የባሕረ ሐሳቡ ደራሲ ቅዱስ ድሜጥሮስ
ጥቅምት ፲፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ከምንባባት ዐውድ
አካሄዱን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ፣ እርፍ አርቆ፣ ድኮ ታጥቆ፣ ወይን አጽድቆ የሚኖር፣ የቀለም ትምህርት ብዙም ያልነበረው ሰው ድሜጥሮስ በቅን ልቡናው መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ባሕረ ሐሳብን የደረሰ ቅዱስ ሰው ነው፡፡ ጌታ ባረገ በ፻፹(180) ዓ.ም የእስክንድርያ መንበር ዐሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሹሟል። በሹመቱም ጊዜ በትህርምት ኗሪ ነውና አሁን አጽዋማትንና በዓላትን የምናወጣበትን ይህን የቁጥር ዘመን ባሕረ ሐሳብ ተገልጾለት ደርሶታል፤ ተናግሮታል፤ ተናግሮት ብቻም አልቀረም፤ ለሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ለሮሙ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ሥር ለነበረው ለአባ ፊቅጦር፣ በቅዱስ ዮሐንስ መንበር ሥር ለነበረው ለኤፌሶኑ ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ጴጥሮስ ካልእ ሥር ለነበረው ለአንጾኪያው መንበር ለቅዱስ መክሲሞስ ዐራተኛ፣ ለኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ለአባ አጋብዮስ ልኮላቸዋል። እነርሱም ሐዋርያት ከአስተማሩት ትምህርት ጋር አንድ ቢሆንላቸው ተቀብለው ኑረውበታል፤ አስተምረውበታል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፬፥፵፩፣ ስንክሳር ኅዳር ፲)
ባሕርን ዘመን ሲል የት ይገኛል ቢሉ “እስመ በመዳልው ተደለወ ዓለም ወበመሥፈርት ሰፈራ ለባሕር፤ ዓለም በመስፈሪያ ተሰፍሯልና ባሕርንም በመስፈሪያ ሰፈራት” እንዳለ ዕዝራ (ዕዝራ ፪፥፴፯) ቅዱስ ዳዊትም “ዛቲ ባሕር አባይ ወረሐብ፤ ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት” ብሏል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት ፻፫፥፳፭) ሐሳብንስ ቁጥር ሲልስ የት ይገኛል ቢሉ ለትኩነኒ ሐሳበ ብላለች ኦሪት፡፡ ነቢዩ ዳዊትም “ብፁዓን እለ ተሐድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ፤ መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው” ብሏል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት ፴፩፥፩) ይህን የመሠለው ሁሉ ብዙ ነው። አንድም እንዳለ ባሕረ ሐሳብ ይለዋል፡፡ ባሕር አለው ባሕር እስኪለምዱት ያስፈራል። ከለመዱት በኋላ ግን ዘግጦ ጠልቆ ግጫውን ጭንጫውን ይዞ እስከመውጣት ይደረሳል፡። ይህም ባሕረ ሐሳብ እስኪለምዱት ያስፈራል፡፡ ከለመዱት በኋላ ግን በዓላትን አጽዋማትን አወጣጣቸውን ብቻ ሳይሆን ኢይዐአርግ ኢይወርዳቸውን ሠርቀ መዓልታቸው ሠርቀ ሌሊታቸውንም ያሳውቃልና።
ነገር ግን ከእርሱ በፊት አጽዋማት አይጾሙም፤ በዓላት አይውሉም ማለት አይደለም። ከእርሱ በፊት ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ሳሉ ከምእመናን ጋር ጾምን ይጾሙ፣ ትንሣኤንም ያከብሩ ነበር። ጌታ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት የጾመውን ሥጋ ቅቤ አንቅመስ እንጂ እየዋልን እህል ውኃ ብንቀምስ እዳ እንደማይሆን ትንሣኤንም በመጋቢት በ፳፱ (29) ያከብሩ የነበረውን ከእሑድ አይውጣ እንጂ በሚያዝያ ይሁን ተለይቶ የነበረ ሰሙነ ሕማማት በአንድ ላይ እንዲሆን ያደረጉ ሐዋርያት ናቸው።
አበዊነ ሐዋርያት አፍለስዎ ለጾመ አርብዓ ወአስተላጽቅዎ ምስለ ጾመ ሕማማት፤ አባቶቻችን ሐዋርያት ተለይቶ የነበረውን አርባ ጾም ከጾመ ሕማማት ጋር አንድ አድርገውታል” እንዳለ አቡሻክር። አቆጣጠሩን ግን ለስብከተ ወንጌል ይፋጠኑ ስለነበር አንድም ወደፊት ድሜጥሮስ እንደሚነሣ በመንፈስ ቅዱስ አውቀው ለይተው አላስተማሩም። ከሐዋርያትና ከ፸(70) አርድዕት በኋላ የተነሡ መምህራንም እንዲሁ ከዘመን ብዛት የተነሣ ዕለቱ ቢጠፋባቸው ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ሳኒታ ጥር ፲፩(11) ቀን ጀምረው በየካቲት ፳(20) ቀን ፈጽመው በዓልን ሳይሹ ያከብሩ ነበር። በዓላትን ሲሹ ደግሞ ሰሙነ ሕማማትን በመጋቢት ፳፪(22) ቀን ጀምረው በመጋቢት ፳፰(28) ቀን ፈጽመው በ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ትንሣኤን ያከብሩ ነበር። ከዚህም የተነሣ ዐቢይ ጾም ከእሑድ ውጭ በሌሎችም ቀን ሰኞም ማክሰኞም ይውል ነበር። በዚህ መንገድ ሲያያዝ መጥቶ ከቅዱስ ድሜጥሮስ ደርሷል። ይህም ድሜጥሮስ ከላይ እንዳልነው በሊቀ ጳጳስነቱ ዘመን ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፣ በዓለ ደብረ ዘይት፣ በዓለ ሆሳዕና፣ በዓለ ትንሣኤና በዓለ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፣ በዓለ ርክበ ካህናትና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፣ በዓለ ስቅለት ከዓርብ ባይወጡ፣ ባይነዋወጡ ይመኝ ነበር፡፡ እነዚህ በዓላት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን በእነዚህ ቀናት ውለዋልና፡፡
የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው ብሎ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረ (ምሳሌ ፲፩፥፳፫)፤ ይህም ቅዱስ ድሜጥሮስ ይህን በጎ ሐሳብ ሲመኝና ሲያስብ ለመንፈስ ቅዱስ የተመኙትን መግለጽ ልማድ ነውና የታዘዘ መልአክ ወደ እርሱ መጥቶ “ነገር በምኞት ይገኛልን? ሱባኤ ገብተህ አግኘው ብሎ ከሌሊቱ ፳፫ (23) ሱባኤ ከቀኑ ሰባት ሱባኤ ግባ” ብሎታል፤ ስለምን “ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ለምን አሳነሰው” ቢሉ ቀን የታመመ ሲጠይቅ፣ የታሰረ ሲጎበኝ፣ ወንጌል ሲያስተምር ስለሚውል ቀኑን አሳጥሮ ሌሊቱን አስረዝሞታል፡፡ አያይዞም “የሌሊቱንም የቀኑንም ሱባኤ በሰባት እያበዛህ ከ፴ (ሠላሳ) ከበለጠ በ፴ ግደፈው” ብሎታል። እንደሚታወቀው አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት ቀናት ናቸው፡፡ ሰባት ጊዜ ሃያ ሦስት መቶ ስድሳ አንድ ይሆናል፡፡ መቶ ስድሳ አንድን በሠላሳ ስንገድፈው/ስናካፍለው/ አምስት ዐውደ ወርኅ ሆኖ ዐሥራ አንድ ይቀራል፡፡ ይህ አበቅቴ ይሁንልህ ብሎታል።
የቀኑን ሰባት ሱባኤ በሰባት ስናባዛው ዐርባ ዘጠኝ ይሆናል፡፡ በሠላሳ ስንገድፈው /ስናካፍለው/ አንድ ጊዜ ደርሶ ዐሥራ ዘጠኝ ይተርፋል፤ ይህንን “መጥቅዕ” ይሁንልህ ብሎታል። በዚህ እየቀመረ በዓላትንና አጽዋማትን አውጥቷል።
የእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ የተገለጠለት ይህ ቅዱስ ሰው ድሜጥሮስ የስሙ ትርጓሜ “መስታወት” ማለት ነው። መስተወት የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ እንደሚያሳይ እርሱም በባሕረ ሐሳብ ድርሰቱ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ ያሳያልና ነው፡፡ አንድም “ፀሐይ” ማለት ነው፡፡ ፀሐይ ጨለማን አጥፍቶ ብርሃን እንደሚሰጥ እርሱም የደነቆረውን ጨለማውን አእምሮ በብርሃን እውቀት ያጠፋዋልና።
ትውልደ ነገዱ ከእስክንድርያ የሆነው ይህ ቅዱስ ሰው አባቱ ደማስቆ ወይም እንድራኒቆስ አጎቱ ደግሞ አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ ይባላሉ። ሁለቱም በረኃብ ምክንያት ወደ ሞአብ ሀገር ተሰደው ሲኖሩ የልዕልተ ወይን አባት አርማስቆ ሚጠት(መመለስ) ሳይደረግ ዕለተ ሞቱ በደረሰ ጊዜ የልጁን የልዕልተ ወይንን ነገር ከአሕዛብ እንዳያጋባት በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያሳድጋት አደራ ሰጥቶት ሞተ። ልዕልተ ወይንም አባቷ ከሞተ በኋላ ከአጎቷ ቤት ከድሜጥሮስ ጋራ በአንድ ላይ አፈር ፈጭተው ውኃ ተራጭተው ዘንባባ ቀጥፈው አደጉ። ሁለቱም ለአካለ መጠን በደረሱ ጊዜ የነበሩበት ቦታ አሕዛብ የበዙበት ምእመናን ያነሱበት ስለነበር ለማን እናጋባቸው ብለው ካወጡ ካወረዱ በኋላ ለአሕዛብ አጋብተናቸው ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ እርስ በእርሳቸው አጋብተናቸው ሕንጻ ሥጋ ቢፈርስ ይሻላል ብለው እርስ በእርሳቸው አጋብተዋቸዋል። ጻድቃን ሳይቀጣጠሩ ይገናኛሉ፤ እንደሚባለው ሁለቱም ፈቃዳቸው አልነበረምና ትዳሩን ካፈረሱ ለሌላ እንዳይድሯቸው አብረው ለመኖር ተስማምተው በአንድ አልጋ ተኝተው፣ አንድ መጋረጃ ጥለው፣ አንድ አንሶላ ለብሰው፣ ወንዶችና ሴቶች በሚተዋወቁበት ግብር ሳይተዋወቁ ፵፰/48/ ዓመት ኑረዋል።
በዚህ ግብርም ሲኖር የሕዝቡ ኃጢአት ተገልጾ እየታየው ሊቆርቡ ሲመጡ “አንተ በቅተሃል ቊረብ፤ አንተ አልበቃህም ቆይ” ባላቸው ጊዜ በዚህም “በንጹሑ በማርቆስ ወንበር ሚስቱን ይዞ እያደረ ሲሾም ዝም ብንለው ደግሞ እንዲህ ይለን ጀመር” ብለው አምተውታል፡፡
በዚህ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾ “ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእከ አላ ክሥት ሎሙ ክብረከ ዘሀሎ ማዕከሌከ ወማዕከለ ብሲትከ ከመ ኢይትሀጐሉ ሕዝብ በእንቲኣከ። ሕዝቡ አንተን እያሙ እንዳይጎዱ በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ግለጽላቸው” ብሎታል። እርሱም “የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነማ ብሎ ሕዝቡን እንጨት እንዲያመጡ አዘዛቸው። ያን አስደምሮ በእሳት አቃጥሎ ቅዳሴ ገባ፤ ቅዳሴውን ሲጨርስ ልብሰ ተክኖውን እንደለበሰ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በእሳቱ መካከል ያጥን ነበር። አንድም “ከደመራው ላይ ቁሞ በእሳት አቃጥሉት” አላቸው። “በምን ምክንያት እንሽረዋለን ስንል በፈቃዱ ገብቶ ሊሞትልን ነው” አሉት። እርሱ ግን ምንም ሳይሆነው በመካከሉ እየተመላለሰ ያጥንና ይጸልይ ጀመር። ሚስቱንም ከምቅዋመ አንስት ከመካነ ደናግል ነበረችና አስጠርቶ ስትመጣ “ስፍሒ አጽፈኪ፤ ልብስሽን ዘርጊ” ብሎ ከፍሕሙ በእጁ እያፈሰ ከአጽፋ ላይ አደረገላትና አስታቅፎ “እየዞርሽ ተናገሪ” አላት፡፡ እርሷም ሦስት ጊዜ እየዞረች ፵፰ /48/ ዓመት ሲኖሩ በልማደ መርዓት ወመርዒዊ እንደማይተዋወቁ ገለጸችላቸው። ሕዝቡም ከጫማው ሥር ወድቀው “ኅድግ ለነ አበሳነ፤ አባታችን በድለናል ይቅር በለን” አሉት። እርሱም “ይኅድግ ይፍታሕ፤ እግዚአብሔር ይፍታ” ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜም የተጀመረ በዚህ ጊዜ ነው።
የአባታችን ቅዱስ ድሜጥሮስ ጸሎት፣ ምልጃ እና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!