አርባእቱ እንስሳ

ኀዳር ፰፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ዓለምን በመላ ከእነ ጓዟ ድንቅ አድርጎ የፈጠረ የሁሉን ቻይ የአምላክን ክብር መግለጽ ማን ይቻለዋል? ለእርሱ ክብር የሚመጥንስ ዙፋን ከየት ይገኛል? መንበረ ሥላሴን መሸከምስ ምንኛ ድንቅ ነው? እኒህ ቅዱሳን ኪሩቤልና ሱራፌል ግን ለእዚያ ክብር በቅተዋልና በዓላቸውን እናደርግ ዘንድ ይገባል፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ላይ እንደገለጸው “ኪሩቤል ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ሲፈጥራቸው ዐይናቸው ብዙ ነው፤ አለቃቸውም ኪሩብ ሲሆን የሰው መልክና የአንበሳ መልክ ያለው ነው፡፡”
ሱራፌል ደግሞ “የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፤ አለቃቸውም ሱራፊ ሲባል ሲፈጥራቸውም ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ አለቃቸው የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፡፡”

ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም” ይላቸዋል። (ራእይ ፬፥፯-፱)
ነቢዩ ኢሳይያስ ሲገልጻቸው “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር፤ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተመልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ይላል፤ (ኢሳ.፮፥፩-፫) ይህ መሸፈናቸው ያድናቸዋል ቢሉ? ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ ዛሬ በዚህ ዓለም ሴቶችን ሕፃናትን እንመታችኋለን ባሏቸው ጊዜ እጃቸውን መጋረዳቸው የሚያድናቸው ሆኖ ሳይሆን ትእምርተ ፍርሀት እንደሆነ ሁሉ፡፡

አንድም በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ፊትህን ማየት አይቻለንም ሲሉ፣ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ከፊትህ መቆም አይቻለንም ሲሉ፣ ሁለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ ያደርጋሉ አለ፤ ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

አንድም በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ባሕርይህን መመርመር አይቻለንም ሲሉ፣ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ባሕርይህን መረማመድ መተላለፍ አይቻለንም ሲሉ ሁለት ክንፋቸውን ወዲያ ወዲህ ያደርጋሉ፤ ከእእምሮ ወደ አእምሮ የመፋለሳቸው ምልክት ነው፡፡

አንድም ሁለት ክንፋቸውን ወደ ላይ አድርገው ይታያሉ አለ፤ ወደላይ ቢወጡ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፣ ሁለት ክንፋቸውን ወደታች አድርገው ይታያሉ፤ ወደታች ቢወርዱ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፣ ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ ያደርጋሉ፤ ወዲያና ወዲህ ቢሉ አትገኝም ሲሉ፤ አንድም ወደላይ መዘርጋት በሰማይ ምሉእ ነህ ሲሉ፣ ወደታች መዘርጋቸው በምድርም ምሉእ ነህ ሲሉ፤ ወዲያና ወዲህ መዘርጋታቸው በሁሉ ምሉእ ነህ ማለታቸው ነው፤ አንድም ወደላይ መዘርጋት ትእምርተ ተመስጦ ወደታች መዘርጋት ትእምርተ ትሕትና፣ ወዲያና ወዲህ ረብቦ መታየት ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

ሁለት ክንፋቸውን ወደላይ ሁለት ክንፋቸውን ወደታች ሁለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ አድርገው ትእምርተ መስቀል መሥራታቸው በብሉይ ኪዳን ከሆነ እንዲህ ባለ መስቀል ተሰቅለህ ዓለምን ታድነዋለህ ሲሉ፣ በዘመነ ሐዲስ የሆነ እንደሆነ እንዲህ ባለ ትእምርተ መስቀል ተሰቅለህ ዓለምን አድነኸዋል ሲሉ ነው፡፡ የእነዚህ አርባእቱ እንስሳ መላእክት ፊታቸው በርካታ ምሥጢራትን ሲያመለክቱ ገጸ ሰብእ በማቴዎስ፣ ገጸ አንበሳ በማርቆስ፣ ገጸ ላህም በሉቃስ፣ ገጸ ንስር በዮሐንስ ተመስሏል።

ዳግመኛም የሰው ፊት ያለው መልአክ ለሰው ልጆች ይማልዳል። የአንበሳ ፊት ያለው መልአክ ለዱር አራዊት ይለምናል። የላም ፊት ያለው መልአክ ለእንስሳት ይጸልያል። የንስር ፊት ያለው መልአክ ለሰማይ አዕዋፋት ሁሉ ይለምናል በማለት ሊቃውንት ያመሰጥራሉ።
በሌላ ምሥጢር የሰው ገጽ ያለው የጌታን ሰው የመሆንን ነገር፣ የላም መልክ ያለው በቀራንዮ ላይ ደሙን ማፍሰሱ፣ የአንበሳው መልክ ያለው የጌታችንን ትንሣኤ፣ የንስር መልክ ያለው የጌታን ዕርገት እንደሚያመለክቱ ቀደምት መተርጒማን ይተነትኑታል።

ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ በራእይ ያየውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ፤ በዙፋኑም መካከል፣ በዙፋኑ ዙሪያም አራት እንስሶች አሉ፤ ….. እነዚህ እንስሶችም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴን ምስጋናንም ይሰጣሉ” በማለት ገልጿቸዋል፡፡ (ራእ.፬.፮-፱፣ ስንክሳር ዘኅዳር ገጽ ፪፻፸፯)

ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ኅዳር ስምንት ቀን “ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ነው፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ሠረገላዎቹ ናቸው” በማለት ይገልጻል፡፡

የቅዱሳኑ ኪሩቤልና የሱራፌል ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!