አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል ስድስት
መጋቢት ፲፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ማኅበረ ቅዱሳን ለሀገር

፲.፩.አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች

የአቡነ ጎርጎርዮስ የመጀመሪያው ትምህርት ቤት የተመሠረተው በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አገልግሎት እየሰጠ ባለው ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ‹‹አቡነ ጎርጎርዮስ›› የሚለው ስያሜ ለትምህርት ቤቱ የተሰጠው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ በሆኑትና በተለይ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ሕፃናት እና ወጣቶች ላይ መሥራትን እንደ መርሕ አድርገው ያገለግሉ ለነበሩትና ለማኅበረ ቅዱሳንም መመሥረት ጽኑ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎዮስ ካልእ (፲፱፻፴፪-፲፱፻፹፪ ዓ.ም.) የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ካህናት ማሠልጠኛ መሥራች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነው፡፡

አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህር ቤት ከተመሠረተበት ከ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. እስከ ፳፻፮ ዓ.ም. በባለቤትነት የአስተዳድረው የነበረው ማኅበረ ቅዱሳን ነበር፡፡ ከአገልግሎቱ እና መዋቅራዊ አደረጃጀት ባሕርይው አንጻር ሁለት መሠረታዊ ተግዳሮቶች ሲፈትኑት ቆይተዋል፡፡ የመጀመሪያው ለትምህርት ቤት የሚሆን የራሱ የሆነ ሕንፃ አለመኖር ሲሆን ሁለተኛው የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ለማምጣት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማሟላት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ማነስ ነው፡፡ ይህንን ችግር በዘለቄታው ለመፍታት ይቻል ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አባላቱ፣ የተማሪዎች ወላጆች እና የዓላማው ደጋፊዎች የሆኑ ግለሰቦች በጋራ ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር (ኤስድሮስ በ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአንድምታ ትርጓሜ መምህር የነበሩ ናቸው) በማቋቋም ከሐምሌ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ የባለቤትነት ዝውውር ተደረገ፡፡ (የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች መተዳደሪያ ደንብ)

አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት እንደ ማንኛውም ትምህርት ቤት በዋናነት ከሚሠጠው ጥራቱን የጠበቀ የቀለም ትምህርት የማስተማር አገልግሎት ባለፈ የትምህርት የመጨረሻው ግብ የሆነውን የተማሪዎች የሰብእና ግንባታ ውጤታማ ከማድረግ እና በሀገራችን በትውልዱ ላይ ከሚታዩት መሠረታዊ ችግሮች መካከል የግብረ ገብነት መጓደል እንዲሁም ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ቦታ ያለመስጠት ችግሮችን ለመቅረፍ የግብረ ገብ፣ ልሳነ ግእዝ እና መዝሙር ትምህርቶችን ያስተምራል፡፡ መሪ ቃሉ ‹‹ትውልድ የሚተካ ትውልድ በተሻለ ጥራት እናፈራለን›› የሚለውም ለዚህም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው ከ፲፱፻፺፭ እስከ ፳፻፮ ዓ.ም. ድረስ በማኅበረ ቅዱሳን ባለቤትነት ሥር በቆየባቸው ጊዜያት ሦስቱን የትምህርት ዓይነቶች (ግብረ ገብ፣ ልሳነ ግእዝ እና መዝሙር) በሚፈለገው ጥራትና ብቃት ማስተማር የሚያስችል ወጥና የተደራጀ ሥርዓተ ትምህርት አልነበረም፡፡

ከዚህም አንጻር የግብረ ገብ ትምህርት ይሰጥ የነበረው ‹‹የሥነ ምግባር ትምህርት›› በሚል መጠሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የሚሠጠውን ‹‹ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር›› የተሰኘውን የትምህርት ዓይነት ይዘት በየክፍል ደረጃው በመከፋፈል ሲሆን የልሳነ ግእዝ ትምህርት ይሰጥ የነበረው ደግሞ ከትምህርት ቤቱ መምህራን አንዷ የነበረችው መምህርት ኑኃሚን ዋቅጅራ በሰንበት ትምህርት ቤት የተማረችውን መሠረት አድርጋ በአዘጋጀቻቸው የማስተማሪያ ማኑዋሎች ነበር፡፡ የመዝሙር ትምህርት የሚሰጠው ልዩ ልዩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዝሙራትን ለተማሪዎች በማስጠናትና እንዲዘምሩ በማድረግ ነበር፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ቤቱን (አቡነ ጎርጎርዮስ) ሲመሠርት እነዚህን ሦስት የትምህርት ዓይነቶች እንዲካተቱ ያደረገበት መሠረታዊ መርሕ/ፍልስፍናዊ እሳቤ ባለመተግበሩ፣ መንግሥት ያስቀመጠውን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ እንደመጠቀሚያ በማድረግ ጫናዎች እየበዙ በመምጣታቸው እንዲሁም ከወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከሚነሡ አስተያየቶች አንጻር ለሦስቱም የተደራጀ ሥርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀት በተለያዩ ጊዜያት ጥረት ቢደረግም በገንዘብ አቅም እጥረት ምክንያት ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ባለቤትነት ወደ ኤስድሮስ አክሲዮን ማኅበር ባለቤትነት ሲሸጋገር የሥራው መጀመሪያ ካደረጋቸው ተግባራት ዋነኛው ለእነዚህ የትምህርት ዓይነቶች የተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍትን ያካተተ የተደራጀ ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት በመሆኑ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን የግብረ ገብ እና ልሳነ ግእዝ ሥርዓተ ትምህርት የተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍት እንዲዘጋጁ ተደርጓል፡፡ በአሀኑ ጊዜ ከዋናው የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቅርንጫፍ በተጨማሪ በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ሥር በአዲስ አበባ ዘጠኝ ቅርንጫፎች፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋና ወልድያ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ቅርንጫፎች ተከፍተው አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ፡፡

፲.፪.ሀገራዊ እሴቶችን በውጭ ሀገራት ከማስቀጠል አንጻር

እሴት ማንኛውም ክርስቲያን ሊከተለውና ሊጠብቀው የሚገባ መርሕ ነው፤ በአንድነትታችንና በኅብረታችንም ወስጥም እንጋራቸዋለን፤ እሴቶች መንፈሳዊ አገልግሎቱ ከሚፈልገው ጠባይ አንጻር ሊለያዩም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ ሁሉም ክርስቲያን የጋራ ሊያደርጋቸው የሚገባ ናቸው፡፡

በማኅበሩ ውስጥ ባሳለፈው ከሠላሳ በላይ ዓመታት ውስጥ ቆጥረንና ለክተን መጠኑን መግለጽ ባንችልም በምሳሌነት ግን ልናነሣቸው የምንችላቸው በርካታ እሴቶች አሉ፤ አንደኛው መልካም ሥነ ምግባር ነው፤ አሁን ያለውን ትውልድ በሥነ ምግባር ከመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለሃይማኖቱ በሚሠራበት ተቋም የተማረ ኃይል ከመሆኑ ባሻገር በተማረበት ሙያም ለሀገሪቱና ለኅብረተሰቡ ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ እንዲተገብር በሚያስችል መልኩ ተቀረጾ የሚወጣበት ተቋም ነው፡፡ ሥራ ወዳድ እንዲሆንና በፈሪሃ እግዚአብሔር ቤተሰቡንና ሀገሩን አገልጋይ ለማድረግ ትምህርት በመስጠቱ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ታማኝነትም ገንዘቡ የሚያደርግ ትውልድ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ታማኝ ስለሚሆን በሚያከናውናቸው ተግባራት በሙሉ ውጤታማ ይሆናል፡፡ አገልግሎቱንም አስፍቶና አምልቶ ይፈጽማል፤ ክርስቲያን ከአምላኩ እግዚአብሔር ቀጥሎ ሀገሩን ሊያገልግል ይገባል፡፡ ይህንንም አገልግሎት ማኅበሩ ውጪ ሀገር ባሉት ሰባት ማእከላት በውጭ ዓለም ባሉት አማካኝነት በሀገር ውስጥ የሚያከናውነውን ተግባር በውጭ ዓለምም ያከናውናል፡፡ እነዚህ በሥነ ምግባር የታነጹና የተማሩ አገልጋዮች በሞያቸውና በጉልበታቸው ብቻ ሳይሆን ለሀራችን የልማትና የብልጽግና ዕድገት ያበረከቱት ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሬ ሂደትና የገንዘብ ድጎማ አብያተ ቤተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በመደጎም ሀገራዊ ጠቀሜታቸው የላቀ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ መነኰሳት ለአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ሲደረግላቸው ጥቅሙ ለሀገራችን በሙሉ ነው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሠቱ የእርስ በእርስ ጦርነትና ሀገራዊ እንዲሁም ማኅበረሰባዊ ቀውስ ሳቢያ ሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሚደርሰው መፈናቀሎች የሚደረገው ድጋፍ እንደ ሀገር ነው፡፡ መንግሥት ተደራሽ ያላደረገባቸው ቦታዎች ላይ ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ አባላትን በማስተባበር እርዳታ አድርጓል፡፡

ባህልን ጠብቆና እሴትን አስጠብቆ ከመኖር አንጻር የወንድሞቻችንና የእኅቶታችን ውጤት በመግለጽና ተአማኒ በማድረግ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራታችን እሙን ነው፡፡ ከክርስቲያናዊ ምግባር ጀምሮ እስከ ሥርዓቱን የጠበቀ አመጋገብ እንዲሁም የአነጋገርና የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ሕፃናቱን ጭምር እያሰባሰበ የሀገራቸውን ባህል እንዳይረሱ ከማድረጉ በተጨምሪ እዚህ ሀገር ያሉ በርካታ ሰዎች የማይችሉትን የግእዝ ቋንቋና ቅዳሴ ተሰጥኦ በውጭ ሀገር ሆነው እንዲተብሩት አስችሏቸዋል፡፡ በቅርቡ አሜሪካ ሲያትል ባለው አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት አማካኝነት አሜሪካ ተወልደው በእንግሊዝኛ አፍ ፈተው ያደጉ ዐሥራ ስድስት የሚሆኑ ወጣች ለአምስት ዓመታት ተምረው ዲቁና የተቀበሉት የዚህ አገልግሎት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ለማደግ በአሉበት ሀገርም ሌላውን አስተምረው ለመመለስ ትልቅ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ የገደማትና አድባራት እንደሁም የቤተ ክርስቲያናትን ታሪክ እንዲሁም ስለ ገዳማዊ አኗኗር ባለቡት ሆነው ይማራሉ፡፡ ይህንንም ለማየት ጓጉተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ሙሉ በሙሉም በዓለማዊ ጫና እንዳይወድቁ ለማድረግም ሀገራችውና ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ደረጃ እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡

ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የዜማ መሣሪያዎችን መቋሚያ፣ ጸናጽል፣ ከበሮና በገና ጠንቅቀው ይማራሉ፡፡ መዝሙራትን በመዝሙር ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያከናውናሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በየትኛውም ዘርፍ ላይ በትጋት የሚሠሩ አገልጋዮችን አፍርቷል፤ በችግር፣ በመከራና በድኅነት ውስጥ ያለ ሕዝብ በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ትጉሁ ሊሆን እንደሚገባ ሁሉ ትጋትና ለሥራ ተነሣሽነት ያለው ኅብረተሰብ ሲኖር ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ይቆየን!