ወርኃ ግንቦት
መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ
ሚያዝያ ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዘጠነኛው ወር “ግንቦት” በመባል ይታወቃል፡፡ ግንቦት “ገነበ፣ ገነባ፣ ሠራ፣ ቆፈረ፣ ሰረሰረ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጒሙም “ገቦ፣ ክረምት፣ የክረምት ጎን፣ ጎረ ክረምት (የክረምት ጉረቤት)” ይባላል። ይህንም ስም የሰጡት የክረምት መግቢያ ምድር ለእርሻ የምትዘጋጅበት ወቅት በመሆኑ ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ውስጥ የዚህን ወር ቃል ሲተረጒሙ “ስመ ወርኅ፣ ታስዕ እመስከረም፣ ገቦ ክረምት፣ ጎረ ክረምት” ይልና በግንብ ዘይቤ ሲፈቱት ግን “ወርኀ ሡራሬ” ያሰኛል፡፡ የባቢሎን ግንብ ሳይቀር ሁለቱ መቅደሶች በግንቦት ወር ተመሥርተዋል፡፡ (፫ኛ ነገ.፮፥፩፣ ዕዝ.፫፥፰) ይሉታል። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፫፻፳፪)
በምዕራባውያን አጠራር ደግሞ ግንቦት ወር “አያር” ወይም በእንግሊዝኛው “May” ብለው የሚጠሩት ሲሆን ይህንም ስያሜውን ያገኙት የአትክልት ሴት አምላክ ብለው ከሚያለምኩት የጣዖት ስም ነው። በሮማውያን ይህ ወር አምስተኛ ወራቸው ሲሆን የዚህ ወር የቀኑ ቁጥር እንደ ሌሎች ወራቶች በየጊዜው የተቀየረ ሳይሆን ቀድሞ ከልደተ ክርስቶስ ከ፵፭/፮ ዓመት በፊትም አሁንም ያው ፴፩ ቀን ነው፡፡
የግንቦት ወር የክረምት ጎረቤት ቢሆንም ሙቀታማና ደረቃማ ወር ነው። በዚህም ጸባዩ ብዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን አፍርቷል። አባቶች “በግንቦት አንድ ዋንጫ ወተት” ይላሉ። ”ኅብረ ብዕር” በተባለው መጽሐፋቸው፣ አቶ ካሕሣይ ገብረ እግዚአብሔር ይህን ብሂል እንዲህ በማለት ይፈቱታል፤ ሰውነታችን ኃይለኛውን የግንቦት ሙቀት መቋቋም ይችል ዘንድ አንጀት የሚያርስ፣ ቆዳን የሚያለሰልስ፣ የጠፋ ዓቅምን የሚመልስ ወተት ማግኘት አለበት ለማለት ነው” ይላሉ፡፡
ሌላም ብሂል አለ። “በነሐሴ ባቄላ፣ በግንቦት አተላ” የሚለውም ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም በደረቃማው ገጽታ ምክንያት በግንቦት ወር ምን ያህል እንደሚጐዱና አተላ እንደሚ ያስፈልጋቸው አመልካች ነው።
የአቡሻክር መምህራን ግን ይህንን እንዲህ ይራቀቁበታል። ኢትዮጵያ የዓውደ ዕለታትና የወር አቆጣጠሯን ማለትም ዐሥራ ሁለቱን ወር በ፴ በ፴ ቀን መድቦ መጠቀም ከእነ ድሜጥሮስ በፊት ትሠራበት እንደነበር፣ ይህንም የተቀበለችው ብሉይ ኪዳንን ከእስራኤል ቀጥላ የተቀበለች ሀገር በመሆኗ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አድርጋ እንደሆነ ይናገራሉ። (ዘፍ.፯፥፲፩፣፰፥፫) ይህም ከዓመተ አዳም፣ ከዓመተ ኖኅ ጋር የተያያዘ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ እንዳልሆነ ገልጸው ይህንንም በቀመረ ፊደል የዕውቀት ርቀታቸው እንዲህ በማለት አሳይተውናል። በ2256 ዓመት የመጣው የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሁለተኛው ወር የተባለ ግንቦት ነው፡፡ ለእስራኤል ሚያዝያ የመጀመሪያ ወራቸው ስለሆነ እስከ ሰባተኛው ወር ቆይቷል። (ዘፍ.፰፥፫)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን መሠረት አድርጋ የቅዱሳንን በዓላት በዓመትና በወር ትዘክራለች፡፡ በየቀኑ የሚታሰቡትን የወርና የዓመት የቅዱሳንን በዓላት ቢኖሩም ለዚህ ጽሑፍ ግን ቦታ ስለሚገድበን የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡ (የሌሎች ቅዱሳንን ታሪክ ለማግኘት የግንቦትን ስንክሳር ይመልከቱ።)
፩. የከበረች የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደችው በዚህ ወር የመጀመሪያ ቀን ነው፡፡
፪. ሁለተኛው ቀን ደግሞ ጻድቁ ኢዮብ ያረፈበት ነው፡፡
፫. ታላቁ ነቢይ ኤርምያስ ደግሞ በዚህ ወር አምስተኛው ቀን ዐርፏል፡፡
፬. “ጥንተ ዕርገት” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በአርባኛው ቀን ያረገበት መታሰቢያ ዕለት በዚህ ወር ስምንተኛው ቀን ነው፡፡
፭. የጻድቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስ ዕሌኒ ያረፈችውም በግንቦት ወር በዘጠነኛው ቀን ነው፡፡
፮. የከበሩ ጻድቃን ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ፣አዛርያ፣ሚሳኤል) ያረፉት በዚህ ወር በዐሥረኛው ቀን ነው፡፡
፯. በከበረች ግንቦት ዐሥራ አንድ ቀንም የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ የተሠወረበት ቀን ይታሰባል፡፡
፰. የከበረ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ዐርፏል፡፡
፱. በግንቦት ዐሥራ ስምንት ቀንም የክብር ባለቤት ጌታችን ካረገ በኋላ በኅምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት ቀን ነው፡፡
፲. ግንቦት ሃያ አንድ ቀን ደግሞ በዓለ ደብረ ምጥማቅ ነው፡፡
፲፩. በግንቦት ሃያ አራት ቀንም ጌታችን ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ግብጽ ሀገር የወረደበት ነው፡፡
ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ዕንባቆም ያረፈውም በዚህ ቀን ነው፡፡
፲፪. የእመቤታችን ማርያም የአክስት ልጅ ብፅዕት ሰሎሜ ዕረፍት በግንቦት ሃያ አምስት ቀን ነው፡፡
የክብር ባለቤት ጌታችን ደግሞ የዮሴፍን በትሮች በአረንጓዴ ቦታ ላይ ተከለ፤ ወዲያው ዛፎች ሆኑ፡፡
፲፫. በዚህ ወር በሃያ ስድስተኛው ቀን ዲዲሞስ የተባለ የከበረ ሐዋርያ ቶማስ ዐረፈ፡፡
፲፬. በግንቦት ሃያ ሰባት ደግሞ የማርያምና ማርታ ወንድም ጻድቊ አልዓዛር ዐረፈ፡፡
የቅዱሳን ጸሎት፣ አማላጅነት እና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!