በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስም የተገነባው ዘመናዊ ሕንጻ ተመረቀ፡፡

ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በደመላሽ ኃይለ ማርያም

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በከላላ ወረዳ ቤተ ክህነት በ፳፻፫ ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ መሠረቱ የተቀመጠው፣ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት በአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስም የተገነባው ባለ ሦስት ፎቅ ኹለገብ ዘመናዊ ሕንጻ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይም ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባኤ ሓላፊ፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝና ሌሎችም የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የዞኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ማኅበሩ ከሚሠራቸው ፻፳ወ፮ (126) ፕሮጀክቶች መካከል ይህ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ፕሮጀክት አንዱ መኾኑን ገልጸው፣ ከመሠረቱ መቀመጥ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የየመምሪያ ሓላፊዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ ዘመናዊ ሕንጻ በከተማው ካሉት አራት ሕንጻዎች መካከል አንዱ ሲኾን፣ በውስጡም ለእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት የሚውሉ ዐሥራ ስምንት ክፍሎች፣ የባንክ ወይም የምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል፣ ለንግድ ሥራ የሚኾኑ ሱቆች እና ሌላም ሥራ ሊሠራባቸው የሚችሉ ክፍሎችን የያዘ ሲኾን፣ ከዚህ ኹሉ አገልግሎት የሚገኘው ገንዘብ ተሰብስቦ ለደብረ ባሕርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና አባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም አገልግሎት ማጠናከሪያነት እንደሚውል የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር የኾኑት ዲ/ን አእምሮ ይሄይስ አስረድተዋል፡፡

ዲ/ን አእምሮ አያይዘውም የአባ ጊዮርስ ዘጋሥጫ ዘመናዊ ሕንጻ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የበላይ ሓላፊነት በሚዋቀረው ኰሚቴ እንደሚመራ ገልጸው፣ በዚህም የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ የሚቀጥል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና ሌሎች የክብር እንግዶች ሕንጻውን ከጐበኙ በኋላ በአባቶች ጸሎት እና ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡

የ፭ኛው አገር ዓቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አጭር ዳሰሳ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሳምንት የአንድነት ጉባኤውን ያካሒዳል፡፡

በያዝነው ዓመትም ከሰኔ ፲-፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሦስት ቀናት በቆየው ጉባኤ የየአህጉረ ስብከቶች ሰ/ት/ቤቶች ሪፖርቶችና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

ለሦስት ቀናት በቆየው በዚህ የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ የአንድነት ጉባኤ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች፣ እንደዚሁም የወጣቶች የአገልግሎት ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው፣ በ፳፻፰ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተዳስሰዋል፡፡

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የአሕዛብንና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ በሚመለከት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በተገኙበት ለጉባኤው የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

በጉባኤው መዝጊያ ዕለትም የ፳፻፱ ዓ.ም ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተካሒዷል፡፡

በውይይቱም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የዕድሜ ገደብና የሥራ አስፈጻሚዎች የአገልግሎት ዘመን መሻሻል አለበት ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የ፳፻፱ ዓ.ም ዓመታዊ የተግባር ዕቅድ በጉባኤው ውይይት ከተደረገበት በኋላ ዕቅዱ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡

የ፳፻፱ ዓ.ም የመሪ ዕቅዱ ግቦች፡- ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤት አገልግሎትን ለማስፋትና ለማጠናከር መዘገጀቷን ማሳወቅ፣ በዓላማው ዙሪያ ሕዝቡን በስፋት ማነሣሣትና ለተግባር ማንቀሳቀስ፤ ቢጽ ሐሳውያንን የመከላከል ዘመቻ፤ እንደዚሁም የሰ/ት/ቤቶችን ሥርዓተ ትምህርት የማስቀጠልና የመከለስ ጥናት ሲኾኑ፣ በመሪ ዕቅዱ በመጀመሪያ አንድ ዓመት ከመንፈቅም፡- የሰንበት ት/ቤቶችን የዝማሬ ሥርዓት እና የሰንበት ት/ቤቶችን አንድነት መዋቅር ማጠናከር የሚሉ ነጥቦች ተካተዋል፡፡

በጉባኤው መዝጊያ ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ካልዕ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የተገኙ ሲኾን፣ በዕለቱ ቅዱስ ፓትርያርኩ ‹‹አንትሙሰ ንበሩ በኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤›› /ሉቃ.፳፬፥፵፱/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ትምህርት በሰጡበት ወቅትም ‹‹ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድላቸው ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲቆዩ ታዝዘዋል፡፡ እኛም እግዚአብሔር ማስተዋሉን፣ ጥበቡንና ጸጋውን እንዲያድለን በቤተ ክርስቲያን መቆየት ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡

እንደዚሁም ‹‹ወጣቱ ትውልድ ትኩስ ስለኾነ ኹሉም ነገር የሚጎዳ አይመስለውም፡፡ ክፉዉን ከበጎው ለመለየት የሚቻለን መንፈስ ቅዱስ ሲያድርብን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚያድርብን ደግሞ ሐቀኝነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ እምነት፣ አንድነት ሲኖረን ነው፡፡ ጊዜውም መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ወቅት ነውና ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት ማዘጋጀት ይገባናል፤›› ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹ይህ ዓለም በብዙ ጣጣዎች የተሞላ ነውና በአገልግሎታችሁ ላይ ልዩ ልዩ ፈተና ሊመጣባችሁ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ፀላዔ ሠናያት ሰይጣንን ፃእ መንፈስ ርኵስ ማለት ያስፈልጋል፤›› ካሉ በኋላ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለቤተ ክርስቲያን ሞገስ፣ ድምቀትና ተጨማሪ ሀብት መኾናቸውን ጠቅሰው ‹‹የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ስትሉ የምታነሡትን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም ‹‹ይህንን ሰላማዊ ጉባኤ በሰላም በማካሔዳችሁ ለደስታችን ወሰን የለውም፡፡ በዛሬው ዕለት በዚህ ጉባኤ ተገኝቼ ቡራኬ በመስጠቴ ደስታ ይሰማኛል፤›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መ/ር ዕንቈባሕርይ ተከሥተ የመዝጊያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ለጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትንና በጉባኤው የተገኙ የየሰንበት ት/ቤት ተወካዮችን ካመሰገኑ በኋላ ለየሀገረ ስብከቱ ሰ/ት/ቤት መምሪያዎች ፴፬ የመዝሙር ሲዲዎች በነጻ እንዲሠራጩ መደረጉን ገልጸው ‹‹ከእንግዲህ የመናፍቃንን ዘፈንና ቀረርቶ የምንሰማበት ጊዜ አይኖርም፡፡ ከዚህ በኋላ ኹላችንም ወደ ድጓው፣ ጾመ ድጓው ነው የምንሔደው!›› የሚል ቁጭት አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ረፋድ ላይ በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተው ይህ የአንድነት ጉባኤ ባለ ፲፭ ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫውን በፓትርያርኩ ፊት ካቀረበ በኋላ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከምሽቱ ፲፩ ተፈጽሟል፡፡

በጋራ የአቋም መግለጫውም፡- የተሐድሶ መናፍቃን የእምነት መግለጫ፣ የሰ/ት/ቤቶች በየቦታው መቋቋም፣ የአባላት የአገልግሎት ዘመን መሻሻል፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እንግልትና ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ዐበይት ነጥቦች ተካተውበታል፡፡ የጉባኤውን ሙሉ የጋራ አቋም መግለጫ ተራ ቍጥሮችን፣ አንዳንድ ቃላትንና ፊደላትን አስተካክለን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፭ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የወጣ የጋራ አቋም መግለጫ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃለ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የወሊሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡባዊ ዞን የማይጨው፤ የምሥራቅ ትግራይ አዲግራትና መቐለ ዙሪያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ፤ የጉራጌ ስልጤ፣ ከምባታና ሐድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤

የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላችሁ የክብር እንግዶች፤

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤን ወክለን በ፭ኛው አገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የተሳተፍን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ ከሰኔ ፲-፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ላለፉት ሦስት ቀናት በማደራጃ መምሪያው ዓመታዊ የአገልግሎት ዘገባ፣ በ፳፭ አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍል የሥራ ክንውን ሪፖርት፤ እንደዚሁም የሰንበት ት/ቤቶች አባላት በኾኑ ባለሙያዎች በቀረቡ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡

የመምሪያው ዘገባም ኾነ ከ፳፭ አህጉረ ስብከት የመጡ ተወካዮች ያቀረቡት ሪፖርት ሰንበት ት/ቤቶች እጅግ በርካታ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማፋጠን እየተጉ መኾናቸውን አስገንዝቧል፡፡

ኾኖም ግን በየአህጉረ ስብከቱ ያሉ መናፍቃን እና አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖዎች፣ በየአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እየደረሱ ያሉ የአስተዳደር በደሎች፣ የበጀት እና የመምህራን እጥረት፣ የመሰብሰቢያና የመማሪያ ቦታ አለመኖር፣ የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ስፋት እና ለትራንስፖርት አመቺ አለመኾን አገልግሎቱን እየተፈታተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ኾነው ተመዘግበዋል፡፡

በመጨረሻም በሪፖርቱም ኾነ በጥናታዊ ጽሐፎቹ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በተደረገው የጋራ ውይይት በቀጣይነት ሰንበት ት/ቤቶች በጋራ የምንሠራቸውን እና የምንስማማባቸውን የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል፤

፩.የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የ፭ ዓመት ዕቅድ ማለትም ከ፳፻፮-፳፻፲ ዓ.ም ድረስ የታቀደውን መሪ ዕቅድ በቀሩት ጊዜያትም ለመፈጸምና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

፪.የሰ/ት/ቤቶች አጠቃላይ መሪ ዕቅድ የኹሉም አጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዕቅድ አካል እንዲኾን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችም የሰ/ት/ቤቶችን መሪ ዕቅድ ከዕቅዳቸው ጋር በማገናዘብ በዕቅድ እንዲካተቱ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤

፫.መልክዓ ምድርን መሠረት ያደረገ የሰንበት ት/ቤቶች ትስስር በማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች ባልተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች እንዲቋቋሙ፣ በተቋቋሙባቸው ደግሞ የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው ለማድረግ እንሠራለን፡፡

፬.በአገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴና መጠነ ሰፊ ጥፋትን አስመልክቶ በመረጃ ክፍል የተሰበሰቡና የተደራጁ ማስረጃዎችን ለቅዱስነትዎና ለቅዱስ ሲኖዶስ እንድናቀርብ እንዲፈቀድልን በአንድነት እንጠይቃለን፡፡

፭.በ፳፻፬ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙ ፲፮ ግለሰቦችና ፰ ማኅበራት ያስተላለፏቸው የምንፍቅና ትምህርቶችና መጻሕፍት በሊቃውንት ጉባኤ መልስ እንዲሰጣቸው የታዘዘ ቢኾንም ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ምላሽ ባለመሰጠቱ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ የሚል የክህደት መግለጫ እስከ ማውጣት ደርሰዋል፡፡ ስለኾነም ለእነዚህ አካላት አስቸኳይ ምላሽ ይሰጥልን ዘንድ በአንድነት እንጠይቃለን፡፡

፮.በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያኒቷ ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለማስቆም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፡፡

፯.ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ሰ/ት/ቤቶች የቀረበው የፕሮቴስንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ መረጃ ውሳኔ እንዲሰጠው፤ ውሳኔው ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቷ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፡፡

፰.በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በተሳሳተ አመክንዮ በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አባላት ላይ እየደረሰ ያለው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲቆምልን በአንጽዖት እንጠይቃለን፡፡

፱.ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰር እና ከማንገላታት እንዲታቀቡ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል መመሪያ እንሰጥልን እንጠይቃለን፡፡

፲.በቃለ ዓዋዲው እና በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በወጣው ውስጠ ደንብ ላይ የተጠቀሰው የሰ/ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣልን በድጋሜ እንጠይቃለን፡፡

፲፩.ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች የሚደርስ የፋይናንስ ትስስር እና አያያዝ ሥርዓት በመምሪያው በኩል ተጠንቶ እንዲጸድቅልን እንጠይቃለን፡፡

፲፪.በዘመናችን ሚዲያ በወጣቱ እና በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለሚገኝ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተምህሮ ለምእመናን በስፋት ማዳረስ እንዲቻል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ እና የሚተዳደር፣ ቤተ ክርስቲያኒቷንም የሚወክል የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ሥርጭት በመጀመሩ ከመምሪያው ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በጋራ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡

፲፫.ተወካዮቻቸውን ያልላኩ አህጉረ ስብከት ተለይተው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፡፡

፲፬.በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶቻችን ጋር በመኾን ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት እና ልዕልና የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡

፲፭.የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ምሩቃን ጋር ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፡፡

ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም፡፡

የደቡብ ማእከላት የአንድነት ጉባኤ አካሔዱ፡፡

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በሐዋሳ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በሐዋሳ ማእከል አዘጋጅነት በደቡብ ማስተባበሪያ ሥር ያሉት የዘጠኝ ማእከላት ሥራ አስፈጻሚዎችና አባላት ከሰኔ ፫-፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ በሐዋሳ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የግቢ ጉባኤ አዳራሽ የልምድ ልውውጥና የአንድነት ጉባኤ አካሔዱ፡፡

በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ፣ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባል አቶ ፋንታኹን ዋቄ የተገኙ ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይም የነቃህ ኹን /ራእ.፫፥፪/ በሚል ኃይለ ቃል ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ሓላፊነትን መሠረት ያደረገ ትምህርተ ወንጌል በዲያቆን ስንታየሁ ጂሶ ተሰጥቷል፡፡ በጉባኤውም ፺ የየማእከላት ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤና የሐዋሳ ማእከል አባላት ተሳትፈዋል፡፡

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ አገልግሎት ለመደገፍ የማኅበረ ቅዱሳንን ድርሻ የሚያመለክት ሥልጠና በማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የተሰጠ ሲኾን፣ በልምድ ልውውጡ መርሐ ግብርም መልካም አርአያነት ያላቸው ማእከላትና ንዑሳን ክፍሎች የልምድ ተሞክሯቸውን ለጉባኤው ተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡

እንደዚሁም በደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊ በመ/ር ዘሪሁን ከበደ የዘጠኙም ማእከላት የአራት ዓመት የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ የቀረበ ሲኾን፣ በተጨማሪም በጉባኤው ፫ኛ ቀን ውሎ፣ Living the Orthodx Life in the Era of Globalization and Secular Humanism፤ ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት በዘመነ ሉላዊነትና ዓለማዊነት በሚል ርእስ በአቶ ፈንታሁን ዋቄ የግማሽ ቀን ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊ ይህ ጉባኤ ለየማእከላቱ አገልግሎት መነሣሣት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከገለጹና የ፳፻፱ ዓ.ም ተመሳሳይ ጉባኤ አዘጋጅ ወላይታ ዶ ማእከል እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ሰኔ ፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከምሽቱ ፭ ሰዓት የአንድነት ጉባኤው ተፈጽሟል፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት ማኅበረ ቅዱሳን አዝኗል

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በጅማ ሀገረ ስብከት የም ልዩ ወረዳ ቁንቢ ቀበሌ ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት በእጅጉ ማዘኑን ገለጸ፡፡

አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ‹‹ስለ ኹኔታው የሚደረገው የማጣራት ሥራ እንደ ተጠበቀ እና ወደፊት የሚገለጽ ኾኖ፣ አጥቂዎቹ በወገኖቻችን ላይ ያደረሱት ጉዳት በእጅጉ የሚያሳዝን፤ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊትም ነው፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች አካሔዳቸው በየትኛውም የእምነት መሥፈርት፣ ይልቁንም በክርስትና አስተምህሮ ከመንፈሳዊ እምነትና ዓላማው ውጪ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው አያይዘውም ‹‹ክርስትና የመስቀል ጉዞ እንደ መኾኑ ብዙ ፈተና አለው፡፡ እምነታችን እስከ ዛሬ ድረስ የቆየውም በደማቸው ሰማዕት ኾነው ባለፉ አበውና እማት ተጋድሎ ነው፡፡ በመኾኑም ምእመናን ይህንን ተረድተው በጉዳዩ መደናገጥ የለባቸውም፡፡ ማኅበራችንም በተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰበት ያለውን የጅማ ሀገረ ስብከት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጋር በመተባበር እና መመሪያቸውንም በመቀበል በተቻለው ኹሉ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ድጋፉን ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በምእመናን ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው፣ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት በተመረጡ አባላት የተዋቀረ ኰሚቴ ጉዳዩን እያጣራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ የኰሚቴውን የምርመራ ውጤትም በሀገረ ስብከታቸው በኩል ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለዝግጅት ክፍላችን ይፋ እንደሚያደርጉ ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡

በአጥቂዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት እኅትማማች ምእመናት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ እየተደረገላቸው ሲኾን፣ በትናንትናው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመኾን በሆስፒታሉ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናትና ቤተሰቦቻቸውን ማጽናናታቸው ይታወሳል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥንና ሬድዮ ሥርጭቶች ብዙ አድማጭ ተመልካች እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ዋና ክፍል በብሮድካስት ሚድያ ክፍል ተዘጋጅተው በየሳምንቱ የሚተላለፉት የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥንና ሬድዮ ሥርጭቶች ከፍተኛ ተመልካችና አድማጭ እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የብሮድካስት ሚድያ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የኾኑት ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በኅትመት ውጤቶች (ሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ) በመታገዝ በመላው ዓለም ለሚገኙ ምእመናን መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን፤ እንደዚሁም ከ፲፱፺፯ ዓ.ም ጀምሮ በሬድዮ፣ ከ፳፻፭ ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በቴሌቭዥን መርሐ ግብር አገልግሎቱን በማፋጠን ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡

በአኹኑ ሰዓትም ዘወትር እሑድና ሐሙስ በኢቢኤስ የቴሌቭዥን ጣቢያ ይቀርብ የነበረው የአንድ ሰዓት መርሐ ግብር አገር ውስጥ በቀጥታ ባይተላለፍም፣ በአሜሪካን አገር በበርካታ ግዛቶች በማኅበረሰብ ቴሌቭዥን በመተላለፍ ላይ እንደሚገኝ፤ በአገር ውስጥና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ ተመልካቾች ደግሞ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው ድረ ገጽ ላይ በሰፊው እየታየ መኾኑን ዲ/ን ቴዎድሮስ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርት በስፋት ያገኙ ዘንድ በአማርኛ ቋንቋ ከሚያስተላልፈው ከሁለት ሰዓታት የኢንተርኔት ቴሌቭዥን ዝግጅት በተጨማሪ ለኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ምእመናን በየሳምንቱ እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 በኦቢኤስ አማካይነት በአፋን ኦሮሞ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እንደሚያስተላልፍ የጠቀሱት ዲ/ን ቴዎድሮስ፣ ኹሉም የማኅበሩ ዝግጅቶች በመላው ዓለም ብዙ ተመልካቾችና አድማጭች እንዳሏቸው በየጊዜው ከሚያደርጓቸው የዳሰሳ ጥናቶች መረዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ከቴሌቭዥን ዝግጅቶቹ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ እምነት እንዲሁም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ጉዳዮች የሚቀርቡበት ሳምንታዊ የሬድዮ መርሐ ግብር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የማኅበሩ የየሳምንቱ የሬድዮና የቴሌቪዥን ዝግጅቶች Radio/Tv by Phone በሚል መርሐ ግብር በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች በመሠራጨት ላይ እንደሚገኙ፤ እነዚህን መርሐ ግብሮችም አሜሪካ፡- በ(605)475-8172፤ ጀርመን፡- በ+49699.432.98.11፤ ዩናይትድ ኪንግደም፡- በ+4433.0332.63.60፤ ካናዳ፡- በ(604) 670-9698 ላይ ስልክ በመደወል መከታተል እንደሚቻል ዲ/ን ቴዎድሮስ የሰሜን አሜሪካ ማእከል የላከውን ምንጭ ጠቅሰው ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ኹሉንም የማኅበረ ቅዱሳን የሬድዮና ቴሌቭዥን መርሐ ግብሮች በwww.eotc.tv እና በfacebook አድራሻ mahiberekidusan.mkusa መከታተል እንደሚቻል ዝግጅት ክፍሉ አስታውቋል፡፡

የጎንደር ማእከል ፮ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሔደ፡፡

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በጎንደር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ግንቦት ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ፮ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደንቢያ ወረዳ በግራርጌ መካነ ሕይወት አባ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን አካሔደ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአካባቢው ምእመናን፣ የየወረዳ ማእከላት አባላት፣ የደንቢያ ከተማ መንፈሳውያን ማኅበራት እና የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የተገኙ ሲኾን፣ በአጠቃላይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጨምሮ ከ፲፭፻ በላይ ምእመናን በጉባኤው ተሳትፈዋል፡፡ በዕለቱ በተደረገው ጉባኤም በጎንደር ማእከል የመዝሙርና የኪነ ጥበባት ክፍል አባላት መዝሙርና መንፈሳዊ ሥነ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡

በጠዋቱ መርሐ ግብር የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ በአስተዳዳሪው ከተነገረ በኋላ እጅግ ጠቢብ አትሁን /ጥበ.፯፥፲፯/ በሚል ኃይለ ቃል በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የቀረበ ሲኾን፣ በመቀጠልም የአብርሃም ቤት እንግዳ ተጋባዥ የኾኑት በማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት መካናት እና ገዳማት ክፍል ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረትና እስከ ዛሬ ድረስ ስላለው የአገልግሎት ኹኔታ ሰፋ ያለ ገለጻ በማድረግ የሕይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን ለገዳማት፣ ለአብያተ ክርስቲያናት እና ለአብነት ትምህርት ቤቶች እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል፡፡

ከሰዓት በቀጠለው መርሐ ግብርም በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ የመጻሕፍት ጉባኤ ቤት ደቀ መዝሙር የኾኑት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ናት /ሉቃ.፲፯፥፳፩/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ከሰጡ በኋላ ሰባኬ ወንጌል ዋኬ ጉንዳ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ሀገረ ስብከት ዙሪያ ያለውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ኹኔታ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

ሰባኬ ወንጌል ዋኬ አያይዘውም የመተከል ሀገረ ስብከት የሰባክያነ ወንጌል፣ የአገልጋይ ካህናትና የሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት እጥረት ያለበት አካባቢ መኾኑን ጠቅሰው ምእመናኑ ቃለ እግዚአብሔርን ለተራቡ ለአካባቢው ወገኖች ሰፊ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱ በወጣትነት እና ክርስትና፣ በክርስቲያናዊ አለባበስ፣ በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በ፵ ቀን ዕድል፣ በካህኑ መልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ፣ ለአብርሃም በተገለጹት ሥላሴ ዙሪያ ከምእመናን የተነሡ ጥያቄዎች በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ሰፊ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የማእከሉ ሰብሳቢ መምህር ዓለማየሁ ይደግ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዲህ አይነት መርሐ ግብራት መዘጋጀታቸው በዓለም የባዘኑትን ምእመናን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹ ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ ምእመናንም ጉባኤው አእምሯቸውን ያጎለመሱበት፣ መንፈሳቸውን ያደሱበት፣ ሕይወታቸውን የተፈተሹበትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የተረዱበት መኾኑን ገልጸው እንደዚህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ለወደፊቱ በዓመት ሦስት አራት ጊዜ ቢዘጋጅ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ለቤተ ክርስቲያኑ ገቢ የሚሆን ገንዘብ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከተሰበሰ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን Encyclopedia ዝግጅት መጀመሩ ተበሠረ፡፡

ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከረፋዱ 5፡45 ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ሆቴል አዳራሽ ባደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን Encyclopedia (በጊዜያዊ ትርጕሙ ባሕረ ጥበባት) ዝግጅት በይፋ መጀመሩ ተበሠረ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደ ገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን በዕቅድ ከሚሠራቸው ዐበይት ተግባራት መካከል ይህ በማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል የሚሠራው የEncyclopedia ዝግጅት አንዱ መኾኑን ጠቅሰው ለዚህ ተግባር መሳካት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመስግነዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር አባተ መኩሪያው የማእከሉን ዓላማ ለጉባኤው ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሀብት ምንጭ፣ የጥንታውያን ቅርሶች ባለቤትና የብዙ ሺሕ ምእመናን መገኛ ኾና ሳለ እስከ አሁን ድረስ Encyclopedia ሳይኖራት መቆየቷ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም ክፍተት የሚፈጥር መኾኑን ገልጸው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ይህንን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ባሕረ ጥበባት ለማዘጋጀት መወሰኑን አብሥረዋል፡፡

የዝግጅት ሥራውን በተመለከተ የEncyclopedia ዝግጅቱ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ የአማካሪ ቦርድ፣ እንደዚሁም የአርትዖት ክፍል አባላት እንዳሉትና በዝግጅቱም ከሦስት መቶ ሰባት ባላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት ዶ/ር አባተ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከአማካሪ ቦርድ አባላት መካከል አንዱ የኾኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን በዕለቱ አስተያየት ሲሰጡ የአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ ርምጃ ይጀምራል የሚለውን ብሂል ጠቅሰው ይህ የባሕረ ጥበባት ዝግጅትም ጥሩ ጅማሬ ነውና እንደ ጥሩ ፍጻሜ ይቈጠራል ብለዋል፡፡ ሥራው ብዙ ፈተናና ድካም እንደሚኖረው የተናገሩት መልአከ ታቦር እኛ ከማለፋን በፊት ጅማሬውን ብናየው ደስ ይለናል ካሉ በኋላ አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም በቅርቡ ለንባብ እንዲበቃ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ Encyclopedia ከሚለው ቃል ትርጕም አኳያም መድበል የሚለው ቃል በትርጕሙ ውስጥ ቢካተት የተሻለ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው የአማካሪ ቦርድ አባል ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል በበኩላቸው ለዚህ ሥራ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ጥረት ሲያደርግ የቆየውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነው የቤተ ክርስቲያን Encyclopedia እስከ አሁን ድረስ አለመዘጋጀቱ ቢያስቈጭም እኛ ግን መቀመጥ የለብንም ብለዋል፡፡ አያይዘውም Encyclopedia የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደና ትርጕሙም የጥበብ (የዕውቀት) መገኛ (ስብስብ) ማለት መኾኑን ጠቅሰው ባሕረ ጥበባት ከሚለው ትርጕም በበለጠ ሊገልጸው የሚችል አቻ ትርጕም ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው እንደ መነሻም መዝገበ አእምሮ፣ መዝገበ ጥበባት ወይም ፈለገ አእምሮ፣ ፈለገ ጥበባት፣ ወዘተ በሚል ቢተረጐም የሚል ዐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ሌሎች የአማካሪ ቦርዱ እና የአርትዖት ክፍሉ አባላትም አስተያየት በሰጡበት ወቅት በዝግጅቱ መጀመርና የዝግጅቱ አባላት በመኾቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ይህ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ ልዩ ልዩ ፈተናዎችና ነቀፋዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ከወዲሁ በመረዳት ኹሉንም ነገር ለበጎ መኾኑን ማስተዋልና ችግሮችንም በትዕግሥት ማለፍ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ እንደሚገባ ለራሳቸውም ለሌሎች የዝግጅቱ አባላትም አባታዊና ወንድማዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያም የአማካሪ ቦርድ እና የአርትዖት ክፍል ሥራ አስፈጻሚ ኰሚቴ የተዋቀረ ሲኾን፣ በዚህ መሠረት ለአማካሪ ቦርዱ፡- ፕ/ር ሽፈራው በቀለ ሰብሳቢ፣ ፕ/ር ባየ ይማም ምክትል ሰብሳቢ፣ ዶ/ር አባተ መኩሪያው ጸሐፊ፤ ለአርትዖት ክፍሉ ደግሞ፡- ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ ሰብሳቢ፣ ዶ/ር አበባው ምናዬ ምክትል ሰብሳቢ፣ ዲ/ን ሙሉዓለም ካሣ ጸሐፊ ኾነው በምልዓተ ጉባኤው ተመርጠዋል፡፡

በመጨረሻም በዕለቱ የመርሐ ግብሩ መሪ የነበሩት የEncyclopedia ዝግጅት ክፍል ሰብሳቢው ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ ለጉባኤው ተሳታፊዎችና ውይይቱ የተካሔደበትን አዳራሽ በነጻ ለፈቀደው ለሰሜን ሆቴል ምስጋና ካቀረቡና ለእንግዶቹም የምሳ መስተንግዶ ከተደረገ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈሰ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቍጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የዘንድሮዉን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረ ለዐሥራ ስድስት ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፤

፩. የ፳፻፰ ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባኤን በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳበቃ ጉባኤው ሥራውን ቀጥሏል፡፡

፪. የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በጽሑፍ ቀርቦ ጉባኤው ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱ የሚወሰኑት ኹሉ የአፈጻጸምƒƒ‚ ችግር እንዳይደርስባቸው ክትትል ይደረግ ዘንድ ተወስኗል፡፡

፫. እስከ አሁን እየተሠራበት ያለው ቃለ ዓዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል በተሰጠው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ረቂቅ ቀርቦ ምልዓተ ጉባኤው ከተነጋገረበትና ከታየ በኋላ የረቂቁ ዝግጅት በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲታተም ተወስኗል፡፡

፬. ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ እንደራሴ አስፈላጊነት ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተነጋገረ በኋላ የእንደራሴ አስፈላጊነት በምን ዓይነት ሕግ ላይ ተመሥርቶ መመረጥ አለበት የሚለዉን በማጥናት ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ሰባት አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል፡፡

፭. ተፈጥሮ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ ርዳታ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ለመልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎት የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ ይደረግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ የድርሻዋንም አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡

፮. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚያገለግል ሕንፃ ƒƒመገንባት ይቻ ዘንድ ቦታ እንዲሰጥ ከገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት የቀረበውን ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው የተቀበለው ስለኾነ፣ በቤተ ክርስቲኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በኩል ቦታ ተፈልጎ እንዲሰጥ ተዋስኗል፡፡

፯. ቅዱስ ሲኖዶስ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች ብቁ የኾኑ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ለመሾም ባለው ዕቀድ መሠረት፣

ፈተናዉንና መሰናክሉን ኹሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን፤

በብሔር ዓቀፍና በዓለም ዓቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤

የወቀውቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸውን፤

ለተልእኮ የሚፋጠኑትን መነኰሳት በመመርመር፣ በማጥናትና በማጣራት ውጤቱን እስከ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ የሚያቀርብ አስመራጭ ኰሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

፰. ሀ. ብፁዕ አባ ያሬድ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሥራን እንደያዙ በአርሲ ሀገረ ስብከት፤

ለ.ብፁዕ አባ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከ፤

ሐ.ብፁዕ አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት፤

መ.ብፁዕ አባ እንድርያስ ሊቀ ጳጳስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊነቱን ሥራ እንደያዙ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ በመኾን ተመድበው እንዲሠሩ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

፱. በውጭ ላሉት አህጉረ ስብከት ጥናት ተደርጎ በቋሚነት የሚሠሩ አባቶች እስኪመደቡ ድረስ፣

ሀ/ ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት፣

ለጊዜው በብፁዕ አባ ሙሴ የደቡብ ምዕራብና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤

ለ/ አውስትራልያ ሀገረ ስብከት፣

በብፁዕ አባ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤

ሐ/ ምሥራቅ አፍሪካ፣ ኬንያና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት፣

በብፁዕ አባ ዳንኤል የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤

መ/ ሥራቅ አፍሪካ፣ ሰሜን ሱዳንና ግብፅ አህጉረ ስብከት፣

በብፁዕ አባ ሉቃስ በክልል ትግራይ ዞን ወልቃይት ጸገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ኾኖ፣

በተጨማሪም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ፤

ሠ/ ደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት፤

በብፁዕ አባ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሲል ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

፲. በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው የሰላሙ ንግግር ይቀጥል ዘንድ ሰላም ለማንኛውም መሠረት መኾኑ ታምኖበት ይህንኑ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊው ጥረት ኹሉ እንዲደረግ፡፡

፲፩. ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወያየ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፶ መሠረት ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል በያዙት ሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ ደርበው እስከ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም ድረስ የፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ ተስማምቷል፡፡

፲፪. በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ እኪኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በማወዳደር፡-

ሀ. ብፁዕ አባ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣

ለ. ብፁዕ አባ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል፡፡

፲፫. በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ሓላፊነት በቤተ ክርስቲያናችን እየተረዱ የሚያድጉ እጓለ ማውታ ሕፃናት በየአህጉረ ስብከቱ መኖራቸው የሚታወቅ ነው፤ ይኸው የሕፃናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት እጓለ ማውታ ሕፃናትን በማሳደግና በማስተማር ረገድ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ አለኝታ ስለኾነ፣ አስከ አሁን ከነበረው ይዘት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኗል፡፡

፲፬. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደ ኖረ ኹሉ አሁንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

፲፭. በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አሰዝተዳደር ቀልጣፋና ቅንነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር፣ በየደረጃው የተዘረጉትም የልማት አውታሮች የበለጠ ውጤት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ኹሎችም የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሓላፊነት ያለባቸው ስለኾነ ተከታትለው እየሠሩ እንዲያሠሩ ተወስኗል፡፡

፲፮. በመከናወን ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጀማመር ኹሉም ኅብረተሰብ እጁን ሲዘረጋ እንደቆየ ኹሉ፣ አሁንም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም መላው ኀብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ይፈጽም ዘንድ ቀዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

፲፯. ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጭ ባሉት አንዳንድ አህጉር እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር በጆራችን እንሰማለን፤ በዓይናችንም እናያለን፡፡ ለማስረጃም ያህል፡-

በመሬት መንቀጠቀጥ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅና በሰደድ እሳት ዘግናኝ አደጋ የሚደርስ ኅልፈተ ሕይወት፤

በእርስበርስ የውስጥ ጦርነት የደረሰውና እየደረሰ ያለው ዕልቂት፤

የእግዚአብሔርን ህልውና በሚፈታተኑ አንዳንድ ግለሰቦች ግንዛቤ ጉድለት እየደረሰ ያለው የጦርነት አደጋ፤

በየብስ፣ በውቅያኖሶችና በሰማይ ላይ በሚበሩ አውሮፕላኖች የሚደርሰው ዘግናኝ ዕልቂትና የመሳሰሉት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ጉዳት ለደረሰባቸው መጽናናትን፣ መረጋጋትን እንዲሰጥልን፤ ቅን ልቡና፣ ትሑት ሰብእና ለሚጎድልባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ትዕግሥቱን፣ ርኅራኄውን እንዲያበዛልን እንጸልያለን፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን ጎልቶ የሚታየው ድህነት እንዲወገድ፤ የተራበው፣ የተጠማው፣ የታረዘው መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት እንዲኖር፤ በሀገራችን ኢተዮጵያ፣ በዓለሙም ኹሉ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ በመጸለይ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤

አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም፡፡

፲፰ኛው የአሜሪካ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ተካሔደ።

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአሜሪካ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ፲፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሲያትል ዋሺንግተን ቅዳሜ ግንቦት ፳ እና እሑድ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተካሔደ።

በጉባኤው ወደ ፬፻ የሚደርሱ የማእከሉ አባላት፤ የዲሲና የአካባቢው እንዲሁም የካሊፎርንያና ምዕራብ አሜሪካ አህጉረ ስብከት ተወካዮችና የሥራ አስፈጻሚ አባላት፤ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጉባኤው በጸሎተ ኪዳን በተጀመረበት ቅዳሜ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ሕልምነህ ስንሻው የእንኳን ደኅና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ በማእከሉ የተተገበሩ ዋና ዋና የአገልግሎት ሥራዎችን ዘገባ አቅርበዋል። የዲሲ እና የአካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መሥፍን ተገኝም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን መልእክት ለጉባኤው ካስተላለፉ በኋላ በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው “ሥራ የበዛበት ትልቅ በር” /፩ኛቆሮ. ፱፥፲፮/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡

በመቀጠል የማእከሉ የአገልግሎት ክፍሎች ዓመታዊ ጠቅላላ ሪፖርትና የቀጣይ ዓመት ዕድቅ ለጉባኤው ቀርቧል፡፡ በቀረበው ሪፖርትም በንዑሳን ማእከላት በርካታ ትምህርታዊ ጉባኤዎች እንደተካሔዱ፣ በልዩ ልዩ ከተሞች የማኅበረሰብ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደተጀመረ፣ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ኢአማንያንን ለማስተማርና ለማስጠመቅ ለተዘረጋው የስብከተ ወንጌል ፕሮጀክት ከአባላት እና ከምእመናን የተሰበሰበ የእርዳታ ገንዘብ ወደ ዋናው ማእከል እንደተላከ ተገልጿል።

የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ተወካይ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም የዋናውን ማእከል መልእክት እና ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከጉባኤው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠታቸው በተጨማሪ የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በሁለቱ ቀናት ጉባኤ ላይ በሲያትል ንዑስ ማእከል የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ውዳሴ ማርያምና ሰዓታት በንባብና በዜማ፤ የጸሎተ ቅዳሴ ተሰጥኦና ምስባክ፤ እንደዚሁም የአብነት ትምህርትን አሰጣጥና ሒደት የሚያሳይ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ቅኔ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ እና የተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።

በተጨማሪም የሲያትል ንዑስ ማእከል የአገልግሎት ተሞክሮዉን ለጉባኤው ያካፈለ ሲኾን፣ የማእከሉ የአገልግሎት ክፍሎች የበጀት ሪፖርትም ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ከስድስት ወር በኋላ የማእከሉ የዕቅድ ክለሳ እንደሚደረግም በጉባኤው ተገልጿል።

እንዲሁም ዝክረ አበው በሚል መርሐ ግብር የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ በማስመልከት የተዘጋጀ ፊልም ለእይታ በቅቷል።

በዕለቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ማዕከሉን ይመራ የነበረው የሥራ አስፈጻሚ የሥራ ዘመን በመፈጸሙ፣ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማእከሉን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ፲፫ አባላት በጸሎትና በዕጣ ተመርጠዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ በማእከሉ ፲፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የዝግጅቱ ሒደትና በሲያትል ከተማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ያበረከቱት ከፍተኛ አገልግሎት በዝርዝር የቀረበ ሲኾን ይህ አሳታፊነትና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቅንጅት የመሥራት ልምድ ለሌሎች ንዑሳን ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች ያለው አርአያነት የጎላ መኾኑ ተገልጿል።

በመጨረሻም ፲፱ኛው የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በቦስተን፣ ፳ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ በቨርጂንያ እንዲካሔድ ተወስኖ ጠቅላላ ጉባኤው በዝማሬ እና በጸሎት ተጠናቋል።

የቅዱስ ያሬድን ፲፭፻፫ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የቅኔ ውድድር ተካሔደ፡፡

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በጎንደር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤተፐች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በጎንደር ማእከል አዘጋጅነት ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የቅዱስ ያሬድን ፲፭፻፫ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በጎንደር ከተማ በርእሰ አድባራት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ውድድር ተካሔደ፡፡

የውድድሩ ተሳታፊ ጉባኤ ቤቶች፡- የደብረ ፀሐይ ቍስቋም ማርያም፣ የደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፣ የቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ፣ የመካነ ሕይወት ፊት አቦ እና የደብረ ገነት አዘዞ ቅዱስ ሚካኤል ቅኔ ጉባኤ ቤቶች ሲኾኑ፣ መምህራኑ የመረጧቸው ደቀ መዛሙርትም ጉባኤ ቤቶቹን ወክለው ለውድድር ቀርበዋል፡፡

ውድድሩን በዳኝነት የመሩትም መምህር ፍቅረ ማርያም የመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም የ፬ቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር፣ ሊቀ ብርሃናት ኤልያስ አድማሴ በዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት የብሉይ ኪዳን መምህር እና መምህር ቃለ ሕይወት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት የሐዲስ ኪዳን መምህር ሲኾኑ የውድድሩ መሥፈርቶችም አንደኛ የቅኔው ምሥጢር፣ ሁለተኛ የዜማው ልክ፣ ሦስተኛ ገቢር ተገብሮ አገባብ፣ አራተኛ የቃላት አመራረጥ እና አምስተኛ የጊዜ አጠቃቀም ናቸው፡፡ እያንዳንዱ መሥፈርት ፳፣ ባጠቃላይም ፻ ነጥቦችን የያዘ ሲኾን ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪም የ፲፭ ደቂቃ የማቅረቢያ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡

በውድድሩ ከአንደኛ አስከ ሦስተኛ ደረጃ የያዙት የወንጌል አንድምታ ትርጓሜ መጻሕፍትን፤ አራተኛና አምስተኛ የወጡት ደግሞ የትንቢተ ኢሳይያስን አንድምታ ትርጓሜ መጽሐፍ ተሸልመዋል፡፡ ይኸውም ቅኔ ተምረናል በቃን ብለው እንዳያቆሙ እና ቀጣይ መጻሕፍትን እንዲማሩ ለማሳሰብ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማእከሉ ሰብሳቢ መምህር ዓለማየሁ ይደግ እንደተናገሩት የውድድር መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዓላማ በጉባኤ ቤቶች መካከል መልካም የሆነ የውድድር መንፈስ እንዲኖር፣ ተማሪዎቹ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግ፣ የቅኔ ትምህርት በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲታወቅ፣ የበታቾቻቸውን ለማነሣሣት እና በዋናነት ቅዱስ ያሬድን ለመዘከር ነው፡፡

የጎንደር ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ሊቀ አእላፍ ጥበበ አወቀ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደዚህ ዓይነቱ መርሐ ግብር እየቀዘቀዘ የመጣውን የአብነት ትምህርት በተለይ የቅኔ ትምህርት እንደሚያጠናክር ጠቅሰው ይህም ማኅበረ ቅዱሳንን እንደሚያስመሰግነው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለደቀ መዛሙርቱ አባቶቻችን ይህን ትምህርት በእግዚአብሔር ኃይል ጸንተው፣ ኮቸሮ በልተው፣ በውሻ ተበልተው አቆይተውናል፤ እኛም ጠብቀን ለትውልድ ማቆየት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በስድስቱም ጉባኤ ቤቶች የሚገኙ በርካታ የአብነት ተማሪዎች እና በርካታ ምእመናን የተገኙ ሲኾን፣ ከምእመናኑም ይህ የቅኔ ትምህርት እንዲስፋፋ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባው አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

የጎንደር ማእከል መዘምራንም ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ የሰማይ ምስጋና የሚል የንስሐ መዝሙር እና ያሬድ ማኅሌታይ ለእግዚአብሔር ካህኑ የሚል ወረብ አቅርበዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ መምህር በጽሐ ዓለሙ በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የ፬ቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር በአብነት ትምህርት ቤት ሦስት ዓይነት ተማሪ አለ፤ እነሱም፡- እግረ ተማሪ፣ ልብሰ ተማሪ እና ልበ ተማሪ ናቸው ካሉ በኋላ ኹላችንም ልበ ተማሪን ኾነን ትምህርታችንን በሚገባ መማር አለብን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡ ይህ መርሐ ግብር በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የሬድዮ ጣቢያም የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡