ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ካለፈው የቀጠለ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቀሲስ ስንታየሁ አባተ አባባል የፍልሰታ ጾም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ይህም ከእመቤታችን ጋር ያለንን የጠበቀ ትስስር የሚያመላክት ሲኾን ከዚህም ሌላ አገራችን ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር ናት፡፡ እመቤታችን ልጇ ወዳጇ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ይዛ በተሰደደችበት ወቅት በግብጽ ብቻ ሳይኾን በኢትዮጵያ ምድርም መጥታ ዐርፋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አራቱንም የአገሪቱን መዓዝን ባርካለች፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩት ነቢዩ ዕንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ›› በማለት የተናገረው ትንቢትም እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሥርዓት አድርገን ፍልሰታን በልዩ ኹኔታ እንጾማለን፡፡

ድርሳነ ዑራኤልም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ወራት ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ከምድረ እስራኤል ወደ ምድረ ግብጽ፣ ከዚያም ወደ ብሔረ ኢትዮጵያ መጥታ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት በደብረ ዳሞበትግራይ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በደብር ዐባይ፣ በጐጃምና በጣና በአደረገችው የስደት ጉዞ ሕፃኑ ኢየሱስ ለድንግል እናቱኢትዮጵያን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ››› በማለት በሸዋና በወሎ፣ በሐረርጌና በአርሲ፣ በሲዳማና በባሌ፣ በከፋና በኢሉባቦር፣ በወለጋና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍላተ አህጉር በብሩህ ደመና ተጭነው በአየር እየተዘዋወሩ ተራራውንና ወንዙን (አፍላጋቱን) እንደ ጐበኙ ይናገራል፡፡ ይህም የቀሲስ ስንታየሁን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት የምእመናን ቅድመ ዝግጅት

በጾመ ፍልሰታ ወቅት ምእመናን ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው? ሱባዔ ከገቡ በኋላስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? የሚለውም ሌላው ጥያቄአችን ነበር፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እንዲህ ይመልሳሉ፤

‹‹ምእመናን ጾም (ሱባዔ) ከመጀመራቸው በፊት የሥጋን ኮተት ዅሉ ማስወገድ አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ዅሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባዔ የሚያቋርጣቸውን ጉዳይም አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡ በኋላሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ተሰጣቸው ጸጋ መጠን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመን መርዳት የማይችል ደግሞ ምክርና ሐሳብ በመስጠት ክርስቲያናዊ ድርሻውን ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂት በመመገብ፣ ብዙ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን ያህል እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተም ሥርዓት ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ  ልብስ መኾን የለበትም፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ የተናገሩትም ከሊቀ ማእምራን ደጉ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እንዲህ ይላሉ ቀሲስ፤ ‹‹ጾም ማለት ለእግዚአብሔር ማመልከቻ ማስገባት ማለት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ሦስት ቀን ጾሙ፤ በሦስት ቀናት ውስጥ አገራቸው ከመከራ ዳነች፡፡ የፍልሰታ ጾምም የወገኖቻችንን፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ጥፋት አታሳየን› ብለን ቦታና ጊዜ ወስነን ሱባዔ የምንይዝበት ጾም ነው፡፡ እኛ ምእመናን ከሁለት መቶ ኀምሳ ቀናት በላይ እንጾማለን፡፡ ነገር ግን ስንጾም ማየት የሚገባን ነገር አለ፡፡ ፍቅር እንደ ሸማ ያላብስህ እንደሚባለው ስንጾም ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾም ያለ ፍቅር፣ ፍቅርም ያለ ጾም ዋጋ የለውም፡፡ ቁም ነገሩ እኛ በጾም ደርቆ መዋል ሳይኾን ፍቅርና ሰላም መታከል አለበት፡፡ የተጣላ መታረቅ አለበት፡፡ በቅዳሴ ሰዓት ቦታ ላጡ ቦታ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ በተለይ አረጋውያንንና ሕፃናትን መደገፍ የወጣቶች ድርሻ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የበረታው ለደከመው ቦታ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሐሜትናሁካታቂም በቀል ያዘለ ንግግር ቦታ ሊኖረው አይገባም፡፡››

እንደ ቀሲስ ስንታየሁ ገለጻ ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ከኾነ ለምንድን ነው በጾማችን፣ በጸሎታችን ኅብረተሰባችን ከጉስቁልና ያልወጣው? ብለን ብንጠይቅ ሳይጾም ሳይጸለይ ቀርቶ ሳይኾን ፍቅር ስለሌለው ነው እንጂ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፊትም አሁንም ኾነ ወደፊት የሕዝቡን ልመና ይሰማል፡፡

ሱባዔ የገቡ ዅሉ ራእይ ያያሉን?

ለሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እና ለቀሲስ ስንታየሁ አባተ በመጨረሻ ያነሣንላቸው ጥያቄ ራእይ ከማየትና አለማየት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲታመሙ ከሕመማቸው ለመፈወስ ወይም በምድራዊ ሕይወት ለሚያነሧቸው ጥያቄዎች መፍትሔ ለማግኘት ሱባዔ በመግባት ራእይ ማየት አለብን ይላሉ፡፡ ራእይ ካላዩ ደግሞ ተስፋ ይቈርጣሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የምታስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መምህራኑ ምላሽ አላቸው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ፡- ‹‹ምንም እንኳን ወሩ ከሌላው በተለየ የሱባዔና የራእይ ወቅት ኾኖ ቢገለጽም በፍልሰታ ጾም ራእይ ማየት አለማየት የሚለው የብቃት መለኪያ (ማረጋገጫ) መኾን የለበትም፡፡ ቦታ ቀይረውና ከሰው ተለይተው እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት መጠየቅ በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዟል፡፡ ምእመናን ወደ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንወቅ ብለው እርሱን ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሳካላቸው በተለያየ ጊዜ በሱባዔው ይቀጥላሉ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም›› ሲሉ ምእመናንን መክረዋል፡፡

ቀሲስ ስንታየሁም፡- ‹‹አንድ ሰው የሚጾመው ራእይ ልይ ብሎ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን ሲጾሙ፣ ሲጸልዩ ኃጢአታቸው እንዲገለጽላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው አይደለም፡፡ ኃጢአታን ከተገለጸልንና ንስሐ ከገባን እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ተሞልቶ እግዚአብሔርን ልይ ቢል ሊኾን አይችልም፡፡ እኛንና እግዚአብሔርን የሚለያየን ኃጢአትና በደል ነው፡፡ ስለዚህ የሚያራርቀንን ነገር ለማስወገድ መጾም አለብን፡፡ ምእመናን በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ችግር፣ ለሰው ልጅና ለአገር የሚበጅ ነገር አምጣልን ብለው ሱባዔ በመያዝ መጾም መጸለይ ይገባቸዋል እንጂ ራእይ እንዲገለጥላቸው መጓጓት፣ ራእይ አላየንም ብለውም ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም፤›› በማለት መንፈሳዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያህል በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት፤ እንደዚሁም መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ምእመናን በምንጾምበት ወቅት የተራቡትንና የታረዙትን በማሰብ ካለን ከፍለን ለተራቡና ለታረዙ ማብላት፣ ማልበስ ይገባል፡፡ ይህን የምናደርገውም በፍልሰታ ወይም በሌሎችም አጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይኾን በማንኛውም ጊዜ ነው፡፡ የተቸገሩትን መርዳት ወይም እርስበርስ መረዳዳት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግዴታ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባህልም ነውና፡፡ ይህ ጾም ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን የምናሰፍንት፤ መንፈሳዊ ዕድገትን የምናመጣበት ይኾንልን ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት አይለየን፡፡

                                                              ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅታችን ጾም ምንድን ነው? እንዴትና ለምን እንጾማለን? መጾም ምን ጥቅም ያስገኛል? ባንጾምስ ምን ጉዳት አለው? የሚሉ ጥያቄዎች በቤተ ክርስቲያን መምህራን ምላሽ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው የፍልሰታ ጾም በደመቀና በተለየ ኹኔታ የሚጾምበት ምክንያት ምን እንደ ኾነና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ከምላሾቹ በኋላም ጾመ ፍልሰታን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ መልካም ንባብ!

የጾም ትርጕም

‹‹ጾም›› ማለት ‹‹ጾመ –  ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ፤›› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲኾን የቃሉ ትርጕም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው ሲሉ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ባዘጋጁት ‹‹ጾምና ምጽዋት›› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ ፰ ላይ ገልጸውታል፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትም የሚያትተውም ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡ ጾም ጥሉላትን፣ መባልዕትን ፈጽሞ መተው፣ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንደዚሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ዅሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቈጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ማለት ነው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተ የሚሰጡት ማብራርያም ይህንኑ ትርጕም የሚያጠናክር ነው፡፡

የጾም ሥርዓቱና ጥቅሙ 

‹‹መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ› ነው፡፡ ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለ ኾነ ሳይኾን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ስንጾምከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከርወዘተ. መቆጠብ አለብን›› ሲሉ ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የጾም መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡ በሃይማኖት የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከልበት ኹኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጾም ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዓይነት መስመር አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽዋማት ወቅት ከምግበ ሥጋና ከኃጢአት ትከለክላለች፡፡ ከኃጢአት ዅልጊዜም እንከላከላለን፡፡ ከምግብ የምንከለከለው ምግብ ኃጢአት ስለኾነ ሳይኾን ከሃይማኖት የተነሣ ነው፡፡ ምግብ በልተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን ጎስመን ያለ ምግብና ያለ መጠጥ እግዚአብሔርን እያመሰገንን የምንኖርበትን ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ሕይወት የምናስብብት መንገድ ነው›› የሚሉት ደግሞ ቀሲስ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡

የጾም ዓይነቶች

ጾም የግል እና የዐዋጅ (የሕግ) ጾም በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ የግል ጾም ደግሞ የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የዐዋጅ (የሕግ) አጽዋማት ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም)፣ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ስለኾነ፡፡

የፍልሰታ ጾም 

ከዚህ በመቀጠል ጾመ ፍልሰታን ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምን እንደ ኾነ እንመለከታለን፡፡ የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ሳይቀር በልዩ ሥነ ሥርዓትና በደመቀ ኹኔታ ይጾማል፡፡ አብዛኞቹ ምእመናን የዕረፍት ጊዜ በመውሰድ በገዳማትና በየአብያተ ክርስቲያናት ሱባዔ በመግባት ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ አሥራ አምስት ቀን ድረስ ጾም፣ ጸሎት በማድረግ ይቆያሉ፡፡ ጾም ጸሎት ሲያደርጉ ደግሞ በድሎት ሳይኾን በየዋሻው፣ በየመቃብር ቤቱና አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እንጨት ረብርበውና ሳር ጎዝጉዘው ጥሬ እየበሉ ነው፡፡

ፍልሰታ ምን ማለት ነው?

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ለዚህ ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፤ ‹‹ፍልሰታ ማለትፈለሰ – ተሰደደ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ፍልሰትማለት ደግሞ የተለያየ ትርጕም ቢሰጠውምፍልሰታ ለማርያም› ተብሎ ሲገለጽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት (የተነሣችበት) ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ማለት ነው፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ አባተም በተመሳሳይ መልኩ ስለ ፍልሰታ እንዲህ በማለት ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹‹ፍልሰታ ለማርያም› የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾንፍልሰታ› ማለት ደግሞፈለሰ› ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ፍልሰት› ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን (መፍለስን) ያመለክታል፡፡ እመቤታችን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደ ተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር የእመቤታችንን ሥጋ እንዲገልጥላቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን በማየት በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለኾነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቍረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡›› 

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ‹‹የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ‹‹እመቤታችንማ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ናት››  ብሎ ነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሣሣት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባዔ ያዙ፡፡ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋ ነሐሴ ፲፬ ቀን ተቀብራለች፡፡

ይኹንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያየው ሲቀብሯት ያላየው ሐዋርያው ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ አገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችን ስታርግ ሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ ምእመናን ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚዘከርበት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነ ጾም ነው፡፡ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ጾሙን ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቈርባሉ፡፡

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ደጉ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር በመኾኗ እና ሕዝበ ክርስቲያኑ ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው መሬት ላይ እየተኙ፣ ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡ ምእመናን ፍልሰታን ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስለሳባቸው ነው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡

ይቆየን

የቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ተጋድሎ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፱ .

በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ስማቸውን የሚጠሩ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የሰጠበት ቀን ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የተራዳቸውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ገድል በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲኾን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፤›› (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡

እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል ‹‹አይዞህ! አይዞሽአትፍራ! አትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሥላሴ በአብርሃም ቤት

ሥላሴ በአብርሃም ቤት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው፤

አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፬፥፴፪)፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡

የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን ‹‹ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ›› ሲላቸው ‹‹ደክሞናልና አዝለህ አስገባን›› አሉት፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ (በአምላካዊ ጥበብ) ከቤቱ ገቡ፡፡ አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ሔደና ‹‹ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ አብርሃምም ወይፈን አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡ ወይፈኑም ተነሥቶ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፤›› ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡

በዚህ ትምህርት ብዙ ምሥጢራት ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹን በመጠኑ ለማስታወስ ያህል፦ ‹‹… ሦስት ሰዎች … ሊቀበላቸው … ወደ እነርሱ …›› የሚሉትና ሌሎችም በብዙ ቍጥር የተገለጹ ተመሳሳይ ሐረጋት የእግዚአብሔርን ሦስትነት፤ ‹‹… በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ? …›› የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡ ሣራ ዳቦ ያዘጋጀችበት ሦስቱ መሥፈሪያ የሦስትነቱ፤ ዳቦው አንድ መኾኑ ደግሞ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡ ሥላሴ አብርሃም ያዘጋጀውን እንስሳ ተመገቡ ተብሎ መነገሩም በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ነው እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ አይስማማቸውም (አይነገርላቸውም)፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ (እግዚአብሔር ምግብ በላ) ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣትን የመሰሉ የሥጋ ተግባራት የመለኮት ባሕርያት አይደሉምና፡፡ ከዚህ በተለየ ምሥጢር ሥላሴ ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› ብለው ከጠየቁበት ኃይለ ቃል መካከል ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› የሚለውን እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› (ሉቃ. ፩፥፴፯) ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ መናገሩ የእግዚአብሔር ቃል በዘመን ብዛት የማይለወጥ ሕያውና እውነተኛ መኾኑን ያጠይቃል፡፡

እግዚአብሔር አብርሃምን ‹‹ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል መጠየቁም ያለችበት ጠፍቶበት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ የምሥራች እንዳለ ለማጠየቅ ነው፡፡ ሰውን ያለበትን ጠይቆ፣ ጠርቶ፣ አቅርቦ አስደሳች ዜና መንገር የተለመደ ነውና፡፡ ይኸውም ‹‹አዳም ወዴት ነህ?›› ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው (ዘፍ. ፫፥፱)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አዳምን ‹‹ወዴት ነህ?›› ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረው፣ ‹‹ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚለውን የድኅነት ቃል ኪዳን ሊሰጠው ፈቅዶ ነበር፡፡ እንደ አዳም ዅሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከምትኾን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለሙን እንደሚያድነው ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ጠይቆታል፡፡ ከዚያም የይስሐቅን መወለድ አብሥሯቸዋል፡፡ ይኸውም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሔር ከአብርሃም የልጅ ልጅ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደ (በአካለ ሥጋ ወደ ምድር እንደ መጣ)፤ በዚህ ጊዜም በሣራ የተመሰለች ወንጌል በይስሐቅ የሚመሰሉ ምእመናንን እንዳስገኘች ማለትም ሐዲስ ኪዳን ተመሥርታ ብዙ ክርስቲያኖችን እንዳፈራች የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደ ተረጐሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ‹‹ተናግዶቱ (ተአንግዶቱ) ለአብርሃም፤ ለአብርሃም የሃይማኖቱን (የእንግዳ ተቀባይነቱን) ዋጋ የምታሰጪው አንቺ ነሽ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ፡፡ በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚው ይመግብበት፣ ያርፍበት እንደ ነበረ ዅሉ በእመቤታችንም አማላጅነትም መንገደኞች ማረፍያ፤ እንግዶች መጠለያ፤ ስደተኞች ተስፋ ያገኛሉና፡፡ ከዅሉም በላይ የነፈስ የሥጋ መድኀኒት፤ የዘለዓለም ማረፍያ፤ እውነተኛ መብልና መጠጥ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ ዅሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፡፡ በዚህ ቃለ ወንጌል ‹‹ስድስተኛው ወር›› የሚለው ሐረግ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ለብሥራት መላኩን ያመለክታል፡፡

በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ እንዳመሰገነ ዅሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ›› እያሉ እግዚአብሔርን በአንድነት አመስግነዋል (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድ እና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡፡ ‹‹ሔዷል›› ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት በሰው አምሳል ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ዅሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡

ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ዅሉ በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የተማጸነው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ ድኅነት እንደሚጸልዩ እና እንደሚያማልዱ፤ እንደ አብርሃም ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ተግባራቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እግዚአብሔር እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤት ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡፡

በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የመገለጥ ትምህርት በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና ‹‹ነበር›› እየተባለ የሚነገር ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህንም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመለየት በተጨማሪ ለተቸገሩ በመራራት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፤ ይቀደሳልና፡፡ ደግሞም ልጅ ለሌለን ልጅ፤ ዘመድ ላጣን ዘመድ በመስጠት ዘራችንንም ይባርክልናል፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ዅሉ ይፈጽምልናል፡፡ ይህ ዅሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ እኛም በርትዕት የተዋሕዶ ሃይማኖት እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባርም እንትጋ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዕረፍት

ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በየዓመቱ ሐምሌ ፭ ቀን በአንድ በኩል የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በዓለ ዕረፍትም በዚሁ ዕለት ይዘከራል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የእነዚህን ቅዱሳን ታሪክ በቅደም ተከተል በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ቅዱስ ጴጥሮስ

ቅዱስ ጴጥሮስ በአባቱ የሮቤል፣ በእናቱ የስምዖን ነገድ ሲኾን፣ የተወለደውም በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ‹ስምዖን› ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ጴጥሮስ› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ትርጕሙም በግሪክ ቋንቋ ዓለት (መሠረት) ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሚተዳደረው በዓሣ አጥማጅነት የነበረ ሲኾን፣ ሰዎችን በወንጌል መረብ እያጠመደ ወደ ክርስትና ሕይወት ይመልስ ዘንድ ጌታችን ለሐዋርያነት ጠርቶታል (ሉቃ. ፭፥፲፤ ማር. ፩፥፲፮)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ቅንዓቱና ለጌታችን በነበረው ፍቅር የሐዋርያት አለቃ ኾኖ ተሹሟል፡፡ ለአገልግሎት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በእስያ፣ በሮም፣ በሰማርያ፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በአንጾኪያ፣ በገላትያና በሌሎችም አገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በስብከቱ ምክንያትም ልዩ ልዩ መከራን ተቀብሏል፡፡ በክርስቶስ ኀይል አጋዥነት ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከተሰጠው ጸጋ ብዛት የተነሣ በጥላው ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፭፥፲፭)፡፡ ሐዋርያው በቃል ካስተማረው ትምህርት በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ሁለት መልእክታትን ጽፏል (፩ኛ እና ፪ኛ ጴጥሮስ)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ በሰማዕትነት ሲያርፍ

የቅዱስ ጴጥሮስ ምድራዊ የአገልግሎት ዘመኑ ሊፈጸም ሲቃረብም እንዲህ ኾነ፤ በዘመኑ የክርስቲያኖች ጠላት የነበረው የሮም ንጉሥ ወደ አካይያ ዘምቶ ድል አድርጎ በደስታ ወደ ሮሜ ሲመለስ መኳንንቱን ለማስደሰት፤ ጣዖታቱንም ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ላይ የሞት ፍርድ ዐወጀ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በሮም ሲያስተምር ቆይቶ የሮም መኳንንት እንዳይገድሉት ትጥቁን ለውጦ ከሮም ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ተገለጸለት፡፡

በዚህ ጊዜ ‹‹አቤቱ ጌታ ሆይ ወዴት ትሔዳለህ?›› ሲል ቢጠይቀው ጌታችንም ‹‹ልሰቀል ወደ ሮም እሔዳለሁ›› አለው፡፡ ‹‹ዳግመኛ ትሰቀላለህን?›› ባለው ጊዜም ‹‹አንተ ስትፈራ ጊዜ ነው እንጂ›› ሲል መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሔድ ነበር፡፡ ስትሸመግል ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል፤›› (ዮሐ. ፳፩፥፲፰) በማለት ጌታችን የነገረው ቃል አሟሟቱን የሚያመለክት መኾኑን አስታውሶ ወደ ሮም ተመልሶ ስብከቱን ቀጠለ፡፡

በሮማውያን ሕግ ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሮም አገር ተወላጅ ከኾነ የወንጀሉ ክብደትና ቅለት እየታየ ግርፋት ወይም ሞት ይፈረድበታል እንጂ በአንድ ወንጀል ሁለት ቅጣት አይቀጣም ነበር፡፡ ወንጀለኛው የውጪ አገር ዜጋ (ከሮም ውጪ) ከኾነ ግን ለምሳሌ ቅጣቱ ግርፋት ከኾነ ከተገረፈ በኋላ እስራት ይጨመርበታል፤ ቅጣቱ ሞት ከኾነም ከገረፉት በኋላ በመስቀል ወይም በሌላ መሣርያ ይገድሉት ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ዜግነቱ ሮማዊ አልነበረምና በግርፋትም፣ በእስራትም በሞትም እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡

እንደ ሥርዓታቸውም ቅዱስ ጴጥሮስን ከገረፉት በኋላ ሊሰቅሉት ሲሉ ወታደሮቹን ‹‹እንደ ክብር ንጉሥ እንደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አቁማችሁ ሳይኾን፣ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እንዳላቸው አድርገው ሐምሌ ፭ ቀን ዘቅዝቀው ሰቅለውታል፡፡ በመስቀል ላይ ሳለም ተከታዮቹን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ካዘዛቸው በኋላ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡ ሥጋውንም መርቄሎስ የሚባለው ደቀ መዝሙሩ ሽቱ ቀብቶ፣ በነጭ ሐር ገንዞ ዛሬ ቫቲካን በምትባለዋ ስፍራ በክብር ቀብሮታል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ

ቅዱስ ጳውሎስ ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ‹ሳውል› ይባል ነበር፡፡ ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ሕገ ኦሪትንና መጻሕፍተ ነቢያትን ተምሯል፡፡ ለሕገ ኦሪት ቀናኢ ከመኾኑ የተነሣም የክርስቶስ ተከታዮችን ዅሉ ያሳድድ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ የገዳዮቹ ልብስ ጠባቂ ነበር (ሐዋ. ፯፥፶፰፤ ፳፪፥፳)፡፡ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ ከመንገድ ላይ ለሐዋርያነት ተጠርቷል (ሐዋ. ፱፥፩-፴፩፤ ፳፪፥፩-፳፩)፡፡

ለሐዋርያነት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሳምኗል፡፡ ሲሰብክም ጣዖት አምላኪ፣ ሕመምተኛ፣ ችግረኛ፣ አረማዊና አይሁዳዊ እየመሰለ ብዙዎችን አስተምሮ ለእግዚአብሔር መንግሥት አዘጋጅቷል (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፲፱-፳፫)፡፡ ዐረብ፣ አንጾኪያ፣ እልዋሪቆን፣ ሊቃኦንያ፣ ሦርያ፣ ግሪክና ልስጥራን ካስተማረባቸው አገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ወንጌልን በመስበኩ ምክንያትም ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡ በልብሱ ቅዳጅም ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፲፱፥፲፩)፡፡ ሐዋርያው በቃል ካስተማረው ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ፲፬ መልእክታት አሉት፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ሲያርፍ

አገልግሎቱን ሊፈጽም ሲልም የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር የክርስቲያኖች ቍጥር እየጨመረ የመጣው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በመማረካቸው ምክንያት መኾኑን ተረድቶ፤ ይልቁንም የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሳይቀር በቅዱስ ጳውሎስ በመማረካቸው ተቈጥቶ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎው አስቀረበው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቀኝ እጁ ከሰንሰለቱ ጋር መስቀሉን ይዞ ንጉሡንና ወታደሮችን ሳይፈራ የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነትና አምላካዊ ሥልጣን ይመሰክር ነበር፡፡

ንጉሡም በቍጣ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ሮማውያን የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የሚቀጣው ሰው የሌላ አገር ዜጋ ከኾነ ከፍርዱ ውጪ ተጨማሪ ቅጣት ይቀጡትና ይገድሉት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን የሮም ዜግነት ስለ ነበረው ሳይገርፉ በአንድ ቅጣት ብቻ በሰይፍ እንዲገደል ወስነውበታል፡፡ ወደሚገደልበት ስፍራ ሲወስዱትም በንግግሩና በአስተያየቱ ዅሉ ምንም ፍርኀት አይታይበትም ነበር፡፡ እንዳውም በጦርነት ድል አድርጎና ማርኮ እንደ ተመለሰ ወታደር ይደሰት ነበር እንጂ፡፡ ለሚገድሉትም ይቅርታን ይለምን ነበር፡፡

በገዳዮቹና በተከታዮቹ ፊትም የክርስትና ሽልማቱ የእግዚአብሔር መንግሥት መኾኑን የሚያስገነዝብ ቃል እያስተማረ እግዚአብሔር የሚሰጠውን የጽድቅ አክሊል ለመቀበል ይቻኮል ነበር (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፮-፲፰)፡፡ ወታደሮች ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የኾነችውን የአንዲት ብላቴና መጐናጸፊያ ‹‹ዛሬ እመልስልሻለሁ›› ብሎ ከተቀበላት በኋላ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊትም የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤›› በማለት ራሱ በመልእክቱ እንደ ተናገረው (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፯-፰)፣ ፊቱን በብላቴናዋ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ አገልግሎቱን በሰማዕትነት ፈጽሟል፡፡

ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል፡፡ ሰያፊው ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገደለው ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና ‹‹ጳውሎስ ወዴት አለ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ራሱን ተቈርጦ በመጐናጸፊያሽ ተሸፍኖ ወድቋል›› ሲላት ‹‹ዋሽተሃል፤ እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ፡፡ እነርሱም የመንግሥት ልብስ ለብሰዋል፡፡ በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል፡፡ መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ፡፡ ይህችውም እነኋት፤ ተመልከታት›› ብላ ሰጠቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው፡፡ አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡

ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ጨለማውን ዓለም በማድመቃቸው ‹ብርሃናተ ዓለም› ተብለው ይጠራሉ፡፡ የቅዱሳኑ አገልግሎት፣ ገድላቸው እና ተአምራቸው በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በዜና ሐዋርያት እና በገድለ ሐዋርያት በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ እኛም በዓለ ዕረፍታቸውን ለማስታወስ ያህል ታሪካቸውን በአጭሩ አቀረብን፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንድንኖር፤ በመጨረሻም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሐምሌ ፭ ቀን፤
  • ዜና ሐዋርያት፤
  • ገድለ ሐዋርያት፡፡

ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ቀን ፳፻፱ .

ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ የኾው ቅዱስ ታዴዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ሐምሌ ፪ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ የቅዱስ ታዴዎስን ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት አስቀድሞ ቅዱስ ታዴዎስን እንደ መረጠው መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ ቅዱስ ታዴዎስ አባቱ እልፍዮስ ይባላል (ማቴ. ፲፥፫)፡፡ ሐዋርያው – ‹ልብድዮስ›፣ ‹የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ› እየተባለም ይጠራል (ሉቃ. ፮፥፲፮፤ ዮሐ. ፲፬፥፳፪፤ ሐዋ. ፩፥፲፫)፡፡  ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ከአይሁድ እና ከአረማውያን ወገን ብዙዎችን በክርስትና ሃይማኖት አሳምኖ በክርስቶስ ስም አጥምቋል፡፡ አንድ ቀን ወደ ሀገረ ስብከቱ ወደ ሦርያ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲሔድ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጐልማሳ አምሳል ተገልጦ ‹‹ወዳጄ ታዴዎስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ›› በማለት ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም የሐዋርያት አለቃ ነውና እንደ አባትነቱ ወደ ሦርያ ለማድረስ ከቅዱስ ታዴዎስ ጋር ሔደ፡፡ ከከተማዋ አጠገብ ሲደርሱም አንድ ሽማግሌ በሮችን ጠምደው ሲያርሱ አገኙ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሽማግሌውን ምግብ በለመናቸው ጊዜ ‹‹በሮቼን ጠብቁ›› አሏቸውና ምግብ ሊያመጡላቸው ወደ ቤታቸው ሔዱ፡፡ ሽማግሌው እስኪመለሱ ድረስም ቅዱስ ጴጥሮስ በሮችን ጠምዶ ሠላሳ ትልም አረሰ፡፡ ቅዱስ ታዴዎስም በዚያ የነበረውን የሥንዴ ዘር መዝራት ጀመረ፡፡ የተዘራው ዘርም ወዲያዉኑ በቅሎ፣ አድጎ፣ እሸት ኾነ፡፡ ሽማግሌው ምግብ ይዘው ከቤታቸው ሲመለሱም ቅዱሳን ሐዋርያት ያደረጉትን ተአምር አይተው ደነገጡ፡፡ ከእግራቸው ሥር ወድቀውም ለሐዋርያት ሰገዱላቸው፡፡ በኋላም ‹‹እናንተ ከሰማይ የወረዳችሁ አማልክት ናችሁን?›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛ የእግዚአብሔር ባሮች እንጂ አማልክት አይደለንም›› አሉ፡፡

ሽማግሌውም ‹‹ስላደረጋችሁልኝ በጎ ሥራ በምትሔዱበት ቦታ ዅሉ ልከተላችሁን?›› ባሏቸው ጊዜ ሐዋርያት ‹‹ይህንን ልታደርግ አይገባም፤ ነገር ግን በሮችን ለጌታቸው መልስና በቤትህ የምንበላውን ታዘጋጅልን ዘንድ ለባለቤትህ ንገራት፡፡ እኛ ወደዚህች ከተማ ገብተን እግዚአብሔር እስከሚጠራን ጊዜ ድረስ እንቆያለንና›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ሽማግሌውም የሥንዴውን እሸት ይዘው በሮችን እየነዱ ወደ ከተማ ሲሔዱ ወቅቱ የእርሻ እንጂ የእሸት ጊዜ አልነበረምና እሸት ይዘው በመመልከታቸው የከተማው ሰዎች ተገረሙ፡፡ ሽማሌውንም ‹‹ይህንን እሸት ከወዴት አገኘኸው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸው ግን ምላሽ አልሰጧቸውም ነበር፡፡ ሽማግሌው ሐዋርያት እንዳዘዟቸው በሮቹን ለጌታቸው መልሰው ቤታቸውን አሰናድተው ራት እንድታዘጋጅላቸው ለሚስታቸው ነገሩ፡፡

ወሬውን የከተማው መኳንንት በሰሙ ጊዜም ‹‹በክፉ አሟሟት እንዳትሞት እሸቱን ከወዴት እንዳገኘኸው ንገረን›› ብለው በሽማግሌው መልእክተኞችን ላኩባቸው፡፡ ሽማግሌውም ‹‹ሕይወት ከእኔ ጋራ ሳለ ሞትን አልፈራም!›› አሉ፡፡ ከዚያም ሐዋርያት ያደረጉትን ዅሉ ነገሯቸው፡፡ መኳንንቱም ‹‹ሐዋርያቱን አምጣቸው›› አሏቸው፡፡ ሽማግሌውም ወደ እርሳቸው ቤት ሲመጡ ማግኘት እንደሚችሉ ነገሯቸው፡፡ ሰይጣን የልቡናቸዉን ዐሳብ ወደ ክፋት ለውጦታልና ከመኳንንቱ ከፊሎቹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ለመግደል ተነሣሡ፡፡ ከፊሎቹ ግን ‹‹አምላካቸው ኢየሱስ የሚሹትን እንደሚያደርግላቸው ሰምተናልና ልንገድላቸው አንችልም፡፡ ነገር ግን አመንዝራ ሴት ወስደን በከተማው በር ርቃኗን እናስቀምጣት፡፡ እርሷን ሲያዩ ወደ ከተማችን አይገቡም፤›› አሉ፡፡ ይህን ማለታቸውም ቅዱሳን ሐዋርያት ንጹሐን እንደ መኾናቸው በዓይናቸው የሴት ልጅን ርቃን እንደማይመለከቱ መመስከራቸው ነበር፡፡

መኳንንቱ እንደ ተነጋሩት ሴትዮዋን በከተማው በር ርቃኗን አስቀመጧት፡፡ ሐዋርያው ታዴዎስ ባያት ጊዜም ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ወደ ከተማው ገብተን በከበረ ስምህ እስክንሰብክ ድረስ ይህቺን ሴት በአየር ላይ ይሰቅላት ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላክልን›› ብሎ ጸለየ፡፡ ጌታችንም ጸሎቱን ተቀበለውና ሴትዮዋ አየር ላይ ተሰቀለች፡፡ በዚህ ጊዜ የከተማው ሰዎችና መኳኳንንቱ ዅሉ እያዩአት ‹‹አቤቱ ፍረድልኝ›› እያለች ትጮኽ ጀመር፡: መኳንንቱ ግን ሰይጣን ልቡናቸውን አጽንቶታልና የሐዋርያትን ትምህርት አልተቀበሉም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ የሰዎቹን ልቡና የማረኩ መናፍስትን ርኩሳንን አባረረላቸው፡፡

ሰዎቹም የሐዋርያትን ትምህርት ተቀብለው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ሐዋርያው ታዴዎስም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ካጠመቃቸው በኋላ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው፡፡ በአየር ላይ የተሰቀለችውን ሴትም አውርዶ ዲያቆናዪት አደርጎ ሾማት፡፡ በዚያች ከተማ በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዕውሮች አዩ፤ ሐንካሶች ቆመው ሔዱ፤ ዲዳዎች ተናገሩ፤ ደንቆሮዎች ሰሙ፤ ለምጻሞች ነጹ፤ አጋንንትም ካደሩባቸው ሰዎች እየወጡ ተሰደዱ፤ ሙታንም ተነሡ፡፡ የከተማው ሰዎችም ይህንን ተአምር አይተው በቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ በእግዚአብሔር አመኑ፡፡

አንድ ሰይጣን ያደረበትና ገንዘብ የሚወድ ጐልማሳ ባለ ጠጋም ወደ ሐዋርያው ታዴዎስ መጥቶ ሰገደለትና ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ! እድን ዘንድ ምን ላድርግ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፡፡ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር፡፡ በአንተ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌላው ላይ አታድርግ፡፡ ደግሞም ገንዘብህን ሸጠህ ለድኆችና ለምስኪኖች ብትሰጥ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ድልብ ታገኛለህ›› በማለት ሕገ ወንጌልን አስተማረው፡፡ ጐልማሳውም ትምህርቱን በሰማ ጊዜ ተቈጥቶ ሐዋርያውን አነቀው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹የክርስቶስን አገልጋይ እንዴት ደፍረህ ታንቃለህ?›› ባለው ጊዜ ጐልማሳው ቅዱስ ታዴዎስን ለቀቀው፡፡ የእግዚአብሔር ኀይል በይረዳው ኖሮ ሐዋርያው ከመታነቁ ጽናት የተነሣ ዓይኖቹ ሊወጡ ነበር፡፡

ያን ጊዜም ቅዱስ ታዴዎስ ‹‹ጌታችን ሀብታም መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል› ሲል በእውነት የተናገረው እንዳንተ ላለው ሀብታም ነው›› አለው፡፡ ጐልማሳውም ‹‹ይህ ሊኾን አይችልም!›› ባለ ጊዜ ሐዋርያው ታዴዎስ በመንገድ ሲያልፍ ያገኘውን ባለ ግመል አስቁሞ መርፌ ገዝቶ ሊያሳየው ወደደ፡፡ መርፌ ሻጩ ሐዋርያውን ለመርዳት ፈልጎ ቀዳዳው ሰፊ የኾነ መርፌ አመጣለት፡፡ ቅዱስ ታዴዎስም ‹‹እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ፤ ነገር ግን በዚህች አገር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ቀዳዳው ጠባብ የኾነ መርፌ አምጣልን›› አለው፡፡ ቀዳዳው ጠባብ የኾነውን መርፌ ቅዱስ ታዴዎስ ተቀብሎ ‹‹ኀይልህን ግለጥ›› ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እጁንም ዘርግቶ ባለ ግመሉን ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከግመልህ ጋር በመርፌ ቀዳዳው ውስጥ እለፍ›› አለው፡፡ ሰውየውም እስከ ግመሉ ድረስ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡

ዳግመኛም ‹‹ሕዝቡ የፈጣሪያችንን የክርስቶስን ኀይል ይረዱ ዘንድ ዳግመኛ ገብተህ እለፍ›› አለው፡፡ ሰውየውም እንደ ታዘዘው ሦስት ጊዜ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡ ሕዝቡም ይህንን ተአምር አይተው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ‹‹ከቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ በቀር ሌላ አምላክ የለም›› እያሉ ተናገሩ፡፡ ያ ጐልማሳ ባለ ጠጋም ከሐዋርያው ታዴዎስ እግር በታች ወድቆ ሰገደና ‹‹ኀጢአቴን ይቅር በለኝ፡፡ ገንዘቤንም ዅሉ ወስደህ ለድኆችና ለምስኪኖች አከፋፍልኝ›› ሲል ተማጸነው፡፡ ሐዋርያውም እንደ ለመነው አደረገለት፡፡ የክርስትናን ሃይማኖትን ሕግ አስተምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጠመቀው፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ አከናውኖም ሥጋውን፣ ደሙን አቀበለው፡፡ በዚያች አገር አካባቢ የነበሩትን ዅሉንም በቀናች የክርስትና ሃይማኖት አጸናቸው፡፡ ከዚያ በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ከዚያች ከተማ ወጡ፤ ሕዝቡም በሰላም ሸኟቸው፡፡

ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ ቆይቶ ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራ ከደረሰበት በኋላ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሐምሌ ፪ ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመንም ሐምሌ ፳፱ ቀን የከበረ ዐፅሙ ከሦርያ ፈልሶ በቍስጥንጥንያ ከተማ በስሙ በታነጸች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ከዐፅሙም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገልጠዋል፡፡ ዅላችንንም የሐዋርያው ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሐምሌ እና ሐምሌ ፳፱ ቀን፤
  • ገድለ ሐዋርያት፣ ፲፱፻፺፬ .ም፤ አዲስ አበባ፣ ገጽ ፻፷፭ – ፻፸፩፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ልደት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

 ሰኔ ቀን ፳፻፱ .

ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የልደቱን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ፣ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዅሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅ እና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡

ካህኑ ዘካርያስም መልአኩን ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በኹኔታውም በቤተ መቅደስ ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ›› ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ዘመነ ብሉይ ሊፈጸም፣ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን (በሥጋ ሊገለጥ) ስድስት ወራት ሲቀረው፣ ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ዘመዶቹ ስሙን በአባቱ መጠርያ ዘካርያስ› ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን ‹‹ዮሐንስ ይባል› አለች፡፡ የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኀጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ነቢይነት እና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት አብሣሪነት የሚመለከት ትንቢት አስቀድሞ ተናገሯል (ሉቃ. ፩፥፶፯-፸፱)፡፡

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፤ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፤ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፤ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹… ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ሲል ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱ ይደርብን፤ ጸሎቱ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፴ ቀን፤
  • የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ. ፩፥፩-፹፤
  • ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፡፡

የአባ ሙሴ ጸሊም ዕረፍት

አባ ሙሴ ጸሊም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልዩ ልዩ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስ እና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ተመልሰው ለመንግሥተ ሰማያት ከተጠሩ ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን የአባ ሙሴ ጸሊምን የዕረፍት ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤

የአባ ሙሴ ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) በዓለ ዕረፍት በየዓመቱ ሰኔ ፳፬ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ አባ ሙሴ ቆዳቸው ጥቁር በመኾኑ ‹ጸሊም› (ጥቁር) በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡ እኒህ ቅዱስ ለሰማዕትነት ክብር ከመብቃታቸው በፊት በቆዳቸው ብቻ ሳይኾን በግብራቸውም የጠቆሩ ማለትም ኀጢአትን የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ያለ መጠን ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይቀሙ፣ ያመነዝሩ እንደዚሁም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡ በሥጋቸው ጠንካራ፣ በጕልበታቸውም ኃይለኛ ከመኾናቸው የተነሣም ሊቋቋማቸው የሚችል ማንም እንዳልነበረ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ በባዕድ አምልኮ ተይዘው የኖሩት አባ ሙሴ ጸሊም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይም ነበሩ፡፡

በዚህ ዓይነት ሰይጣናዊ ሥራ ከኖሩ ከዓመታት በኋላ የሰውን ልጅ ጠፍቶ መቅረት የማይወደው አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ወደ ቤቱ መልሶ አምላክነቱን ለመመስከር፣ ስሙን ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መርጧቸዋልና የፀሐይን ፍጡርነት፣ ግዑዝነት ገለጸላቸው፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ ወደ ፀሐይ በማንጋጠጥ ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንኽ አነጋግረኝ … የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ›› እያሉ ይመራመሩ ጀመር፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም፣ የገዳመ አስቄጥስ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታል፤ እንደዚሁም ያነጋግሩታል እየተባለ ሲነገር ይሰሙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ወደ ገዳሙ ይሔዱ ዘንድ አነሣሣቸው፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደዉም ከካህናቱ አንዱ የኾኑትን አባ ኤስድሮስን ‹‹እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ›› አሏቸው፡፡ እርሳቸውም እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ገዳሙ መምጣታቸውን አድንቀው ከአባ መቃርስ ጋር አገናኟቸው፡፡ አባ መቃርስም የክርስትና ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቀው ‹‹ታግሠህ የማስተምርህን ትምህርተ ወንጌል ከጠበክ እግዚአብሔርን ታየዋለህ›› እያሉ በተስፋ ቃል እያጽናኗቸው ቆዩ፡፡ ከዓመታት በኋላም በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ፈትነው አመነኮሷቸው፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም ብዙ ገድልን ከሚጋደሉ ቅዱሳን አብልጠው መጋደል በጀመሩ ጊዜም ሰይጣን ለማሰናከልና ከገዳሙ ለማስወጣት በማሰብ ቀድሞ ያሠራቸው በነበረው ግብረ ኃጢአት ሊዋጋቸው ጀመረ፡፡ አባ ኤስድሮስም እያጽናኑ፣ እየመከሩ በተጋድሏቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ያተጓቸው ነበር፡፡ የመነኮሳቱ የውኃ መቅጃ ሥፍራ ሩቅ ነበርና አረጋውያን መነኮሳት በመንገድ ብዛት እንዳይደክሙ አባ ሙሴ ዘወትር ውኃ እየቀዱ በየበዓታቸው ደጃፍ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረጉ በመጋደልና በማገልገል ላይ ሳሉ ጸላዔ ሠናያት ሰይጣን እግራቸውን በከባድ ደዌ መታቸውና ለብዙ ቀናት የአልጋ ቁራኛ ኾነው ኖሩ፡፡ እርሳቸውም በደዌ የሚፈታተናቸው ጥንተ ጠላት ሰይጣን መኾኑን ተረድተው ሰውነታቸው ደርቆ በእሳት የተቃጠለ እንጨት እስኪመስል ድረስ ተጋድሏቸውን እጅግ አበዙ፡፡ እግዚአብሔርም ትዕግሥታቸውን ዓይቶ ከደዌያቸው ፈወሳቸው፤ የሰይጣንን ውጊያ አርቆ ጸጋውን አሳደረባቸው፡፡

አባ ሙሴ፣ እርሳቸው ወደሚኖሩበት ገዳም የተሰበሰቡ ፭፻ የሚኾኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ሳሉ ‹‹በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጧቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና›› (፩ኛጢሞ.፫፥፲፫) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው፣ ከተጋድሏቸውና ከትሕትናቸው አኳያ ማኅበረ መነኮሳቱ ለቅስና መዓርግ መረጧቸው፡፡ ሥርዓተ ክህነት ሊፈጽሙላቸው ወደ ቤተ መቅደስ በአቀረቧቸው ጊዜም ሊቀ ጳጳሳቱ ‹‹ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት›› ብለው አረጋውያኑን ተቆጧቸው፡፡ አባ ሙሴ ይህን ቃል ከሊቀ ጳጳሳቱ በሰሙ ጊዜም ‹‹መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ! መልካም አደረጉብህ›› እያሉ ራሳቸውን በመገሠፅ ከቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን የተመለከቱት ሊቀ ጳጳሳቱም በሌላ ቀን አባ ሙሴን አስጠርተው በአንብሮተ እድ በቅስና መዓርግ ሾሟቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ሙሴ ሆይ! እነሆ በውስጥም በውጪም ዅለመናህ ነጭ ኾነ›› ብለው በደስታ ቃል አናገሯቸው፡፡ ሙሴም በተቀበሉት መዓርግ እግዚአብሔርን፣ መነኮሳቱንና ገዳሙን በትጋት ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡

እግዚአብሔር በአባ ሙሴ ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና አባ ሙሴ የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም ከመነኮሳቱ ተለይተው ‹‹ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?›› እያሉ እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ እርሱም በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ ነውና ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዝንቦ የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡ እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑ በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን ‹‹ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኹት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን›› አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

በአንዲት ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ ገዳም በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት ለአባ ሙሴ ጸሊም ስለ ተዘገጀው የሰማዕትነት ክብር አስቀድመው ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰሙ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለው መለሱ፡፡ በብሉይ ኪዳን ‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ›› የሚል አንድ ሰው በሠራው ወንጀል መጠን እንዲቀጣ የሚያስገድድ ሕግ ነበር (ዘፀ. ፳፩፥፳፬-፳፭፤ ማቴ. ፭፥፴፰)፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም ለገዳማዊ ሕይወት ከመብቃታቸው በፊት ሰዎችን በሰይፍ ሲያጠፉ እንደ ነበሩት ዅሉ እርሳቸውም በሰይፍ ለመሞት መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለዋል፡፡ ይህም በንጹሕ ልቡናቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውን የሚያመለክት ንግግር ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ያገኙትን ዅሉ በሰይፍ የሚገድሉ የበርበር ሰዎች ወደ በዓታቸው መጡ፡፡ አባ ሙሴም አብረዋቸው የነበሩትን መነኮሳት ‹‹መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን አንተስ አትሸሽምን?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም እኔ ‹‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላልስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ይቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠባበቃት ኖሬአለሁ›› በማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀታቸውን ነገሯቸው፡፡ ይህን ቃል እየተነጋገሩ ሳሉም የበርበር ሰዎች ከበዓታቸው ገብተው በሰይፍ ቈርጠው ገደሏቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ሰባት መነኮሳት በሰማዕትነት ሞቱ፡፡ አንደኛውም ከምንጣፍ ውስጥ ተሠውረው ከቆዩ በኋላ በእጁ አክሊል የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ሲጠባበቅ በተመለከቱ ጊዜ ከተሠወሩበት በመውጣት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት የተናገሩት ትንቢት ደረሰ፡፡ ‹‹አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› ሲል ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም በአባ ሙሴ ተጋድሎ ተፈጸመ  (ሮሜ. ፰፥፴)፡፡ የአባ ሙሴ ጸሊም ሥጋም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ እንደሚገኝ፤ ከእርሱም ብዙ ድንቆችና ተአምራት እንደሚታዩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተገልጿል፡፡

‹‹እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ማቴ.፲፩፥፲፪/፣ አባ ሙሴ ጸሊም አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍተዋታል፤ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርሰውን የጽድቅ ሥራ ትተው ወደ ገሃነም በሚያስጥል ኃጢአት ኖረዋል፡፡ በኋላ ግን እግዚአብሔርን ፈልገው ከማግኘታቸው ባሻገር በመንፈሳዊ ተጋድሎ በመበርታት ለክህነት እና ለቅድስና በቅተው ምድራዊ ሕይወታቸውን በሰማዕትነት አጠናቀዋል፡፡ በክህደት፣ በኑፋቄ እንደዚሁም በኀጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር እቅፍ ርቀን የምንኖር ክርስቲያኖችም ከሃዲ፣ ሰውን ገዳይ፣ ቀማኛ፣ ዘማዊ የነበረውን ሰው ወደ አሚነ እግዚአብሔር እና ወደ ገቢረ ጽድቅ በመለወጥ ደግ አባት፣ መምህር፣ የሚያጽና እና ሥርዓትን የሚሠራ ካህን፣ እንደዚሁም ሰማዕት ለመኾን ያበቃችውን፤ በተጨማሪም በዅሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስሙ ለዘለዓለሙ እንዲጠራ ያደረገችውን የንስሓን ኃይል በማስተዋል ዛሬዉኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡ ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድም ዘወትር እንማጸነው፡፡ እግዚአብሔር እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኀጢአትንም ይቅር የሚል አምላክ ነውና (ዘፀ. ፴፬፥፯፤ ማቴ. ፮፥፲፪)፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን! እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊምና በሰማዕታት ዅሉ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፬ ቀን፡፡

የንጉሥ ሰሎሞን ዕረፍት

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ሰኔ ፳፫ ቀን ንጉሥ ሰሎሞን፣ አባ ኖብ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ፣ ቅዱስ ፊልጶስና ሌሎችም ቅዱሳን ይታወሳሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በመጽሐፈ ስንክሳር የተመዘገበዉን የንጉሥ ሰሎሞንን የዕረፍት ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ንጉሥ ዳዊት ሕግ ተላልፎ ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር በዝሙት በመውደቅ እና ባሏን በማስገደል ኀጢአት በመፈጸሙ እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩ ናታንን ልኮ ስለ በደሉ ገሠፀው፡፡ በዚህ ጊዜ ንስሐ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ እግዚአብሔርም ንስሐዉን ተቀብሎ ኀጢአቱን ይቅር አለው፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤርሳቤህን ሚስቱ አደረጋትና ሰሎሞንን ወለዱ፡፡ ሰሎሞን ሲያድግም በዙፋኑ እንደሚተካው ንጉሥ ዳዊት ለቤርሳቤህ ቃል ገባላት፡፡ ብላቴናው ሰሎሞን ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜም አዶንያስ በዳዊት ምትክ ለመንገሥ ዐስቦ በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ኤልቲ ዘዘኤልቲ በሚባል ቦታ ላሞችን፣ በጎችንና ፍየሎችን አርዶ የሠራዊት አለቆችን፤ የንጉሥ አሽከሮችንና ካህኑ አብያታርንም ጠርቶ ግብዣ አደረገ፡፡ እነርሱም ‹‹አዶንያስ ሺሕ ዓመት ያንግሥህ!›› እያሉ አወደሱት፡፡

ዳዊትም የአዶንያስን ሥራ ከቤርሳቤህና ከነቢዩ ከናታን በሰማ ጊዜ የዮዳሄን ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን፣ ነቢዩ ናታንንም፣ ግራዝማችና ቀኛዝማቹን ዅሉ አስጠርቶ ሰሎሞንን በራሱ በቅሎ ላይ አስቀምጠው፡፡ ሠራዊቱም ወደ ግዮን እንዲያወርዱትና በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅ ቀብተው እንዲያነግሡት፤ ሰሎሞንም በአባቱ ፈንታ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ንጉሥ ዳዊት አዘዘ፡፡ ካህኑ ሳዶቅም እንደታዘዘው ሰሎሞንን የንግሥና ቅባትን ቀባው፡፡ ቀርነ መለከቱንም ነፉ፤ ሕዝቡም ዅሉ ሰሎሞንን ‹‹ሺሕ ዓመት ያንግሥህ!›› እያሉ ተከትለዉት ወጡ፡፡ ከበሮም መቱ፤ ታላቅ ደስታም አደረጉ፡፡ ከድምፃቸው ኃይል የተነሣ ምድሪቱ ተናወጠች፡፡ ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ፡፡ የንጉሡ አሽከሮችም ‹‹እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ ከፍ ከፍ ያድርገው›› እያሉ ዳዊትን አመሰገኑት፡፡ ዳዊትም ‹‹ዐይኖቼ እያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ለእኔ ለባሪያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን›› አለ፡፡

ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ በደረሰ ጊዜም ‹‹እኔ ሰው በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ፡፡ አንተ ግን ጽና፤ ብልህ ሰውም ኹን፡፡ በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈዉን የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ጠብቅ›› ብሎ ልጁ ሰሎሞንን አዘዘው፡፡ ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን በገባዖን ምድር መሥዋዕትን በሠዋ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጾ ‹‹እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበዉን ለምነኝ›› አለው፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኔ ባሪያህ መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝና ለዚህ ለብዙ ወገንህ በእውነት እፈርድ፤ ክፉዉን ከበጎው ለይቼ ዐውቅ ዘንድ ዕውቀትን ስጠኝ?›› ብሎ ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹ብዙ ዘመንንና ባለጠግነትን፤ የጠላቶችህንም ጥፋት አለመንኸኝምና፡፡ ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እነሆ እንዳልህ አደረግሁልህ፡፡ እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ፤ ከአንተም በኋላ እንደ አንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን፤ ያለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ዅሉ ሰጠሁህ›› አለው፡፡

ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንዳለመ ዐወቀ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶም በጽዮን በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለው መሠዊያ ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ ለሰዎቹና ለእሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ፡፡ በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ እርሱ መጥተው በአንድ ቤት እንደሚኖሩና በሦስት ቀን ልዩነት ልጆችን እንደ ወለዱ፤ አንደኛዋ ሴትም ልጇን በሌሊት ተጭናው በሞተባት ጊዜ ያልመተዉን የሌላኛዋን ልጅ ወስዳ የሞተዉን ልጅ እንዳስታቀፈቻት በማብራራት ‹‹የሞተው ልጅ ያንቺ ነው፤ ደኅናው ልጅ የኔ ነው›› የሚል አቤቱታ ለንጉሥ ሰሎሞን አቀረቡ፡፡ ንጉሡም የሁለቱንም ንግግር ካደመጠ በኋላ ‹‹ደኅነኛዉን ልጅ በሰይፍ ቈርጣችሁ እኩል አካፍሏቸው›› ብሎ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ያልሞተው ልጅ እናት ‹‹ልጁን አትግደሉት፡፡ ደኅናዉን ለእርሷ ስጧት›› ስትል፤ ሁለተኛዋ ሴት ግን ‹‹ቈርጣችሁ አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርሷም አይኹን›› አለች፡፡ ንጉሡም እውነቱን ከሴቶቹ አኳኋን ተረድቶ ‹‹‹ልጁን አትግደሉት› ላለችው ሴት ደኅነኛዉን ሕፃን ስጧት፤ እርሷ እናቱ ናትና›› ብሎ ፈረደ፡፡ በዚህ ፍርዱ ምክንያትም እስራኤል ዅሉ ቅን ፍርድ ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በእርሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና ንጉሡን ፈሩት፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ማነጽ ጀመረ፡፡ ቤተ መቅደሱንም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በ፬፻፹ኛው፤ ሰሎሞን በነገሠ በ፬ኛው ዓመት፣ በ፪ኛው ወር ጀምሮ በ፲፩ኛው ዘመነ መንግሥቱ፣ በ፰ኛው ወር ሠርቶ በ፯ ዓመታት ውስጥ ፈጸመው፡፡ የራሱን ቤትም በ፲፫ ዓመት ሠርቶ ጨረሰ፡፡ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና የራሱን ቤት ከፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሎች፣ የነገድና የአባቶቻቸዉን ቤት አለቆች ዅሉ በ፯ኛው ወር (በጥቅምት) በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው፡፡ ካህናቱም ታቦቷን፣ የምስክሩን ድንኳንና ንዋያተ ቅድሳቱን ዅሉ ተሸክመው ንጉሡና ሕዝቡም በታቦቷ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸዉን በጎችንና ላሞችን እየሠዉ ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አገቧት፡፡

ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ የእግዚአብሔር ብርሃን ቤተ መቅደሱን ሞላው፡፡ ካህናቱም ሥራቸዉን መሥራትና ከብርሃኑ ፊቱ መቆም ተሳናቸው፡፡ ያንጊዜም ሰሎሞን ‹‹‹እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁብሏል፤ እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደሱን በእውነት ሠራሁልህ›› አለ፡፡ ከዚያም ፊቱን ወደ መሠዊያው መልሶ፣ እጆቹን ዘርግቶ፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ሰገደና ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አደረሰ፤ ሕዝቡንም ዅሉ መረቃቸው፡፡ ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላም ከመሠዊያው ፊት ተነሥቶ ቆመና ‹‹ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን›› እያለ በታላቅ ቃል የእስራኤልን ማኅበር መረቃቸው፡፡ ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርበው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ሰሎሞን ስለ ሰላም ለእግዚአብሔር የሠዋቸው በጎች በቍጥር ፳፪ ሺሕ ነበሩ፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጾ ‹‹የለመንኸኝን ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ፤ እንደ ልመናህም ዅሉ አደረግሁልህ፡፡ ስሜ በዚያ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸዉን ቤተ መቅደስ አከበርሁት፡፡ ልቡናዬም፣ ዐይኖቼም በዘመኑ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ›› ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ጥበብና ጸጋን የሰጠው ይህ ታላቅ ንጉሥ ለዐርባ ዓመት እስራኤልን በቅንነት አስተዳድሯል፡፡ ከንግሥናው በተጨማሪም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅሙ፣ ትንቢትንና ትምህርትን የያዙ የጥበብና የመዝሙር መጻሕፍትንም ጽፏል፤ እነዚህም፡- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ ተግሣፅና መጽሐፈ ጥበብ ናቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ከመንገሡ በፊት ፲፪፤ ከንግሥናው በኋላ ፵፤ በድምሩ ፶፪ ዓመታት በሕይወተ ሥጋ ከኖረ በኋላ በዛሬው ዕለት ሰኔ ፳፫ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፏል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን፡፡ የአባቶቻችን በረከት ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፫ ቀን፡፡

ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ቀን ፳፻፱ .

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበልን ሰኔ ፳ ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከሚከብሩ ከእመቤታችን በዓላት አንደኛው ሲኾን ታሪኩንም በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ወደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ርእሰ ሐዋርያት እያለ እኛ መሥራት አይገባንም ብለው በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡

በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ኾኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡

ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲኾን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲኾኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መኾኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲኾን፣ ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡

አንድም መጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲኾኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡

ይህም በታች (በምድር) የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት እንደማይቻላቸው፣ ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት (መፈጸም) እንደማይቻላቸው ያጠይቃል፡፡ እንደዚሁም በላይ የሚኖሩ መላእክት ወደ ታች መውረድ እንደሚቻላቸው ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም (መሥራት) እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡

በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን (የብርሃን መንበር)፤ ታቦተ ብርሃን (የብርሃን ታቦት)፤ መንጦላዕተ ብርሃን (የብርሃን መጋረጃ)፤ እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር (መንበሩን የሚሸከሙ)፤ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡ ጽርሐ አርያም – የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን – የመንበር፤ መንጦላዕተ ብርሃን – የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፤ ፬ቱ ፀወርተ መንበር – የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፤ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር – የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) አምሳሎች ናቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ቀን፡፡
  • መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱ – ፫፻፶፩፡፡