‹‹አትጨነቁ…›› (ማቴ.፮፥፴፬)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሐምሌ ፲፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ሰዎች  መልካምና ክፋ ነገርን ለማሳካት ይጨነቃሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አትጨነቁ›› ያለን ለክፋትና ለኃላፊው ዓለም ተጨንቀን መፍትሔ ለማናመጣለት ነገር ነው፡፡ (ማቴ.፮፥፴፬) ፈጣሪያችን ለእኛ ለልጆቹ በዚህ ምድር በእንግድነት ስንኖር ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል፤ የሚያሻንንም ይሰጠናል፤ እናስብ ዘንድ አስተዋይ አእምሮ ሰጥቶናል፤ ማሰብ ከሚገባን በላይ ደግሞ ልንጨነቅ ስለማይገባ ‹‹አትጨነቁ›› አለ፡፡ አበው በብሂላቸው ‹‹…አስብ እንጂ አትጨነቅ..›› የሚሉን ለዚህ ነው፡፡ በምድር ስንኖር በማሰብ በመጠንቀቅ፣ በመጠበቅ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ደግሞ ብልህ ሆነን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ልንፈራና ልንጨነቅ እንደማይገባ ግን ክርስትናችን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን ለአባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያት ስለሚቀበለው መከራ፣ ስለሞቱ ሲነግራቸው ባዘኑ ጊዜ ‹‹…ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ…›› በማለት በአንዳች ነገር እንዳይጨነቁ ልባቸው እንዳይታወክ ነገራቸው፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥፩)

በእርሱ ያመነ መጨነቅ እንደሌለበት ገለጠላቸው፤ በእግዚአብሔር የሚያምን፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የሆነ አይፈራም፤ አይጨነቅም፤ ምክንያቱም የሚገጥመውን የዓለም ውጣ ውረድ በድል መወጣት ይቻለዋልና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ            ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል ?…›› በማለት እንዳስተማረን እምነታችን በእግዚአብሔር ከጸና የሚያስፈራንና የሚያስጨንቀን ነገር አይኖርም፤ (ሮሜ ፰፥፴፩) በዓለማችን እኛ ባልነበርንበት ዘመን ሰዎችን ለጭንቀት የሚዳርጉ፣ የመኖርን ተስፋ የሚያጨልሙ ብዙ ክስተቶች ተከስተዋል፡፡ እግዚአብሔርን ያመኑ እንደ ሐሳቡም ለተጠሩ ግን ሁሉ ለበጎ ሆኖ አልፈውታል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይለናል፤  ‹‹…አምላካችን መጠጊያችን ኃይላችን ባገኘንም በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው፤ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም..›› (መዝ.፵፭(፵፮)፩-፪) ያለንባት ዓለም በስደት የመጣንባት ምድረ ፋይድ (የግዞት ቦታ) የእንግድነት መኖሪያችን ናት፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ‹‹..በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?..›› እንዳለው እንግዲህ ብርቱውን ሰልፍ በድል ተወጥተን ከሞት በኋላ ላለው ሕይወታችን መልካም እንሠራ ዘንድ ልናስብ እንጂ ልንጨነቅ፣ ልንጠነቀቅ እንጂ ልንፈራ አይገባም፡፡ (ኢዮ.፯፥፩) ምክንያቱም ‹‹ኃይልን በሚሰጠን በክርስቶስ ሁሉን እችላለው…››  እንዲል፡፡ (ፊሊ.፬፥፲፫) ቅዱስ ጳውሎስ በዓለም ስንኖር መከራ እንዳለብን የመከራውም ዓይነት ልዩ ልዩ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ከዚህ መከራ እንዴት መጠንቀቅና መጠበቅ እንዳለብን ልናስተውል ይገባል፤ በፍርሃትና በጭንቀት ግን እምነታችን ሊላላ፣ ልባችን ሊታወክ፣ አቅላችንን ልንስት ግን አይገባም፡፡

“መጠበቅ አለብን” ስንል ክፉ መሆኑን ከተረዳነው ነገር ሁሉ እንዳይጎዳን መጣር ይገባል ማለታችን ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይመክረናል፤ ‹‹…እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ…፡፡›› (ኤፌ. ፭፥፲፭)  በነጻነት እንደ ትናንቱ ከቤተ እግዚአብሔር ተገኝተን አምልኮተ እግዚአብሔርን እንዳንፈጽም ፈተና የሆነን፣ የመዋደዳችን የአብሮነታችን መገለጫ ከሆኑ አብሮ  በፍቅር በጋራ ሆኖ  ከመመገብ፣ ተቀራርቦ ደስታን ከመግለጥ፣ ከመጋራት፣ ኀዘንተኛን ከማጽናናት ያለንን በጋራ ከመቋደስ የሚቃረነን ያለመተማመን፣ የጎጠኝነት ክፉ ደዌ  ገጥሞናልና ይህን በጥበብና በማስተዋል ልናልፈው ይገባል፡፡ የማያልፍ ጊዜ፣ የማይነጋ ሌሊት፣ የማይታበስ እንባ የለምና፤ … ከዚህ መጠበቅ አለብን፤ “መጠንቀቅ” ስንል ደግሞ ካላወቅነው ነገር ግን ሊሆን ይችላል ተብሎ ከሚገመት ነገር ሁሉ ራስን ለማዳን መታገል፡፡

ውድ ክርስቲያኖች! በዘመናችን በገጠመን የራስ ወዳድነት፣ ያለማስተዋል፣ የጥርጥር፣ የጎጠኝነት፣ የመለያየት ክፉ ደዌ ተይዘናል፡፡ ይህንን ክፉ ደዌ ከእኛ እንዲወገድ የፍቅርን፣ የመተሳሰብን፣ የቅንነትን፣ የማስተዋልን መድኃኒት ለራሳችን እናብጅ፤ ሳንጨነቅ፣ ሳንፈራ እንዴት በጥበብና በማስተዋል ከሰዎች ጋር መኖር እንደሚገባን እናስተውል፤ በእርሱ እሳከመንን ድረስ የምናምነው አምላካችን ‹‹…ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም…››  ብሎናልና አይተወንም፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፲፰) ከእኛ የሚጠበቅብንን፣ እንደቃሉ መኖር በትእዛዙ መጓዝ ነው፤ ትእዛዙ ደግሞ ቀላል ነው፤ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹….እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እርስ በእርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ፡፡›› (ዮሐ.፲፫፥፴፬) ከኃጢአት ደዌ ተላቆ ከጭንቀት ሕይወት ለመውጣት እርስ በእርስ በመዋደድ ትእዛዙን መፈጸም አለብን፡፡

ሕጉን ከፈጸምን እንደፈቃዱ ከኖርን፣ በጽድቅ ሥራ ከተመላለስን ከሚገጥመን ፈተና፣ ሰቆቃ፣ በጨለማ የብርሃን ዓምድ  አቁሞ፣ በቀን ከሚያሳድደን ከጠላታችን እይታ ደመናን ጋርዶ፣ በድንቅ ጥበቡ ባሕሩን የብስ፣ በረሃውን ለምለም፣ አቀበቱን መስክ አድርጎ ከምንመኘው፣ ከምንሻው ያደርሰን ዘንድ ይቻለዋል፡፡ ግን እኛ ይህ ሁሉ እንዲሆን እንደአቅማችን ለሕጉ እንገዛ፣ እንደፈቃዱ እንጓዝ፤ እንጸልይ እንጹም፤ ከትእዛዙ የወጡ እና እንደፈቃዱ ያልተመሩትን እንዲህ በሏቸዋልና፤ ‹‹..የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቴንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ፣ ባታደርግም እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል፤ ….በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ….፡፡›› (ዘዳ. ፳፰፥፲፭- ፴)፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር  ሕጉን ፣ጠብቀን ሥርዓቱን አክብረን ከጭንቀት ተላቀን እንኖር ዘንድ ይርዳን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!