‹‹ኢያቄም እና ሐና ሰማይን ወለዱ›› ቅዱስ ያሬድ

መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

ሚያዝያ ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች፣ የፈጣሪ እናት፣ የአምላክ እናት ለመሆን የበቃች በመሆኗ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይ ትመሰላለች። አምላኳን በክንዶቿ ለመታቀፍ፣ ጡቶቿን ለማጥባት፣ በጀርባዋ ለማዘል የበቃች እመቤት ናትና። ባለማለፍ ጸንተው የሚኖሩት ሰባቱ ሰማያት እንዴት ነው ለእመቤታችን ምሳሌ የሚሆኑት እንል? ይሆናል። ይህም እንዲህ ነው፤ ከሰባቱ ሰማያት አንዱ ጽርሐ አርያም ይባላል። ይህ ሰማይ የቅድስት ሥላሴ የእሳት ዙፋን ያለበት ነው። ‹‹ኢያቄም እና ሐና ሰማይን ወለዱ›› ስንል ጽርሐ አርያምን ወለዱ ማለታችን ነው።

በጽርሐ አርያም ያንን የእሳት ዙፋን፣ ያንን የእሳት መንበር፣ የማይደፈረውን፣ የሚፈራውን የሥላሴን መንበር የሚሸከሙ አርባዕቱ እንስሳ ወይም ኪሩቤል የሚባሉ አሉ። እነዚህ ኪሩቤል የሚባሉ መላእክት በጀርባቸው ያንን የእሳት ዙፋን ተሸክመው በዙፋኑ ላይ ያሉት ሥላሴን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግናሉ፤ ሲያመሰግኑም ይኖራሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚባሉ ሱራፌል ተብለው የሚጠሩ ቅዱሳን መላእክት አሉ። እነርሱም ስድስት ክንፍ ነው ያላቸው። በሁለት ክንፎቻቸው ፊታቸውን ሸፍነው፣ ሁለት ክንፎቻቸውን አመሳቅለው፣ ግራ እና ቀኝ ዘርግተው፣ በሁለት ክንፎቻቸው ረበው አክሊላቸውን አውርደው ልክ እንደ አንድ ካህን፣ ልክ እንደ አንድ ጽና ይዘው ያንን የእሳት መንበር ያጥናሉ።  ሱራፌል የእሳትን መንበር ያጥናሉ። ኪሩቤል የእሳቱን መንበር ይሸከማሉ። እመቤታችን ግን እሳት ለሆነው አምላክ ማደሪያ ሆናለችና ከሁሉም ትበልጣለች፤ ትልቃለች፡፡

ቅዱስ ያሬድ ‹‹ህየንተ አርያም ዘበሰማያት ዘኮንኪ አርያመ በዲበ ምድር፤ በሰማይ ባለ ጽርሐ አርያም ፈንታ በምድር ላይ ጽርሐ አርያምን ሆንሽ›› እያለ እመቤታችንን እንዳመሰገናት የእመቤታችን ማኅፀን የእሳት መንበር ሆኖ ተገኘ። አይደንቃችሁም? የእግዚአብሔር መንበሩ፣ የእግዚአብሔር መቀመጫው፣ የእግዚአብሔር ዙፋኑ የእሳት ነው። በእመቤታችን ማኅፀን በማደሩ የእመቤታችን የድንግል ማርያም ማኅፀን የእሳት መንበር ሆነለት።

ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ወበቃል እግዚአብሔር ጸንዓ ሰማያት፤ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ›› እንዳለው ባለማለፍ ጸንተው ለዘለዓለም የሚኖሩ፣ የማያልፉ፣ የማይጠፉ ሰማያት እንዳለው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን በእነዚህ በማያልፉት ሰማያት  ትመሰላለች። (መዝ.፴፫፥፮) ክብሯ ታላቅ ስለሆነ የተሰጣት ጸጋ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነውና። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልዕልተ ፍጡራን (ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ)፣ መትሕተ ፈጣሪ (ከፈጣሪ በታች) ሆና የምትመሰገን የምትከበር ስለሆነ በብዙ በጎ በጎ ምሳሌዎች ትመሰላለች። በብዙ በጎ በጎ ምሳሌዎች ትመሰል እንጂ እመቤታችንን የሚመስላት፣ የሚተካከላት የለም። ከፍጡር ወገን ለእመቤታችን የተሰጠ ጸጋ ለማንም አልተሰጠም።

የድንግል ማርያም ክብሯ ታላቅ ነው። እንኳን ለነቀፋ እርሷን ማመስገንም ያስቸግራል፤ በምን አንደበታችን፣ በምን ቃል፣ በምን ቋንቋ እንገልጻታለን። ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹አይ ልሳን ዘይክል ነቢበ ዘይትናገር በእንቲአኪ፤ ድንግል ሆይ፥ እመቤቴ ሆይ፥ ስላንቺ መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው?›› በማለት እንደጠየቀው መላእክትም፣ ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንኳን ስለ እርሷ ተናግረው መጨረስ አልተቻላቸውም።

ቅዱስ ገብርኤል  ‹‹ተፈስሒ ፍስሕት፤ ደስተኛይቱ ደስ ይበልሽ›› እያለ እየሰገደ እና እየወደቀ እየተነሣ ነው እመቤታችንን ያበሠራት። በእኔ አንደበት አይቻለኚም ብሎ ‹‹ተፈስሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ ኢትፍርሒ ማርያም እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፥ ደስ ይበልሽ፣ ማርያም ሆይ አትፍሪ፥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለማልነትን አግኝተሻልና እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ›› እያለ አመስግኗታል። ለምን ቢባል ማኅፀኗ የእሳት መንበር ሆኖ ተገኝቷልና።

ቅዱሳኑ ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ እእላፍ መላእክትም አምላካቸውን ቢፈልጉት በድንግል ማርያም ማኅፀን አግኝተውታል። በዚህ ጊዜ ሱራፌል ድንግል ማርያምን አመሰገኗት፡፡

መላእክት በቅዳሴ ከፍ ከፍ ያደረጓትን ድንግል ማርያምን ማነው ዝቅ ዝቅ የሚያደርጋት? እግዚአብሔር እናቱ፣መንበሩ፣ ዙፋኑ፣ መቅደሱ ያደረጋትን ድንግል ማርያምን ማነው የሚቃልላት? እንደ ጽርሐ አርያም ዙፋኑ ማደሪያው ስላደረጋት ሊቃውንቱ ምን አሉ? ‹‹ኢያቄም እና ሐና ሰማይን ወለዱ፡፡›› ይህ የሚደንቅ ምሥጢር ነው። ጽርሐ አርያምን ወልደዋልና።

ቅዱስ ያሬድ ‹‹በምድር ላይ የተገኘሽ መንበር፣ ዙፋን፣ ዳግሚት ሰማይ›› እያሉ እመቤታችንን ያመሰገኗት ለዚህ ነው። በጽርሐ አርያም የሥላሴ ዙፋን ስላለ፤ በጽርሐ አርያም ሰባቱ የእሳት መጋረጃወች ስላሉ፤ በጽርሐ አርያም ሱራፌል እና ኪሩቤል ስላሉ የተቀሩት ስድስቱ ሰማያት ለጽርሐ አርያም እንደ አጥር፣ እንደ ቅጥር ሆነው አክብረዋት፣ አስከብረዋት ለዘለዓለም ይኖራሉ ማለት ነው። ጽርሐ አርያም ለድንግል ማርያም ምሳሌ መሆኗን ምሥጢሩን ትርጓሜውን ተመልክተናል። የተቀሩት ስድስቱ ሰማያትስ ለእመቤታችን ምሳሌ መሆን ይችላሉ? አዎ! ምሳሌ መሆን ይችላሉ። በበጎ ነገር ሆኖ እመቤታችን ትመሰላለችና። ስድስቱ ሰማያት ለድንግል ማርያም የንጽሕናዋ እና የድንግልናዋ ምሳሌዎች ናቸው። የእመቤታችን ንጽሕና እና ድንግልና እንዴት በስድስቱ ሰማያት ይመሰላል ትሉ ይሆናል።

ስድስተኛ ድንጋሌ ልቡና (የልብን ድንግልና) እነዚህን አስተባብራ በመገኘቷ በነዚህ ታጥራ ተከብራ እንደምትኖር የሚያመለክት ምሥጢር ነው። ‹‹ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱ›› ማለት  ይህ የምናየውን ሰማይ ስናሰተውለው ድንኳን ይመስላል። ለመሬት የተተከለ ድንኳን። እግዚአብሔር ይህን የምናየውን ሰማይ የሚያልፈውን ሰማይ ለምንድን ነው የፈጠረው?

አምላካችን እግዚአብሔር እያንዳንዱን ፍጥረት በሙሉ የፈጠረበት ዓላማ አለው፤ ፈጣሪያችን አስቀድሞ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሁሉን በጥበብ አደረግክ›› እንዳለ ይህን ሰማይ የዘረጋው ከፀሐይ የሚወጣውን ኃይለኛ ሙቀት እንዲከልልልን ነው። (መዝ.፻፬፥፳፬) ልክ በፀሐይ ጊዜ ጣሪያ ፀሐዩን እንደሚከላከልን፣ ሙቀቱን እንደሚከለክልልን ሰማይም እንደ ድንኳን ተዘርግቶ ያንን ሙቀት ይከለክልልናል ማለት ነው፡፡ እንደ ቸርነቱ ቃጠሎውን እንዲከለክልልን ሰማይን ፈጠረልን።

የገሃነመ እሳትን ቃጠሎ እንድትከለክልልን እግዚአብሔር የሰጠን ሰማይ፣  የተከለልን ድንኳን፣  የዘረጋልን ድንግል ማርያም ናት። በእርሷ ጥላ ከለላ ውስጥ ነውና ያለነው ቃጠሎው ወይም እሳቱ አያስፈራንም።

ሁለተኛው እግዚአብሔር ይህንን ሰማይ የፈጠረበት ምክንያት ነው፡፡ ፈጣሪ ሰማይን ዝም ብሎ ቢተወው ኖሮ የሰው ልጅ ዓይን ማረፊያ አይኖረውም ነበረ። አንገታችንን አቅንተን ቀና ስንል የዓይናችን ማረፊያ ሰማዩ ነው። ዓይን ማረፊያ ባይኖረው  ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን እንደነገሩን ከሆነ ለዓይናችን ማረፊያ ይህንን ሰማይ ባይዘረጋልን ኖሮ ዓይናችን ተጎልጉሎ ይወጣ ነበረ። ስለዚህ ይህንን ሰማይ ለዓይናችን ማረፊያ ፈጠረልን። ለዓይነ ሥጋችን ይህንን ሰማይ ከፈጠረልን፣ ለዓይነ ልቡናችን፡ ለዓይነ ነፍሳችን ማረፊያ ሆና የተሰጠችን ሰማይ ደግሞ ድንግል ማርያም ናትና።

በብዙ ሥዕለት፣ በብዙ ዕንባ፣ በብዙ ልቅሶ ድንግል ማርያምን ለመፅነስ የበቁት ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወልደውልናልና ይህን ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማኅፀን እያለች ተአምራትን ታደርግ ነበረ በተአምረ ማርያም የምንሰማው ነው፡፡ ዕውር ታበራ፣ ሙታንን ታስነሣ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ገና በማኅፀን ሳለች ጠላት ተነሣባት። ‹‹በሐና ማኅፀን ያለ ፅንስ ሙት እያስነሣ፣ ዕውር እያበራ ነውና ነገ ተወልዶ ንጉሥ ሆኖ፣ ንግሥት ሆና ከምትገዛን ዛሬውኑ እና ጥፋት›› ብለው ተነሱ። እመቤታችንን፣ ስሟን፣ ኅልውናዋን፣ ለማጥፋት ገና በማኅፀን እያለች ጠላት ተነሳባት።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወርዶ ኢያቄምና ሐናን ካሉት ቦታ እንዲሸሹ ነገራቸው፤ ሊባኖስ ተራራም ሔደው ተቀመጡ። እመቤታችንም ከተራራ ላይ ነው ተወለደች። ግንቦት አንድ ቀን ስትወለድ ያ ተራራ በብርሃን ተሞላ። የሥላሴ መንበር፣  ዳግሚት ሰማይ፣ ጽርሐ አርያም ተወልዳለችና። ሰማያውያን መላእክት ወርደው ያንን ተራራ ስለሞሉት ያ ተራራ በብርሃን ተሞላ። ወገኖቼ! ያ ግዑዝ ፍጡር፣ ያ ተራራ፣ የአራዊት መፈንጫ፣ የእንስሳት መዋያ የሆነ ተራራ በእመቤታችን ምክንያት በብርሃን ከተሞላ የእኔና የእናንተ ሕይወት በድንግል ማርያም ምክንያት በብርሃን እንዴት አይሞላ? በብርሃን ይሞላል።

ነገር ግን ይህ ኃጢአት የሚባል ደዌ እያለ ጆሯችንን፣ ዕዝነ ልቡናችንን ደፍኖት በየት በኩል እንስማው እንጂ እነ ቅዱስ ሚካኤል፣ቅዱስ ገብርኤል በእመቤታችን ልደት ቀን እኮ አብረውን እልል ይላሉ፡፡ አብረውንም ይዘምራሉ።

የዓይን ማረፊያ፣ የልብ መደገፊያ፣ ከገሃነመ እሳት የምንሰወርባት፣ የምንከለልባት ድንግል ማርያም ተሰጥታን ክብራችንን ልንረዳ ይገባል!

መንፈስ ቅዱስ ይህን ድንቅ ምሥጢር ለአባቶቻችን ገልጦላቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ድንግል ማርያምን ‹‹ጽርሐ አርያም አንች ነሽ›› ብሏታል፡፡ ስለዚህ ከአምላክ እናት ጋር ካላችሁ በምድር ሳይሆን በሰማይ አላችሁ ማለት ነው። አይደንቅም!? በምድር ላይ እኮ የለንም ማለት ነው። ለምን? ድንግል ማርያም ሰማይ ናታ። ለካ በሰማይ ነው የምንኖረው ነውና ደስ ይበላችሁ!

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን!