የአበባ በዓል
መስከረም ፰፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
ምድር በአበባ በምታሸበርቅበት በክረምት መውጫ በተለየ መልኩ የሚከበረው ተቀጸል ጽጌ (የአበባ በዓል) መስከረም ፲ ቀን ነው፡፡ ተቀጸል ጽጌ ማለትም (አበባን ተቀዳጀ) የሚባለውን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብራለች፡፡
በአበባ በምትዋብበት ወቅት ምድር በአረንጓዴ ተክሎች በምትዋውበት፣ በዕፅዋቶች ልምላሜ በምትደምቅበት፣ በአዝእርቶች ቅጠል ልምላሜ በምትሸለመብበት ጊዜ በዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል በመስከረም ፲ በአረንጓዴ፣ በቢጫ እና በቀይ ቀለም ደምቆ የጽጌረዳ አበባ በመሰለ ፈርጥ የተሠራ ዘውድ ደፍተው በአደባባይ በሠራዊቶቻቸው ታጅበው የክረምቱን ማለፍ እያበሰሩ በክብር በሰዎች መካከል ይገኛሉ፡፡
በዚያን ጊዜም በወቅቱ የነበሩት ካህናት በዝማሬ ምእመናኑ በእልልታ የክረምቱን ማለፍ የዘመነ ጸደይን መተካት እያገለጹ እግዚአብሔር አምላክን ያመሰግናሉ፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ግብር ያበላሉ፡፡ ተቀጸል ጽጌ በዚህ መልኩ እየተከበረ አስከ ዐፄ ዳዊት ፲፫፻፺፭ ዓ.ም እንደደረሰ ታረክ ያወሳናል፡፡ ከዚህም በኋላ በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከሊፋ የሚባል የግብጽ ንጉሥ ተነሥቶ በግብጻውያን ክርስቲያኖች ላይ ጭቆና ሲያደርስባቸው ፓትርያርካቸውን ጭመር በማሰር በብዙ አሠቃያቸው፡፡
ንጉሡም ወደ ግብጽ ንጉሥ “እርዳን፤ እምነትህ እምነታችን ነው” የሚል መልእክት ላኩ፡፡ ከዚያም ሠራዊቱን አስከትሎ የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ሱዳን እና የግብጽ ድንበር ላይ ስናር በሚባለው ቦታ ሆኖ ለግብጹ መሪ “በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሰውን መከራ የማታቆም ከሆነ ዘምቼ እዋጋሃለው፤ አባይንም እገድባለሁ” በማለት መልእክት ይልክበታል፡፡ ከዚያም የግብጹ መሪ በክርስቲኖች ላይ የሚያደርሰውን ግፍና መከራ አቆመ፡፡
የግብጽ ክርስቲኖችም ነጻነታቸውን በማግኘታቸው ደስ ተሰኝተው ለኢትዮጵያው ንጉሥ እጅ መንሻ አድርገው ወርቅ፣ ብር እና አልማዝ ይልካሉ፤ ንጉሡ ዐጼ ዳዊት ግን “ይህ ምን ያደርግልኛል፤ ወርቅማ በሀገሬም ሞልቶኛል፤ የምፈልገው የክርስቶስን ግማደ መስቀል የቀኝ እጁ ያረፈበትን መስቀል ነው” በማለት ይመልሳል፡፡ ምንም እንኳን ለመስቀሉ ያላቸው ፍቅር ታላቅ ቢሆንም በእምነታቸው ተከብረው እንዲኖሩ ያደረጋቸው የንጉሡ የዐፄ ዳዊት እርዳታ ስለሆነና አሁንም ከንጉሡ ጋር ካልተባበሩ የግብጹ መሪ ሊያጠቃቸው ስለሚችል ዐጼ ዳዊትን ለማስደሰት የክርስቶስን ግማደ መስቀል ከልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ጋር ላኩላቸው፡፡ ሆኖም ንጉሡ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ሳያስገቡ ያርፏሉ፡፡
ለ፵፯ ዓመትም መስቀሉም በዚያው ቆይቶ ንጉሡ ልጅ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ በ፲፬፻፵፫ ዓ.ም መስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ለመስቀሉ ክብር እንዲሆን በማሰብም በመስከረም ፳፭ ቀን የሚከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓል መስከረም ፲ ቀን እንዲከበር ተወሰነ፡፡ በዚህም ሁኔታ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ “ተቀጸል ጽጌ፣ የዐፄ መስቀል፣ ሐፀጌ” በማለት እየተከበረ እስከ ፲፱፻፷፮ ቆይቶአል፡፡ በቤተ መንግሥት በመሪዎች ደረጃ ግን መከበሩ አልቀጠለም፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት የተወሰኑ አድባራት ካህናት አባቶች፣ መዘምራን በተገኙበት እስከ አሁን ድረስ ታከብራለች፡፡ በዓሉ መስከረም ፲ ቀን በየዓመቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬም ይከበራል፡፡
ከመስቀሉ በረከት ሁላችንንም ያሳትፈን፤ አሜን!