መስቀል

መስከረም ፲፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ፍጹም ድንቅ የሆነው የጌታ ፍቅር የተገለጸበት፣ ሰላም የተበሠረበት፣ የነጻነታችን መገለጫ፣ የድኅነታችን መረጋገጫ ቅዱሱ መስቀል የተገኘበት ዕለት የከበረ ነውና በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም በበደሉ ምክንያት ዕዳውን ይከፍለለት ዘንድ ሰው ሆኖ በሞቱ ሕይወትን የሰጠን አምላክ በመስቀል ተሰቅሎ ስለሆነም የመስቀሉ ነገር ለክርስቲያኖች ብዙ ትርጒም አለው፡፡

ለሰው ዘር በሙሉ በተገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ጌታችን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡

በሐዲስ ኪዳን መስቀል የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ የተነሣበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር … እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ›› (መዝ. ፸፫፥፲፪) እንዳለው መድኃኒት የሆነው አምላካችን በመስቀሉ አዳነን፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፲፯፣ኤፌ. ፪፥፲፮፣ ቆላ. ፩፥፳)

ከበዓሉ በረከት ይክፈለን፤ አሜን!!!