የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ

“ወይኩን ጉባኤ ሊቃነ ኤጴስ ቆጶሳት ወኤጲስ ቆጶሳት ክልዔተ ጊዜ በበዓመት ወይትናገሩ በእንተ ግብረ አብያተ ክርስቲያናቲሆሙ ወያሰስሉ ዕቅፍታተ …

የሊቃነ ጳጳሳትና የጳጳሳት ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን ስለአብያተ ክርስቲያናት የሚገባውን ሁሉ ይነጋገሩ የሐዋርያዊ ተልእኮ መሰናክሎችንም ሁሉ ያስወግዱ” ተብሎ በመጀመሪያው የሐዋርያት ቀኖና፣ በሁለተኛው ቀሌምንጦስ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት 11 – ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት  ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነት ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

ወቅቱን ያማከሉና ዘላቂ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ሕልውና የሚያረጋግጡ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልናንን የሚያስጠብቁ፣ ለምእመናን ደኅንነትና ለአገልጋዮች ሕይወት በሚጠቅሙ፣ መንሳፈዊ አስተዳደርንና ማኅበራዊ ጉዳዮችን መሠረት ባደረጉ አጀንዳዎች ላይ በመንፈስ ቅዱስ አንድነት በመወያየት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

1.ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖታዊ መሠረቷ፥ የሥርዓተ ቅዳሴዋና የምሥጢራት አገልግሎቷ አካል፣ የመንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥምሪቷ ማእከላዊ ዐምድ በመሆኑ በግንቦት 2017 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሠየመው የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የደረሰበትንም ውጤት ለግንቦት 2018 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያን አስተላልፏል::

2.በትግራይ አህጉረ ስብከት የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ሕዝባችንና ወገናችን ስለሆነ አብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱም የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሀብቶች በመሆናቸው፣ አህጉረ ስብከቱም የተደራጁት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ቀኖና ተጠብቆ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተከብሮ፣ የመዋቅር ግንኙነቱን ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም፣ የአንድነትና የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን ከመግለጽ ጋር ቅዱስ ሲኖዶስ በክልሉ ለሚገኙት አባቶች፣ ካህናትና ምእመናን ያልተቋረጠ የሰላም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የቀድሞዎቹ ቅዱሳን አባቶቻችን ዋጋ ከፍለው፣ ቀኖናዊ ሥርዓቷንና ክብሯን ጠብቀውና አስጠብቀው ፣  አንድነቷን አጽንተው ያወረሱንን አሐቲ ቤተ ክርስቲያን የቀደመ ሉዓላዊ ክብሯ እንደተጠበቀ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የበለጠ ዋጋ ያሰጣልና ቀደም ሲል ለዚሁ ጉዳይ የተሠየመው ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ሊቃውንቱ፣ ካህናቱና መላው ሕዝባችንም  የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ሁሉ  የበኩላችሁን እንድትወጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአጽንኦት ያሳስባል፡፡

3.ቅዱስ ሲኖዶስ አባት እንዲመደብላቸው ጥያቄ ባቀረቡ አህጉረ ስብከት ዙሪያ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርቡ ብፁዓን አባቶችን በመሰየምና ተገቢውን ውይይት በማድረግ፡

ሀ) ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ የኢሉ አባቦራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣

ለ) ብፁዕ አቡነ ቶማስ የአዊና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የምሥራቅ ጎጃምን ሀገረ ስብከት ደርበው እንዲመሩ፣

ሐ) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የደቡብ ወሎና ከሚሴ አህጉረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣

መ) ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የምሥራቅ ወለጋና ሆሮ-ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ

ሠ)  በተጨማሪም የሸካ ዞን ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተብሎ ራሱን ችሎ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዲቋቋም፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሀገረ ስብከቱን እንዲያደራጁና እንዲመሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

4.ነባሩና ጥንታዊው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ገድል እንደተጠበቀ ሆኖ ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሚል ያለአግባብ በአንድ ግለሰብ ተዘጋጅቶ እየተሠራጨ ያለው መጽሐፍ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ ያለበት ግድፈትና የስሕተት ትምህርት በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የማይወክል ሆኖ በመገኘቱ ተወግዟል፤

በውስጡ የያዛቸውም የተሳሳቱ ትምህርቶች በሙሉ ተቀባይነት ስለሌላቸው መጽሐፉ ለጥናትና ምርምርም ሆነ ለማጣቀሻ አገልግሎት እንዳይውል፣ በሥርጭት ላይ የዋለው መጽሐፍ እንዲታገድና በድጋሚም እንዳይታተም፣ ለየአህጉረ ስብከቱ ሠርኩላር እንዲተላለፍ፣ የአፈጻጸም ክትትል እንዲደረግና አጠቃላይ ሁኔታው በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በሚዲያ እንዲገለጽ፣ የአስተምህሮ ስሕተትን በማካተት አሳትመው ያሰራጩት ግለሰብ በቋሚ ሲኖዶስ ተጠርተው እንዲጠየቁና የፈጸሙትን ስሕተት ዐውቀው ወደፊት ተመሳሳይ ስሕተት እንዳይፈጽሙ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጣቸው፣

መጽሐፉ እንዲመረመር ያደረገው የደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳምና የገዳሙ የቅኔ መምህር መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤል ወልደ ገብርኤል የምስጋና ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

5.በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም መንፈሳዊ ኮሌጅና የአብነት ምስክር ጉባኤ ቤት ለማቋቋም በጠየቀው መሠረት እንዲፈቀድ ሆኖ የትምህርት አሰጣጥ ፖሊሲውና ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀቱና መዋቅራዊ ተጠሪነቱ ተዘጋጅቶ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተጠንቶ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለግንቦት 2018 ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

6.በምዕራብና በመካከለኛው ካናዳ የሚገኙት ሁለቱ አህጉረ ስብከት ከአሁን በፊት በ2017 ዓ.ም. በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ያለ ጣልቃ ገብነት በየራሳቸው እንዲተዳደሩና የኤድመንተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የመካከለኛው ካናዳ ኤድመንተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሚል ሥያሜ እንዲስተካከል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

7.በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዓል ለማክበር ሄደው አዲሱን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በመጐብኘት ላይ እያሉ አደጋ በደረሰባቸው ምዕመናን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ እግዚአብሔር አምላካች ላረፉት ወገኖቻችን ዕረፍተ ነፍስ እንዲሰጥልን ከመጸለይ ጋር አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማሳከምና የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመርዳት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ለወደፊቱም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ በሚገነቡ ሕንጻ ግንባታዎች አደጋ ከመድረሱ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፤

8.በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ገዳማት ያሉት መነኰሳትና መነኰሳይያት ለአገልግሎትና ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ክብራቸውና ገዳማዊ ሕይወታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን እስከሚፈጽሙ ድረስ የገዳማት ኅብረቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል ማረፊያ የሚሆን ቦታ እንዲዘጋጅላቸው፣

የአንድነት ገዳማት ኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ አገልግሎት መምሪያ በኩል ታይቶና ተመርምሮ እንዲቀርብ፣

በአጠቃላይ በአንድነት ገዳማት ኅብረት የቀረበው የገዳማውያንና ገዳማውያት ማረፊያ እና የገቢ ማስገኛ ሁለገብ ሕንጻ ግንባታ የትግበራ ዕቅድ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል በዘርፉ ባለሙያዎች ታይቶና ተገምግሞ ከባለሙያ አስተያየቶችና የውሳኔ ሐሳብ ጋር ተጠንቶ ለግንቦት 2018 ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ እንዲቀርብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

9.በበዓላት አከባበር፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት አፈጻጸም ዙሪያ የሚታዩ ግድፈቶች፣  ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችና ከሥርዓት የወጡ የአገልግሎት አፈጻጸሞች መታረም ስላለባቸው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሚሰየሙ ሊቃውንትና ባለሙያዎች ለመመሪያና ለማስተማሪያ የሚሆን ሰነድ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተገቢውን ውሳኔ ያስተላለፈ መሆኑን እየገለጽን ያለጠባሳ የሚያድኑ ሐኪሞች፣ ያለቅሬታ የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች በነበሩባትና ባሉባት ሀገር ተመካክሮ ችግርን አለመፍታት ተገቢ አይደለምና ሀገራችንን እንወዳለን፣ ሕዝባችንን እናከብራለን የምትሉ፣ የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባችሁ ሁሉ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ እንዳይጠፋ፣ አካሉ እንዳይጐድል የሀገር ልማትና መልካም ገጽታ እንዳይበላሽ ጠላት መባባሉ ቀርቶ፣ የጦር መሣሪያ ትግል ተወግዶ፣ በእኩልነትና በመስማማት ሰላማዊ የችግር አፈታት መንገድን ተከትላችሁ በውይይትና በጥበብ ልዩነቶችን በመፍታት የተሟላ ሀገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ታደርጉ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአደራ ጭምር ሐዋርያዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም የሀገራችን ኢትዮጵያና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና ስለማይነጣጠሉ፣ ሀገራችን በሉአላዊነቷ እንድትቀጥል የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት መዋቅሯ የበለጠ ተጠናክሮ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ሰፍቶ፣ ለትውልድ እንድትሻገር፣ ሕዝባችን ደኅንነቱና ሰላሙ ተጠብቆ እንዲኖር ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን፣ ካህናትና ሕዝባውያን፣ መነኰሳትና መነኰሳይያት በሙሉ በፍቅርና በአንድነት ዘወትር በመጸለይ  ዘመኑ ከደረሰበት አሠራርና ጥበብ በላቀ ሁኔታ ከፍ ብለን ትውልዱን ለመዋጀት እንድንችል የበኩላችሁን እንድትወጡ በማሳሰብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፯/፳፻፲፰ ዓ.ም

አዲስ አበባኢትዮጵያ

 

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

ያለምንም ደመወዝ በራሳቸው ዓቅም በግብርና እየተዳደሩ ቤተ ክርስቲያንን በጥሩ ሰብእና በንጽሕና እና በቅድስና ጠብቀው ያስረከቡ እልፍ አእላፍ አበው እንዳልነበሯት ዛሬ የተሻለ ኑሮና ደመወዝ እያገኘን እግዚአብሔርን እንደቀኖናው በጥንቃቄ ማገልገል አቅቶናል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ

ጥቅምት ፬/፳፻፲፰ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ

የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ

የአዲስ አበባና ሐድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች ፣

ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የመጣችሁ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ተወካዮች፣

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣

የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች

የምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣

በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራና ክቡራት

እግዚአብሔር አምላካችን ዓመቱን ጠብቆ በከፍተኛ ጉጉት ለምንጠብቀው አርባ አራተኛው የሰበካ ጉባኤ አጠቃላይ መንፈሳዊ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡ እናንተንም እንኳን በደኅና መጣችሁ እንላለን፡፡

“ዑቁ እንከ ዘከመ ተሓውሩ ከመ ጠቢባን በንጽሕ ወአኮ ከመ ዓብዳን፤ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት በንጽሕና እንደምትመላለሱ ዕወቁ” (ኤፌ.፭፥፲፭)፤ ሁሉንም መስጠትና መንሣት የሚችለው እግዚአብሔር አምላክ ጥበብን ለሰው ልጆች ሰጥቶአል፤ የሚሰጠው የጥበቡ ደረጃ የተለያየ ቢሆንም እግዚአብሔር ከጥበብ ባዶ አድርጎ የፈጠረው ግን የለም፤ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ለፍጡራን ሲሰጡ ሊጠቀሙባቸው እንጂ እንዲሁ በከንቱ ሊያባክኑዋቸው አይደለም፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጥበብ አስፈላጊነት በብዙ ቦታ ያስተምራል፤ በተለይም ጠቢቡ ሰሎሞን “ጥበብ ትኄይስ እምኲሉ መዛግብት ወኲሉ ክብር ኢመጠና ላቲ፤ ከሀብት ሁሉ ጥበብ ትበልጣለች፤ ክብርም ሁሉ አይመጣጠናትም” በማለት የጥበብ ብልጫ ተወዳዳሪ የሌላት እንደሆነች ያስገነዝበናል፤ እግዚአብሔርም ሥራውን ሁሉ በጥበብ እንደሚሠራ “ወኲሎ በጥበብ ገበርከ፤ ሁሉንም በጥበብ አደረግህ” በሚል ተጽፎ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ሥራውን በጥበብ እንደሚሠራ፣ እኛንም በጥበብ መሥራት እንዳለብን ሲያስተምረን፣ ‹‹ኩኑ ጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር እንደ እባብ ብልሆች ሁኑ›› ብሎናል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት!

ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች!

ዘመንና ቦታ ሳይገድበን ምንጊዜም ሥራችንን በጥበብ መሥራት እንዳለብን ቢታወቅም ዛሬ ላይ ከምን ጊዜውም በበለጠ በጥበብ መመላለስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፤ የዛሬዎቹ ችግሮች በአንድ አካባቢ ብቻ ያሉ ሳይሆኑ ዓለም ዓለፍ ቅርጽ ያላቸው እንደሆኑ ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ በዓለም መድረክ ላይ ስሞታ ሲያቀርቡ በዓይናችን አይተናል፤ በጆሮአችንም ሰምተናል፤ በሁኔታውም የክርስትና ሃይማኖት በአጠቃላይ በተለይም ደግሞ የኦርቶዶክሱ ወገን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡

እኛም የዚሁ ወገን አካል በመሆናችን የችግሩ ቀማሽ መሆናችን አልቀረም፤ በየቀኑ ካህናትና ምእመናን ይገደሉብናል፤ አብያ ክርስቲያናት ይቃጠሉብናል፤ የእምነትና የኅሊና ነጻነት በእጅጉ የሳሳ ሆኖብናል፤ አላስፈላጊ ጫናዎችም በዝተውብናል፤ ከውጭና ከውስጥ በተቀነባበረ ስሌት የቤተክርስቲያናችንን ስም ማጥፋት የዕለት ተግባራቸው ያደረጉ አካላት ተበራክተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ከነባሩና ረጅም ዘመን ካስቈጠረው ሰፊ ማእዷ እያበላቻቸው ያለች መሆኗን ዘንግተው እንብላሽ፣ እንዋጥሽ የሚሉዋት ወገኖች በዝተዋል፣ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች አባቶች እንደልብ ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉባቸው አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ነው፤ የወለጋው ችግር ለዚህ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡

ታድያ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ጥበብ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ጥበብ መከተል ማለት ዝም ብሎ ማለፍ ወይም አይተው እንዳላዩ ሆኖ መኖር ማለት አይደለም፤ በጥበብ መመላለስ ማለት ከሁሉ በፊት ችግሮችንና የችግሮችን መንሥኤዎች በአግባቡ መረዳትና መለየት መቻል ነው፤ ከዚያም ራስን ለከፋ አደጋ በማያጋልጥ መልኩ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም መሸጋገር መቻል ነው፤ በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ ጥበብ መጠቀም የግድ ያስፈልጋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት!

ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች! ቤተ ክርስቲያናችን እየተፈተነች ያለችው ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ጭምር እንደሆነ መካድ የለብንም፤ ንጽሕትና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥር የሰደደ የቅድስና ሕይወትና በፈሪሀ እግዚአብሔር የተቃኘ ሥነ ምግባር ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፤

በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ቦታቸውን እየለቀቁ ያሉ መስለዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ ታሪኳ ሲያስተምሩም ሆነ ሲማሩ፣ ሲመንኑም ሆነ ሲመነኲሱ፣ ሲቀድሱም ሆነ ሲያስቀድሱ ያለምንም ደመወዝ በራሳቸው ዓቅም በግብርና እየተዳደሩ ቤተ ክርስቲያንን በጥሩ ሰብእና በንጽሕና እና በቅድስና ጠብቀው ያስረከቡ እልፍ አእላፍ አበው እንዳልነበሯት ዛሬ የተሻለ ኑሮና ደመወዝ እያገኘን እግዚአብሔርን እንደቀኖናው በጥንቃቄ ማገልገል አቅቶናል፤ ምእመናንም በዚህ ምክንያት እየተሰናከሉ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡ ሚድያውም ስሕተቶችን ወደ ውጭ በማውጣት ሰድቦ ለሰዳቢ እየዳረገን ነው፤ ይህ ሊሆን የቻለው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በአግባቡ በመያዝ ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለመቻላችን ነው፤ ይህ ችግር ባለበት ከቀጠለ ሌላ ጦስ ይዞብን እንዳይመጣ ሁነኛ ለከት ማኖር የግድ ይሆናል፡፡

የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት የቤተ ክርስቲያናችንን ሀብተ ጸጋ በማሳደግ ረገድ አስተማማኝ ስልት እንደሆነ በተግባር የተረጋገጠ ነው፤ ሆኖም ሲጀመር ሳለ የነበረ መነቃቃት በአሁኑ ጊዜ የቀነሰ መስሎ ይታያል፤ አሁን በቤተ ክርስቲያን ሰፊ ሽፋን ይዞ የሚገኘው የሙዳየ ምጽዋት ገቢ እንጂ የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደአይደለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በተለይም በከተሞች ውስጥ ነገሩ ጎልቶ ይታያል፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባትም በየደረጃው በኃላፊነት ያለን ሰዎች ሻል ያለ ደመወዝ ስለምናገኝ የሰበካ ጉባኤው ተልእኮ ከሚፈለገው ደረጃ ላይ  የደረሰ መስሎን ይሆናል፤ ነገር ግን ከሰማንያ ከመቶ ያላነሰ የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መምህርና ካህን አሁንም ያለ ደመወዝ የሚኖር ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከቤተ ክርስቲያኑ ሊያገኘው የሚገባ የበጎ አድራጎት የጤና የትምህርትና የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት በሚጠበቀው ደረጃ ሊያገኝ አልቻለም፤ የገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ችግሮችም በነበሩበት የልመና ኑሮ እየቀጠሉ ነው፤ በውጤቱም በችግር የሚኖሩ ገዳማት የተዘጉ የአብነት ት/ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት ከተበራከቱ ሰነባብቶአል፡፡

ታድያ ይህንን ሁሉ መልክ ማስያዝና ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የሚቻለው በጥበብና በጥበብ ብቻ መሥራት ሲቻል ነው፤ ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችል ጥበብ ደግሞ በዘመናችን አለ፤ የጠፋው ቅንነቱና ፈቃደኝነቱ ነው፡፡

በየዓመቱ የምናካሄደው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ካልሆነ ተሰብስበናል ማለቱ ብቻ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፤ ስለሆነም ከዚህ በላይ የተጠቃቀሱና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮቶች ካሉ በዚህ ጉባኤ በማንሣት በማየትና በመገምገም ለቤተ ክርስቲያን አሻጋሪና ጥበባዊ ውሳኔ እንዲያሳልፍ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም

ዓመታዊው ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎተ ወንጌል የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን፡፡

መልካም ጉባኤ ያድርግልን!

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ !!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!!

አሜን!!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የአዲስ ዓመት አባታዊ መልእክት !!!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የ፳፻፲፰ ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፣ የቅዱስነታቸው ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው።

ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰንመቱ ዓመተ ምሕረት፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ኣሜን!

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
  • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
  • በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣

አምላክነቱን ኣውቀን እንድናመልከው ዕድሜንና ዘመናትን የሚሰጠን እግዚብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺህ ዐሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት የርእሰ ዐውደ ዓመት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!

‹‹ወገብረ ኵሎ ኅቡረ ወኵሎ ኣሕዛበ እምአሐዱ ዕጓለ እመሕያው ከመ ይንበሩ ዲበ ኵሉ ገጸ ምድር፤ ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እመ ይረክብዎ፤ ወያደምዕዎ፤ ወኢኮነ ርሑቀ እምኵልነ፡-

ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከኣንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ደረጃ መደባላቸው፤ ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም›› (የሐ. ሥራ. ፲፯÷፳፮)፤

ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ትዕይንተ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታትን የፈጠረ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚታዩና የማይታዩ ተብለው በጥቅል በቅዱስ መጽሓፍ ተገልጸዋል፤

የሰው ልጅ ከፍጥረታት መካከል ሆኖ ከኣንድ ወገን የተገኘ እንደሆነ በዚህ ጥቅስ ተጽፎአል፤

የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሓፍ በተደጋጋሚ ተገልጾአል፤ ልዩ የሚያደርገውም ከኣፈጣጠሩ ጀምሮ ነው፤

ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱ “ሰውን በኣርኣያችንና በኣምሳላችን እንፍጠር” በሚል ልዩ ኣገላለጽ መፈጠሩ፣ ኣፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና ኣምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው፤ የሁሉም ገዥ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓለም ከሰው በላይ ሆኖ የፍጡራን ገዥ የሆነ ፍጡር እንደሌለ ሁላችንም የምናየውና የምናውቀው ነው፤

በላይኛው ዓለምም ቢሆን መላእክትን ጨምሮ ሰማይና ምድርን ከነግሣንግሡ እየገዛ ያለው ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ገዥ ነው፤ እሱ ሰብእናችንን በፍጹም ተዋሕዶ የተዋሓደ በመሆኑ ሰብእናችን በተዋሕዶተ ቃል ኣምላክ ሆኖ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖኣልና ነው፤

ቅዱስ መጽሓፍም “ወተኰነኑ ሎቱ መላእክት ወሥልጣናት ወኵሉ ኃይል፡- መላእክት፣ ሥልጠናትና ኃይል ሁሉ ተገዙለት” በማለት ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች ያጐናጸፈን ግሩምና አስደናቂ ጸጋ ነው፤ ለዚህም ነው “ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፡- ሰው ከፍጥረት ሁሉ ይከብራል” ተብሎ የሚዘመረው፤

  • የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት!

እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከኣንድ ፈጠረ የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮም ይህንን ያመለክታል፤

ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል፤በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው፤

እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ኁልቈ መሣፍርት የሌለው ገንዘብ አይወጣም ነበር፤

ይህ ክፉ የዓለም ዝንባሌ እንደ ክፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞኝነትም የሚያሳይብን ነው፤ማንኛችንም ሰዎች ‹‹ሰው ማጥፋት ይሻላል ወይስ ማዳን›› ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን እንደሚሆን ይታወቃል፤

ነገር ግን ኣንፈጽመውም፣ ሞኝነት የሚያሰኘውም እዚህ ላይ ነው፤ የሚጠቅመንንና የመሰከርንለትን ትተን የሚጐዳንንና፣ ያልመሰከርንለትን እንፈጽማለንና ነው፤ ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የኣዲሱ ዓመት ትልቁ ኣጀንዳ ኣድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናልና እንቀበለው እንላለን፤

  • የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!

ሰው በሕይወት እንዲኖር በእግዚአብሔር ሲፈጠር እግዚአብሔርን የሚፈልግበትና የሚያገኝበትን ዕድሜና ዘመንም እንደተሰጠው ከተጠቀሰው ክፍለ ንባብ እንገነዘባለን፤ መቼም እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ በስራ ለስራ እንደሆነ የምንስተው ኣይሆንም፤

እግዚአብሔር ዕድሜና ዘመን ለሰዎች ሲሰጥ ሊሠራበት ነው፤ ስራውም መንፈሳዊና ዓለማዊ ነው፤ ተደምሮ ሲታይ ደግሞ ለሰው ጥቅም የሚውል ነው፤

እኛ ሰዎች በተሰጠን ዕድሜና ዘመን በመንፈሳዊው ሥራችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንድናገኝ ተፈጥረናል፤ እሱን ማግኘት የማይቻል የሚመስለን ካለንም እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም ተብለናልና በመንፈስ ከፈለግነው በመንፈስ እንደምናገኘው መጽሐፉ ያስረዳናል፤ ስለሆነም በተሰጠን ዘመን ይህንን ሥራ መሥራት ይኖርብናል፤

በሌላ በኩል ለኑሮኣችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን ኣንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፤ ይህም ከሰራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጐደሉብን በኛ አስተሳሰብ፣ አሠራርና አጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን አይደለም፤

እግዚአብሔር የሰጠን ምድር በልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ የተሞላች እንደሆነች፣ የምንረግጠው መሬትም ወደ ሀብት መቀየር እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው፤

ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው፤

ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኣድርገን በማመን በእኩልነት፣ በኣንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ ያ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል ኣባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፤

ይህ ግለኝነት ያየለበት አስተሳሰብ ገታ አድርገን በእኩልነትና በአብሮነት የሚያሳድገንን አስተሳሰብ በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ይህንንም የአዲሱን ዓመት ምርጥ እሳቤ ኣድርገን ብንወስድ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፤ አዲሱ ዓመት በኣዲስ እሳቤ ካላጀብነው አዲስ ሊሆን አይችልምና ነው፤

ስለሆነም ኣዲሱን ዓመት መልካም በሆነ ኣዲስ ኣሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ወቅታዊ ጥሪያችን ነው፤

በመጨረሻም፣ አዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለሕዝቦች ኣንድነትና ስምምነት እንደዚሁም ኣለመግባባትን በፍትሕና  በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ፣ በዚህም መላ ሕዝባችን ጠንክሮ እንዲሠራ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤

እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

መስከረም ቀን ፳፻፲፰ .

አዲስ አበባኢትዮጵያ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አደረሳችሁ!

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ፳፻፲፯ ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት ዐዋጅ መግለጫ

‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ አስተጋብኡ ሕዝበ ሊቃውንተ ሕዝብ፤ ጾምን ቀድሱ፣ ጉባኤውንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።›› (ኢዩ.፩÷፲፬)

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት ቁጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት ፲፩ እስከ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም. ድረስ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

የአቋም መግለጫ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት