ዝክረ ቅዱስ ያሬድ

ግንቦት፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ውልደቱና እድገቱ አክሱም ከተማ እንደሆነ ታሪኩ ይጠቅሳል፡፡ አባቱ አብዩድ በልጅነቱ በመሞቱ እናቱ ታውክሊያ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ለመምህሩና አጎቱ አባ ጌዲዮን በመስጠት እንዲማር ብታደርገውም ለጊዜው ግን ተቸግሮ እንደነበር ገድሉ ያስረዳናል፡፡ መምህሩን አስቸግሮ ለምትና ለድብደባ ለመጋለጥ ተገዶም ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር በምሬት ማይኪራህ ወደ ምትባል ቦታ ሸሽቶ የሄደው፤ በጉዞውም ላይ ውኃ በመጠማቱ በስፍራዋ በምትገኝ ምንጭ ጠጥቶ ከረካ በኋላ ለማረፍ በዛፉ ሥር ቁጭ ባለበት ሰዓት የገጠመው ነገር ሕይወቱን የቀየረ እውነታ ነበር፡፡ አንገቱን አቅንቶ ወደ ላይም በሚመለከትበት ጊዜ ከዛፉ ላይ አንዲት ትል ፍሬ ለመብላት ከታች ወደ ላይ ስትወጣ ስትወርድ በመመልከቱ ሁኔታዋን ይከታተል ጀመር፡፡ ትሏም ስድስት ጊዜ ያለመሰልቸት ከወጣች ከወረደች በኋላ በሰባተኛው ፍሬው ካለበት ድርሳ ፍሬውንም መብላት ስትበላ አያት፡፡

በዚያን ጊዜ ቅዱስ ያሬድ አሰቦ እንዲህ አለ፤ «ይህች ትል ፍሬውን ለመብላት እንዲህ ከታገሠች እኔም እኮ ትምህርት ለመማር ብታገሥ እግዚአብሔር አምላክ ይገልጽልኛል፡፡» ጉባኤ ቤትም ተመልሶ መምህሩን አባ ጌዲዮን ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ ትምህርቱን ቀጠለ፤ እግዚአብሔር አምላክም የ፹፤፩ መጽሐፍትንና የሊቃውንት መጽሐፍትን እንዲሁም ሌሎች ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሲገልጸለት ሁሉንም ተረዳ፡፡ ከዚህ በኋላ መምህሩና አጎቱ አባ ጌዲዮን በሞት ተለየው፤ የእርሱን ቦታ ተረክቦም ለማስተማር የበቃው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

የአምላክ ሥራ ድንቅ ነውናም ከላይ በአርያም ያለውን ግሩምና ዕጹብ የመላእክት ዜማ ለቅዱስ ያሬድ ያሳውቀው ዘንድ በ፭፻፴፬ ዓ.ም. ኅዳር ፮ ቀን ወደ ሰማይ እንዲነጠቀ አድርጎ በሰማይ ቅዱሳን መላእክት ልዩ በሆነ ጣዕመ ዝማሬ እርሱን ሲያመሰግኑ አሰማው፡፡ ሊቁ ይህን ነበር    ‹‹ዋይ ዜማ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት እምዘይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ በሰማይ ያሉ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ በሚመስጥ ዜማ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ሰማሁ›› ብሎ ያደነቀው፡፡ በሰማያዊ ዜማ በምድራውያን ሰዎች ሊመሰገን በወደደ ጊዜ አምላክ  ቅዱስ ያሬድን ሦስት አዕዋፍ ግእዝ፣ ዕዝል እና አራራይ የሚባሉን የዜማ ስልቶች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዲያስተምሩት አደረገ፡፡

በምድር ተመልሶም በትውልድ ሀገሩ አክሱም ጽዮን ውስጥ ወደ ምሥራቅ በኩል በመዞር ከሰማይ የሰማውን ዝማሬ ዘምሯል፤ ሊቁ ደራሲ ይህን ዜማ ‹‹አርያም›› ብሎም ሰየመው፡፡  በ፭፻፴፰ ዓ.ም. ደግሞ ማኅሌትን ጀመረ፡፡  ቀጥሎም ከታኅሣሥ ፩ ሰኞ እሰከ ታኅሣሥ ፮ ቀዳሚት ሰንበት ድረስ የዘለቀ ምህላ ያዘ፤ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል አንደተሰቀለ ሆነ ከቅዱሳን መላእክት ጋር በዚያች ዕለት ተገለጸለት፡፡

በዚህም ቅዱስ ያሬድ ጌታ የተገለጸለትን የመጀመሪያውን ሳምንት ‹‹ስብከት›› ብሎ ሰየመው፤ በሳምንቱም እንደገና በብርሃን አምሳል ስለተገለጸለት ያን ዕለት ‹‹ብርሃን›› ብሎ ሰየመው፤ በሦስተኛው ሳምንት እንዲሁ በአምሳለ ኖላዊ ስለተገለጸለት ‹‹ኖላዊ›› ብሎ ሰየመው፡፡ በመጨረሻም ሳምንት በአምሳለ መርዓዊ ሲገለጽለት ዕለቱን ‹‹መረዓዊ›› ብሎ ሰይሞታል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ፭ የዜማ መጻሕፍትን የደረሰ ሊቅ ነው፡፡ የደረሳቸውን መጽሐፍትም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሥዕት በማለት ሰይሟቸዋል፡፡ ከእነዚህም የዜማ መጽሐፍት ትልቁ ድጓ ነው፤ የዮሐንስ፣ አስተምህሮና ፋሲካ መጽሐፍት ተብለውም በሦስትም ይከፈላል፡፡ በንባባት ብቻ ይቀደስባቸው የነበሩትን ፲፬ቱ ቅዳሴያት በዜማ የደረሳቸው እርሱ ነው፤  ዝማሬም  ኅብስት፣ ጽዋዕ፣ መንፈስ፣ አኮቴትና ምሥጢር በመባል በ፭ ይከፈላል፡፡

የቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልቶች ግእዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓላትን የምታከብረው ሊቁ የደረሳቸውን ዜማዎች (ሥርዓተ ማኅሌትን) በመጠቀም ነው፡፡ በተለያዩ ጸሎት ጊዜያትም የእርሱን ድርሰቶች ትጠቀማለች፡፡ የሊቁ ሥራዎች በነገረ መለኮት ትምህርትም ያላቸው ሚና ትልቅ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ፣ መምህር ወሐዋርያ፣ መጻሕፍትን በጣዕመ ዜማ የደረሰ፣ መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለያየ ዜማ ያመሳጠረ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡

ሊቁ ደራሲ በተለወደ በ፸፭ ዓመቱ በሰሜን ተራራ ውስጥ ደብረ ሐዊ ከሚባል ገዳም  ግንቦት ፲፩ ቀን የተሠወረ እንጂ የሞተ አይደለም፡፡ እርሱንና ሥራዎቹንም በየዓመቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትዘክራለች፡፡ የዝማሬና መዋሥዕት መምህራን የቅዱስ ያሬድን ጉባኤ ተክተው አሁንም ድረስ በማስተማር ላይ ናቸው፡፡

የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ፣ አማላጅነቱና ተራዳኢነቱ አይለየን፤ አሜን!