ወርኃ ጥር
በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ቀኑ ዐሥር ሰዓት ሲሆን ከዚህ በኋላ ሌሊቱ እየጨመረ ይሄዳል። ጥር የሚለው ስያሜ “ጠር፣ ጠይሮ፣ ጠየረ፣ ጠሪእ፣ (ጠርአ፣ ይጠርእ፣ ጸርሐ) ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም “መጥራት፣ መጮኽ፣ አቤት ማለት” ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፭፻፲) ጥር የወር ስም ሆኖ በታኅሣሥ ወር እና በየካቲት ወር መካከል የሚገኝ፣ ከዐሥራ ሦስቱ ኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር ውስጥ አምስተኛው ነው።
በዚህም ወር ዘመነ አስተርእዮ ይታሰባል፤ አስተርእዮ በጥሬ ትርጉሙ “መገለጥ” ነው፤ ይህም ወቅት በዋናነት ስውር የነበረ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት፣ ሰማያዊ አምላክ በኩነተ ሥጋ ለድኅነተ ዓለም ሲል በዚህ ዓለም የተገለጠበት፣ ሰማያዊ ምሥጢርም የታየበት ድንቅና ልዩ ዘመን ነውና እንዲህ ተብሎ ተጠራ።