“የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” (ዮሐ.፪፥፲፮)

በቃሉ እሱባለው
የካቲት ፳፰፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

በቅዱስ ያሬድ ድጓ ውስጥ የምናገኘው ዐቢይ ጉዳይ አንጽሆ ቤተ መቅደስ ነው። “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” እንዲል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ተቆጣቸው፤ ገሠጻቸው የሚሉ አስተማሪ ቃላቶችን አካቶ ይዟል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡” በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።” (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)

የቅዱስ ዮሐንስ አገላለጾች ይዘን ጌታችን ለምን እንደዚያ እንዳደረገ እንመልከት። ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ በመጀመሪያ ያገኘው በሬዎችን፣ በጎችን እና ርግብ ሻጮችን እንዲሁም ገንዘብ ለዋጮችን ነው። “በግ ሻጮች ለመዳን የተሰጣቸውን የእግዚአብሔር በግ ለገንዘብ ንግድ ብለው አሳልፈው የሚሰጡት፣ ከሰማያዊ ክብር እና ሽልማት ይልቅ ለምድራዊ ጥቅም የመዳን ስጦታቸውን በመፈለግ በቁሳዊ ነገር የሚቀይሩት ናቸው። እንዲህ ላሉት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፤ ዕድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን ዕድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል።” (ኤር.፲፪፥፲)

እነዚህ በሬ፣ ላም፣ በግ እና ርግብ ሻጮች እነማን ናቸው ይልና “እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ ራሳቸውን ለማርካት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የድኅነታቸውን ነገር ሳይሆን ሁሉን ነገር በመሸጥ የሚያምኑ ናቸው። ከመሸጥ ውጭ ስለመግዛት (ጽድቅን) የሚጠይቁት ምንም ነገር የለም። እነዚህ ሰዎች ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ እና ፍሬ ይልቅ ምድራዊ ጥቅምን ይፈልጋሉ። ቅዱስ ጳውሎስም እነዚህን ሰዎች “ስለ እግዚአብሔር ያወራሉ” ብሎ የተናገረላቸው ናቸው። (ፊል. ፩፥፲፮)

ርግብ የሚሸጡት ደግሞ በርግብ አምሳል የተገለጠውን የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታ ያለ አግባብ የሚጠቀሙ ሰዎችን ናቸው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በግብረ ሐዋርያት የተጠቀሰው ሲሞን መሠሪይ ነው። እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በብር ሊገዛ ወድዷልና። ከመንፈሳዊ ጥቅም ይልቅ ቁሳዊ ትርፍን ወይም ጊዜያዊ ክብርን ይፈልጋል። (ሐዋ.፰፥፲፱-፳)

እነዚያን በመቅደስ ሲሸጡ ሲለውጡ የነበሩ ሰዎችን በሬዎቻቸውን፣ ላሞቻቸውን በጅራፍ እየገረፈ አስወጣባቸው፤ ገበታቸውንም ገለበጠባቸው (ዮሐ.፪፥፲፭) ስለ ምንድን ቢሉ መቅደስ የመሥዋዕት ቦታ ነው። በዚያ መሥዋዕት ቦታ ኦሪት የላሙን፣ የበጉን መሥዋዕት ያቀርቡበት ነበር። አሁን ግን ያ አለፈ፤ አሁን አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ቅዱስ ሥጋውና ደሙ የሚፈተትበት ጊዜ ደርሷል፤ እነዚያ ለሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት ጥላ እና ምሳሌ ነበሩ ሲል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስ ቄርሎስ በበኩሉ ይህንን የወንጌል ክፍል የአብራራበት መንገድ እንዲህ በማለት ነው። “እርሱ (ኢየሱስ) ሻጮችን እና ለዋጮችን አላባረራቸውም። ነገር ግን በጎችን እና ላሞችን እንዲሁም ርግቦችን አባረረ እንጂ። የሚሸጡ የሚለውጡበትን ገበታ ገለበጠ፣ ገንዘባቸውንም አፈሰሰ። ለማንጻት እና ለማዳን እንጅ ለመፍረድ አልመጣምና። የወደቀውን ሊያድን መጥቷልና። በእርሱ ዓይን አንድ ነፍስ ከብዙ እንስሳ፣ ወርቅ እና ገንዘብ ትበልጣለች። (ሉቃ.፲፭፥፯፣ ፲፭፥፲ እንዲል)

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “አሳቡን በቃላት (በስሜት) ብቻ ሳይሆን በገመድ በማባረር ገለጠው። ከቅዱሱ ቦታም በጅራፍ እየገረፈ አባረራቸው። ይህ በእርሱ ላላመኑ በፍርድም ሰዓት የሚያባርራቸው ባሪያዎች ምሳሌ ነው” ይላል። (ማቴ.፳፭፥፵፩) (Saint Cyril The Great, Commentary on John, Homily 132)
ወንጌላዊው ይቀጥልና እንዲህ ይላል። “ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።” (ዮሐ. ፪፥፲፮) ርግብ ሻጪዎችን ከሌሎች ለምን ለያቸው?ለምንስ በጅራፍ አላባረራቸውም ቢሉ ርግቦች ግርፋት አይችሉምና፤ በጅራፍ አልገረፋቸውም። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ ፪፥፲፮)

እንስሳትን እየገረፈ ካስወጣ በኋላ ርግብ ሻጮችን፣ ገንዘብ ለዋጮችን፣ በመቅደሱ ውስጥ በንግድ የተሰማሩትን ሁሉ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው። ምነው የአባቴን ቤት አለ በወንጌል ‘አባቱን ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ፣ በሰማይ ያለ አባታችሁ እያለ የጠራው አይደለም? ለምን አሁን ለየው ቢባል አሁንስ ስለ አምላክነቱ እየነገራቸው፤ በጌትነት ክብር ከአባቱ ጋር መተካከሉን እየነገራቸው ነው። እነርሱንም ከዚያ ሲለያቸው ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ይዞ እንዲህ በማለት ይናገራል፤ “እግዚአብሔር (ኢየሱስ ክርስቶስ) ቅዱሱን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉ አላለም፤ ነገር ግን እንዲህ አለ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉ አለ እንጂ። እዚህ ላይ አባቱን ጠራ፤ እነርሱ ግን አልተበሳጩም። ምክንያቱም የተናገራቸው ቀለል ባለ አገላለጽ መሆኑን ስለመሰላቸው እራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚተካከል እስከሚነግራቸው ድረስ የተናገራቸውን ቃል አልተረዱም ነበር። ከዚህ በኋላ ግን በእርሱ ላይ በቁጣ ተነሡ” (Saint John Chrysostom on the Gospel of John Homilies XXIII)

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እርሱ የሚመሰገንበት፣ መሥዋዕት የሚሠዋበት በፍርሃት እና በረዓድ ሊይዙት የሚገባ ቅዱስ ቦታ ነው። ያ መቅደስ በሰማይ ያለ ሥርዓት በምድር የሚከናወንበት ነው። እንዲያውም የአምላክ ሥጋ እና ደም የሚፈተትበት፣ የኃጢአተኞች መድኃኒት ሆኖ ከርኩሰት እና ከእዳቸው የሚያሳርፋቸው ከበሉት የማያስርብ፣ ከጠጡት የማያስጠማ የዘላለም ሕይወት የሚሆነው መሥዋዕት የሚዘጋጅበት እንጂ ምድራዊ ሹመት የሚሿሿሙበት፣ ምድራዊ ሥልጣን የሚታደልበት እና የሥጋ ገብያ የሚዘረጋበት ቤት አይደለም። እንዲህ ያለውን ግብር የሚያደርጉትን በገመድ እየገረፈ “እናንተ የሰይጣን እና የመልእክተኞቹ ልጆች ከእኔ ሂዱ ከቶ አላውቃችሁም” እያለ ያባርራቸዋል። (ማቴ.፳፭፥፬) የእግዚአብሔር ጅራፍ (ቁጣ) በተቀሰቀሰ ጊዜ በፊቱ ስንኳ የሚቆም አንድም የለም። ከሚንበለበለው፣ በላያችን ላይ ሊፈስ ካለው ቅጣትም ለመዳን ያንን ቅዱስ መቅደስ በንጽሕና መጠበቅ ይገባናል። ያ መቅደስ ደግሞ የእኛ አካል ነው።
የሥጋችንን ፍትወት ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለይተን በምድራዊ ቁስ እና በሚታየው ብልጭልጭ (ገንዘብ እና ወርቅ) ብንጠመድ እግዚአብሔር በፍርድ ሰዓት መሥዋዕትን እና ምስጋናን ለማቅረብ በእርሱ ቤት በአባቱ ቤት በመንፈስ ቅዱስም ቤት የምንገባው ያንን የዘረጋነውን የንግድ ጠረጴዛ ስንበትን ነው። ካልሆነ እናንተ የአባቴን ቤት አርክሳችኋል ይለናል። ወደ እኛ የሚመለከቱ ዐይኖቹ ከእኛ ይርቃሉ። እኛን የሚሰሙ ጆሮዎቹ ለመስማት ይዘገያሉ።

ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን እየተፈተነች ያለችበት አንዱ መሠረታዊ ችግር ሲሞናዊነት ነው። የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት (የእግዚብሔርን ስጦታ)፣ የመንፈስ ቅዱስንም ኃይል እንደ ሲሞን መሠሪይ በብርና በወርቅ የሚገዙ ሲሞናውያን በዝተውባታል። የእግዚአብሔር ቁጣ በፊታችን እንደምን ነድዶ ይሆን? እንደምንስ ባለ ቅጣት እንቀጣ ይሆን? የቤተ ክርስቲያንን ውበት የሚያጠፋ ሰዎችንስ እንደምን ባለ ፍርድ ይቀጣን ይሆን?

ከሚመጣው ቁጣ ለመዳን ያበቃን ዘንድ መቅደሱን እንጠብቅለት። የመቅደሱ ውብት ሳይጠፋ እንደተጌጠ በፊቱ ይታይ ዘንድ ከቤቱ የንግድ ሥራዎቻችንን ይዘን ልንሰደድ ያስፈልጋል። ይህን ባናደርግ የሚመጣው ይከፋልና።
እግዚአብሔር በፍቅሩ ስቦ ወደ ቅዱስ መቅደሱ በክብር ያቆመናል። እኛም በእርሱ፣ በአባቱም ፊት ባለሟልነትን እናተርፋለን። ለዚያም ክብር ያብቃን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤አሜን!