ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፳፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የባለፈው የትምህርት ቆይታችሁ ውጤታችሁ እንዴት ነው? መቼም ጠንክራችሁ ስትማሩ ስለነበር በጥሩ ውጤት እንዳለፋችሁ ተስፋ እናደርጋለን! ወርኃ ክረምቱንስ እንዴት ተቀበላችሁት? እንዴትስ ልታሳልፉት አቀዳችሁ! ይህንን ከወዲሁ ማሰብ አለባችሁ! የዕረፍት ጊዜ ነው ብላችሁ በጨዋታ ማሳለፍ የለባችሁም፡፡ በአቅራቢያችሁ ባለው ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በሰ/ት/ቤት በመግባት በአብነት ትምህርቱንና የሥነ ምግባር ትምህርትን መማር አለባችሁ፤ ውድ ልጆች! ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን ጥሩ ውጤት ያላመጣን ካለን በሚቀጥለው በርትቶ መማርና፣ ለማጥናት በመጪው ክረምት ወቅት ማጥናት ያስፈልጋል፡፡
ውድ ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀልናችሁ ባለፉት ጊዜያት ስንማራቸው የነበሩትን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራትን ክለሳ ነው፤ አሁን የተወሰነውን በቀጣይ ደግሞ ቀሪውን እንማራለን! ታዲያ ጥያቄና መልስ ለመለሱ ተማሪዎች እንደተለመደው ሽልማት ስለምናዘጋጅ በደንብ አንብቡና ተዘጋጁ፤ መልካም!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መልካም ምግባርን እንድንፈጽም ያዘዘን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ በክርስትና ሃይማኖት ስንኖር መፈጸም ያሉብን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት አሉ፤ ያንን ከፈጸምን አምላካችን ይባርከናል፡፡ በምድር ላይ ስንኖር የምንሠራው ይቀናል፤ ትምህርታችንን ይገለጥልንና ወደፊት መሆን የምንፈልገውን በጎ ሰው እንሆናለን፡፡
ሌላው ደግሞ በመንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በደስታ፣ በክብር እንኖራለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት የሚባሉትን ባለፉት ጊዜያት ስንማራቸው ነበር፡፡ ለማስታወስ ያህል ቅዱስ ጳውሎስ ገላትያ በሚባል ከተማ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ እንደዚህ ገልጧቸዋል፤ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው…፡፡›› (ገላ.፭፥፳፪) ውድ ልጆች! እነዚህን እያንዳንዳቸውን ባለፉት ጊዜያት ስንማራቸው ነበር፤ አሁን ደግሞ የተወሰኑትን እንድታስታውሱና በሥራ ላይ እንድታውሏቸው እንከልስላችኋለን! መልካም!
ፍቅር
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ፍቅር የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ነው፤ ፍቅር ማለት ደሀ ሀብታም፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ ሳይሉ ሁሉን እኩል መውደድ ነው፤ ፍጹም ፍቅር ያለው ጻድቅ ነው ብሎ አይወድም፤ ኃጥእ ነው ብሎ አይጠላም፤ እኩል ይወዳል፤ ልጆች! ሰው ወንድሙን ከወደደው ክፉ አያደርግበትም፤ በድክመቱ በውድቀቱ አይሳለቅም፤ ገበናውን ይሸፍናል፤ ሲያጠፋ ቢያየው እንኳ ይመክረዋል፤ ገበናውን ይሸፍንለታል፤ አሳልፎ አይሰጠውም፡፡ ለራሱ ብቻ ጥፋቱን ይነግረዋል፡፡
ፍቅር ያለው ሰው ቢበደል ይቅርታን ያደርጋል፤ ከክፉ ነገር የሚጠብቀውን የእግዚአብሔርን ምሕረት ጥበቃ ያስተውላል፤ ክፉ ላደረገበት ሰው ክፉን ከመመለስ ይልቅ ለይቅርታ ልቡን ይከፍታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹…ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ…›› በማለት እንድንዋደድ ይመክረናል፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፰) እስኪ ፍቅርን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ታሪክ እንመልከት፡፡
ፍልስጤማውያንና እስራኤላውያን ለጦርነት ተፋጠው በነበረበት ጊዜ ንጉሥ ዳዊት በፍልስጤማውያን እጅ ወድቃ ከነበረችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ መጠጣት አማረው፤ ይህም ታሞ ስለነበረ ነው፡፡ የታመመ ሰው ያደገበት አካባቢ ትዝ ይለዋልና ካደገበት ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ መጠጣት ፈለገ፤ አንድም መድኃኒት ያላት ስለነበረ ነው፡፡ / ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ/ሲል ተመኘ፡፡
በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች አዲኖን፣ ኢያቡስቴ እና ኤልያና ለዳዊት ካላቸው ፍቅር የተነሣ የማን ጌታ ውኃ፣ ውኃ እያለ ይሞታል ብለው ብቻቸውን ወደ ጠላቶቻቸው ጦር ሄዱ፡ ፍልስጤማውያንም የውጭ በር ከፈቱላቸውና ጦሩን ሰንጥቀው አልፈው ውኃውን ቀድተው ለንጉሣቸው አመጡለት፡፡ ንጉሥ ዳዊትም የኅሊናቸውን ቆራጥነት አደነቀ ለሱ ፍቅር ብለው ደማቸውን ለማፍሰስ መድፈራቸውን ተገነዘበ፤ የወንድሞቼን ደም እንደመጠጣት ነው ብሎ በዚህ ጊዜ ያመጡለትን ውኃ አልጠጣም አለ፡፡ ውኃውንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ብሎ አፈሰሰ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የንጉሥ ዳዊትና የጦር አለቆቹ ፍቅር ለእኛ ምሳሌ የሚሆን ነው፤ (፪ኛ ሳሙ.፳፫፥፲፬-፲፯) ለሰዎች መልካም በማድረግ ፍቅርን ስናሳየቸው እነርሱም ለእኛ መልካምን ነገር ያደርጋሉ፤ ያስባሉ፡፡
እምነት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሃይማኖት ማለት “ተአምነ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን “በሌሎች የታመነ ሆነ፣ ተወከለ፣ የማይጠረጠር፣ ሰው ሐሳቡን የጣለበት” ማለት ነው ፡፡ ‹‹ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ…›› እንዲል፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፪፥፪)
በሰዎች ዘንድ መታመን መታደል ነው፤ እምነትን ጠብቆ መገኘት ደግሞ ታላቅነት ነው፡፡ መታመን የተሰጠን አደራ ጠብቆ መገኘት ለክብር ያበቃል፤ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ መወደድን መከበርን ያተርፋል፤ ለሰዎች ስንታመን እነርሱ ባያዩንም በሁሉ ቦታ ያለ፣ቦ ታ የማይገድበው፣ በእርሱ ዘንድ ጨለማ የሌለበት እግዚአብሔር ያየናል፡፡ መታመናችን ሰው አየን አላየን ብለን ሳይሆን ለታመንንለት ነገር በፈቃዳችን ስንገዛ፣ ስናከብር በምትኩ ለታላቅ ኃላፊነት እግዚአብሔር ይሾመናል (ይመርጠናል)፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሰዎች ዘንድ እምነት ተጥሎባቸው (አመኔታ ተሰጥቷቸው) ታምነው የተገኙና ለክብር የበቁ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የዮሴፍን ታሪክ እንመልከት፡፡
ዮሴፍ ከያዕቆብ ፲፪ ልጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ (ዘፍ.፴¸፳-፳፬) ከጠባዩ መልካምነትና ከፈጸመው ታላቅ ሥራ የተነሣ ከሁሉም ልጆች የከበረ በመሆኑ በአባቱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፡፡ አንድ ቀን ወንድሞቹ ከብቶችን አሠማርተው (ውኃ እንዲጠጡ፣ ሣረ እንደዲነጩ ወደ ሜዳ) ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ አባታቸው ያእቆብም ስንቅ አሠረላቸውና ዮሴፍን አድርስ አለው፡፡ የእርሱንም ለብቻ አሠረለት፤ ወንድሞቹ ያሉበትን ሲፈልግ ቦታው ሩቅ ነበርና ለእርሱ የታሠረለት ስንቅ አለቀበት፡፡ ((ዘፍ.፴፯፥፪-፳፰) በዚያ ላይ ደግሞ ደከመው ራበውም፤ እንዳይበላ ለወንድሞቹ አድርስ የተባለው ነው፡፡ የሚበላ ይዞ ተርቦ ደክሞት ተኛ፤ ለአባቱ ታመነ ለወንድሞችህ አድርስ ነውና የተባለው ቢርበውም አልበላባቸውም፡፡ ለምን ቢባል የእርሱ አይደለምና፤ በመታመኑ (ታማኝ) በመሆኑ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና የሚበላውን ሰጠው (በተአምራት ድንጋዩን ዳቦ አደረገለት)፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ስለ ፍቅርና ታማኝነት ለማስታወስ በጥቂቱ ከልሰናል፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ የተቀሩትን ይዘን እንመጣለን፡፡ በምንማረው ትምህርት እኛም መልካም ሰዎች መሆን አለብን፤ ሰዎችን መውደድ፣ ታማኞች የሰውን ነገር (ዕቃ) የማንነካ የእኛ ያልሆነውን የማንወስድ ታማኞች መሆን አለብን፡፡
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!