ግሸን ማርያም
መስከረም ፳፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
የግሸን ማርያም ደብር መመሥረት ከግማደ መስቀል ጋር የተያያዘ ዋነኛ ምክንያት አለው፡፡ ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ የገባው መስከረም ፲ ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያ ‹‹ግሸን አምባ›› የገባበት፣ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በጽሑፍ በመዘርዘር የገለጹበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡
በየዓመቱ መስከረም በባተ በ፳፩ኛው ቀንም በግሸን ደብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን ዐፅም በረከት ለማገኘት ከየክፍለ ሀገራቱ እየመጡ ያከብራሉ፡፡ ምእመናንም በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ‹‹ጤፉት›› በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን፤ አሜን!!!