ሰማያዊው ቤት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

መዓልት ለሌሊት ጊዜውን ሰጥቶ ሊያስረክብ ከግምሽ በታች ደቂቃዎች ቀርተውታል፤ ጠዋት ለስላሳ ሙቀቷን ከብርሃን ጋር፣ ከሰዓት ጠንከር ያለ ሙቀቷን ለምድርና ለነዋሪዎቿ እየሰጠች ወደ ምዕራብ ስትጓዝ የነበረች ፀሐይ ከአድማሱ ጥግ ግማሽ አካሏን ደብቃለች፡፡ ጠዋት ስትወጣ እየጓጓ ከሰዓት በማቃጠሏ ተማረውባት የነበሩትን ሰርክ በመጥለቋ እንዲናፍቋት ደብዛዛ ብርሃኗን እያሳየች ስንብቷን ጀምራለች!

መምሬ እውነቱ ከግቢያቸው ከሚገኘው ትልቅ ዋርካ ሥር ተቀምጣው ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙር ፵፱ ላይ ስለ ዳግም ምጽዓቱ ‹‹አምላከ አማልክት እግዚአብሔር ነበበ ወጸውዓ ለምድር እምሥራቀ ፀሐይ እስከነ ዓረብ፤ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ከፀሐይ መውጪያ እስከ መግቢያው ምድርን ጠራት›› በማለት የተነበየውን ትንቢት በውስጣቸው አያሰላሰሉ ከምሥራቅ ወጥታ ወደ ምዕራብ እየጠለቀች ያለችውን ጀንበር እየተመለከቱ የፈጣሪን ድንቅ ጥበብ በማድነቅ ላይ ናቸው፡፡

ከገቡበት የሐሳብ ውቂያኖስ ያወጣቸው ከሚጋልቡት የሐሳብ ፈረስ ያወረዳቸው የልጅ ልጃቸው የግርማዬ ንግግር ነበር፤ ‹‹አያቴ መጥቻለሁ›› አለ፡፡ ጉንበስ ብሎ ጉልበታውን ከሳመ በኋላ ሁለት እጆቹን ከደረቱ አጣምሮ ከወገቡ ጎንበስ በማለት ‹‹ባርከኒ አባ እንሣእ በረከትከ›› አለ፤ መምሬ እውነቱ መስቀላቸውን ከደረት ኪሳቸው አውጥተው ‹‹ነዋ መስቀለ ሰላም ዘተሰቅለ ቦቱ መድኃኔዓለም›› አሉት፡፡ ‹‹ይፍቱኝ አባቴ›› አላቸው፤ መስቀሉን እያሳለሙት ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አሉት፡፡

ከእግራቸው ሥር ቁጭ ሲል መምሬ ከሥራቸው ቁጭ ያለውን ግርማዬን አጎንብሰው እያዩት ‹‹ምን ነበር ጥያቄህ?›› አሉት፡፡ የግርማዬ ውጫዊ ጆሮው ብቻ ሳይሆን በውሳጣዊ ጆሮውም ጭምር ከአያቱ አንደበት የሚደመጠውን ለመስማት በዝግጅት ላይ ናቸው! ‹‹አያቴ! ስለ ሰማያዊ ቤት›› አለ፤ መምሬ እውነቱ ለደቂቃዎች በጸጥታ ሆነው ከቆዩ በኋላ ‹‹ሰማያዊ ቤት›› በማለት ቃሉን ደገሙት፤ ‹‹አዎ አያቴ›› አለ፡፡

መምሬ እውነቱ ለተወሰነ ሰከንድ ዝም ካሉት በኋላ በእምት መነጽራቸው ያያትን ከአበው በትምህርት የሰሙላትን ሰማያዊ ቤት ለግርማዬ እንዴት አድርገው እንደሚያስረዱት አሰቡ፤ በቀኝ እጃቸው የያዙትን ጭራቸውን ከቀኝ ወደ ግራ በማወዛወዝ ተዋስያንን እንደማባረር ካደረጉ በኋላ ከአድማሱ ጥግ ዕይታቸውን አድርገው ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ ‹‹አየህ ግርማዬ! ባለፈው ስለ ሥነ ፍጥረት የነገርኩህን ታስታውሳህ አይደል?›› አሉ፡፡ ግርማዬ ሽቅብ አያቱን እየተመለከተ ራሱን በመነቅነቅ ሐሳቡን ገለጠ! መምሬ እውነቱ እይታቸውን ከአድማሱ ጥግ ሆና የምትሰናበት ወደምትመስለው ጀንበር እንዳደረጉ ንግግራቸውን ቀጠሉ፤

‹‹እግዚአብሔር ጠቢበ ጠቢባን ነው፤ በዕለተ እሑድ ቅድሚያ ከፈጠራቸው አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሚባሉት መካከል አንዱ ከሆነው ከእሳት ብርሃኑን ወስዶ ሰባት የብርሃን ሰማያትን ፈጥሯል፡፡ ሰማያዊ ቤት የምንላት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወይም መንግሥተ ሰማያት የምትባለው አንዷ ናት፤ በረቂቅ የልብ ሃብት በሆነች እምነት መነጽር ብቻ ተመልክተው የሚረዷት፣ በሥጋው ዕውቀትና ፍልስፍና፣ በሥጋዊ ጥበብ የማትገለጥ የማትዳሰስ፣ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጃት ሰማያዊ፣ ዘለዓለማዊ የተድላ ደስታ መኖሪያ ቤት! እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሰባቱ ሰማያት ከጽርሐ አርያም፣ ከመንበራ መንግሥት እና ከሰማይ ውዱድ ቀጥላ ከሦስቱ የመላእክት ከተሞች ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር በላይ ያለች ሰማይ! ይህች ሰማይ ለሰባቱ ሰማያት መካከለኛ ስትሆን በፊት ሳጥናኤል የተፈጠረባት፣ ቢክድ የወጣባት፣ ለአዳም የተሰጠችው የምእመናን ቦታ ናት፡፡

በዚህች ሰማይ ላይ እግዚአብሔር ታቦት ዘዶርን (የብርሃን ታቦትን) በመካከሏ ቀርፆባታል፡፡ (ራእይ ፲፩÷፲፱) ታቦት ዘዶር ማለት የአምላክ መሥዋዕት፣ የብርሃን ታቦት ማለት ነው፡፡ ይህች ታቦት የእመቤታችንና ምሳሌ ናት፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ‹‹ታቦት ዘዶር እንተ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም፣ ታቦት ዘዶር ይህቺውም እመቤታችን ማርያም ናት›› እንዳለ!

አሁንም ለአፍታ ዝም አሉ! አንገታቸውን ዘንበል አድርገው ወደ ግርማዬ ተመለከቱ፤ የደስታ ይሁን የኀዘን ያልታወቀ ዕንባ የዓይናቸውን ሽፋሽፍት ከፍታ ብቅ አለች፤ ከፊታቸው ገጽ ግን የኀዘን ሳይሆን የደስታ ፈገግታ ይንጸባረቅ ነበር፤ ‹‹አባ ኤፍሬም ሶሪያዊ ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያምን ያወደሰበት የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዓው ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት…፤ ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ፤!›› የሚለውን አስታወሱ!

‹‹አየህ ግርማዬ!›› አሉ፤ ዕንባ ባቀረረ ዓይናው እየተመለከቱት ‹‹ሰማዕታት መሪር ሞትን የታገሡላት ሰማያዊቷ ቤታችንን በእምነት መነጽር ተመልክተዋት ነው! ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህች ሰማያዊት ቤታችን ለቆሮንቶስ ምእመናን በላው መልእክቱ እንዲህ ሲል ይገልጣታል፤ ‹‹…ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማችው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው …፡፡›› ( ፩ኛ ቆሮ. ፪፥፱)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ዳግም ለፍረድ በሚመጣ ጊዜ ጻድቃን የሚወርሷት (የሚገቡባት) መሆኗን እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ…›› አሉ! ግርማዬ በሁለት እጆቹ የእግሮቹን ጉልበቶች ታቅፎ ዓይኑን ወደ ላይ አቅንቶ የአያቱን ዓይን ዓይን እየተመለከተ ከአንደበታቸው የሚወጣውን ቃል ነፍሱ ሐሴትን ተመልታ በተመስጦ እያዳመጠ ነው!

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ መንግሥተ ሰማያትን በብዙ ምሳሌ መስሎ አስተምሮላታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፷፭ ቁጥር ፴፪ ላይ የመንግሥተ ሰማያትን ነገር እንደሚገባው መስሎ ሊናገር የሚችል ማንም የለም በእርሱ መኖርን እንወዳለን›› በማለት እንደገለጸው አንደበት ሊገልጣት አይችልም፡፡ ግን ደግሞ በሚረዳንና በሚገባን መልኩ ሲገልጣት እንዲህ ብሏል፤ ‹‹የመንግሥተ ሰማያትን ምሳሌ ለመናር ባይቻለንም ለምትመጣይቱ ክብር በቅቶ የሚገኝ ሰው አንደህ ነው፤ ዳግመኛ ሌላ መምሳሌ ልንሻ ይገባል፤ በማኅፀን ሳለ ድኃ የነበረ ሕፃን በተወለደ ጊዜ በምድር ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ለመንግሥተ ሰማያት የበቃ ሰው እንደዚህ ነው፡፡ ዳግመኛም ይህ ለዚህች ክብር ምሳሌዋ ሆኖ አይደለም›› አሉ መምሬ እውነቱ፡፡

መድኅን ዓለም ክርስቶስ በብዙ ምሳሌ መስሎ ያስተማረላትን ሰማያዊቷ ቤት መንግሥተ ሰማያትን ክብሯን እንዴት አድርገው መግለጽ እንዳለባቸው ቃላት ያጠራቸው ይመስላሉ! በውስጣቸው ከራሳቸው ጋር ያወሩ ጀመር ሰማዕታት፣ ቅዱሳን፣ ጻድቃን ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት መነኮሳት ሁሉን ጥለው ዓለምን ንቀው በዱር በገደል በበረሃ ሁነው ድመፀ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሠው በጾም በጸሎት ተወስነው የኖሩላት ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ሊኖሩባት ተስፋ ያረጓት ሰማያዊቷ ቤት ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን እንዴት ባለ የእምነት መነጽር ቢመለከቷት ይሆን በማለት ራሳቸውን ጠየቁ፤ ሰማያዊቷ ቤት!

ክርስቲያኖች የምንጠብቃት፣ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ እንዳለ አምነን ለክብሯ ያበቃን ዘንድ ተስፋ የምናደርጋት እንደፈቃዱ ኑረው የተገኙ የሚወርሷት ዘለዓለማዊ ቤት፣ መምሬ እውነቱ ግርማዬ በሚረዳው መልኩ ስለ ሰማያዊቷ ቤት አብራርተውለት ባይጨርሱም የጀንበሯን መጥለቅ ተከትሎ መዓልት ለሌሊት ሥፍራውን አስረክቦ ኑሮ መጨለሙን ሲመለከቱ! ‹‹በል ግርማዬ ለዛሬ በዚህ ይብቃን! አምላከ ቅዱሳን በእናቱ በቤዛዊት ዓለም ቃል ኪዳን፣ በቸርነቱ እርሷን ለመውረስ ያብቃን!›› አሉ። ጸሎት አድርሰው እርሳቸው ከፊት እርሱ ከኋላ ሁነው ወደ ቤት አመሩ፡፡