ሥዕለ አድኅኖ
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኀዳር ፩፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በዘመናዊ ትምህርታችሁስ እየበረታችሁ ነው? ትምህርት ከተጀመረ ሁለት ወርን አስቆጥረናል፡፡ ምን ያህል ዕውቀትን ገበያችሁ? ጊዜ አለን ብላችሁ እንዳትዘናጉ የተማራችሁትን ወዲያው በመከለስ አጥኑ፤ ያልገባችሁን ደግሞ መምህራንን ጠይቁ፤ በሰንበት እሑድ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርና ማገልገልን እንዳትረሱ፡፡ መልካም! ባለፈው ትምህርታችን ስለ ቅዱሳት ሥዕላት በተማርነው ትምህርት ቅዱስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ሥዕል ማለት ምን ማለት እንደሆነና ለምን ቅዱሳት ሥዕላት እንደሚሣሉ በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ ቀጣዩን ክፍል “ሥዕለ አድኅኖ” በሚል ርእስ ስለ ቅዱሳት ሥዕላት አሣሣል ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አድኅኖ ማለት “ማዳን፣ መታደግ፣ መቤዠት፣ ነጻ ማውጣት” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፫፻፵፬)፤ “ሥዕል ማለት ምን ማለት ነው” የሚለውን ባለፈው ትምህርታችን ነግረናችኋል፤ ሥዕለ አድኅኖ የሚለው ስያሜ የሚሰጠው ለቅዱሳት ሥዕላት ነው፡፡ ሥዕለ አድኅኖ ስንል የሚታደጉ፣ ከክፉ የሚጠብቁ ቅዱሳት ሥዕላት ማለት ነው፡፡
የሥዕለ አድኅኖ አሣሣል
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የሥዕለ አድኅኖ የራሳቸው የሆነ አሣሣል አላቸው፤ ዝም ብሎ በዘፈቀደ አይሳሉም፤ ለሥዕለ አድኅኖ የምንጠቀምባቸው ቀለማት እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ትርጕም (ምሥጢር) ምሳሌ ስላላቸው ያንን ምሥጢር ጠብቀው መሳል አለባቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ ልዩ የሚያደርጋቸው መለያ ባሕርያት አሏቸው፡፡ የቀለም አቀባቡ፣ የሚሣሉበት ቦታ፣ ለሥዕላቱ የሚሰጠው ክብር፣ ከሌሎች ሥዕላት የሥዕለ አድኅኖ በሚሣሉበት ጊዜ ዋና ትኩረት ለሥዕሉ ባለቤት መንፈሳዊ ማንነት ላይ ያኩራል፡፡ ሥዕላቱ ሲሣሉ ባለቤቱ እንደዚህ ይመስላል ለማለት አይደለም፡፡ ሥዕላቸው ሲሣል ከገድላቸው መካከል፣ ካደረጉት ተአምራት መካከል ዋና የሆነውን ጎልቶ የሚታወቀውን ሥራቸውን የሚያንጸባርቅ (የሚያስተምር፣ የሚገልጥ) ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለምሳሌ የቅዱሳን አባቶቻችንን ሥዕል ብንመለከት የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ሥዕል ለሃያ አንድ ዓመት ቆመው ሲጸልዩ አንድ እግራቸው ከመቆማቸው ብዛት ብትሰበር (ብትቆረጥ) እግዚአብሔር የጸጋን ክንፍ እንደሰጣቸው በአንድ እግራቸው ቆመው ሲጸልዩ ይሣላል፡፡ የተቆረጠው እግራቸው በክብር አርፎ፣ ጦር ከጎናቸው ተክለው በተመስጦ ሲጸልዩ ተሥሎ ስንመለከት ተጋድሏቸውን፣ የጸሎት ሕይወታቸውን፣ በሥዕሉ ውስጥ እናስተውላለን፡፡
ባለፈው ትምህርታችን ሥዕለ አድኅኖ የሚሣልበት ምክንያት ለምንድን ነው የሚለውን ስንማር ለመታሰቢያ እንዲሁም ለመማሪያ እንዲሆን የሚለውን ተመልክተን ነበር፤ “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው።” (መዝሙረ ዳዊት ፻፲፪፥፮) በዚህም መሠረት አሁን ለምሳሌ በገለጽነው የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል በዚህ መልኩ መሳሉ ብዙ ነገሮችን እናገኝበታለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመለከት፤ የቅዱሳን መላእክት ሥዕል ሲሣል በድርሳናት፣ በስንክሳር እንዲሁም በተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ መላእክቱ ከእግዚአብሔር ተልከው የሰው ልጆችን ለመራዳት ሲመጡ በወቅቱ በተገለጹበት አምሳል ይሣላሉ፤ እንደ አብነት ብንወስድ ቅዱስ ገብርኤል ሦስቱ ወጣቶች አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል “ለጣዖት አንሰግድም፤ እግዚአብሔርን አንክድም” ብለው በሃይማኖታቸው በመጽናታቸው ናቡከደነጾር የተባለ ንጉሥ እሳት አስነድዶ ከዚያ ሲያስጨምራቸው ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ መጣና እሳት ውስጥ አብሯቸው ሆነ፤ ከሚነደው እሳት አዳናቸው፡፡ (ት.ዳን ፫፥፩-፴)
ታዲያ ይህንን ታሪክ በሥዕል ለማስተማር በሚነድ እሳት ውስጥ ሦስቱ ወጣቶችና ቅዱስ ገብርኤል ይሣላሉ፡፡ ሌሎችንም የቅዱሳን መላእክት ሥዕለ አድኅኖ የሚሣለው በዚሁ መልክ ነው፡፡ (በወቅቱ በተገለጹት አኳኻን)፡፡ የቅዱሳን መላእክትን ሥዕለ አድኅኖ ስንመለከት መስቀል፣ ሰይፍ፣ ይዘው ይሣላሉ፡፡ መስቀል መያዛቸው ለምሕረት፣ ሰዎችን ለማዳን መላካቸውን ለመግለጽ፣ ሰይፍ መያዛቸው ደግሞ ክፉ ሰዎችን ለመቅጣት መላካቸውን ለመግለጽ ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥዕለ አድኅኖ የአሣሣል ዘዴ፣ የሚሣሉበት ጥበብ ከሌሎች አገራት የአሣሣል ትውፊት ይለያል፡፡ ሥዕለ አድኅኖዎች ሲሳሉ የፊት ቅርጻቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡ በራሳቸው ላይም የብርሃን አክሊል ይሣላል፡፡ ጎላ (ተለቅ) ተደርጎ መሣሉ የጎላች የተረዳች ሃይማኖት (ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) ያላቸው ጠብቀውም የኖሩ ዓይናቸው ጎላ ተደርጎ ይሣላል፡፡ ዓይናቸው የሚመጣውን ያለፈውንም ዓለም በትንቢት መነጽርነት ይመለከታሉና የጎላ ዓይን ሁሉን የሚመለከት ንጹሕ ዓይን እንዳላቸው ለማሳየት ዓይናቸው ጎልቶ ይሣላል፡፡ በራሳቸው ዙሪያ ደግሞ ክብ ቅርጽ ያለው ብርሃን ያለው ተደርጎ ይሣላል፤ ይህም የሚገልጸው ክብራቸውንና ንጽሕናቸውን ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል ምንን ምክንያት (መሠረት) አድርጎ እንደሆነና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሥዕለ አድኅኖ እንዴት እንደሚሳል ምሳሌነቱን በመጠኑ ተመልክተናል፤ በቀጣይ ክፍል ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል የምንጠቀማቸው ቀለማት (ከለር) ምን ዓይነት መሆን እንዳበትና ምክንያቱን እንዲሁም በሥዕለ አድኅኖ ከተደረጉ ተአምራት የተወሰኑትን ለአብነት እንመለከታለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ፤ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ይቆየን ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!








