‹‹በእንተ አቡነ አቢብ!››
ጥቅምት ፳፬፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
በዐሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በሮሜ ሀገር የተወለዱት ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብ የስማቸው ትርጓሜ “የብዙኀን አባት” አንድም ቡላ ማለት “የተወደደ፣ እግዚአብሔር የተለየ” ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ታላቅና ክቡር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ ተብሎም የሚታወቅ አባት በከበረች ዕለት ጥቅምት ሃያ አምስት (፳፭) እንዳረፈ ይጠቅሳል፡፡
አስቀድሞም ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ክርስቲያኖች ላይ ባመጣባቸው ስደት ምክንያት አባትና እናታቸው አብርሃምና ሐሪክ ተሰደው ሲኖሩ ልጅን ባማጣታቸው በጸሎትና በጾም አምላካቸው እግዚአብሔርን በመለመናቸው መልአክ ለአብርሃም ተገልጾ “ይህ ፍሬ የአንተ ነው፤ እርሱም ወደ እኔ የሚቀርብ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ፈቃዱንም የሚፈጽም የአመረ መባዕ ነው” በማለት እግጅ መልካም ፍሬን ሰጠው፡፡ ደጉ ሰው አብርሃምም ከእንቅልፉ ነቅቶ ለሚስቱ በሕልሙ ያየውንና መልአኩ የነገረውን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ደስ ተሰኘች፤ ሁለቱም በአንድነት እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የአብርሃም ሚስት ሐሪክ በፀነሰች ጊዜም በቤታቸው አደባባይ ሁለንተናው መልካምና ታላቅ ዛፍ በቀለ፡፡ በቅጠሉም ላይ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ “በጽዮን አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ የእግዚአብሔር አገልጋይ ቡላ” የሚል ጽሕፈት አገኙ፡፡ በዚህም ጊዜ በተአምሩ ተደንቁ፡፡
ቀጥሎም መልኩ ያማረ ከብርሃናት ይልቅ ፊቱ የሚያበራ ወንድ ልጅን ወለደች፡፡ ከዚህም በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ክርስትናን ሳይስነሡ ሲያኖሩት እመቤታችን ድንግል ማርያም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትሮዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት በመሄድ ሕፃኑን እንዲያጠምቀው ስላዘዘችው የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው፡፡ ስሙንም “ቡላ” ብላ ሰየመው፤ ወላቹም በዚህን ጊዜ አደነቁ፡፡ ጸሎትም አድርጎ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ስለወረደ ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን ሕፃኑንና ወላጆቹን አቀበላቸው፡፡ በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን “በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ አብ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው፤ በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው፤ በባሕርይ በህልውና በመለኮት በአብ ከወልድ ጋር አንድ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው” ብሎ ተናገረ።
ጥቂት ዓመታት ካለፉም በኋላ በኅዳር ሰባት ቀን አባቱና እናቱ ዐረፉ፤ ሕፃን ቡላ ዐሥረኛው ዓመቱ ላይ ሌላ መከራ አጋጠመው፤ ሕዝቡን ለጣዖት መስገድ የሚያስገድድ መኮንን እንደመጣ በሰማ ጊዜም ሕፃኑ በፊቱ ቀርቦ የረከሱ ጣዖታትን ረገመ፡፡ በአካል ትንሽ መሆኑን የተመለከተው መኮንኑ ለጊዜው ቢያደንቅም በችንካር ቸንክረው፣ ሥጋውን ሰነጣጥቀው፣ ቆዳውንም ከአጥንቱ እንዲገፉት፣ እጁቹንና እግሮቹን በመጋዝ እንዲቀርጡ፣ በሶሾተልና በጦሮች አድርገው ከመንኮራኩር ውስጥ እንዲጨምሩት፣ ዳግመኛ በመንገድ ላይ እንዲጎትቱት አዘዘ፡፡ ሆኖም መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ስላዳነው ያለ ጉዳት ጤነኛ ሆነ፡፡ ቅዱሱ ሕፃን ቡላ ግን ሌላ መኮንን ጋር ሄዶ የረከሱ ጣዖታትን ገረመ፡፡ በዚህም ጊዜ መኮንኑ ተቆጥቶ ሚያዝያ ወር በባተ በዐሥራ ስምንተኛው ቀን ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ስላዘዘ ቆረጡት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሞት አስነሣው፡፡ በዚህም ጊዜ የመነኮስ ልብስንና አስኬማን በመስቀል ምልክት አለበሰውና እንዲህ አለው፤ “ከቅዱሳንና ከጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አዝዞአል፡፡”
ቅዱስ አባታችንም በዚህ ጊዜ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጥተው በውስጧ እየታገደሉ ሲኖሩ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል በማሰብ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሳቸውን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም በዛፍ ላይ ሲወረወሩ ሰይጣን በቅናት ተነሣስቶ ገደላቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አነሣቸውና “ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን፤ አቢብ ይባል እንጂ፤ የብዙዎች አባት ትሆናለህና” አላቸው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ አቡነ አቢብ የክርስቶስን ፍቅር በመጨመር ፊታቸውን ይጸፉ፣ ሥጋቸውን በጥቂት ይቆርጡ፣ ጀርባቸውን ሰባት ጊዜ ይገርፉ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ጊዜም ከእርሳቸው ሳይለይ ይፈውሳቸው ነበር፡፡ በየእሑድም ቀን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ፣ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽላቸው ነበር። በዚህም የተነሣ ለአርባ ሁለት ዓመታት ምግብ ሳይበሉና ውኃ ሳይጠጡ ከኖሩ በኋላ ለዐሥራ ሁለት ወር በራሳቸው ተተክለው ሲኖሩ ናላቸው ፈስሶ አለቀ፡፡
የጌታችንን መከራ በአሰቡ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰይፉን በአንጻሩ ተክለው ከዕንጨት ላይ በመውጣት በላዩ ወድቀው ሞቱ፤ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ “የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ” አለችው። ከበድኑም ቃል ወጥቶ “የሰማይና የምድር ንግሥት እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል” አላት፡፡ እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።
ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብ ከዚህ ዓለም ድካም የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለትና እንዲህ አላቸው፤ “ወዳጄ አቢብ ሆይ፥ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደ እኔ ና፤ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ፤ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን፣ ለተራበም የሚያጠግበውን፣ ለተጠማ የሚያጠጣውን፣ የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን፣ በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ፤” ይህንም ብሎ አፋቸውን ሳማቸው፤ በደረቱም ላይ አድርጎ ወደ አየር አወጣቸው፤ የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።
እነሆ ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ምእመናን በሚቀምሱት የዕለት ምግብ አማካኝነት በነፍስም በሥጋም እንዲድኑ አስገራሚ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደተቀበሉ የሚናገር የገድል ተአምራታቸው ይህ ነው፡- ብዙዎች ስማቸውን ጠርተው በሚቀምሱት ምግብ አማካኝነት ከተለያዩ በሽታዎች የተፈወሱ አሉ፡፡ ይህ ቃል ኪዳናቸው ለሁላችን ይደረግልን ዘንድ ከመመገባችን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም እንጥራ (አቡነ ዘበሰማያትን ማለቱ ነው፡፡) ከተመገብን በኋላም የዕለት ምግባችንን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እናመስግን፡፡ ዘወትር ከተመገብን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹ስለ ወዳጅህ ስለ አቡነ አቢብ›› እያልን ሦስት ጊዜ እንቅመስ፡፡ አስቀድሞ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ አቢብ ተገልጦላቸው ‹‹…ወዳጄ አቢብ ሆይ! የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበልኩትን ሕማማተ መስቀል እያሰብህ ይህንን ሁሉ ገድል ፈጽመሃልና ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብም ‹‹ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መቼም ሰው ሁሉ ሳይመገብ አይውልም፤ አያድርምና በተመገበ ጊዜ ስሜን ጠርቶ የተማጸነውን ማርልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባታችን አቡነ አቢብ ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ካደነቀ በኋላ ‹‹…ከማዕድ በኋላ ስብሐት ተብሎ የተረፈውን ‹በእንተ አቢብ› ብሎ ሦስት ጊዜ የተመሰገበውን ሰው ሁሉ እምርልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ያልተጠመቀ አረማዊ አሕዛብም እንኳን ቢሆኖ ‹‹ስለ አቡነ አቢብ›› ብሎ ከተማጸነ ጌታችን ያንን ሰው ወደ ቀናች የእምነት መንገድ ሳይመራወና በንስሓ ሳይጠራው በሞት እንደማይወስደው ለአባታችን ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ለማዳን ትንሽ ምክንያትን የሚፈልግ ያለ ምክንያትም የማያድን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይክበር ይመስገን! ሰው ተመግቦ እንኳን መዳን እንዲችል ይህን ድንቅ ቃል ኪዳን ለአባታችን ሰጥቷቸዋልና በየቀኑ በዚህ ቃል ኪዳን እንጠቀምበት፡፡ ተመግበን ከጨረስንና ስብሐት ካልን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹በእንተ አቡነ አቢብ›› ብለን እንቅመስ፡፡ በጥቅምት ፳፭ ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ጻድቁና ሰማዕቱ አቡነ አቢብ የቃል ኪዳናቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!
(ምንጭ፡– ደብረ ሰላም ቃጭልቃ አቡነ አቢብ ገዳም ያሳተመው ገድለ አቡነ አቢብ፣ ገጽ ፻፭)
በእንተ ቅዱሳን ኀሩያን)
