‹‹በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለው›› (ማቴ.፳፭፥፳፩)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፲፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በሰዎች ዘንድ መታመን መታደል ነው፤ እምነትን ጠብቆ መገኘት ደግሞ ታላቅነት ነው፡፡ መታመን የተሰጠን አደራ ጠብቆ መገኘት ለክብር ያበቃል፤ በሰውም ሆነ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ መወደድንና መከበርን ያተርፋል፡፡ ለሰዎች ስንታመን እነርሱ ባያዩንም በሁሉ ቦታ ያለ፣ በቦታ የማይወሰን፣ በእርሱ ዘንድ ጨለማ የሌለበት እግዚአብሔር ያየናል፡፡ መታመናችን “ሰው አየን አላየን” ብለን ሳይሆን ለታመንንለት ነገር በፈቃዳችን መገዛት ስንችል፣ የታመነንን ስናከብር በምትኩ ለታላቅ ኃላፊነት እግዚአብሔር ይሾመናል (ይመርጠናል)፡፡
መታመን እና አደራን መወጣት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል ናቸው፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈውም ይህን ታሪክ ነግሯቸዋል፡፡ አንድ ባለጸጋ ሦስት አገልጋዮቹን ጠርቶ ሥራ ሠርተው (ነግደው) የሚያተርፉበት ገንዘብ አምኗቸው ለአንደኛው አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጣቸውና ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ እርሱ ባያያቸውም አጠገባቸው ባይሆንም ሁለቱ አገልጋዮቹ በታማኝነት ሠርተው አትርፈው ጠበቁት፤ አንደኛው ግን እምነቱን (መታመኑን) ሳይጠቀም የተሰጠውን ገንዘብ ምንም ሳይሠራበት ቆየ፡፡
ባለጸጋውም ከሄደበት ሲመለስ ሁለቱ አገልጋዮቹ በታማኝነት፣ በትጋት የተሰጣቸውን መክሊት ከነትርፉ አስረከቡ፤ ያ ሰነፉ፣ የተጣለበትን እምነት ያልተወጣው ግን የተሰጠውን ብቻ ይዞ ጠበቀው፤ “ነግዶ ያተርፍበታል” በማለት በእምነት የሰጠውን መክሊት አንዳች ነገር ሳይሠራት ከመጠበቅም ባሻገር ከመሬት ቀበረው፤ በዚህም ባለጸጋው ሰውዬ ወቀሰው፤ የሰጠውን እንዲነጥቁት፣ እርሱን ደግሞ እንዲቀጡትም አደረገ፡፡ ‹‹ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፤ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፤ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት…›› ብሎም አዘዘ፡፡ (ማቴ.፳፭፥፳፰)
ሰዎች አምነውን እንድንሠራ ሲያዙን፣ በአደራ የሰጡንን ነገር ያንን በክብር አስቀምጠን ሲመጡ ማስረከብና መታመንን በአግባቡ መወጣት ተገቢ ነው፤ መታመናችንን መግለጥ (ማሳየት) ይገባናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መልካም ምግባራቸው ተመዝገቦ ከሚገኙ፣ ታምነው የተገኙና እምነታቸውን የጠበቁ፣ ለክብር የበቁ ‹‹በጥቂቱ ታምነው በብዙ ከተሾሙት›› መካከል ለአብነት (ለምሳሌ) አንዱን እንመልከት፡፡ (ማቴ.፳፭፥፳፩)
ዮሴፍ ከያዕቆብ ፲፫ ልጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ (ዘፍ.፴፥፳-፳፬) ከጠባዩ መልካምነትና ከዝናው እንዲሁም እጅግ አብልጦ ይወዳት ከነበረችው ሚስቱ ራሔል የወለደው ከመሆኑ የተነሣ ከሁሉም ልጆች መካከል በአባቱ ዘንድ በተለይ የተወደው ሆነ፡፡ አንድ ቀን ወንድሞቹ ከብቶችን አሠማርተው (ውኃ እንዲጠጡ፣ ሣር እንዲነጩ ወደ ሜዳ) ይዘዋቸው ሄዱ፤ አባታቸው ያዕቆብም ስንቅ አሰራላቸውና ዮሴፍን “አድርስ” አለው፤ የእርሱንም ለብቻ አሠረለት፤ ወንድሞቹ ያሉበትን ስፍራ ሲፈልግ ሩቅ ነበርና ለእርሱ የታሰረለት ስንቅ አለቀበት፤ በዚያ ላይ ደግሞ ደከመው ራበውም፤ እንዳይበላ ለወንድሞቹ አድርስ የተባለው ነው፡፡ የሚበላ ይዞ ተርቦ ደከመው፤ ለአባቱ ታመነ፤ ለወንድሞችህ አድርስ ነውና የተባለው ቢርበውም አልበላባቸውም፤ ለምን ቢባል የእርሱ አይደለምና፤ በመታመኑ (ታማኝ) በመሆኑ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና ‹‹…የአባትህን ፈጣሪ ድንጋዩን ዳቦ አድርግልኝ ብለህ ለምነው…›› አለው፤ ለምኖ በተአምራት ድንጋዩን ዳቦ ሆኖለት ተመገበ፡፡ (ዘፍ.፴፯፥፲፬፣ ማቴ.፬፥፫ አንድምታ)
ሕልሞችንም ባየ ጊዜ ለአባቱና ለወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ እነርሱ ግን “በላያችን ሊነግሥብን ነው” በማለት ጠልተውት ሸጡት፡፡ (ዘፍ፡-፴፯) በግብጽ ባሪያ (አገልጋይ) ሆኖ በጲጥፋራ ቤት ሲያገለግል በነበረበት ጊዜ በጣም ታማኝ ነበር፤ ስለዚህም በአስተዳዳሪነት ተሾመ፡፡ ‹‹… ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፤ እርሱንም ያለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፴፱፥፬)
የጌታው ሚስት ግን መታመኑን ይተላለፍ፤ በክፉ ሥራዋ (በዝሙት ከእርሷ ጋር ይወድቅ) ይተባበራት ዘንድ ግድ አለችው፤ እርሱ ግን እንዲህ አላት፤ ‹‹… እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፤ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለው? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለው…?›› (ዘፍ.፴፱፥፱) መታመኑንም በዚህ ገለጠ፤ ጌታው አብሮት ባይሆንም በመታመኑ ታላቅነቱን ገለጠ፤ ይህ ግን ለሹመት ለሽልማት አላበቃውም፡፡ የክፋትና የሐሰተኛ አባት የሆነው የመልካም ነገር የማይወደው ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ በሐሰት አስመስክሮ ለወኅኒ ዳረገው፡፡
በዚያም በእስር ሳለ ታማኝ ነበርና ክብርን፣ ሞገስን አገኘ፤ በግዞትም ቤት አለቃ ሆነ፡፡ (ዘፍ፡-(ዘፍ.፴፱፥፵፩)፡፡ በአባቱ ዘንድ በመብል፣ በጲጥፋራ ቤት በዝሙት፣ በወኅኒ ቤት ለታራሚዎች ፊት የቀረበለትን ፈተና በመታመን የተወጣውን ዮሴፍ እግዚአብሔር ሞገስን አጎናጽፎ ለታላቅ ኃላፊነት መረጠው፤ በባዕዳን አገር፣ ወገኖቹ ባልሆኑ በግብጽ አገር ሾመው፡፡ ‹‹… አንተ በቤቴ ላይ ተሾምክ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ…›› (ዘፍ.፵፩፥፴፱) አደራን መወጣት ምን ያህል መታደል ነው!
ውድ ክርስቲያኖች! እስኪ ለደቂቃ በሰዎች ዘንድ (በቤተሰብ፣ በሰፈር፣ በሥራ ቦታ…) ታምነን ኃላፊነት የጠበቅንባቸውን ነገሮች እናስታውስ! በስንቱ ታምነናል? የስንቱንስ አደራ በልተን እምነታችንን አጉድለናል? ለድክመታችን ምክንያት በማበጀት ለታመነን ያልታመንን ስንትቶቻችንን ነን?
ዮሴፍ ለራሱ ታመነ፤ በነበረው የሕይወት ውጣ ውረድ ታማኝነቱን እያጎላ መጣ፤ መታመን ለራስ ነው፤ ነጻነትን፣ ክብርን፣ ሞገስን የሚያጎናጽፍ፣ መመረጥንና መከበርን የሚያሰጥ፣ ተናግሮ መደመጥን የሐሳብ ልዕልናን የሚያስገኝ ነው፡፡ በትንሽ ነገር እንኳን በታመንን ቁጥር እግዚአብሔር ለታላቅ ኃላፊነት ይመርጠናል፤ ምን ጊዜም፣ የትም ቦታ ቢሆን ታማኞች መሆን አለብን፡፡
በቤታችንና በትምህርት ቤት ውስጥ በቤተሰቦቻችንና በጓደኞቻችን ዘንድ ታማኞች ልንሆን ይገባል፤ “እርሱ እኮ ታማኝ ነው!፤ እርሷ እኮ ታማኝ ናት!” ልንባል ያስፈልጋል፤ እምነትን ማጉደል (አለመታመን) ለመከራ ይዳርጋል፤ ሰው አላየንም ብለን የእኛ ያልሆነውን ብንነካ እግዚአብሔር ያየናል፤ ስለዚህ መታመን (ታማኝ) መሆን አለብን፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን፣ የምሠራው እንዲባረክ፣ የተሰወረው እንዲገለጽልን፣ የሰው ምርቃት እንዲደርሰን (እንድንባረክ) ታማኞች መሆን አለብን፤ የምንታመነው ለሰዎች ብለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን መሆን አለበት፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!