የሥራ አጥነት ተጽዕኖ
ጥቅምት ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
“በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ” የሚለው አምላካዊ ቃል ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፯) ሰው በሠራው ኃጢአትና ጥፋት የተነሣ ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የሥጋችንን በተለይም መሠረታዊ ፍላጎታችንን ሟሟላት የምንችለው ሥራ ሠርተን በምናገኘው ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ነው፡፡
በዘመናት ሂደት ሰዎች በተለያዩ ችግሮችና መከራዎች ውስጥ ገብተው የሚዋዥቁበት ምክንያት አንድም በሥራ አጥነት ሳቢያ በሚያጋጥም የገንዘብ አቅም ማነስና ችግር በመሆኑ የምግብ አቅርቦት፣ የመጠለያ እጦትና የአልባሳት እጥረት ለረኃብ፣ ለመራቆት እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች ባስ ሲል ደግሞ ለሞት ይዳርጋሉ፡፡
የሥራ አጥነት ችግር አስከፊነት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በደረስንበት በዚህ ወቅት በተለይም ወጣቶች ከዚህ ለባሳ ችግር ተጠቂ ሆነዋል፡፡ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው እንዲሁም በተሰጣቸው ተሰጥኦ ለፍተው፣ ጥረው፣ ግረው የመኖር ሐሳባቸው ከማንኛውም የዕድሜ ክልል የበለጠ በመሆኑ አእምሮአቸው ሥራ ሲፈታ ይረበሻል፤ ተስፋም ያጣሉ፤ ወደ ጭንቀትና የተለያዩ የሥነ ልቡና ቀውስ የሚገቡ ወጣቶች ቁጥርም ጥቂት አይባልም፡፡
በየዓመቱ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎችም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት ብዙ ሳይገፉ በአጋጣሚዎች ተጠቅመው በሙያቸው አልያም በጉልበታቸው ሠርተው ለመኖር የሚጥሩ ወጣቶች በልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ሥራ አግኝቶ በቋሚነት አንድ ቦታ ላይ ገንዘብም፣ ዕውቀትም ሆነ ልምድ ማካበት ያልቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህም እራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፤ አብዛኞቻችን በእራሳችን፣ በዘመዶቻችንና በጎረቤቶቻችን ሕይወት የሰማነውና የተመለትነው ነገር ነው፡፡
በርካታ ወጣቶች የሱሰኝነት ተጠቂ የሆኑት በዚህ ምክንያት እንደሆነ ከገዛ አንደበታቸው ሰምተንም ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም ወጣት ወንዶች ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው፡፡ ሱሰኝነት የሚያመጣው የጤንነት እክል ብቻ እንዳልሆነ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች አበክረው ይናገራሉ፡፡ እንደ እነርሱ ገለጻ ከሆነ ሱሰኞች ከቤተ ሰቦቻቸው ጋርም ሆነ ከማንኛውም የማኅበረሰብ አካል ጋር መልካም ግንኙነት አይኖራቸውም፡፡ የተዛበ ቀኖችን በማሳለፋቸው የተነሣ ከማንም ጋር የሰላም ግንኑነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ቀኑ ለእነርሱ ሌሊት፣ ሌሊቱ ደግሞ ቀን የሚሆንባቸው ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ንግግራቸው በአብዛኛው ቀና ያልሆነና የተጣመመ እንዲሁም ስድብና አጸያፊ ቃል የተቀላቀለበት ሲሆን ከሰዎች ጋር የመጣላቱ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ የሚወዷቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች ሳይቀር ስለሚያስቀይሙ በብቸኝነት ዓለም ውስጥ ይገባሉ፡፡
ሱሰኛ የሚሆኑ ወጣቶች ዓለማዊ ሕይወትን የሚኖሩ ብቻ ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን በስመ ኦርቶዶክስ የሚኖሩና በሥራ አጥነት እንዲሁም በሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ምክንያት ባክነው የቀሩ ብዙዎች እንዳሉ ማወቅ ይገባል፡፡
በዚህ ጊዜ ደግሞ የተጋፈጥነው ሌላ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ከምዕራባውያን በኩል ወደ ሀገራችን የገባና የተስፋፋ ተብሎ የሚታመነው “የሰይጣን አማኞች ማኅበረሰብ” ወጣቶችን በገንዝብና ሌሎች ጥቅሞች በማጥመድ የጠላት መረብ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ፡፡ በየአደባባይ እየተመለከትናቸው ያለነው የእምነቱ ተከታዮች ሳያውቁም ይሁን አውቀው ለሰይጣን እየተገዙ ነው፡፡ ድህነትን ሸሽተው፣ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ችግራቸውን ፈትተው ገንዘብና ሀብት ለማካበት በሚደረግ ጥረት ነፍሳቸውን ካጡት ውስጥ ኦርቶዶክሳውያን እንዳሉበት ተአማኒ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ወጣቶቹ ታዲያ እያጡ ያሉትን መንፈሳዊነትም ሆነ እየገቡበት ያለውን አዘቅት በደንብ የተረዱ አይመስሉም፡፡ ብቻ የዕለት ጉርሰን ለሟሟላትና ከተቻለም በርከት ያለ ገንዘብ ለማግኘት ወደዚህ ዝቅተት ይገባሉ፡፡ በኋላ ግን ከገቡበት ለመውጣት ቢፈለግ እንኳን ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን እያስተናገደች ያለችው አስተዳደራዊ ለውጥና ማኅበረሰባዊ አኗኗር ያመጣው የኑሮ ውድነትም ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደረገ ነው፡፡ ቢያንስ መሠረታዊ ነገሮች ሁሉም ሊኖረው ይገባልና በእራሱ ለፍቶ እንዲያገኝ የማድረግ ዕድል ተጠያቂው አካል ሊያመቻች ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን እንደምትደግፍ አስቀድመን በጠቀስነው የአምላካችን ትእዛዝ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ይቆየን!
