‹‹በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር›› (ዘፀ.፳፥፲፮)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! በፈቃደ እግዚአብሔር የጀመርነው ዐቢይ ጾም (ጾመ ክርስቶስ) አምስተኛው ሳምንት ላይ እንገኛለን፤ በአቅማችሁ በመጾም በጸሎት እየበረታችሁ እንደሆነ ተስፋችን ነው፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ማስቀደስና መንፈሳዊ ትምህርትን ከመማርም መዘንጋት የለብንም!
በእግዚአብሔር ቤት ስናድግ እንባረካለን፤ አምላካችንም ጥበቡንና ማስተዋሉን ያድለናል፤ በጥሩ ሥነ ምግባር አድገን፣ ለራሳችን ለቤተሰቦቻችን እንዲሁም ለአገራችን መልካም የምንሠራም እንሆናለን፡፡ በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርትታችሁ መማር ይገባል፡፡ የሁለተኛ መንፈቀ ዓመት እየተገባደደ ነውና በርትታችሁ ትማሩ ዘንድ አጥኑ፤ ያልገባችሁን ጠይቁ፤ አብዛኛውን ጊዜያችሁን በትምህርታችሁ አተኩሩ፡፡ መልካም! በዛሬው ትምህርታችን ሐሰት (ውሸት) በሚል ርእስ እንማራለን፡፡