ጽዮን ማርያም
ኀዳር ፲፱፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ጽዮን “”ጸወን” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን “አምባ፣ መጠጊያ” ማለት ነው፡፡ እመ ብዙኀን የሆነችውን የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚገለጽ መሆኑን “ማኅደረ አምላክ” በሚለው ትርጒም እንረዳለን፡፡ ጽዮን የሚለው ስያሜ በቁሙ ለታቦት፣ ለጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስተ መንግሥተ ሰማያት ያገለግላል::
ታቦተ ጽዮን “ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ” እየተባለችም ትጠራለች:: “ጽሌ” ማለት “ሰሌዳ” ማለት ሲሆን “ጽላት” ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው:: “ኪዳን” ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ “ውል፣ ስምምነት” ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈባት በመሆኗ የእግዚአብሔር ሕግጋትን የያዘ ናት፡፡ በዚህም በሕጉ እንድመራ ትእዛዙን እንድፈጽም ያሳስበናል፡፡
አልፋና ኦሜጋ፣ ኤልሻዳይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ቅድስት የምትሆን ማደሪያውን ታቦተ ጽዮንን በነቢዩ ሙሴ አካማኝነት የሰጣቸው ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ እንድትሆናቸው ነው፡፡ (ዘጸ. ፴፩፥፲፰) ለ፭፻ (አምስት መቶ) ዓመት ከእነርሱ ሳትለይ ከአምላክ ጋር መገናኛ፣ በጦርነት ጊዜም ማሸነፊያ ኃይላቸው ሆናም ኖራለች፡፡
ሀገረ እግዚአብሔር የሆነችው ኢትዮጵያም ለከበረች ታቦተ ጽዮን መቀመጫ ለመሆን ታድላለች፡፡ በቀዳማዊው እብነ መለክ፣ እብነ ሐኪም/በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አማካኝነት ወደ ሀገራችን የመጣችው ታቦቷ እስከ አሁን ድረስ በአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እንደምትገኝ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ (መጽሐፈ ክብረ ነገሥት) የጌታችን ድንቅ ቸርነት የተደረገልን እኛ የድንግል ማርያም የዐሥራት ልጆች የአምላክን ሥራ ልናደንቅና ልናመሰግን ይገባል፡፡
ሀገራችን የገባበትን እንዲሁም አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የተቀመጠበት ኅዳር ፳፩ ቀንንም ታላቅ በዓልን እናደርጋለን፡፡
የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!
