የእምነት አርበኛ

መስከረም ፳፰፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ጽኑ ሰማዕት የእምነት አርበኛ፣ ጠላትን ተዋጊና ድል አድራጊ እናታችን ቅድስት አርሴማ የሰማዕትነት አክሊል የተቀበለችበት የከበረች በዓል መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡

እጅግ መልከ መልካም የነበረችው ሮማዊቷ ዕንቁ ከልጅነቷ ጅምሮ ራሷን በድንግልና ሕይወት ጠብቃ የኖረች ቅድስት እንደነበረች ታሪክ ይነግረናል። በዘመኑ ነግሦ የነበረው ከሀዲው ድዮቅልጥያኖስም መልኳ ውብ የሆነች ድንግል ሊያገባ ፈልጎ ከየሀገራቱ ቆንጆ መርጠው ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም በፍለጋቸው በሮሜ አገር ባለች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት አርሴማን በማግኘት ሥዕሏን ሥለው ለንጉሡ ላኩለት፡፡ እርሱም በእጅጉ ተደስቶ እንዲያመጧት በማዘዝ ወደ ሰርጉም እንዲመጡ ለመኳንንቱ ላከ፡፡ እርሷና አብረዋት የነበሩትም ደናግል ይህነን በሰሙ ጊዜ በማዘን ድንግልናቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በመለመን ከሮም ተነሥተው በስውር የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደነበረችው ወደ አርመን ሸሽተው ሄዱ፡፡

ቅድስት አርሴማም ወደ አርመንያ ሀገር በገባች ጊዜ ከሃድያኑ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የሚያምኑትን ክርስቲያኖችን ላይ መከራን ሲያጸኑባቸው ተመለከተችና አምላካችን ክርስቶስ “እኔ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የማምን ክርስቲያን ነኝ” በማለት መሰከረች፡፡ የመልኳን ደም ግባትም በማየት ንጉሥ ድርጣድስም ለራሱ ስለተመኛት አምላክን እንድትክድ በብዙ ሽንገላን ሊሸነግሏት ቢሞክሩም አልሆነላቸውም፤ ፈርታ ትክዳለችም ብለው በማሰብ ክርስቲያኖች ለአናብስት ወደሚጣሉበት አደባባይ በመውሰድ የተራቡ አናብስትን በላያቸው ለቀቁባቸው፤ ቅድስት አርሴማ በዚህ ጊዜ ወደ አምላክ ጸሎት አደረገች፤ ድንቅ በሆነው ተአምሩም እግዚአብሔር አናብስቱ ወደ ቅድስቷ ሳይሆን  ወደ ንጉሡ ወታደሮች በመወርወር ብዙዎችን እንዲገድሉ አደረገ፤ በኋላም ተንበርክከው ሰገዱላት፡፡

ንጉሡም በሌላ መንገድ የቅድስት አርሴማን ሐሳብ ለማስቀየርና በግድ ለጣዖታቱ እንድትሰግድ ለማድረግ አሳስሮ አማልክቱ ወዳሉበት ቤተ ጣዖት ወሰዳት፤ ይህን ጊዜ በመስቀል ምልክት ብታማትብ በጣዖታቱ ላይ አድረው ሰዎችን የሚያስቱ አጋንንት እየጮኹ ሲወጡ ጣዖታቱ በመላ እየተሰባበሩ ወድቁ፤ ዳግመኛም እስር ቤት አስገብቶ ሊያስርባት ቢጥርም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ኅብስትን መገባት፡፡ ቀጥሎም ንጉሡ ወዳለበት እየጐተቱ ወስደው ሲያቆሟት ንጉሡ ይዞ ወደ እልፍኙ ሊያስገባት ከአደባባይ ተነሥቶ ድንግል አርሴማን በያዛት ጊዜ ቅድስቷ በላይዋ ላይ ባደረው የእግዚአብሔር ኀይል በምድር ላይ ጣለችው፤ ያን ጊዜ በንዴትና በአፍረት አገልጋዮቹን ራሳን እንዲቈርጡ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን አስከትሎ ተገለጸላት። ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ምሕረትን እንደሚያደርግ ቃል ኪዳንን ገባላት፡፡ በክርስቶስ ፍጹም ፍቅር፣ በእምነት ጽናትና ተጋድሎ ዕጹብ ድንቅ የሆነው ገድሏን ፈጽማ አንገቷን በመሰየፍ መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጅታለች።

የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፤ በጸሎቷ ይማረን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!