ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ

ጥቅምት ፲፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የቴዎዶስዮስ ልጅ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ጥቅምት ፲፬ የከበረ በዓል ነው። ቴዎዶስዮስ የተባለው ንጉሥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው፤ ሚስቱም በጎ የምትሠራ እግዚአብሔርንም የምትፈራ ናት፤ ስሟም መርኬዛ ነው። እነርሱም ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ነበር፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሒደው ስእለትን ተሳሉ፤ ቸር መሐሪ ወደሆነ እግዚአብሔርም ለመኑ፤ እርሱም ልመናቸውን ተቀበሎ ይህን ያማረ ልጅ ሰጣቸው፤ ስሙንም አብደልመሲህ ብለው ሰየሙት፤ ትርጓሜውም ገብረ ክርስቶስ ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ የሥጋዊንም ትምህርት አስተማሩት።

አድጎ በጕለመሰም ጊዜ የሮሜውን ንጉሥ ልጅ አጭተው እንደ ሥርዓቱ አጋቡት ከሌሊቱ እኩሌታም በሆነ ጊዜ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ተነሥቶ ወደሙሽራዪቱ ገባ፤ እጅዋንም ይዞ ከእርስዋ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ። ከዚያም የሃይማኖት ጸሎት በአንድ አምላክ እናምናለን የሚለውን እስከ መጨረሻ ጸለየ፤ የተሞሸረበትንም ልብስ ከላዩ አውልቆ የግምጃ ልብስን ለበሰ፤ ወደ ሙሽሪቷም ሒዶ ራስዋን ሳማት፤ እንዲህም እያለ ተሰናበታት፤ “እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኑር፤ ከሰይጣን ሥራ ሁሉ ያድንሽ።” እርሷም አልቅሳ “ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ? ለማንስ ትተወኛለህ? አለችው፤ እርሱም “በእግዚአብሔር ዘንድ እተውሻለሁ፤ እኔም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሔዳለሁ፤ የአባቴ መንግሥት አላፊ ነውና አንቺም መሐላሽን አስቢ” አላት፤ ያን ጊዜ መሐላዋን አስባ ዝም አለች።

ለሠርጉም የታደሙት ሁሉ እንደተኙ በሌሊት ወጥቶ ሔደ፤ ወደ ባሕርም ዳርቻ ደርሶ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞችን አገኘ፤ የዓመት መንገድ ወደሚሆን አርማንያም እስከሚደርስ ከእነርሱ ጋር ተጓዘ።

ነግቶ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ በገቡ ጊዜ ሙሽራውን ልጃቸውን አላገኙትም፤ ሙሽሪትንም “ልጃችን ወዴት አለ?” ብለው ጠየቋት፤ እርሷም እንዲህ አለቻቸው። “በሌሊት ወደ እኔ ገባ፤ መሐላን አማለኝ፤ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ ራሴንም ስሞኝ ከእኔ ዘንድ ወጣ፤ እኔም እያለቀስኩ ብቻዬን አደርኩ፤” ነገርዋንም ሰምተው ወድቀው በመጮህ ታላቅ ልቅሶን አለቀሱ።

በዚያችም ጊዜ በሀገሮች ውስጥ ሁሉ ልጁን ገብረ ክርስቶስን ይፈልጉት ዘንድ ንጉሡ አምስት መቶ አገልጋዮቹን ላከ፤ ለድኆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት አድርገው የሚሰጥዋቸውን ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው።

ገብረ ክርስቶስ ግን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአርማንም አገር በተሠራች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚኖር ሆነ። አባቱ የላካቸውም ሁለቱ አገልጋዮች ከዚያ ደርሰው ስለርሱ መረመሩ፤ ግን ወሬውን ማግኘት ተሳናቸው፤ ለድኆችም ምጽዋትን ሰጡ፤ እርሱም ከድኆችም ጋር ምጽዋትን ተቀበለ።

በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት ከኖረ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአንድ ቄስ ተገለጸችለት፤ ቦታውንም አመልክታ እንዲህ አለችው። “የእግዚአብሔር ሰው ገብረ ክርስቶስን ይዘህ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስገባው፤ ከውጭ አትተወው፤” ቄሱም እመቤታችን እዳዘዘችው አደረገ።

ከዚህም በኋላ የተመሰገነ ገብረ ክርስቶስ በሌሊት ተነሣ ከእመቤታችንም ሥዕል ፊት ቁም ጸለየ፤ እንዲህም አላት፤ “እመቤቴ ሆይ የተሠወረ ሥራዬን አንቺ ለምን ገለጥሽ፤ አሁንም ወደሚሻለኝ ምሪኝ፤” ይህንንም ብሎ የእመቤታችንን ሥዕሏን ተሳልሞ በሌሊት ወጥቶ ወደ ባሕሩ ወደብ ደረሰ፤ ወደሌላ ሀገርም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ተሳፈረ። ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቱ አገር ደረሰ የአባቱና የእናቱም ባሮች እየናቁትና እየሰደቡት በአባቱ ደጅ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

ሲገቡና ሲወጡም “ሽታው እንዳያስጨንቀን ይህን ምስኪን አስወግዱልን” ይላሉ፤ ወጭትና ድስትም አጥበው በላዩ ይደፉበታል፤ ውሾችም እንዲናከሱበትና እንዲበሉት የሥጋ ትርፍራፊ ይጥሉበታል፤ ውሾች ግን ቁስሉን ይልሱለት ነበር፤ እንደዚህም አብዝተው አሠቃዪት።

ከዚህም በኋላ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ፤ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ለአባቴና ለእናቴ ባሮች በደል እንዳይሆንባቸው ወዳንተ ውሰደኝ።” በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው። ከዚህም በኋላ ገድሉን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጻፈ፤ በእጁም ጨብጧት ዐረፈ።

በእሑድ ቀንም ሕዝቡ ሁሉና ካህናቱ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳሉ የእግዚአብሔርን ሰው በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ቤት ፈልጉት የሚል ቃል ከሰማይ ሰሙ፤ በዚያን ጊዜ ሔደው በአረፈበት ቦታ አገኙት። በእጁም ውስጥ የተጨበጠ ክርታስን አዩ፤ ሊወስዷትም ሽተው መውሰድ ተሳናቸው።

በአንድነትም በጸለዩ ጊዜ እጁ ተፈትታ ወስደው አነበቧት፤ አባትና እናቱም ልጃቸው እንደሆነ አወቁ፤ ታላቅ ጩኸትም ሆነ፤ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ፤ አክብረውም ቀበሩት፤ መቃብሩም በሽተኞችን ሁሉ በመፈወስ ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራትን የሚያደርግ ሆነ።

አምላካችን እግዚአብሔር በቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን።

መጽሐፈ ስንክሳር ዘጥቅምት ፲፬