ቅዱሳት ሥዕላት

ክፍል አንድ
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥቅምት ፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ትምህርታችን የሆነውን በፈቃደ እግዚአብሔር ጀምረናል፤ ባሳለፍነው ዓመት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ስንማር ቆይተን ከዚያም ክለሳ አድርገን ጥያቄና መልስ ማዘጋጀታችን ይታወሳል፡፡ እናንተም ለቀረበላችሁ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ተሳትፋችኋል፤ ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ የማበረታቻ ስጦታንም አበርክተንላቸዋል፡፡ (ሰጥተናቸዋል)፤ እንግዲህ በዚህም ዓመት የምናቀርብላችሁን ትምህርት በደንብ ደግሞ መከታተል እንዳለባችሁ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

መርሳት የሌለባችሁ ሌላው ነገር በዘመናዊ ትምህርታችሁ ከአሁኑ ያልገባችሁን በመጠየቅ፣ የቤት ሥራን በመሥራት፣ በማጥናት ጎበዞችና አስተዋይ ልጆች መሆን እንዳለባችሁ ነው!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወላጆቻችን ከእኛ በጣም ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፤ ጥሩ ውጤት እንድናመጣ፣ ወደፊት ትልቅ ደረጃ እንድንደርስም ይመኛሉ፤ ስለዚህም እኛ ስንፍናን አርቀን፣ ጨዋታን ቀንሰን፣ በርትተን በመማርና በማጥናት ጎበዝ ልጆች መሆን ይገባናል! ወላጆቻችንን እኛን ለማስተማር ብዙ ነገርን ያደርጋሉ፤ ታዲያ እኛ ጎበዞች በመሆን ደስተኞች ልናደርጋቸው ይገባል፡፡ መልካም! በአዲሱ ዓመት በመጀመሪያው ትምህርታችን ስለ ቅዱሳት ሥዕላት እንማራለን፡፡

ወላጆች ከእኛ ጋር ትምህርት ቤት አይሄዱም፤ ከእኛ ክፍል ገብተው አብረውን አይማሩም፤ ግን ልጆቻችን ትምህርት ቤት ሄደው ተምረው ይመጣሉ ብለው አምነው ይልኩናል! አያችሁ እኛ ትምህርት ቤት ገብተን ተምረን በአግባቡ ወደ ቤት በመመለስ መታመናችንን መግለጥ (ማሳየት) ይገባናል፡፡

ቅዱሳት ሥዕላት

‹‹ሥዕል›› ማለት “መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ንድፍ፣ አምሳል፣ ንድፍ በውኃ፣ በመጽሔት፣ በጥልፍ፣ በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ፣ ከዕብን፣ ከዕፅ፣ ከማዕድን ታንጦ፣ ተቀርጦ፣ ተሸልሞ፣ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር” ነው፡፡›› (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት)
ቅዱሳት የሚለው ቃል ደግሞ «ቀደሰ» ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም “ለየ፣ አከበረ፣ መረጠ” ማለት ነው። ውድ

የእግዚአብሔር ልጆች ቅዱሳት ሥዕላት ለእግዚአብሔር የተለዩ፣ የተቀደሱ፣ ልዩ፣ ምርጥ፣ ንጹሕ እና ጽሩይ የሆኑ የቤተ መቅደሱ መገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በመሆናቸው «ቅዱሳት» ተብለው ይጠራሉ። እንዲሁም ደግሞ ቅዱሳት ሥዕላት የቅዱሳንን ታሪክ እና ማንነት በጊዜው ላልነበርን በመንፈስ ዓይን እንድናይ ስለሚያደርጉን፣ አንድም ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለማውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው፣ አንድም የቅዱሳን ቅድስና ሥዕላቱን ቅዱስ ስላሰኛቸው፣ አንድም በሥዕላቱ አድሮ እግዚአብሔር ስለሚፈጽመው ገቢረ ተአምራት የተነሣ ሥዕላቱ «ቅዱሳት ሥዕላት» ተብለው ይጠራሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት ተብለው የሚጠሩት ሐዋርያዊ ትውፊትንና ቀኖናን ጠብቀው የሚሣሉ የቅዱስ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ነቢያት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት እና የሌሎች ቅዱሳን ጻድቃን ማንነት፣ ሕይወትና ታሪክ የሚያሳዩ እና የሚወክሉ ሥዕሎች ናቸው፡፡

የቅዱሳንን ሥዕል መሳል ለምን አስፈለገ?

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን ሥዕላትን በመሳል ለአገልግሎት እንጠቀም ዘንድ ያዘዘን እራሱ የሰማይና ምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የቃል ኪዳኑን ማደሪያ ታቦት እንዴት እንደሚሠራ ሲነግረው እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ እንዳዘዘው እናነባለን፤ “ከሥርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ።” (ዘፀ.፳፭፥፲፱) ይህንንም ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሙሴ መፈጸሙን ሲገልጥልን “ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው። ክንፎቻቸውን ወደላይ የዘረጉ ሆኑ” በማለት መስክሮታል። (ዘፀ. ፴፯፥፰-፱)

የቅዱሳንን ሥዕል መሳል ያስፈለገው የቅዱሳን መታሰቢያ /ማዘከርያ ስለሆነ፦ እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱሳንን ስለ ቅድስናቸው እንዲሁም ስለ እርሱ ብለው ለፈፀሙት ተጋድሎ እንድናስባቸውና እንድንዘክራቸው ትእዛዝ እንዲህ ሲል አስተላልፎልና፤ “በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያ ስም እሰጣቸዋለሁ፣ የማይጠፋ የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡” (ኢሳ.፶፮፥፭)።

በሌላም በኩል (በመጽሐፈ ምሳሌ ፲፥፯) “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው።” (መዝሙረ ዳዊት ፻፲፪፥፮) “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል” ተብሎ እንደተመሠከረላቸው በረከታቸውን ለማግኘት ለመታሰቢያቸው መለያቸውን ቅዱሳት ሥዕላት እንጠቀማለን።

ሌላው ደግሞ ከእነርሱ በረከት አልፈን ቅዱሳት ሥዕላት በተሳሉበት በቅድስና ስፍራው እግዚአብሔር ራሱንም ስለምናገኝበት ነው፤ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ “በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል በሥርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ” ብሎታልና። (ዘፀ.፳፭፥፳፪)

ጠቢቡ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ባነፀ (በሠራ) ጊዜ ቅዱሳት ሥዕላትን ሠርቶ ነበር፤ “በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ፤ ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው፤ በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ፤ ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልንና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው” ተብሎ ተጽፏል። (፩ኛ ነገ ፮ ፥፳፫-፴፭)።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቅዱሳት ሥዕላትን ይሥሉ ነበር። ነባቢ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ የተመለከታትን የቃል ኪዳኑ ታቦት ነው፡፡ (ራእይ ፲፩፥፲፱)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ስለ ቅዱሳት ሥዕላት የቃሉን ፍቺ እና ቅዱሳት ሥዕላት ለምን እንደሚሳሉ በመጠኑ ተመልክተናል፤ በቀጣይ ስለ ቅዱሳት ሥዕላት ጥቅምና አሳሳል እንመለከታለን፡፡ (ምንጭ ኦርዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት አሳሳል)
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!