“የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” (ማቴ.፳፬፥፯)
የምድር መናወጥ ወይም መንቀጥቀጥ በታሪክ መመዝገብ ከተጀመረበት ዘመን አንሥቶ እስከደረስንበት ዘመን ድረስ ከባድ የሚባል በሬክተር ስኬል ሰባት ነጥብ ሁለት እና ከዚያ በላይ በዐሥርት ዓመታት ቢበዛ አንድ ጊዜ ነበር የሚከሠተው፡፡ ከ፲፱፻ ዓ.ም ወዲህ ግን ክብደቱም ብዛቱም የሚያደርሰውም ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና መሠረተ ልማታዊ ውድመቱና ጥፋቱ ጨምሯል፡፡ ከ ፲፱፻ እስከ ፲፱፻፵፱ በየዐሥርት ዓመቱ የሚደርሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ሦስት እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡ በ፲፱፻፶ዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ዘጠኝ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል፡፡ በ፲፱፻፸ዎቹ ፻፳፭ አደገኛ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ስንመለከተው ምድራችን በመሬት መንቀጥቀጥ ብዛትና ክብደት እየፈረሰች መሄዷ የማይቀር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡