ከራድዮን
ከራድዮን ነጭ ወፍ ሲሆን በሊቃውንቱም ዘንድ የታወቀ ነው። ጠቢባን በድካም ፈልገው አድነው ይይዙታል፤ የታመመ ሰው ቢኖር ያቀርቡታል፤ እርሱም በሽተኛውን ትኩር ብሎ ያየዋል፤ የማይድን ለሞት የቀረበ ከሆነ ፊቱን አዙሮ ይመለሳል፤ ቀኑ ገና ከሆነ ግን አፉን ከፍቶ ከበሽተኛው አፍ እስትንፋሱን ይወስዳል፤ በልዑል እግዚአብሔር ኃይል የሰውየው ደዌ ሙሉ ለሙሉ ወደ ወፉ በእስትንፋሱ ይተላለፋል። ሰውየው ይድናል፤ ወፉ ይታመማል። ፊት ነጭ የነበረው እንደ ከሰል ይጠቁራል፤ ሕመም ሲሰማው ወደ አየር ይነጠቃል፤ ሲብስበት ወደ ባሕር ራሱን ይወረወራል። በባሕር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ቆይቶ ጠጉሩን መልጦ በዐዲስ ተክቶ፣ ድኖ፣ታድሶ፣ ኃያል ሆኖ ይወጣል። ይህ ፍጥረት በዕለተ ሐሙስ የተፈጠረ ፍጥረታት ነው፡፡ ስለምን ፈጠረው? ቢሉ የወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማያምኑ ትምህርት ምሳሌ አብነት ይሆን ዘንድ ይህን ወፍ የማዳን ኃይል ሰጥቶ ፈጥሮታል።