“እግዚአብሔርን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ” (መዝ.፺፯፥፲)
ሐምሌ ፰፤ ፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በባሕርይው ፍጹም፣ ቅዱስ፣ ንጹሕ የሆነና ምንም ዓይነት ርኩሰት የማይስማማው አምላካችን እግዚአብሔር መልካም አባት ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የነበረ፣ አሁን ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር በመሆኑም ለዘለዓለም በቅድስና ይኖራል፡፡ ፍጥረቱን በሙሉም በቸርነቱ ከመፍጠሩ በፊት ሲቀደስ ሲለስ ይኖር የነበረ፣ አሁንም በፍጥረቱ እንዲመሰገን፣ እንዲቀደስ፣ እንዲወደስ የፈቀደ፣ ወደፊት ደግሞ በክብር ምስጋና በመንግሥቱ ሊገዛ የሚወድ ፈጣሪያችን ክብሩንና ቅድስናውንም ለፍጥረቱ በተለይም ለቅዱሳን መላእክት እና ሰው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ሁሉም በቸርነቱ፣ በመልካምነቱ፣ በበጎነቱ፣ ስለ ቅዱስ ፈቃዱ አድርጓል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ በሰማይም ይሁን በምድር ላይ ሊያኖር የፈቀደው በበጎነት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ እርሱ መልካም አባት ነውና እኛ መልካም፣ የዋህ፣ ቸርና በጎ ልጆቹ እንድሆን “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ (ማቴ. ፲፩፥፳፱) ቅዱስ ነውና በቅድስና እንድንኖር ይወዳል፤ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” እንዲል፡፡ (ዘሌ.፲፩፥፵፭)
በዘመናት ሂደት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግን ይህን የአምላክ ፈቃድ ለመፈጸም በጎ ፈቃድ የነበራቸውና በመልካምነት የኖሩ፣ ትእዛዙንና ሕጉን ጠብቀውም ለቅድስና የበቁ ጥቂት እንደሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ አምላክን በድለናል፡፡ ለዚህም መነሻ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው በጎ ከማሰብና መልካም ከማድረግ ይልቅ በክፋትና በተንኮል ለመኖር መሻትና ማሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ክፉ ሐሳብ መጥፎ ነገር ለማድረግ ከመነሣሣት አልፎ ወደ ጥፋትም ጎዳና እንደሚመራ እንደታወቀ ሁሉ ከአምላካችን ፍቅር፣ ቸርነት፣ ረድኤትና ጠበቆት መራቅም ዋነኛው የክፋት መንሥኤ ነው፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔርን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከኃጥአንም እጅ ያድናቸዋል” በማለት የተናገረው ቃል ለዚህ ምስክር ነው፡፡ (መዝ.፺፯፥፲) ለአምላካችን ፍጹም ፍቅር ሲኖረን ምንም ያህል መከራ ቢጸናብን፣ ፍቅሩ ትዕግሥት ሆኖን ችግራችን እንድንወጣ፣ ጽናትና ጥናካሬ ሆኖ ሥቃዩን እንድንችል ያደርገናልና ክፋትን ፈጽሞ አንፈጽምም፤ በጎነትን እንወዳለን እንጂ ክፋትን አይደለም፡፡ ለፈጣሪያችን መልካምነት በሚኖረን ቅንዓትም ክፋትን እንጠላለን፡፡
የኢትዮጵያዊው አባት የአባ ሙሴ ጸሊምን ታሪክ እዚህ ላይ መንሣት ተገቢ ነው፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሣ የሚያደንቁት ኢትዮጵያዊው ቅዱስ አባት አባ ሙሴ ጸሊም አስቀድሞ ለሥጋው የሚኖር ወንበዴና አመንዛሪ እንዲሁም ቀማኛ ነበር፡፡ እንዲያውም የሥጋውን መሻት ለመፈጸም ሰዎችን እስከ መግደል የሚደርስ ጨካኝ ሰው እንደነበር ገድሉ ይናገራል፡፡ መብልንና መጠጥንም ከልክ ባለፈ መልኩ ይመገባል። መጽሐፈ ስንክሳር ላይ እንደተመዘገበው በአንድ ጊዜ አንድ ሙሉ በግ እና አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ እንደሚጨርስ ራሱ ይናገር ነበር፡፡
በሥራውም እግዚአብሔር አምላኩን ይበድል ነበር፡፡ ፀሐይን የሚያመልኩ ሰዎችን ያገለግል ስለነበር ፈጣሪውን አያውቀውም፡፡ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ›› በማለት ይጠይቃል፡፡ በልቡም ‹‹የማላውቅህ ሆይ፥ ራስህን አሳውቀኝ›› ይል ነበር፡፡
በአንድ ወቅትም ሰዎች ‹‹በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታልም›› ብሎ ሲነጋገሩ ሰማቸው፡፡ ሙሴ ጸሊምም ወደ ገዳሙ ለመሄድ በማሰብ ሰይፉን ታጠቀ፤ ተጉዞም በዚያ እንደደረሰ አባ ኤስድሮስን አገኘው። የመልኩን መጥቆርና ደፋርነቱን አይቶም አባ ኤስድሮስ ፈራው፡፡ ሙሴ ጸሊምም ‹‹እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ›› አለው፡፡ ይህንንም በሰማ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ወደ አባ መቃርስ ወሰደው፡፡
በተገናኙም ጊዜ የአምላክን መኖር ማወቅ እንደሚሻ ስለነገረው አባ መቃርስ ሃይማኖትን አስተማረው፡፡ ‹‹ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ›› በማለትም አስረዳው፤ የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆ አመነኰሰው፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ተባለ። ከዚህም በኋላ በጽኑ ገድልም ከሌሎች ቅዱሳን ይልቅ የበለጠ አብዝቶ መጋደል ጀመረ፡፡ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስም ሊያስተው በመጣር ቀድሞ ሲሠራው በነበረው ኃጢአት በዝሙት፣ በመብሉና በመጠጡ ይፈታተነው ነበር፡፡ እርሱም በእነዚህ የኃጢአት ፍትወት እንደሚፈተን ለአባ ኤስድሮስ ይነግረዋል፡፡ እርሱም አጽናንቶ ሊሠራ የሚገባውን ያስተምረዋል፡፡
በገድልም ተጠምዶ በኖረበት ረጅም ዘመናት አረጋውያን መነኰሳት ውኃ የሚቀዱበት ቦታ ከእነርሱ በዓት ሩቅ ስለነበረ በሚተኙበት ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ ሞልቶ በየደጃፎቻቸው ያኖር ነበር፡፡ በዚህም ሥራው ሰይጣን ቀናበት፤ በእግሩ ውስጥም አስጨናቂ ሕመምን አመጣበት፤ በደዌም ተይዞ እየተጨነቀ ለብዙ ቀናት ታመመ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም በዚህ ክፉ ደዌ የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህም ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቅ እንጨት እስኪሆን ድረስ ተጋድሎን አበዛ፡፡ በዚህም ትዕግሥቱን ተመልክቶ እግዚአብሔር ከደዌው ፈወሰው፤ የሰይጣንንም ጦር ከእርሱ አራቀለት፤ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት፤ በአስቄጥስ ገዳም የነበሩት ፭፻ (አምስት መቶ) መነኰሳት ወንድሞቹ ከተሰበሰቡ በኋላ አባ ምኔት ሆኖ ተሾመ፡፡
መነኰሳቱም ቅስና ሊሾሙት መርጠው በቤተ መቅደስ በሊቀ ጳጳሳቱ ፊት አቆሙት፤ እርሱ ግን አልፈቀደም፤ ‹‹ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት›› በማለትም አረጋውያኑን ተናገራቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ሙሴ ጸሊም በልቡ ራሱን ‹‹መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ፥ መልካም አደረጉብህ›› በማለት ገሠጸ፤ ከቤተ መቅደሱም ወጥቶ ሄደ፡፡ ሆኖም ግን ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሱ ጠርቶ ቅስና ሾመው፤ እንዲህም አለው፤ ‹‹ሙሴ ሆይ፥ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ፡፡››
ከዕለታት በአንድ ቀንም አረጋውያን መነኰሳቱ ወደ እርሱ መጡ፤ ሆኖም ግን ለእነርሱ የሚያጠጣቸው ውኃ አልነበረውም፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ከበዓቱ መግባትና መውጣት አበዛ፤ ብዙም ሳይቆይ ዝናም ዘንሞ ጒድጓዶችን ሁሉ ሞላው፡፡ መነኰሳቱም አብዝቶ መውጣቱን ተመልክተው ‹‹ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ አልክ?›› በማለት ጠየቁት፤ እርሱም ‹‹እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር፤ በቸርነቱም ዝናም ልኮልን ውኃን አገኘን›› ብሎ መለሰላቸው፡፡
በሌላ ወቅትም አባ ሙሴ ጸሊም ከአረጋውያን መነኰሳቱ ጋር በመሆን ወደ አባ መቃርስ ዘንድ ሄደው ጠየቁት፤ እርሱም ‹‹የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ‹‹አባት ሆይ፥ ምናልባት እኔ እሆናለሁ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ›› የሚል ጽሑፍ አለና ብሎ መለሰ፡፡ (ማቴ.፳፮፥፶፪) በዚህም ጊዜ የበርበር ሰዎች ሲመጡ ተመልክቶ መነኰሳቱን ‹‹እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ፤መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ›› በማለት አስታወቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን አንተስ አትሸሽምን?›› ብለው ጠየቁት፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ከመቅጽበትም ደርሰው የበርበር ሰዎች በሰይፍ ገደሉት፤ ከእርሱ ጋር የነበሩትም ሰባት መነኰሳት መሸሽን አልመረጡምና አብረው ተገደሉ፤ አንዱ ግን ከምንጣፍ ስር ተደበቀ፤ በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእጁ አክሊል ይዞ ቆሞ ሲጠብቅ ሲመለከት ከተደበቀበት ወጥቶ ቆመ፤ የበርበር ሰዎችም ገደሉት፤ የሰማዕትነትንም አክሊል ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቀበለ፡፡ የአባ ሙሴ ጸሊም ሥጋም ደርምስ በተባለ ቦታ በአስቄጥስ ገዳም ውስጥ እንደሚገኝ ገድሉ ይጠቅሳል፡፡ ከዐፅሙም ድንቅ ተአምራት ይደረጋል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ሰኔ ፳፬)
ከወንበዴነት ወደ ቅዱስ አባትነት ከፍታ የደረሰው አባታችን አባ ሙሴ ጸሊም የፈጠረውን አምላክ ሽቶ፣ በፍቅር ለእርሱ መገዛትን ስለፈቀደ ነው፡፡ አስቀድሞ ክፋት አብዝቶ በመውደድ የተነሣ የፈጸመውን ድርጊት ለመስማት እንኳን እጅግ ቢከብድም፣ በንስሐ በመመለስ፣ ቅድስና ያለውን ሕይወት ለመኖር ከዚያም አልፎ የሰማዕትነት አክሊል ለመቀዳጀት ለመቻሉ ምስክሮች ልንሆን ይገባል፡፡
ዛሬ ግን ከመልካምነት ይልቅ ክፋት እንደ ትክክለኛነት፣ ጥሩ ከማድረግ የበለጠ መጥፎ መሆን እንደተፈቀደ ነገር ተደርጎ መቆጠር ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ እውነት የሆነው አምላክ ተክዶ የሐሰት አባት ምድር ላይ በመንገሡ ዓለም ጥላቻና ማስመሰል ወደ በዛበት የሐሰት መንደር ተለውጧልና ይታክታል፡፡ በዚህም አዘቅት ወስጥ መሆኑን መረዳትና ማዘን ያስፈልጋል፡፡
በዙሪያችን የከበቡን አስመሳዮች ክፋት በወለደው ስሜት ለጥፋት ሲዳረጉ፣ ማንነታቸው ተቀይሮ እንደ እንስሳ ሆነው ማየት በእውን ነው ወይስ በሕልም ያስብላል፡፡ “ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?” ብለን በአእምሮአችን ማሰላሰል ይገባል፤ “እኛስ አምላክን እንዲህ አስከፍተነው ይሆን?” ብለን ራሳችንን መጠየቅም አለበን፡፡ ጥፋትን እንደ ጀብድ ክፋትንም እንደ ቀልድ ከሚያዩ ሰዎች መካከል መኖር ምንኛ ያስከፋል! “ግፍና በደል የሚፈጽሙ ሰዎች ባደረጉት ጥፋት የተነሣ ይህ ሁሉ እልቂት የደረሰው በእርሱ ቁጣ ይሆን?” በማለትም ደጋግመን መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕጉን በመተላለፍ አምላካችንን መበደል መቅሠፍት እንደሚያመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ መመዝገቡንም አንርሳ! (ዘጸ.፲፩፥፩፣ ዘሌ.፳፮፥፳፩፣ ዘኅልቁ.፲፩፥፴፫፣፲፬፥፴፯፣፳፭፥፱)
ሰው ለሰው ፍቅር አጥቶ፣ በጥላቻ መንፈስ ሲሰዳደብ፣ ሲነቃቆር፣ ሲገዳደል፣ ፈጣሪን ረስተውና ሰውነታቸውን አርክሰው በርኩስ መንፈስ እንደ እንስሳ የሚነዱ ሰዎች በዚህ ጊዜ የበዙበት ምክንያት ክፋትን በመውደዳቸው እንደሆነ የማይካድ እውነት ነው፡፡
ሰዎች አብሮ ለመኖር የሚያስችላቸው ምድራዊ ዕውቀቸው፣ የገንዝብ አቅማቸው አልያም በጊዜ ሂደት ያካበቱት የማኅበረሰባዊ ትስስር ወይም ግንኙነት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ከምንም በላይ በሰዎች መካከል ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘንና የአብሮነት ስሜት ከሌለ ምድር በጭከና በተገዳደሉ ፍጥረት ደም የተጨማለቀች ከመሆን ባሻገር ወደ ምድረ በዳነት እንደምትቀየር አያጠራጥርም፡፡ ለዚህም ተጠያቂዎች እኛና እኛ ብቻ ነን! ለአምላኩም ሆነ ለባልንጀራው ፍቅር የሌለው ሰው በክፋቱና በመጥፎነቱ የተነሣ ለማኅበረሰባዊም፣ ለሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥፋት ተጠያቂ ነው፡፡ ምንም ዓይነት መልካምነትም ስለማይኖረው የርኩስ መንፈስ ማደሪያ ይሆናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ልጆቿን እንድታጣ እንዲሁም ለተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ተጋላጭ እንድትሆን የሚያደርጋት ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ፍቅር እጅጉን ኃይልን ያደርጋልና “አምላክህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደድ” ተብለናል፡፡ (ዘዳ.፮፥፭) በእግዚአብሔር ፍቅር እንድንኖር የተፈለገው በክፋት ከእርሱ ርቀን እንዳንጠፋ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የምድራዊ ሕይወትን በእርሱ የፍቅር ኃይል እንድናሸንፍ ነው፡፡
ስለዚህም በአርአያውና በአምሳሉ አክብሮና ቀድሶ ለፈጠረን፣ በቸርነቱ ለሚያኖረን፣ ከሰው ልጅ (አዳም) መበደል በኋላ ክብሩን ዝቅ አድርጎ፣ ሥጋን ተዋሕዶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ እንደ ሰው በእግር ተመላልሶ፣ በደል ሳይኖርበት ተወንጅሎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተነሥቶ ሕይወትን የሰጠን አምላካችንን ፈጽመን ልንወደው የተገባን ነን፡፡ እርሱ በፈቀደው መልካምነት መኖርም ያስፈልገናል እንጂ ክፋት በበዛበት በጠማማው መንገድ አንጓዝ፡፡
አምላካችንን በመውደድ ክፋትን እንጥላ!
ስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!