ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ዮሐ.14፥18
ግንቦት 24/2004 ዓ.ም.
ይህንን የተስፋ ቃል ለቅዱሳን ሐዋርያት የተናገረው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ደቀ መዝሙርነት የተጠሩት በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው ሳለ ነው፡፡ በየሙያቸው ሥራ እየሠሩ ከሚተዳደሩበት ሥፍራ ሁሉ ደርሶ ፈጣሪያችን በቸርነቱ ለከበረው የወንጌል አገልግሎት ጠራቸው፡፡ “ወእንዘ ያንሶሱ መንገለ ባሕረ ገሊላ፤ ርእየ ክልኤተ አኅወ፥ ስምዖንሃ ዘተሰመየ ጴጥሮስ ወእንድርያስሃ አኅዋሁ እንዘ ይወድዩ መርበብቶሙ ውስተ ባሕረ፤ እስመ መሠግራነ እሙንቱ፡፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ንዑ ትልዉኒ፤ ወእሬስየክሙ ትኩኑ መሠግራነ ሰብእ፡፡…. በገሊላ ባሕር ዳር ማዶ ሲመላለስ ሁለት ወንድማሞችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፣ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና፡፡ ጌታችንም “ለጊዜው በእግር ተከተሉኝ ፍጻሜው በግብር ምሰሉኝ፡፡ እኔም ሰውን እንደ ዓሣ ወንጌልን እንደ መረብ፣ ይህን ዓለም እንደ ባሕር አድርጋችሁ እንድታስተምሩ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ያን ጊዜ መርከባቸውንና መረባቸውን ትተው ተከተሉት” የተቀሩትም ሁሉ እንዲህ ባለ ጥሪ ጠራቸው /ማቴ.4፥18-22፣9፣ ዮሐ.1፥46፤ 44፥51/
ቅዱሳን ሐዋርያትም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጌታችን በዋለበት ውለው ባደረበት እያደሩ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፡፡ በኋላም የተጠሩለትን አገልግሎት በመፈጸም ክብርን አግኝተውበታል /ማቴ.13፥42፣ ሕዝ.47፥10/፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ትተው ጥለው የተከተሉትን ሐዋርያትን “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” አላቸው፡፡ አጽናኝ ጰራቅሊጦስ ይሰጣችኋል፡፡
“እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሏቸዋል፡፡ /ሉቃ.24፥49፣ ዮሐ.15፥26፣ 16፥7 ሐዋ.1፥4/ በዚሁ መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን ጋር ሆነው በኢየሩሳሌም በአንድነት በጸሎት እየተጉ ሳለ አምላካችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በእያንዳንዳቸው አድሮባቸዋል፡፡
እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ፥ በአእምሮ ጎለመሱ፥ሕጹጻን የነበሩ ፍጹማን፥ ፍሩሃን የነበሩት ጥቡዓን ሆኑ ባንድ ልሳን ይናገሩ የነበሩ ሰባ አንድ ልሳን ተገለጸላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሩሳሌምን ባንድነት ዓመት በኅብረት አስተማሩ፡፡ “ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም” እንዲል፡፡ ዓለምን 12 አድርገው ተካፍለው በእየ ሀገረ ስብከታቸው ሄደው አምልኮተ እግዚአብሔርን አስተማሩ፡፡ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መለሱ፡፡
በዓለ ሃምሳ በኦሪት የነበረው ገጽታ
እስራኤል ከሀገራቸው ወጥተው በልደት ለ430 ዓመታት መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው ኖረው በሙሴ መሪነት በፋሲካው በግ ከሞተ በኲር ድነው ምድረ ርስትን እንዲወርሱ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ መጀመሪያ ወር /ሚያዚያ 14 ቀን/ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ /ዘጸ.12፥1-13/ ይህን በዓል ካከበሩ ሰባት ሱባኤ ቆጥረው በማግስቱ /በሃምሳኛው ቀን/ ደግሞ የእሸት በዓል /በዓለ ሠዊትን/ ያከብራሉ፡፡ ይህም በኦሪቱ እንደተገለጸው የስንዴ በኲራት አጨዳ መታሰቢያ፣ የምስጋና ጊዜ ነው፤ /ዘጸ.23፥16፣ ዘሌዋ.23፥15-18፣ ዘኁ.28፥26/
በዓለ ሠዊት በበዓለ ሃምሳ
ጌታችን እርሱ ባወቀ ይህንኑ በዓል በበዓለ ሃምሳ /በበዓለ ጰራቅሊጦስ/ እንዲተካ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ወዲህ በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡ ጰራቅሊጦስ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ የሆነው አካሉ መጠሪያ ስም ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ በችግር ጊዜ ተራዳኢ፣ በሃዘን ጊዜ አጽናኝ፣ መዘንጋት ላለበት ልብ አስታዋሽ፣ በአላውያን ፊት ተከራካሪ ጠበቃ ማለት ነው፡፡ /ዮሐ.14፥16-26፣ 15፥26፣ 16፥7/ ዘመነ ጰራቅሊጦስ የሚባለው ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ ከሃምሳኛው ቀን ጀምሮ ቀጥሎ እስከ አለው እሑድ ድረስ ያለው 8 ቀን ነው፡
“ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ” የሐዋ.ሥራ.2፥2
በዓለ ሃምሳ በተባለው በዓል መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ባለ ድምጽና ግርማ ተገለጠ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዲስ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደ ተገለጠላቸው ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡፡
“በዓለ ሃምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ፥ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዪአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፣…” /የሐ.ሥራ.2፥1-4/
መንፈስ ቅዱስ ስለምን በንፋስና በእሳት አምሳል ተገለጠ?
ሀ/ መንፈስ ቅዱስ በንፋስ /በዓውሎ ነፋስ/ ድምጽ መጣ ብሎ የተናገረበት ምክንያት?
– ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር የማይዳሰስ ረቂቅ ነውና፤
– ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤
– ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል፤ መንፈስ ቅዲስም ጻድቃንን ከኀጥአን ይለያልና፤
– ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጥ ይታወቃል እንጂ፡፡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር፤ ምሥጢር ሲያስተረጉም ይታወቃልና፡፡
– ነፋስ መንቅሂ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ሰማእታትን ወደደም ጻድቃንን ወደ ገዳም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን አነቃቅቶ የሚመራቸው እርሱ ነውና በነፋስ መስሎ ተናገረለት፡፡
ለ/ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች /በእሳት አንጻር የተገለጠውም/ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አባቶቻችን መምህራን የመንፈስ ቅዱስን በእሳት የመመሰል ትርጉም እንዲህ ገልጠው ያስተምሩናል፡፡
እሳት ምሉዕ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና፤ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገልጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው፤ ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው፡፡ ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤ እሳት ጣዕመ መዓዛን ያመጣል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን ያመጣልና፡፡ እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፡፡ ከመጠን አልፎ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ “እሳት በላኢ ለዓማጽያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ” እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡
እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቀጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላልና፡፡ እሳት ውኃ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጻልና፡፡ እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡ እሳት ካንዱ ፋና አምሳ፣ ስልሳ፣ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም፤ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና፡፡
ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያስፈለጋቸው ለምንድር ነው?
ሐዋርያት “ወረደ፣ ተወለደ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ተነሣ አረገ” ብለው ለማስተማር ለማሳመን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋው ባይታደላቸው ኖሮ በራሳቸው ብቻቸውን በደከሙ፣ ደክመውም በቀሩ ነበር፡፡ ሰው ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ተግባር ቀርቶ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አይቻለውም፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ደግሞ በሰይጣን ዲያብሎስና በሠራዊቱ /ርኲሳን መናፍስት/ ልዩ ልዩ ፈተናና መሰናክል ያጋጥመዋል፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ርኲስ የሚመጣውን ፈተና ለመቋቋም ምንጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ያሻል፡፡
ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊትና በኋላ
ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመሳተፋቸው በፊት ምንም እንኳን ከጌታችን ባለመለየት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቢቆዩ ነገር ግን በልብ የሚያምኑትን በአንደበታቸው ገልጸው ለመመስከር ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ የችግሩም መንስኤ “የምናምነውን ብንመሰክር እንገረፋለን፣ እንሰቀላለን” የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ አርብ ጌታችን በቀያፋ ግቢ ውስጥ መከራን ሲቀበል ተከትሎት ወደዚያው አምርቶ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ሰዎች ለሦስት ጊዜያት “ከገሊላው ኢየሱስ ጋር አይደለህምን?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ የሰጠው ምላሽ “ሰውየውን /ጌታችንን ነው/ አላውቀውም” የሚል ነበር /ማቴ.26፥69-72/ በኋላ ግን /ማለትም መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ካሳደረበት በኋላ/ በሸንጎ ሹማምንት “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው /የጌታችንን ነው/ ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልሰው አሉ፡፡ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡…. ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” /የሐዋ.ሥራ.5፥28-41/
ከዚህ በላይ የትምህርታቸው ቃል በሰማዕያን ልቡና ገብቶ ካለማመን ወደ ሃይማኖት፣ ከአምልኮተ ባዕድ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚመልስ ሆኗል፡፡ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት ያደርጉም ጀመር አንድ ቋንቋ ብቻ ያውቁ የነበሩት ሐዋርያት ሰባ አንድ ቋንቋ ተጨምሮላቸው የጌታችንን ወንጌል በመላው ዓለም ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡
በዓለ ሃምሳ ለቤተክርስቲያን
ይህ በዓል የቤተ ክርስቲያን የልደት በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ያለ ምክንያት የተሰየመ /የተሰጠ/ አይደለም፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ የተነሡ ሊቃውንት ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚገልጹት በዚህች ቀን ቁጥራቸው ከሦስት ሺህ ያላነሱ አይሁድ ወደ ክርስትና የመጡበት፤ወንጌል ከመካከለኛው ምስራቅ አልፋ በመላው ዓለም የተነገረችበት የተስፋፋችበት ቀን ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው ይህንን ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል፡-
“…. ጌታ ባረገ በአስረኛው ቀን ጧት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ተሰጠ፡፡ ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው “መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኑሮ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ኮስምኖ ቀጭጮ ይቀር ነበር፤ ስለዚህም በሚገባ አነጋገር ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች” ይላል፡፡ ብዙ ሊቃውንት ይህችን ዕለት የበዓላት ሁሉ እመቤት ይሏታል፡፡….”
በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ይህንኑ በዓል በጸሎትና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አክብረውት ይውላሉ፡፡
በዚህ ዕለት የሚቀደሰው ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፥ ምንባባቱ ደግሞ፡-
ኤፌ.4፥1-17
/ቁጥር7/ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን፥
1ኛ ዮሐ.2፥1-18
/ቁጥር.17/ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
የሐዋ.ሥራ.1፥1-18
/ቁጥር 4/ በሁሉም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር
የሚለው ሲሆን ምስባኩ “ወወሀብከ – ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው” የሚለው ነው፥ /መዝ.67፥18/
በዚህ ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሰጣቸው ተስፋም በወንጌል ንባብ ጊዜ ይሰማል፡፡ ይኸውም፡- “ወኢየኅድገክሙ እጓለማውታ ትኲኑ” የሚለው ነው፡፡
ኢየሩሳሌም -ቤተ ክርስቲያን
ቅዱሳን ሐዋርያት ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዛቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በኢየሩሳሌም ከተማ ጸንተው /ቆይተው/ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ ቢናወጹ ይህን ጸጋ ለመሳተፍ ባልታደሉ ነበር፡፡ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር /ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ/ ደግሞ ምንም ምን ተግባር ማከናወን ባልተቻላቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ እመቤታችንን ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች የሚያስተምረን ነገር፡- በሃይማኖት በምግባር ጸንቶ የሚኖር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ይጎበኘዋል፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምርለታል፡፡ ኋላም ለመንግሥተ ሰማይ ያበቃዋል፡፡
ይህንን ጸጋ ለማግኘት ፈጣሪያችን ኢየሩሳሌም ከተባለች ለሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳንናወጽ እንዳንወጣ አዞናል፡፡ ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ሀገር /ሀገረ ሰላም/ ማለት እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያን /ቤተ ክርስቶስ/ ማለት ደግሞ የሰላም ቤት ማለት ነው፡፡ የሰላም አለቃ፣ የሰላም ባለቤት የክርስቶስ ቤት ናትና፡፡ /ኢሳ.9፥6/
እንግዲህ አባ ሕርያቆስ ባስተላለፈልን ቡራኬ መሠረት “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን፥ በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት፣ ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት፣ ወበ ኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት፡- እናንተ የክርስቲያን ወገኖች በዚህች ቀን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ፡፡ በልዕልና ባለች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስባችሁ፡፡” እንዳለን እስከ መጨረሻ ሕይወታችን ቅድስት ንጽሕት ርትእት በሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ያጽናን፡፡ በዓሉን የበረከት የረድኤት ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው” /መዝ.86፥1/
በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ
ይህ ቃል የእመቤታችንን አያቶቿን የቀደሙ ወላጆቿን ንጽሕና፣ ቅድስና፣ ክብር አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው የምስክርነት ቃል ነው፡፡ ይህ ምስክርነት አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ለኩነተ ሥጋ የመረጣት ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅዱሳን መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲመላለስ፡- “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡ መልካምም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፥ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም” ማቴ.7፥17-18፡፡ በማለት እንደተናገረው እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተገኘችባቸው ወላጆቿ ሁሉ ቅዱሳን ንጹሐን፣ እግዚአብሔርን የሚወዱና የሚያከብሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ለመሆኑ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘር ሐረግና የትውልድ ታሪኳ ምን ይመስላል?
በነገረ ማርያም ሰፍሮ ከምናገኘው ሰፊ ታሪክ ከፊሉን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!
የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ “ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት “እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል” አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል” አላቸው፡፡ እነርሱም “ጊዜ ይተርጉመው” ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፣ ምክነት ወርዶ እንደ አያቶቿ ሆናለች፤ ብዕሉ ግን በመጠን ሆኗል፡፡
ከጎረቤቷ በዝሙት የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ሐና “ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እስማለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን የምለብሰው ልብስ የለኝም” አለቻት፡፡ እርሷም “ልብስማ የኔ ካንድ ሁለት ሦስት ልብስ አለልሽ አይደለም? ያንን ለብሰሽ አትሄጅምን?” አለቻት፡፡ “ያንቺ ልብስ የተሰበሰበ በዐስበ ደነስ በዐስበ ዝሙት ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገር ይወዳል፤ ይህን ለብሼ ብለምነው ምን ይሰማኛል ብዬ ነዋ” አለቻት፡፡ “ሐና፤ እኔ በምን ምክንያት ልጅ ነሣት እያልሁ ሳዝንልሽ እኖር ነበር፤ ለካ እንደ ድንጊያ አድርቆ ያስቀረሽ ይህ ክፋትሽ ነው” አለቻት በዚህ አዝናለች፡፡
በሌላ ጊዜም ሐናና ኢያቄም “መሥዋዕት እናቀርባለን” ብለው ከቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ሊቀ ካህናቱ ሮቤል ይባል ነበር፡፡ “ወኢይተወከፍ መሥዋዕቶሙ ለመካናት እንጂ ይላል፤ “እናንተማ ብዝኁ ወተባዝኀ… ብሎ ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? ቢጠላችሁ ነው እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን? መሥዋዕታችሁን አልቀበልም” ብሏቸው በዚህ እያዘኑ ተመልሰዋል፡፡ …. ከዛፍ ሥር ተቀምጠው አርጋብ /ርግቦች/ ከልጆቻቸው ጋራ ሲጫወቱ ዕፅዋት አብበው አፍርተው አይታ “አርጋብን በባሕርያቸው እንዲራቡ፣ ዕፅዋትን እንዲያብቡ እንዲያፈሩ የምታደርግ የኔ ተፈጥሮዬ ከድንጋይ ይሆን ልጅ የነሣኸኝ” ብላ አዘነች፡፡ ከቤታቸው ሂደው “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ፤ ጋራጅ ሆኖ ይኖራል፤ ሴት ብንወልድ ዕንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ብፅዓት ገብተዋል፡፡
የሐምሌ 30 ዕለት እሷ ለሱ “ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ” ብላ፤ እሱ ለሷዋ “ጻዕዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፤ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ” ብሎ ያዩትን ራእይ ተጨዋውተዋል፡፡ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም አለና ሂደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ” አላቸው፡፡ “አንተስ አልፈታኸውም ጊዜ ይፍታው” ብለው ተመልሰዋል፡፡ በነሐሴ 7 ቀን መልአክ መጥቶ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ብሏቸው በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ እመቤታችን ተፀነሰች፡፡ በተፀነሰችም ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡
በርሴባ የምትባል አክስት ነበረቻት አንድ ዐይና ነች፤ “ሐና እግዚአብሔር በረድኤት ጎበኘሽ መሰለኝ” ብላ ማኅፀኑዋን ደሳ ዐይኗን ብታሸው በርቶላታል፡፡ ይህን አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀኑዋን እየዳሰሱ የሚፈወሱ ሆነዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ ነበር ሞተ፤ ትወደው ነበርና ያልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት “ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” ብሎ ከመፈክረ ሕልም የቀረውን ተርጉሞላታል፡፡
ከዚህ በኋላ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ቀድሞ ከነዚህ ወገን የሚሆኑ ዳዊት ሰሎሞን አርባ አርባ ዘመን እንደሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙን፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህች የተወለደ እንደምን ያደርገን ይሆን?” ብለው በጠላትነት ተነሡባቸው፤ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለኢያቄም “አድባረ ሊባኖስ ይዘሃት ሂድ” ብሎት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ይህም አስቀድሞ እግዚአብሔር ባወቀ “እምሊባኖስ ትወፅእ መርዓት … ሙሽራ /እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም/ ከሊባኖስ ትወጣለች” በማለት ጠቢቡ የተናገረው ቃለ ትንቢት ነው፡፡ /መኃ.4፥8/
ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በእመቤታችን ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡
በግንቦት 1 ቀን /5ሺ ከ5መቶ የመከራው ዘመን ሊያልቅ 15 ዓመታት ሲቀሩት/ ሊባኖስ በሚባል ተራራ ከፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡ ይህቺውም ፍጥረት ሁሉ /ደቂቀ አዳም ሁላቸው/ ተስፋ ሲያደርጓትና ሲጠባበቋት የነበረች የድኅነታቸው ምልክት እመቤታችን ናት፡፡
ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም “አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኀኒትነ፡፡ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል፡- የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት መናገሩ ስለዚህ ነው፡፡
- አክሊል ምክሐነ፡- አላት ይህም አክሊል የወዲህኛው፣ ምክሕ የወዲያኛው ነው፡፡ ከነገሥታት መካከል እንደ ዳዊት የከበረ የለም፡፡ ምንም እንኳን ቅዱስ ዳዊት የከበረ ቢሆን የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም፡፡
- ወቀዳሚተ መድኀኒተ አላት፡- ቀዳሚተ የወዲህኛው መድኀኒት የወዲያኛው ነው፡፡ ከመሳፍንት ወገን የሚሆን ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢሆን የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለውም፡፡
- ወመሠረተ ንጽሕና አላት፡- መሠረት የወዲህኛው፤ ንጽሕ የወዲያኛው ከነቢያተ እግዚአብሔር ወገን የሚሆን ኤልያስ በድንግልና በንጽሕና መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ንጹሕ ድንግል ቢባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፤ የንጽሕናችን መሠረት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤” በማለት ተናግሯል፡፡ በእርሷ ምክንያትነት መድኀኒዓለም የሚፈጽምልንን ካሳ ነቢያትና የቀደሙ አበው ሁሉ የእርሷን መወለድ በናፍቆት ሲጠባበቁ ነበር፡፡ ከነቢያት አንዱ የሆነ ኢሳይያስም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ጎሞራም በመሰልነ ነበር፡፡” በማለት መናገሩ በእርሷ መገኘት ከጥፋት መዳናችንን ሲገልጽ ነው፡፡ ኢሳ.1፥9
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደች የሐና ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ በሰሙ ጊዜ ፍጹም ደስ ብሏቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰበሰቡ፡፡ ሕፃኗን /እመቤታችንን/ ተመልክተው ፍጹም አደነቁ፡፡ እርስ በርሳቸውም እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አየተን አናውቅም ተባባሉ፤ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ አድሯልና፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና፡፡
ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ ያችንም ብላቴና ስምዋን ማርያም አሏት ይኸውም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሰባቱንም ቀን በፈጸሙ ጊዜ በፍቅር ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡
በዚህ ትውፊት መሠረት ኢትዮጵያውያን ምእመናን በየዓመቱ ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችንን ልደት ከቤታቸው ወጥተውና ከያሉበት ተሰባስበው ንፍሮ ቀቅለው፣ አነባብሮ ጋግረውና ሌላም እንደ አቅማቸው /ዝክር አዘጋጅተው/ በመንፈሳዊ ደስታ ዛሬም ድረስ ያከብሩታል፡፡
የእመቤታችን ስሞችና ትርጓሜያቸው፡፡
ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ማርያም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች፡፡ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታናለችና፡፡
አንድም፡- ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ማርያም ማለት ልዕልት ማለት ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናትና አንድም ማሪሃም ማለት እግዝእተ ብዙኀን ማለት ነው አብርሃም ማለት አበ ብዙሃን እንደሆነ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ለነቢያተ ዜና ትንቢታቸው ለሐዋርያት ስብከታቸው ለክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋቸው የሆነች እመቤታችን የተወለደችበትን ቀን ሁላችን ምእመናን በፍጹም ፍቅርና ደስታ እናከብረዋለን፡፡
ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ለተዋሕዶ ከመረጣት ከዓለመ አንስት ተለይታ በንጽሕና በቅድስና አጊጣ የመመኪያችን ዘውድ ከሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የቀኝ ዐይን – ድንግል ማርያም
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወአጸባ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ውእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡
የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳን እኛ የምናውቀው የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ውዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ውጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸው የምስጋና ድርሰቶችን(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊው ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡
በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ “ዐይን” ነው፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰው የምስጋና መዝሙሩ ውስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለው ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃይልን ከውበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነው፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በውበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያውን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራው ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራው የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየው በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላው ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ውስጥ ሆነው ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እውነት መሰላቸው፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊው ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ውስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸው ውድቀት(የባሕርያቸው መጎስቆል) መሆኑን ተረድተው ወደ ማንነታቸው ተመለሱ (አንድነታቸውን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::
በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸው እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየው ሕልም መሠረት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረው ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችው ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራውና ሌላ ሌላ የሚመስለው ጉቶው፣ ቁጥቋጦው ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታው….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛው ፀሐይ ክርስቶስ መውጣት በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መውጣት ነውና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታውሰውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አድርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነው፡፡ ለነገሩ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነው ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ ፤ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ውቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እንደምንስ ያለ መረዳት ነው? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡
ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሣሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረግሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ውዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ነው (ምነው በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰውን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነው ብለው ነው እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እርሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸው በላይ በውዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነው፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታውም ጊዜውም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡
በርግጥም ፍጹም ልዩ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንግልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጠው ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀው ነበር››/ሉቃ.2፡51/ ተብሎ እንደተጻፈው አትናገረው እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለው ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ እንደገለጸው ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያውቀው የሚቻለው የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሰችው እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪው ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለው እያወቀች ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር – ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችው ፍጡር ሊረዳው የሚቻለው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተውም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባው ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለውን የተወደደውንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀውን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለው? ልዩ የሆነውን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡
ለዚህም የበቃችው ራሷን ለሰው በሚቻለው ከፍተኛው መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያውቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸው የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነው፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰውነት መብራት የምትሆነው የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነው ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሽ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለውን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያውቃት› የሚለውን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለው ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነው ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችው ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችውና ማንነቱን እንኳ በውል የማታውቀው ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀው መሠረት ወላጆቿ ጠርተው ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለው በጠየቋት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችው፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተገልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታውቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችው፡፡
እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከው ይሁንልኝ›› ያለች አንት እንዳልከው የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደውም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለች እንጂ ለሌላው ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነው የቀረው፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤ ነውርም የለብሽም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሽው….›› ያለው ለዚህ ነበር፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነው/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረው ግን ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋላ ተጻፈበት የሚል ነው፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በውስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበው ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸው ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገው ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸው? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእውነት ወዴት ይገኛል፡፡
ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቋት ዘንድ የሰጠው ሁለት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ አንደኛው ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው ነው፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠው ነው፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠው እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነው ይላሉ፡፡
በእነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነው) የተሰጠውም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸው(ምእመናን) የሚመለከት ነው፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለው እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸው ምእመናን ናቸው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከድምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸው ፍጹማንን የሚመለከተው አደራ የተሰጠዉ ለበቃው ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነው፡፡እርሷንም በቤቱ ማስተናግድ የሚቻለው ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነው፡፡
ቅዱስ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለው ጌታ የሰጠው ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነው፡፡ መላእክት ሲጠብቋት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰው ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለውም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳይፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረው ጌታ ነው፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰው ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለው የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠው ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነው፡፡
የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳን መታመን የማይቻላቸው የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊውን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸው ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸውን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ ይታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳው፣ ተኩላው፣ ቀበሮው፣ … የመሳሰለው አውሬ የገደለውን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበው ቀርቶ ልንበላውም የተከለከለ ነው፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አውሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋውን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነው ማለት ነው፡፡ ‹አውሬ የቧጨረውንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካውን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለውን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረው መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማው በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነውና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእውነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረውን አናቀርብም፡፡
እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለው ይህችን ልዩ ድንግል ነው፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገውንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነው፡፡
ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?
አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቅ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸው ቁጥራቸው በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነውና አይፈረድባቸውም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደው ልጇ ጋራ› በምንለው ሥዕል ውስጥ እንኳን በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸው ጌታ ያነሰ የሚመስላቸው ማስተዋል የራቃቸው ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መሰደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤውም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤው በመቁጠር ትንሣኤውን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማስከተልም ርዕደተ መንፈስ ቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸው የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተውሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለው እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናው ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነው ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነው በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸው ቅዱሳን ስም እስካደረግነው ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡
የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስማኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸው ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሽ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆነ የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡
በርግጥም ሊቃውንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለው በረከት መሳተፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸው ምንድን ነው የሚለውን እንመልከትና እንፈጽም፡፡
በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡የምናከብራቸውም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ትእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነው ማለት ነው፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻው ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበው በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻው እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አውራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አውራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላውን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡
‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለው ሊቃውንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራውን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረው፡፡
በኦሪት እንደተጻፈው በፋሲካ የሚሠዋው ልዩ የድኅነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸው ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነው ወይፈኑ፣ አውራ በጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነው የሚቀርበው)፣ ሌላው ሁሉ የማን ምሳሌ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረው ቅዱሳን ለእምነታቸው መሥዋዕት ሆነው ቀርበዋል።ደማቸውንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላው እንደ ወይፈን፣ ሌላውም እንደ አውራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ድኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋው በግ ከጌታ በኋላ ለምናምን ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸውን ያፈሰሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሌላው ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካቀውን በግ ሊተካው እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነው ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የጌታችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነውና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃውንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸው፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉው ይህን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡
ቀደም ብለን እንዳየነው የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸው አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነው ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸው ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነው ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸው፡፡
ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/ በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡
“አብዝቶ የመመገብ ጣጣው”
(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐንስን ወንጌል በተረጎመበት በ21ኛው ድርሳኑ “ ጌታችን በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ በቃና ሰርግ ላይ ስለምን ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት እንደቀየረው ከአብራራ በኋላ ከዛሬ 1500 ዓመት በፊት በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ ግኝት ተደርገው የሚታዩትን አብዝቶ በመመገብ የሚመጡትን የጤና ጉድለቶች ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ጽሑፉ ተተርጉሞ እንዲህ ቀርቦአል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት ያኔ እንደቀየረ ዛሬም እኛን ድካማችንንና እንደ ወራጅ ውሃ በአንድ ቦታ ጸንቶ መቆየት የተሣነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ከመቀየር አልተቆጠበም ፡፡ ዛሬም አዎን ዛሬም ልክ እንደ ወራጅ ውሃ ቀዝቃዛ ፣የፈጠነና ፣ ያልተረጋጋ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡፡ እነዚህን ፈቃዶቻችንን ወደ ጌታችን እናምጣቸው ፤ እርሱ ወደ ወይንነት ይቀይራቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ውኃ ሆነው ከእንግዲህ አይቀጥሉም ፡፡ ነገር ግን ለራሳቸውና ለሌሎች ደስታን የሚሰጡ አካላት ይሆናሉ ፡፡
ባልተረጋጋ ውሃ የተመሰሉት እነማን ናቸው ? ለዚህ ከንቱ ዓለም ሕሊናቸውን ያስገዙ ወገኖች ፣ የዚህን ዓለምን ቅምጥልነት ፣ አለቅነትንና ክብርን የሚሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ፍቃዶቻችን እንደውኃ የሚፈሱ ፣ ፈጽሞ ያልተረጋጉ ፣ ለአመፃ የሚፋጠኑ ቁልቁል የሚምዘገዘጉ ውኆች ናቸው ፡፡
ዛሬ ሀብታም የነበረው ነገ ደሃ ይሆናል ፡፡ በአንድ ወቅት ዝናው ሲነገርለት፣ የተጌጠና የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሶ በሰረገላ ላይ የሚሄድና ብዙ አጃቢዎች የነበሩት ሰው ፣ ያለፈቃዱ ያን የተዋበ መኖሪያውን ተቀምቶ ወደ ወይኒ ተጥሎ ይገኛል ፡፡ ለሥጋው ደስታ የሚተጋው ሆዳሙ ደግሞ የሥጋ ፈቃዱን ከሞላ በኋላ ሆዱ ሳይጎድልበት ለአንድ ቀን መቆየት አይቻለውም ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምግቦች ከሆዱ ሲጠፉ ወደ ቀድሞው ምቾቱ ለመመለስ ሲል ከፊት ይልቅ አብዝቶ ይመገባል ፡፡ አመጋገቡም ሁሉን ጠራርጎ እንደሚበላ እንደጎርፍ ውሃ ነው ፡፡ በዝናብ ወቅት የሚነሣው ጎርፍ አስቀድሞ የነበረ ውሃ በከፈተለት ጎዳና ገብቶ ቦታውን ሁሉ ያጥለቀልቀዋል ፡፡ እንዲሁ በሆዳሙም ዘንድ እንዲህ ይሆናል ፡፡ አስቀድሞ የነበረው ሲጠፋ እርሱ በቀደደው ሌሎች የሥጋ ፍቃዶች በዝተው ይገባሉ ፡፡
ምድራዊው ነገር ይህን ይመስላል ፤ መቼም ቢሆን የተረጋጋ አይደለም ፡፡ መቼም ቢሆን አንዱ ሌላውን እየተካ የሚፈስ እና የሚቸኩል ነው ፡፡ ነገር ግን የቅምጥልነትን ኑሮ በተመለከተ ጣጣው በከንቱ መባከን ወይም መቻኮል ብቻ አይደለም ፡፡ ሌሎችም እኛን ከመከራ የሚጥሉን ችግሮችም አሉበት ፡፡ ቅምጥልነት ባመጣብን ጣጣ የሰውነት አቅማችን ይዳከማል ፣ እንዲሁም የነፍስ ጠባይዋም ይለወጣል ፡፡ ከባድ ጎርፍ ወንዙን በደለል ወዲያው እንደማይሞላው ፣ ቀስ በቀስ ግን እንዲሞላው ፣ እንዲሁ ቅምጥልነትና ዋልጌነት እንደ አልማዝ ብርቱ የሆነውን ጤንነታችንን ቀስ በቀስ ውጦ ያጠፋዋል ፡፡
ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደህ ብትጠይቅ የበሽታዎች ሁሉ ምንጫቸው አብዝቶ ከመመገብ እንደሚመነጩ ይነግሩሃል ፡፡ ጠግቦ አለመብላትና ለሆድ የማይከብዱ ምግቦችን መመገብ ለጤንነት እናት ነው ፡፡ ስለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የጤንነት እናት ብለው ይጠሩታል ፡፡ እናም ጠግቦ አለመብላት የጤንነት እናት ከሆነ ፣ አብዝቶ መመገብ ደግሞ የበሽታዎች ሁሉ እናት እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፡፡ አብዝቶ መመገብ ሰውነታችንን አዳክሞ በሕክምና ባለሙያ እንኳ ለማይድን በሽታ አጋልጦ ይሰጠናል ፡፡
አብዝቶ መመገብ ለሪህ ፣ ለአእምሮ ውስጥ የደም መፍሰስ ፣ ለዐይን የማየት ኃይል መቀነስ ፣ ለእጅ መዛል ፣ ለአካል ልምሾነት ፣ ለቆዳ መንጣት (ወደ ቢጫነት መቀየር ፤ በተለምዶ የጉበት በሽታ ለምንለው ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል ) ስጉና ድንጉጥ መሆን ፣ ለኃይለኛ ትኩሳት እና ከጠቀስናቸው በላይ ለሆኑ ሌሎች ሕመሞች ያጋልጣል ፡፡ በዚህ የሚመጡትን የጤንነት ጠንቆች በዚች ሰዓት ውስጥ ዘርዝሮ ለመጨረስ ጊዜው አይበቃም ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕመሞች በተፈጥሮአችን ላይ የሚከሰቱት መጥኖ በመብላት ወይም በጾም አይደለም ፡፡ ነገር ግን ከሆዳምነታችንና ከአልጠግብ ባይነታችን የተነሣ የሚመጡብን ናቸው ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ በነፍሳችን ላይ የሚከሰቱብንን በሽታዎች ብንመለከት ዋዘኝነት ፣ ስንፍና ፣ ድንዛዜ ፣ የሥጋ ፍትወቶቻችን ማየል፣ እነዚህንና የመሳሰሉ ሕመሞች ነፍሳችንን ያጠቁዋታል ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ምንጫቸው ሳይመጥኑ አብዝቶ መመገብ ነው ፡፡ ከእንዲህ ዐይነት ቅጥ ያጣ አመጋገብ በኋላ የቅምጥሎች ነፍስ ክፉ አውሬዎች ሥጋዋን ተቀራምተው ከተመገቡዋት አህያ ያልተሻለች ትሆናለች ፡፡ ቅምጥሎችን ስለሚጠብቃቸው ሕመሞችና ስቃዮች ጨምሬ ልናገርን ? ከብዛታቸው የተነሣ ዘርዝሬ መጨረስ አይቻለኝም ፡፡
ነገር ግን በአንድ ማጠቃለያ አሳብ ሁሉንም ግልጽ አድርጌ ማስረዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እንዲህ ከሚያደርጉ ከቅምጥሎች ማዕድ ማንም ደስ ብሎት አይመገብ ፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ጾምና መጥኖ መመገብ የደስታና የጤንነት ምንጮች ሲሆኑ ያለቅጥ መመገብ ግን የበሽታና የደስታ ማጣት ሥር እና ምንጭ ናቸውና ፡፡
ሁሉ ነገር ከተሟላልን ፍላጎት የለንም ፡፡ ፍላጎት ከሌለ ደግሞ እንዴት ደስታን ልናገኛት እንችላለን ? ስለዚህም ድሆች ከባለጠጎች ይልቅ የተሻለ ማስተዋልና ጤና ያላቸው ብቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ታላቅ በሆነ ደስታ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ናቸው ፡፡ ይህንን ከተረዳን ከመጠጥና ከቅምጥልነት ሕይወት ፈጥነን እንሽሽ ፣ ከማዕዱ ብቻ አይደለም ፣ ከዚህ ሕይወት ከሚገኙት ፍሬዎች ሁሉ እንሽሽ ፡፡ እነርሱን በመንፈሳዊ ሕይወት በሚገኘው ደስታ ለውጠን በቅድስና እንመላለስ ፡፡ ነቢዩ “ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ እርሱ የልብህን መሻት ይሰጥሃል”(መዝ.36፥4) እንዳለው በጌታ ደስ ይበለን ፡፡ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም በእርሱ በእግዚአብሔር መልካም ስጦታ ደስ ይለን ዘንድ የሰው ልጆችን በሚያፈቅረው በኩል ለእርሱ ለእግዚአብሔር አብ ለመንፈስ ቅዱስም ክብር ይሁን እስከዘለዓለሙ ፡፡ አሜን !!
የትንሣኤው ትርጉም በዓሉና አከባበሩ
ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ምክ/ሓላፊ
-
«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
-
መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
-
«ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
-
«ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
-
«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
-
መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
-
«ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
-
«ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
-
አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
-
ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
-
ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
-
አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የእርሰ ትምህርታችንም መሠረት ይኸው እንደሆነ ይታወሳል፤ ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡
-
ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡
-
ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡
-
«ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡
-
ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
-
ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣
-
ከኀሳር = ከውርደት ወደክብር፣
-
ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
-
ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡
– ካህናቱ ተሰብስበው ሥርዐቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም ይሰበሰባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ይሞላዋል፡፡
– ሕዝቡም የቻለው በዝማሬው ያለበለዚያም በጭብጨባና በልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ይህ ምስባኩ በዲያቆኑ 2 ጊዜ በመላው ካህናትም 2 ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ዲያቆኑም መላው ካህናትም አንድ ጊዜ ብለው 5 ጊዜ ይሆናል፡፡ 5500 ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡
የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ…
ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን፡፡ አሜን!!
“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፤ ሠላም እምይዕዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሐ ወሠላም፡፡”
“ወእምግርማሁ ተሀውኩ ወኰኑ ከመ አብድንት እለ የአቅቡ መቃብረ “እርሱን ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ እንደ በድንም ሆኑ” ማቴ.28፥4 መልአኩም መልሶ ሴቶችን እንዲህ አላቸው “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና በዚህ የለም እርሱ እንደተናገረው ተነሥቶአል፡፡ ነገር ግን ኑና የተቀበረበትን ቦታ እዩ ፈጥናችሁም ሂዱ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብሎ የትንሣኤውን የምስራች ለሴቶች መግለጡን ጽፎአል፡፡
- በጥንት ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ኖሮ እኛን ፈጥሮ ለማስገኘት በኩራችን ነው፡፡
- በተቀድሶ/በመመስገን/ በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን የጸጋ ምስጋና የሚመሰገኑት እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡
- በትንሣኤ በኩራችን ነው፡፡ እርሱን በኩር አድርገን እንነሣለንና “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ” 1ቆሮ.15፥20፡፡
- በዕርገት በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን አረጉ መባሉ እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡ “አርገ ከመ ያሌቡ ዕርገተ ጻድቃን ንፁሀን” የንፁሀን ጻድቃንን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ አረገ ቅዳሴ ዩሐንስ ወልደ ነጎድጓድ”
- ነፍሳትን ከሲዓል አውጥቶ ምርኮን ማርኮ ገነት መንግሥተ ሰማያት በመግባት በኩራችን ነው፡፡
ቅዳሴን በካሴት ማስቀደስ ይቻላል?
ሚያዚያ 3/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
እድሜ ለቴክኖሎጂ ይድረስና ድካምን የሚቀንሱ በርካታ የሥልጣኔ ውጤቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መቅረጸ ድምጽ ሲሆን ያለፈን ለማስታወስ የለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ መዝሙሮች ቅዳሴዎች፣ ትምህርቶች እና የአባቶች ምክር በካሴትና በሲዲ በምስልና በድምጽ እየተዘጋጁ የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከምትገለገልበት ሥርዐተ አምልኮ መካከል ቅዳሴ አንዱ ሲሆን በካሴት ተቀርጾ በገበያ ላይ ይሸጣል፡፡ እኔም ቅዳሴን በካሴት ከቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚል ጥያቄ በውስጤ ይመላለሳል፡፡
እባካችሁ ቅዳሴን በካሴት በቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይቻል ወይም አይቻል እንደሆነ መልስ ስጡኝ?”
የተከበሩ ጠያቂያችን በቅድሚያ ስላቀረቡልን ጥያቄ ምስጋናችንን ስናቀርብ ከልብ ነው፡፡ ማንነትዎንና ያሉበትን ቦታ ስላልገለጡልን ለምንመልሰው መልስ አቅጣጫ ለመጠቆም አልረዳንም፡፡ ቢሆንም መሠረታዊ የሆነው ጥያቄዎ ስለተገለጠ አስቸጋሪ ነገር አይኖረውም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆኑትን ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘን እና በማኅበረ ቅዱሳን የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል አርታኢ የሆኑትን መምህር ተስፋ ሚካኤል ታከለ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን ጋብዘናቸዋል፡፡
ሊቀ ጠብብት ሐረገወይን “ቅዳሴን በካሴት በቤት ውስጥ ሆኖ ማስቀደስ ይገባል?” የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ይላሉ፡፡ “የቅዳሴ ዓላማው አንድ ነው፡፡ እሱም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ፈትቶ ለምእመናን ማቅረብ ሲሆን አባቶች እንደሚሉት ቅዳሴ የሕዝብ ነው፡፡ ሰዓታት የሚባለውን የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ካህናት ሲያደርሱ ምእመናን ቢሳተፉበት በረከተ ሥጋና በረከተ ነፍስን ያገኙበታል፡፡ ማኅሌት ሲቆም ኪዳን ሲደርስ ምእመናን ቢገኙ በረከትን ያገኛሉ፡፡
ቅዳሴ ግን ለሕዝብ የሚፈጸም ሥርዐተ ጸሎት በመሆኑ ቀዳስያኑ እና ምእመናኑ ፊት ለፊት እየተያዩ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ደጅ ሲጠኑ ይታያሉ፡፡ ሥርዐተ ቅዳሴ ሲፈጸምም በካህናትና በምእመናን ተሳትፎ ይከናወናል፡፡ ቴክኖሎጂው በወለደልን ጥበብ ተጠቅሞ መዝሙርን ማዳመጥ ቅዳሴውን መስማት ይቻላል፡፡የተቀረጸውን መስማት ብቻ ሳይሆን ልንማርበትም እንችል ይሆናል፡፡ ከዚህ አልፎ የቤተ ክርስቲያኑን ጸሎተ ቅዳሴ በካሴት በተቀረጸ ድምጽ ማስቀደስ አይቻልም፡፡
በአሕዛብ አገር የሚኖሩ ሰዎች በአንድ የጸሎት ቤት ተሰብስበው ቅዳሴ በቴፕ ያስቀድሱ እንደነበረ ሰምቻለሁ እነዚህ ምእመናን ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ሔደው ቆመው ቅዳሴውን በቴፕ እየሰሙ “እትው በሰላም” /በሰላም ወደቤታችሁ ግቡ/ ሲባሉ ይሰነባበታሉ፡፡ ይህ በጎ አሳባቸውን እግዚአብሔር ተመልክቶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ ካህናቱም ቀድሰው እንዲያቆርቧቸው ረድቷቸዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት ያቀርቡት የነበረው መሥዋዕተ ኦሪት ለሐዲስ ኪዳኑ (አማናዊው) መሥዋዕት ምሳሌ ሆኖ እንዳደረሳቸው ከችግር አንጻር ቅዳሴን ለማስቀደስ ካላቸው ልባዊ ፍላጎት ተነሣሥተው ያን ማድረጋቸው አያስወቅሳቸውም፡፡ ያም ሆኖ ግን በመኖሪያ ቤታቸው ሳይሆን ከቤታቸው ወጥተው መንገድ ተጉዘው የፈጸሙት ተጋድሎ የሚበረታታ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ዝም ብሎ ተኝቶ ቅዳሴን ሰምቶ አስቀድሻለሁ ማለት ድፍረት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቴክኖሎጂ ቅዳሴ የላትም ቅዳሴውም በምንም ዐይነት መንገድ በቴፕ ድምጽ አይተካም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ያልታነጸችበት ቦታ አለ ለማለት ትንሽ ያስቸግራል ስለዚህ ቅዳሴን ማስቀደስ የሚገባው በቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ ነው”
መምህር ተስፋም በማያያዝ ምክራቸውን እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡፡ “ሊቀ ጠበብት የሰጡት አባታዊ ትምህርት እንደተጠበቀ ነው፡፡ የተለየም ዐሳብ የለኝም ቅዳሴ የሚቀደሰው በተቀደሰ ቦታ ነው፡፡ ይህ ማለት ታቦት ባለበት፣ ካህናት በተገኙበት፣ ውግረተ እጣን በሚደርስበት፣ ቡራኬ በሚፈጸምበት ቅዱስ ቦታ ይከናወናል፡፡ በቅዳሴው ጊዜ እጣን አለ፤ ጧፍ ይበራል፤ መሥዋዕት ይሰዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ቅዳሴን ማስቀደስ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ቅዳሴው ቅዳሴ አይሆንም እላለሁ፡፡”
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ እምነቷን ዶግማዋን እና ትውፊቷን ጠብቃ ጸሎተ ቅዳሴን ታከናውናለች፡፡ ጸሎተ ቅዳሴ ተግባራዊ የሆነ አምልኮ የምንፈጽምበት፣ መሠረታዊ እምነታችንን የምንገልጥበት ወደ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን /ምሥጢረ ቊርባን/ የምንደርስበት በምድር ያለ ሰማያዊ ሥርዐት ነው፡፡ በዕለተ ሰንበት በዐበይት በዓላት የሚቻለው አስቀድሶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላል፡፡ በንስሓ ራሱን ያላዘጋጀ ምእመን ደግሞ አስቀድሶ ጠበል ጠጥቶ መስቀል ተሳልሞ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡
ሥርዐተ ቅዳሴ በካህናት መሪነት በዲያቆናት አስተናባሪነት በምዕመናን ተሳትፎ በኅብረት የሚፈጸም ሥርዐት ነው፡፡ ሠራኢ ካህን ከመንበሩ በስተምዕራብ ቆሞ፣ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልስ ንፍቁ ካህን ከመንበሩ በስተደቡብ ፊቱን ወደ ሰሜን መልሶ፣ ሠራኢ ዲያቆኑ በስተምሥራቅ ፊቱን ወደ ምዕራብ፣ ንፍቁ ዲያቆን በሰሜን ፊቱን ወደ ደቡብ በመቆም መንበሩን ይከቡታል፡፡ አምስተኛው ልዑክም ከሠራኢው ካህን በስተግራ ቆሞ ለካህኑ መብራት ያበራለታል፡፡ መጽሐፉ በመንበር ላይ የሚቀመጥ ስለሆነ ሲገልጥ ጠሚችለው ንፍቁ ቄስ ወይም ሌላ ቄስ ብቻ ነው፡፡ ይህ መደበኛ አቋቋማቸው ሲሆን ሥርዐተ ቅዳሴው በሚከናወንበት ጊዜ ለቡራኬ ለጸሎተ እጣን ለስግደት ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በቅኔ ማኅሌት በቅድስትና በመቅደስ ቆመው የሚያስቀድሱና የሚያገለግሉ የምእመናን ወገንና ካህናት አሉ፡፡ በቅኔ ማኅሌት በሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ያለ የአገልግሎት ክፍል ወንዶች ምእመናን ቆመው ያስቀድሱበታል፡፡ በቅድስት ምዕራባዊ ክፍል ቆሞሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ያስቀድሱበታል፡፡ በስተደቡብ በኩልም ደናግል መነኮሳይያት የካህናት የዲያቆናት ሚስቶችና የሚቆርቡ ምእመናን ቆመው ያስቀድሱበታል፡፡ በዚህ ክፍል ቆመው ያስቀደሱ ምእመናን ሥርዐተ ቁርባን ይፈጽሙበታል፡፡ ይህ የቤተ መቅደሱ አሠራር ቤተ ንጉሥ የሆነ እንዳልሆነ ነው፡፡ በመቅደሱ ክፍል ልኡካኑ የሚቀድሱበት ሥጋ ወደሙ የሚፈትቱበት ካህናት ብቻ የሚገቡበት ልዩ ቦታ ነው፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ከላይ ያስቀመጥናቸውና ያልገለጥናቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ይከናወኑበታል፡፡ ሥርዐተ ቅዳሴ ሲፈጸም ካህናትና ምእመናን የድርሻቸውን ቃለ እግዚአብሔር እየተቀባበሉ እየሰገዱ እየተባረኩ ሥርዐቱ ይከናወናል፡፡ ለዚህም ነው ሥርዐተ ቅዳሴ የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ የሚሰማ ክዋኔ አለው የምንለው፡፡ ቅዳሴን በካሴት መስማት /ማዳመጥ/ ይቻል ይሆናል እንጂ ቡራኬ የማስገኘት የምሥጢራት ተካፋይ የማድረግ እድል አያሰጥም፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም እንደታደዘዘው ካህኑ ቅዳሴን ከመጀመሩ በፊት ሊያስተውል ከሚገባው ጉዳዮች አንዲ ምዕመናን መሰባሰባቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ዐይኖች በቤተ መቅደስ ነው፡፡ ጆሮዎቹም ወደ ምእመናን ጸሎት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ዐይኑንና ልቡን በመቅደሱ ሊያኖር ቃል ስለገባልን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የምሥጢራቱም ተካፋይ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ “በጎ እንደሆነ አውቆ ለማይሠራው ለዚያ ሰው ኀጢአት ነው” ያዕ.4፥17 እንዳለው ሐዋርያው ማስቀደስ ንስሓ መግባት ሥጋ ወደሙ መቀበል መልካም ነገር ማድረግ በጎ እንደሆነ እያወቁ ያን አለመፈጸም ኀጢአት ነው፡፡ “በዚህ ሥፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፡፡ ጆሮቼም ያዳምጣሉ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናል” 2ዜና.7፥15-17 ተብሎ እንደተጻፈ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደን የምንጸልየው ጸሎት የምንፈጽመው ሥርዐተ አምልኮ በረከት የሚያሰጥ እንደሆነ አምላካችን ነግሮናል፡፡ አበው ሐዋርያትም ጸሎትን በቤተ መቅደስ በመገኘት ያደርጉ ነበር፡፡ “ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ሐዋ.3፥6 ስለዚህ በአንድነት ለጸሎት በቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ ሐዋርያት ትምህርት ነውና ልንፈጽመው ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
A Burning Heaven in This World – Mt. Zeqwala Monastery


The well preserved and intact nature of the mountain natural forest, Crater Lake, wild life be it mammals or birds is still remembered by the elders up to the beginning of the second half of the 20th century. The reverse began to happen with the land proclamation of 1966 E.C. This policy has its own effect at the local level by creating a power vacuum in the area. As a result with the reigning of chaos the forest on whole area was destroyed. To make matters worse Lutheran Mission was established on the area in 1989 E.C. and converted most of the farming society into Protestants with a deep hostility to the monastery. The so called ‘aid and development’ it planned to do was limited only with a modern headquarters and a huge seedlings of Eucalyptus yearly given to the peasant for free. Thus, the crippled, dependant and perverted peasants (those living at the surrounding lands away from Wanber kebele in most cases) still lead a life of poverty and apathy burning the forest now and then evil for themselves and others with no hope for a better tomorrow.
Today, the extremely dedicated monks in the likeliness of their father Abune Gebre Menfes kidus protect the forest from the surrounding people on and around Zeqwala thirsting for water during the summer months and shivering for warmth in the winter. Therefore, the Children of the EOTC must pay for pipe system to bring water to the place from the town at the base, build a modern hall for the priests and assist them to start apiculture. Helping them to build an all weather gravel road from Dire to the mountain is another area open for the kind laity seeking the blessing of Abune Gere Menfes Kidus. Therefore, all the laity and priests of the Ethiopian Orthodox Church are called to save this wonderful and national heritage from destruction. May the blessing of our God Christ rest on Yuhanis of Debre Wifat the writer of this hagiography in the 15th Century hearing it told from the holy Gebre Menfes Kidus himself and all of us who love the saint.
Amen!
ጦምን አስመልክቶ የቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ
የካቲት 9/2004 ዓ.ም.
“በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ስንሠራ ለእግዚአብሔር አምላካችን ካለን ፍቅር የመነጨ ይሁን፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን በመንጎቹ ላይ ሲሾመው ለእርሱ ያለውን ፍቅር ተመልከቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔን የሚያፈቅር ሰው የሚፈጽማቸው የትኞቹም በጎ ሥራዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱለት ይሆኑለታል፡፡ ፍጹማንም ናቸው፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም በጎ ሥራዎቻችንን ስነሠራ እርሱን በማፍቀር ላይ የተመሠረቱ ይሁኑ፡፡”
“አንድ ሰው ምንም እንኳ መላ የሕይወት ዘመኑን በትኅርምት ሕይወት መምራት ያለበት ቢሆንም በዚህ በዐቢይ ጦም ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኀጢአቱን ለካህን ተናዝዞ ለድሆች ምጽዋትን በማድረግ በአግባቡ ሊጦም ይገባዋል፡፡ እነዚህን ዐርባ የጦም ቀናት በአግባቡ በጎ ሥራዎች አክለንባቸው የጦምናቸው እንደሆነ ቸሩ ፈጣሪያችን ዓመት ሙሉ ባለማወቅ የፈጸምናቸውን ኀጢአቶቻችንን ይደመስስልናል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ )
ነገር ግን ብዙዎቻችን በጦም ራስን መግዛትን ከምንለማመድ ይልቅ ለሥጋ ምቾቶቻችን መትጋታችን የሚያስገርም ነው፡፡ እኛ ለራሳችን የተጠነቀቅን መስሎን ደስታን ይፈጥሩልናል የምንላቸውን ምግቦችንና መጠጦችን አብዝተን እንበላለን እንጠጣለን፡፡ … ነገር ግን መጨረሻችን ሕማምና ስቃይ ይሆንብናል፡፡ የሥጋን ምቾት የናቁና በጦም በጸሎት እንዲሁም በትኅርምት ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመሩ ቅዱሳን ግን ሥጋና ነፍሳቸውን ሕያዋን አድርገው በመልካም ጤንነት ያኖሯቸዋል፡፡ በተድላና በምቾት ይኖር የነበረው ሰውነታችን በሞት ሲያንቀላፋ ከውስጡ ከሚወጣው ክፉ ጠረን የተነሣ ሽቶ በራሱ ላይ እናርከፈክፍበታለን፡፡ ነገር ግን የቅዱሳን ሰውነት በሕይወት ሳሉም ቢሆን በሞት ከሥጋቸው መልካም መዓዛ ይመነጫል፡፡ ይህ እጅግ ድንቅ የሆነ ነገር ነው ፡፡ እኛ ለሥጋችን ምቾት በመጠንቀቅ ራሳችንን ስናጠፋ እነርሱ ግን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በጦምና በጸሎት በማስገዛታቸው ሥጋቸውን ይቀድሷታል፡፡ የነፍሳቸውን በጎ መዓዛ በመጠበቃቸውም ሥጋቸው መልካም መዓዛን እንድታፈልቅ ሆነች፡፡
ነፍሳችን ንጽሕናዋን በጦም ካልጠበቀች በቀር ቅድስናዋን በኀጢአት ምክንያት ማጣቱዋ የማይቀር ነው፡፡ ያለጦም የነፍስን ንጽሕና ጠብቆ መቆየት የማይሞከር ነው፡፡ ሥጋም መንፈስ ለሆነችው ነፍሳችን መገዛትና መታዘዝ አይቻላትም፡፡ አእምሮአችንም በምድራዊ ምቾቶቻችን ስለሚያዝብን ከልብ የሚፈልቅ ጸሎትን ማቅረብ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ሥጋችን ነፍሳችንን በስሜት ስለሚነዳት ነፍስ እውር ድንብሯ በፍርሃት ወደ ማትፈቅደው ትሔዳለች፡፡ በአእምሮአችን ውስጥ ክፉ ዐሳቦች ተቀስቅሰው ኅሊናችንን ያሳድፉታል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ከእኛ ትወሰዳለች፡፡ ስለዚህም በግልጥ አጋንንት እንደ ፈቀዱት ነፍሳችንን ተሳፍረው ወደ ኀጢአት ይመሩዋታል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጦመ በኋላ ተራበ፡፡ ሰይጣንም ወደ እርሱ ይቀርብ ዘንድ መራቡን ገለጠለት፡፡ እንዲህ በማድረግም ጠላታችንን እንዴት ድል እንደምንነሳው በእርሱ ጦም አስተማረን፡፡ ይህ አንድ ጦረኛ ላይ የሚታይ የአሰለጣጠን ስልት ነው፡፡ ለተማሪዎቹ ጠላትን እንዴት ድል መንሳት እንደሚቻል ሊያስተምር ሲፈልግ ለጠላቱ ደካማ መስሎ ይታየዋል፡፡ ጠላቱም የተዳከመ መስሎት ሊፋለመው ወደ እርሱ ይቀርባል፡፡ እርሱም በተማሪዎቹ ፊት ከጠላቱ ጋር ውጊያን ይገጥማል፡፡ ጠላትን በምን ድል መንሳት እንደሚችል በእውነተኛ ፍልሚያ ጊዜ በተግባር ያስተምራቸዋል፡፡ በጌታ ጦም የሆነውም ይህ ነው፡፡ ጠላት ሰይጣንን ወደ እርሱ ለማቅረብ መራቡን ገለጠ፡፡ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ የእርሱ በሆነ ጥበብ በመጀመሪያውም፣ በሁለተኛውም፣ በሦስተኛው፣ ፍልሚያ በመሬት ላይ ጥሎ ድል ነሳው፡፡
እየጦምህ ነውን? ጦምህን በሥራ ተግብረህ አሳየኝ፡፡ ድሀ አይተህ እንደሆነ ራራለት፡፡ ወዳጅህ ከብሮ እንደሆነ ቅናት አይሰማህ፡፡ አፋችን ብቻ አይጡም፤ ዐይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ እግራችንም፣ እጃችንም፣ የሰውነት ክፍሎቻችንም ሁሉ ክፉ ከመሥራት ይጡሙ፡፡ እጆቻችን ከስስት ይጡሙ፤ እግሮቻችን ኀጢአትን ለመሥራት ከመፋጠን ይጡሙ፡፡ ዐይናችም የኀጢአት ሥራዎችን ከመመልከት ይጡሙ፡፡ ጆሮዎቻችንም ከንቱ ንግግሮችንና ሐሜት ከመስማት ይከልከሉ፡፡ አንደበቶቻችንም የስንፍና ንግግርንና የማይገቡ ትችቶችን ከመሰንዘር ይቆጠቡ፡፡ ወንድማችንን እያማን ከዓሣና ከእንስሳት ተዋጽኦዎች መከልከላችም ምን ይረባናል? (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)