ንጽሐ ጠባይዕ
ዲያቆን ዳዊት አየለ
መጋቢት ፱፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
እከብር አይል ክቡር፣ አወድሱኝ አይል በባሕርይው ምስጉን፣ቀድሱኝ አይል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ አምላካችን በዙፋኑ ሆኖ በፍጥረታቱ አንደበት ሲመሰገንና ሲወደስ የሚኖር ነው፡፡ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ሰውንም ቅዱስ፣ ንጹሕና ክቡር አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ከፍጥረት ሁሉ የከበረችውንና የተለየችውን የአምላክ እናት እመቤታችንንም ከተለዩ የተለየች፣ ከተከበሩ የተከበረች፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ቅድስት ድንግል ማርያም እያልን እንጠራታለን፡፡
በቅድስና መኖር ለሰው ዘር የተሰጠ የተፈጥሮ ጸጋ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ “የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል” እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥሮስ ፩፥፲፭-፲፮)
ቅዱስ ሆነን መኖር የምንችለውም ግን ከክፋት ርቀንና ከኃጢአት ነጽተን በበጎ ምግባር መኖር ስንችል እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ሲል ይነግረናል፡፡ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ሊወጣ ይችላል? በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል? ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፣ ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤ በውሸት የማይምል፡፡” (መዝሙር ፳፬፥፫-፬) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ይህን ቃል እንዲህ ሲል አረጋግጦልናል፡፡ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።” (ማቴዎስ ፭፥፰) ልባችን ከክፋትና ከኃጢአት ሁሉ የራቀ ከሆነ ተግባራችን ሁሉ መልካም ይሆናል፡፡ በበጎ ምግባርም የመኖር ብቃት ይኖረናል፡፡ በዚህም የንጽሐ ጠባይዕ ባለቤት እንሆናለን፡፡
ንጽሐ ጠባይዕ ከሁለት የግእዝ “ንጽሕ” እና “ጠባይዕ” ከሚሉ ቃላት የተገኘ ሲሆን “ንጽሕ” ማለት “ንጽሕና፣ ጥራት፣ ጥሩነት፣ ከዝሙት ከርስሐት መራቅ መጠበቅ” ነው፤ “ጠባይዕ” ማለት “ጠባይ፣ ባሕርይ፣ የፍጥረት ሁሉ ጥንት፣ ሥር መሠረት፣ አኳኋን፣ ሁነታ” የሚል ትርጒም አለው። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ)
የቃሉ ሙሉ ትርጒምም “ንጽሐ ጠባይዕ” ማለት “የተፈጥሮ ንጽሕና፣ የቀደመው ንጽሕና” ሲሆን የሰው ልጅን እግዚአብሔር ሲፈጥረው የነበረው ንጽሕና ወይም አዳም እና ሔዋን የእባብን ምክር ሰምተው ከመውደቃቸው አስቀድሞ የነበራቸው ንጽሕና ነው፡፡ እንዲሁም “አበሳ ዘጥንት” የተባለውን የአዳምንና የሔዋንን በውርስ በልጆቻቸው በየትውልዱ እየተዋሐደ ይመጣ የነበረውን የኃጢአት ዕዳ (ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቀር) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በመወለድ የመቤዠት ግብር በኋላ የሚወለዱ ሕፃናት ያላቸው ንጽሕና በኃጢአት እስካላደፈ ድረስ “ንጽሐ ጠባይዕ” እንለዋለን። (መዝገበ ቃላት ዘኪዳነ ወልድ ክፍሌ)
ሕፃናት ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባቸው ናቸው፤ ጌታችን በወንጌል ”…ሕፃናትን ተውአቸው፤ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና…” በማለት እንደተናገረው ነው፡፡ (ማቴ.፲፱፥፲፬) ነፍስ በበደል ምክንያት ንጽሐ ጠባይዕዋ ያድፍባታል፤ ይህም አእምሮዋ ጠባብ ሕሊናዋ ምውት ይሆናል። በዚህን ጊዜ ታዲያ ፍተወታት እኩያት (ክፉ መሻቶች) እንዲሁም የረከሱ ኃጢአቶች ይሠለጥኑባታል። በዚህም ምክንያት “…እንደ እነዚህ ላሉት ናትና…” ተብሎ የተነገረላት መንግሥት ሰማያትን ይህች ነፍስ ታጣለች፤ ዳግመኛ በንስሐ እንባ ታጥባ እንደ ሕፃናት ስትሆን ግን እንደገና ለመንግሥቱ ትታጫለች።
ንጽሐ ጠባይዕ የዋህነት ነው፤ ቅዱስ ወንጌል “የዋሃን ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ ምድርን ይወርሳሉና” ተብሎ እንደተጻፈው የዋህነት ወደ ሰማያዊው አዲስ ምድር የምታስገባ ንጽሐ ጠባይዕ ናት። (ማቴ.፭፥፭) በተጨማሪ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ “…ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ…” ብሎ እንዳስተማረን የዋህነት ከትሕትና ጋር አስተባብረን የያዝን እንደሆነ እርሱን እንመስለዋለን፤ (ማቴ.፲፩፥ ፳፱) ለነፍሳችንም ዕረፍትን የምናገኝባትን ንጽሐ ጠባይዕን ገንዘብ እናደርጋለን።
ንጽሐ ጠባይዕ አድሎና ማስመሰል የሌለበት ንጹሕ ፍቅር ነው፤ ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “…ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው…” በማለት እንዳስተማረን የሕግ ሁሉ ፍጻሜና እግዚአብሔርን ለማስደሰት የምታስችል ንጹሕ መንገድ ፍቅር ናት። (ሮሜ ፲፫፥፲)
ከአበው አንዱ “እግዚአብሔርን የማስደስተው ምን ባደርግ ነው? በጾም ነው? ወይስ በድካም ነው? ወይስ በምሕረት? ወይስ በትጋህ?” ብሎ ለጠየቀው ወንድም “አዎ፤ በእነዚህ ግብራት እግዚአብሔርን ደስ ልታሰኘው ትችላለህ። ነፍሳቸውንና ሥጋቸውን ያለ ዕረፍት ያደከሙ ብዙዎች እንደ ሆኑና ድካማቸው ግን ከንቱ እንደ ሆነ በእውነት እነግርሃለሁ። አፋችን መዓዛው እስኪለወጥ ድረስ አብዝተን ጾምን፣ የመጻሕፍትን ቃልም አጠናን፣ እግዚአብሔር የሚወደውን ፍቅርንና ትሕትናን ግን ገንዘብ አላደረግንም” በማለት ነበር የመለሰለት። ስለዚህ ለሁሉም መንፈሳዊ ተጋድሎዎችም ትጥቆችም መሠረትም ፍጻሜም ናት። ፍቅርንና ትሕትናን ገንዘብ በማድረግ ንጽሕ ጠባይዕን ገንዘብ ማድረግ የክርስትና ሕይወት መሠረት ነው። (ከበረሃውያን ሕይወትና አንደበት በመምህር ያረጋል አበጋዝ)
በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልምምድ ውስጥ (መንፈሳዊ ሕይወት በልምምድ የሚያድጉበት ነውና) በየዋህነት፣ በፍቅርና ትሕትና ተመላልሰን ወደ ንጽሐ ጠባይዕ እንድናድግ፣ የማታልፈውን ዘለዓለማዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ የልዑል እግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ይሁንልን! ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!