭ ሁን፡፡ ሥራው ድካሙ ብዙ ነው፤ ነገር ግን የሚገኘው የበለጠ ነው፡፡
ክርስቶስ በሞትና በሰይጣን ላይ ድል በማድረጉ ምዕመናን ከአምላክ ሕይወትንና ፍቅርን አግኝተዋል፡፡እንዲሁም ከወንድሞቻቸው ጋር በክርስቶስ አንድ ሆነዋል፡፡በክርስቶስ ላለን ሕይወት እምነት የመጀመሪያው ነው፤ ፍቅር ግን የመጨረሻው ነው፡፡ የሁለቱም አንድነት እግዚአብሔር ነው፡፡ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡ለእኛ ሕይወትን እንደ ሰጠን ፍቅርንም ሰጥቶናል፡፡በዚህ ፍጹም ፍቅራችሁ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እንዳለን በዚህ ማወቅ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ ከሌላው ጋር በአንድነት በመዋደድ ቅድስና ይፈጽማል፡፡
በመካከላቸሁ ማንኛውንም ዓይነት መከፋፈል እንዳገኝ አልፈልግም፡፡ ማንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለያየትንና መከፋፈልን የሚያመጣን ሰው የሚከተል እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ማንም ሰው እንግዳ በሆነ አስተሳሰብ የሚነዳ ከሆነ ክርስቶስ ስለ እኛ በተቀበለው በሕማሙ የማያምን ነው ፡፡ በጥቂት አላዋቂ ሰዎች ክፉ ንግግር አጠቃላይ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሰደብ የለበትም፡፡ ‹‹ በሌሎች መካከል በእነርሱ ግብዝነት ስሜ ይሰደባል ›› እንደ ተባለ፡፡(ኢሳ.52፣5)
በንስሐ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ በምህረትና በርህራሄ መቀበል ይገባል፤ ከዲያብሎስ ወጥመድ ያመልጡ ዘንድና በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በእርሱ መንግስት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኙ ዘንድ፡፡ወንድሞች ሆይ አትታለሉ፡፡ራሱን ከእውነት የሚለየውን ሰው የሚከተለው ቢኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ ሐሰትን ከሚናገርና ከሚያስተምር ሰው ራሱን የማይለይ ሰውም እርሱ በሲኦል ይፈረድበታል፡፡ መልካም ከሆነው እንዳንለይ ክፉ ከሆነው ደግሞ እንድንሸሽ ግዴታ ነውና፡፡
ነገር ግን ሁላችሁም መከፋፈል በሌለበት በአንድ ልቡና፣ ሙሉ ፈቃድ ባለው ሕሊና አንድ ሁኑ፡፡ በሰላማችሁ ጊዜም ሆነ በችግር ላይ ስትሆኑ፣ በሐዘንም ሆነ በደስታችሁ ጊዜ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ጳጳሱ ፈቃድ ምንም ነገር አታድርጉ፡፡ ሰውነታችሁን እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጠብቁ፡፡ አንድነትን ውደዱ፤ መለያየትን ግን ፈጽማችሁ ተጸየፉ፡፡
ጌታችን በፈቃድ ከአባቱ ጋር አንድ ስለሆነ ያለ አባቱ ምንም ነገር እንዳልሠራ ፣ ‹‹ እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም››፤   (ዮሐ.5፣19) ይላልና፤ እናንተም ቄስም ቢሆን ዲያቆንም ቢሆን ምዕመንም ቢሆን ማንም ቢሆን ያለ ጳጳሳት ምንም ነገር መሥራት የለባችሁም፡፡ እንዲሁም ለብቻ በመለየት የሚሠራ ምንም ዓይነት ሥራ መቼም ቢሆን ትክክል ይሆናል ወይም አግባብነት ይኖረዋል ብላችሁ አታስቡ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቦታ (በቤተ ክርስቲያን) በመሰባሰብ አንድ ጸሎት፣ አንድ አስተበቁዖት፣ አንድ ሕሊና፣ አንድ ተስፋ ንጹሕ በሆነ ፍቅርና ደስታ ይኑር፡፡ ይህም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ሊኖር ይገባል፡፡ የሁላችን አባት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለን ሁሉ ሁላችሁም ወደ አንድ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገስግሱ ወደ አንድ ምስዋዕ ቅረቡ፡፡
የተለያዩ ሲሆኑ ነገር ግን ተስማምተውና ተዋሕደው ጣዕመ ዜማ ያለውን ግሩም መዝሙር እንደሚያሰሙ መዘምራንና አውታሮች እኛም በስምምነትና አንድ በሚያደርግ ፍቅር ተገጣጥመን ለእግዚአብሔር ልዩ የፍቅርንና የአንድነትን መባዕ የምናቀርብ ልንሆን ይገባናል፡፡ ጌታችን ‹‹አንተ አባት ሆይ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ›› (ዮሐ.17፣21) ብሏልና፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ነውር ነቀፋ በሌለበት አንድነት አንድ ብትሆኑና የክርስቶስ አካል እንደመሆናችሁ ከእርሱ ጋር ተዋሕዳችሁ ብትኖሩ ጠቃሚያችሁ ነው፡፡
መከፋፈልና ቁጣ ባለበት በዚያ እግዚአብሔር አያድርም ፡፡ በንስሐ ለሚመለሱት ግን በእውነት ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ቢመለሱ ጌታ ይቅር ይላቸዋል፡፡ምንም ዓይነት ነገር በሁከትና በጠብ እንዳታደርጉ እመክራችኋለሁ፤ ለእርሱ አስተምህሮ እንደሚገባ ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን መሠረት በፍቅርና በሰላም እንጂ፡፡
የአንድና የሁለት ሰው ጸሎት ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ኅብረትና አንድነትማ ምን ያህል ጠቀሜታና ኃይል ይኖረው ይሆን? በሥርዓትና በአምልኮት ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ጋር አንድ አልሆንም የሚል በትዕቢት ራሱን ከቤተ ክርስቲያን እየለየ ነው፡፡ ከልባችን እርስ በእርስ መከራከርን አስወግደን ለእግዚአብሔር በአንድነት እንገዛ፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔርን ለማመስገን ዘወትር በአንድ ላይ ትሰባሰቡ ዘንድ አስተውሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአንድነት በምትሰባሰቡ ጊዜ የሰይጣን ኃይል ይደክማል፤ እርሱ ያሰበው የጥፋት ዓላማውም በእምነታችሁ በአንድነት ይከሽፋል፤ ይጠፋል፡፡ ‹‹ መጋደላችሁ ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› (ኤፌ.6፣12) በሰማይም ሆነ በምድር ያለውን ጦርነት ጸጥ ረጭ አድርጎ ከሚያጠፋው ከሰላም የበለጠ የከበረ ነገር የለም፡፡ ማንኛውንም የምትሠሩትን ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሆነና እርሱን ደስ በሚያሰኝ አንድነትና ስምምነት አድርጉት፡፡
ወንድሞች ሆይ አትሳቱ፡፡ ቤተሰብን የሚያፈርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡(1ኛ ቆሮ.6፣9) የሰዎችን ቤተሰቦች የሚያፈርሱ ሞት የሚፈረድባቸው ከሆነ፣ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መስቀልን እስኪሸከም ድረስ የወደዳትንና የሞተላትን ቤተ ክርስቲያን በመለያየት የሚያፈርሱትንማ ምን ያህል ቅጣት ይጠብቃቸው ይሆን ? ስለዚህ ጥበብ የጎደለውን እረኛ የሚከተልና ስለ እውነት ፈንታ ሐሰትን የሚቀበል ቢኖር ይቀጣል፡፡
ከእውነተኛው እረኛችሁና መምህራችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ለሌላ ለማንም ጆሯችሁንና ልባችሁን አትስጡ፡፡በመካከላችሁ ወገናዊነትና መለያየት ቦታ አያግኝ፡፡ አንድ ጌታ አንድ እምነት አንድ ጥምቀት አለና፡፡(ኤፌ.4፣4)
ስለዚህ የብርሃን ልጆች እንደ መሆናችሁ ከመለያየትና ከክፉ ትምህርት ሽሹ፡፡ ነገር ግን እረኛችሁ ባለበት እንደ በጎች እርሱን ተከተሉ እንጂ፡፡(ዮሐ.10፣7) ተአማኒና እውነተኞች የሚመስሉ ብዙ ተኩላዎች አሉና ፡፡ እነርሱም ሰዎችን ክፉ በሆነ ምኞትና ሥጋን በሚስቡ ነገሮች ወደ እግዚአብሔር የሚገሰግሱትንና ወደ እርሱ ለመቅረብ በመንገድ ላይ ያሉትን ሰዎች እየጠለፉ ወደ ጥፋት ይወስዷቸዋል፡፡(2ኛ ጢሞ.3፣6) እንዲህ ያሉት በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ ምንም ቦታ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ የሆነውን አንድነታችሁን ለመጠበቅ ትጉ፡፡ አንዳችሁ ሌላውን በትህትና ሆኖ በፍጹም ትዕግሥት ይሸከመው፤ እግዚአብሔር ለእኛ እንዲህ እንደ ሆነ ያህል፡፡

ምንጭ፡ወ/ሮ ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ሐዋርያዊ ጳጳስ ወሰማዕት(ገጽ 80 – 85)