ተስፋ መንግሥተ ሰማያት!
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፲፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በዓለ ኀምሳን እንዴት አያሳለፋችሁ ነው? በዓለ ዕርገትም እየደረሰ ነውና በዓሉን ለማክበር መዘጋጀት ያስፈልጋል! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት በተለያየ ጊዜ ለቅዱሳን ሐዋርያት እየተገለጠላቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያስተምራቸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስናገለግል በሥርዓት ነው፡፡ በትምህርታችንም መበርታት እንዳለብን እንረዳለን፡፡ የፈተና ወቅት እየደረሰ በመሆኑ ከዚያ በፊት በርትተን በማጥናት ዕውቀት አግኝተን ከክፍል ወደ ቀጣይ ክፍል በጥሩ ውጤት መሸጋገር ይገባናል፤ መልካም ልጆች! ለዛሬ ስለ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት እንማራለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታስታውሳላችሁ አይደል ከዚህ በፊት “ተስፋ” በሚል ርእስ ተምረን ነበር፤ ተስፋ ማለት “ከጨለማው ባሻገር ብርሃን፣ ከአቀበቱ ጀርባ ለምለም ሜዳ፣ ከኀዘን ባሻገር ደስታ፣ ከወጀብና ከአውሎ ነፋስ በኋላ ጸጥታ መረጋጋት፣ ከትንሣኤ በኋላ ሕይወት እንዳለ” ማመን ነው፡፡ ተስፋ የእምነታችን ምንጭ ነው፤ በክርስትና ሕይወት ስንኖር ተስፋ የምናደርገው ታላቅ ነገር አለ፤ እርሱም መንግሥተ ሰማያትን ነው፤ ዛሬ የምንነግራችሁም ስለ መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዕለተ እሑድ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሚባት መካከል አንዱ ከሆነው ከእሳት ብርሃኑን ወስዶ ሰባት የብርሃን ሰማያትን ፈጥሯል፤ ሰማያዊ ቤት የምንላት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወይም መንግሥተ ሰማያት የምትባለው ከእነዚህ ሰማያት አንዷ ናት፤ ስለዚህች ሰማያዊት ቤታችን መረዳት፣ መገንዘብ የምንችለው በእምነት መነጽር ብቻ ተመልክተን ነው፤ በቃላት ሊገልጧት አይቻልም፡፡ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጃት ሰማያዊ ዘለዓለማዊ የተድላ ደስታ መኖሪያ ቤት ናት፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መንግሥተ ሰማያት (ኢየሩሳሌም ሰማያዊት) በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩት ሰባቱ ሰማያት አንዷ ናት፤ ከጽርሐ አርያም፣ ከመንበረ መንግሥት እና ከሰማይ ውዱድ ቀጥላ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከሦስቱ የመላእክት ከተሞች ተብለው ከሚጠሩ ሰማያት፣ ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር በላይ በመካከል ትገኛለች፡፡
በዚህች ሰማይ ላይ እግዚአብሔር ታቦት ዘዶርን (የብርሃን ታቦትን) በመካከሏ ቀርጾባታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ስለ ሁኔታው እንዲህ በማለት ጽፏል፤ ‹‹…በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፤ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ…፡፡›› (ራእይ ፲፩÷፲፱) ታቦት ዘዶር ማለት “የአምላክ መሥዋዕት፣ የብርሃን ታቦት” ማለት ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን ባመሰገነበት በቅዳሴ ማርያም “ታቦት ዘዶር ይህቺውም እመቤታችን ማርያም ናት” በማለት ይህች ታቦት የእመቤታችን ምሳሌ መሆኗን ገልጦልናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ (በእርሷ በደስታ ለመኖር) ተስፋ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መልካም ሥራን መሥራት፣ ሕገ እግዚአብሔርን ማክበር፣ ትእዛዙን መፈጸም ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም ላይ አባቶቻችንን ይህችን ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ መከራ መቀበላቸውን እንዲህ ያስረዳናል፤ “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ፡፡” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህች ሰማያዊ ቤታችን ምን ያህል ድንቅና ውብ፣ በአንደበትና በቃላት የማትነገር መሆኗን ሲያስረዳን ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ እንዲህ ሲል ይገልጣታል፤ ‹‹…ዓይን ያላየችው፣ ጆሮም ያልሰማችው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበው፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው …፡፡›› (፩ኛ ቆሮንቶስ ፪፥፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፷፭ ቁጥር ፴፪ ላይ ‹‹የመንግሥተ ሰማያትን ነገር እንደሚገባው መስሎ ሊናገር የሚችል ማንም የለም፤ በእርሱ መኖርን እንወዳለን … የመንግሥተ ሰማያትን ምሳሌ ለመናገር ባይቻለንም ለምትመጣይቱ ክብር በቅቶ የሚገኝ ሰው እንዲህ ነው …›› በማለት እንዳስተማረው! ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን (ሰማያዊት ቤታችን) መረዳት፣ መገንዘብ የምንችለው በእምነት መነጽር ብቻ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሰማዕታት፣ ቅዱሳን፣ ጻድቃን ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት፣ መነኰሳት ሁሉን ጥለው፣ ዓለምን ንቀው፣ በዱር፣ በገደል፣ በበረሃ ሁነው፣ ፈተናውን ታግሠው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው የኖሩላት፣ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ሊኖሩባት ተስፋ ያደረጓት፣ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ተስፋቸው መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰማያዊቷ ቤት! ክርስቲያኖች የምንጠብቃት፣ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ትንሣኤ እንዳለ አምነን ተስፋ የምናደርጋት እንደ ፈቃዱ ኖረው የተገኙ የሚወርሷት ዘለዓለማዊ ቤት ናት፡፡ ታዲያ በእምነት ጸንተን በጎ ምግባራትን እየፈጸምን በመኖር፣ በመጾም፣ በመጸለይ ከክፋት ሥራ በመራቅ በጥበብና በሞገስ በማደግ ይህችን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ መትጋት አለብን፡፡
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ! በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!